በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ሐምሌ 2014

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መከራ ሲደርስብህ—መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

ንብረትን ማጣት

ንብረትን ማጣት

መጋቢት 11, 2011 ዓርብ ዕለት፣ ጃፓን በሬክተር መለኪያ 9.0 በደረሰ የምድር መናወጥ ተመታች፤ በዚህ አደጋ ከ15,000 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ200 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚበልጥ ዋጋ ያለው ንብረት ወድሟል። የ32 ዓመቱ ኬይ፣ ሱናሚ እየመጣ እንዳለ ማስጠንቀቂያ ሲሰማ ሕይወቱን ለማትረፍ ከፍ ወዳለ ቦታ ሄደ። ኬይ እንዲህ ብሏል፦ “በማግስቱ የተረፈ ነገር ካለ ለመውሰድ ብዬ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ይሁን እንጂ እኖርበት የነበረውን አፓርተማ ጨምሮ ሁሉ ነገር ተጠራርጎ ባሕር ገብቶ ነበር። ከሕንፃው መሠረት ሌላ ምንም የቀረ ነገር አልነበረም።

“አንዳንድ ዕቃዎችን ብቻ ሳይሆን ያሉኝን ነገሮች በሙሉ እንዳጣሁ አምኜ ለመቀበል ጊዜ ወስዶብኛል። መኪናዬ፣ ለሥራ የምጠቀምባቸው ኮምፒውተሮች፣ እንግዶቼን የማስተናግድባቸው ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮችና ሶፋ፣ ኪቦርዴ፣ ጊታሬ፣ ዩከሌሌ የሚባለው የሙዚቃ መሣሪያዬና ዋሽንቴ እንዲሁም በውኃና በዘይት ቀለም ለመሳል የምጠቀምባቸው የሥዕል መሣሪያዎቼ ብሎም የሥዕል ሥራዎቼ በሙሉ በጎርፍ ተወስደዋል።”

መከራውን መቋቋም

ያጣኸውን ነገር ሳይሆን አሁን ያለህን ነገር ለማሰብ ሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ [አይደለም]” ብሏል። (ሉቃስ 12:15) ኬይ ያሳለፈውን ሁኔታ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦ “መጀመሪያ ላይ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች በዝርዝር ጻፍኩ፤ ይህ ግን የጠፉብኝን ነገሮች እንዳስታውስ ከማድረግ በቀር የፈየደልኝ ነገር አልነበረም። በመሆኑም በጣም የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ብቻ ለመጻፍ ወሰንኩ፤ እንዲሁም አንድ የሚያስፈልገኝ ነገር በተሟላልኝ ቁጥር የጻፍኩት ዝርዝር ላይ ማስተካከያ አደርጋለሁ። ይህም ሕይወቴን እንደ አዲስ ለመጀመር ረድቶኛል።”

ስለ ራስህ ችግር እያሰብክ ከመቆዘም ይልቅ ባገኘኸው ተሞክሮ በመጠቀም ሌሎችን ለማጽናናት ሞክር። ኬይ እንዲህ ብሏል፦ “የእርዳታ ድርጅቶችና ጓደኞቼ ብዙ ድጋፍ አድርገውልኛል፤ ይሁን እንጂ የሌሎችን እጅ ማየት ልማድ ስለሆነብኝ ለራሴ ያለኝ ግምት እየቀነሰ መጣ። በሐዋርያት ሥራ 20:35 ላይ የሚገኘውን ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አስታወስኩ። በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ልሰጥ የምችለው ብዙም ነገር ስላልነበረኝ አደጋ የደረሰባቸውን ሌሎች ሰዎች ለማበረታታት አሰብኩ። በዚህ መንገድ ልግስና ማሳየቴ በጣም ረድቶኛል።”

ያጋጠመህን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ ወደ አምላክ ጸልይ። ኬይ፣ አምላክ “ወደ ችግረኞች ጸሎት ይመለከታል” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ላይ ጠንካራ እምነት አለው። (መዝሙር 102:17) አንተም እንዲህ ያለ እምነት ማዳበር ትችላለህ።

ይህን ታውቅ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ማንም ሰው በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ንብረቴ አጣለሁ ብሎ የማይሰጋበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጽ ትንቢት ይዟል። *ኢሳይያስ 65:21-23

^ አን.9 አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።