በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ሐምሌ 2014

 አገሮችና ሕዝቦች

አየርላንድን እንጎብኝ

አየርላንድን እንጎብኝ

“ኤመራልድ ደሴት” ተብላ የምትጠራው አየርላንድ ሁለት አገሮችን ያቀፈች ናት፤ ከእነዚህ አገሮች ትልቁ ነፃ አገር የሆነው የአየርላንድ ሪፑብሊክ ሲሆን አነስተኛው ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም ክፍል የሆነው ሰሜን አየርላንድ ነው።

ጃያንትስ ኮዝዌይ

አየርላንድ፣ ኤመራልድ ወይም መረግድ (አረንጓዴ ቀለም ያለው የከበረ ድንጋይ) ደሴት የተባለችው፣ ዝናብ ስለሚበዛባት የገጠሩ አካባቢ እጅግ ለምለም በመሆኑ ነው። የሚያማምሩ ሐይቆችና ወንዞች እንዲሁም ዓለታማ የባሕር ዳርቻዎችና የተራራ ሸንተረሮች ያሏት አገር መሆኗም ተጨማሪ ውበት አጎናጽፏታል።

የሣር ክዳን ቤት

የአየርላንድ ሕዝብ ብዙ መከራ አሳልፏል። ለምሳሌ፣ ከ1845 እስከ 1851 ባሉት ዓመታት የድንች ምርታቸው በሰብል በሽታ በመመታቱ ምክንያት አንድ ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች በረሃብና በበሽታ እንዳለቁ ይገመታል። ብዙዎች ከዚህ ከባድ ድህነት ለመሸሽ ሲሉ እንደ ብሪታንያ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳና ዩናይትድ ስቴትስ ወዳሉት አገሮች ተሰድደዋል። በዛሬው ጊዜ 35 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ አሜሪካውያን የአየርላንድ ዝርያ እንዳላቸው ይናገራሉ።

አየርላንዳውያን ሰው ወዳዶችና እንግዳ ተቀባዮች በመሆናቸው ይታወቃሉ። ተወዳጅ ከሆኑ የጊዜ ማሳለፊያዎች መካከል ፈረስ ግልቢያ እንዲሁም እንደ ክሪኬት፣ ራግቢና እግር ኳስ ያሉ የቡድን ጨዋታዎች ይገኙበታል። ከሞጊ የሚባለው ከገና ጨዋታ ጋር የሚመሳሰል የቡድን ጨዋታ በተለይ በሴቶች ዘንድ ተወዳጅ ነው።

 በተጨማሪም የአየርላንድ ሕዝቦች ከሰዎች ጋር መጨዋወት የሚያስደስታቸው ሲሆን ሙዚቃም ይወዳሉ። ስቴፕ ዳንስ የተባለው የአየርላንድ ጭፈራ በመላው ዓለም የታወቀ ነው። ዳንሰኞቹ ከወገባቸው በላይ ያለው የሰውነታቸው ክፍል ሳይነቃነቅ በእግራቸው ብቻ ፈጣንና ከሙዚቃው ምት ዝንፍ የማይል እንቅስቃሴ ያደርጋሉ።

አንድ የአየርላንድ ሙዚቃ ቡድን

የይሖዋ ምሥክሮች በአየርላንድ ከመቶ ዓመት የሚበልጥ ታሪክ አላቸው። በአሁኑ ጊዜ በዚህች አገር ከ6,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚኖሩ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ በቅንዓት እየተሳተፉ ነው።

በአየርላንድ ባሕላዊ ሙዚቃ ውስጥ ጥቅም ላይ ከሚውሉት የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል ከላይ የሚታዩት ይገኙበታል፤ ከግራ ወደ ቀኝ፦ የኬልቲክ በገና፣ የአየርላንድ ባግፓይፕ፣ ቫዮሊን፣ አኮርድዮን፣ ዋሽንትና ባውሮን (ከበሮ)

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ጃያንትስ ኮዝዌይ የሚባሉትና በሰሜን አየርላንድ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ የሚገኙት ድንጋዮች በሺዎች የሚቆጠሩ የዓለት ዓምዶች ናቸው፤ እነዚህ ዓምዶች የተፈጠሩት በጥንት ዘመን የቀለጠ ድንጋይ ከባሕሩ ጋር ሲገናኝ ቀዝቅዞ በመጠጠሩ ምክንያት ነው።