ተፈታታኙ ነገር

የባንክ ደብተራችሁንና የገንዘብ ቦርሳችሁን ስትመለከቱ ‘ገንዘቡን ምን በላው?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። አዲስ ተጋቢዎች ብትሆኑም ወጪያችሁን መቆጣጠር አቅቷችኋል። ለዚህ ምክንያቱ የትዳር ጓደኛችሁ ነው? እንዲህ ለማለት አትቸኩሉ! ከዚህ ይልቅ ችግሩን በጋራ ለመፍታት ሞክሩ፤ ሁለታችሁም እንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ እንድትገቡ ያደረጋችሁን ምክንያት ለማሰብ ጥረት አድርጉ። *

ምክንያቱ ምንድን ነው?

አዲስ ለውጥ፦ ትዳር ከመመሥረታችሁ በፊት ከቤተሰብ ጋር ትኖሩ ከነበረ የራሳችሁን ወጪ መሸፈንና ወጪን መጋራት አዲስ ሊሆንባችሁ ይችላል። በተጨማሪም አንተና የትዳር ጓደኛህ በገንዘብ አያያዝ ረገድ ያላችሁ ልማድ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንዳችሁ ገንዘብ ማውጣት የሚቀናችሁ፣ ሌላችሁ ደግሞ ገንዘብ ቆጣቢዎች ልትሆኑ ትችላላችሁ። በገንዘብ አያያዝ ልማዳችሁ ላይ ማስተካከያ በማድረግ ተስማምታችሁ አንድ ዓይነት አቋም ላይ እስክትደርሱ ድረስ ጊዜ ይወስዳል።

ዕዳ ልክ እንደ አረም ዝም ከተባለ እያደገ ይሄዳል

ዛሬ ነገ ማለት፦ በአሁኑ ጊዜ የተሳካለት የንግድ ሰው የሆነው ጂም አዲስ ባለትዳር በነበረበት ወቅት የተደራጀ አለመሆኑ ብዙ ኪሳራ እንዳስከተለበት ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ክፍያዎችን በጊዜው ባለመክፈሌ እኔና ባለቤቴ በሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ለመቀጫ ከፍለናል። በዚህም ምክንያት ገንዘባችንን ጨረስን።”

ገንዘቡ ሲወጣ የማታዩት መሆኑ፦ ወጪያችሁን የምትከፍሉት ከኪሳችሁ ወይም ከቦርሳችሁ አውጥታችሁ ካልሆነ ገንዘቡ ከእጃችሁ ሲወጣ አታዩትም፤ በዚህም የተነሳ ሳይታወቃችሁ ብዙ ልታወጡ ትችላላችሁ። ክፍያ የምትፈጽሙት በክሬዲት ካርድ ወይም በዴቢት ካርድ ከሆነ አሊያም በኢንተርኔት አማካኝነት የምትገበያዩ ወይም የኤሌክትሮኒክ ባንክ አገልግሎት የምትጠቀሙ ከሆነ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥማችሁ ይችላል። በቀላሉ ዱቤ ማግኘት መቻልም አዲስ ባለትዳሮች ከአቅማቸው በላይ እንዲያወጡ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ገንዘቡ የወጣበት መንገድ ምንም ይሁን ምን የገንዘብ ችግር ትዳራችሁን ሊበጠብጠው ይችላል። ትዳራችሁን መታደግ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ “አብዛኞቹ ባለትዳሮች ምንም ያህል ገንዘብ ቢያገኙ በትዳራቸው ውስጥ በዋነኝነት ችግር የሚፈጥረው ገንዘብ እንደሆነ ይናገራሉ።” አክሎም “ገንዘብ በአብዛኛው ለግጭት መንስኤ ነው” ብሏል።

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

እርስ በርስ ተባበሩ። አንዳችሁ ሌላውን ከመውቀስ ይልቅ ተባብራችሁ ወጪያችሁን ለመቆጣጠር ጥረት አድርጉ። ስለዚህ ጉዳይ በምትነጋገሩበት ወቅት ገንዘብ በሁለታችሁ መካከል እንዲገባ ጨርሶ ላለመፍቀድ በቅድሚያ ቃል ግቡ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ኤፌሶን 4:32

በጀት አውጡ። የወር ወጪያችሁን በሙሉ አነስተኛም ቢሆን ጻፉ። ይህም ገንዘባችሁ ምን ላይ እንደሚውልና አላስፈላጊ የሆኑት ወጪዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለይቶ ለማወቅ ያስችላችኋል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጂም “የሚፈስሰውን ደም ማቆም አለባችሁ። ይህ በሕክምናውም ሆነ በንግዱ ዓለም የሚሠራ አባባል ነው” ብሏል።

የምግብ፣ የልብስ፣ የቤት ኪራይ ወይም የሞርጌጅ (ለቤት ብድር የሚከፈል)፣ የመኪና እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ወጪዎቻችሁን በዝርዝር ጻፉ። ከእያንዳንዱ ወጪ ትይዩ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚፈጅባችሁ ጻፉ፤ በየስንት ጊዜው መክፈል እንደሚጠበቅባችሁ ግምት ውስጥ በማስገባት ምናልባትም በየወሩ ወጪዎቻችሁን ማስላት ትችላላችሁ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ሉቃስ 14:28

“ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው።”—ምሳሌ 22:7

በየወሩ ለእያንዳንዱ ወጪ (ለምግብ፣ ለኪራይ፣ ለነዳጅ፣ ወዘተ) የሚያስፈልገውን ገንዘብ መድቡ። አንዳንዶች ለእያንዳንዱ ወጪ የመደቡትን ገንዘብ በተለያዩ ፖስታዎች ውስጥ ያስቀምጣሉ። * በአንዱ ፖስታ ውስጥ ያለው ገንዘብ ካለቀ ለዚያ ጉዳይ ገንዘብ ማውጣታቸውን ያቆማሉ ወይም ከሌላ ፖስታ ገንዘብ ያዛውራሉ።

ለቁሳዊ ነገሮች ያላችሁን አመለካከት አስተካክሉ። ደስታ ማግኘታችሁ የተመካው አዳዲስ ነገሮችን በመግዛት ላይ አይደለም። ደግሞም ኢየሱስ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ” እንዳልሆነ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:15) በአብዛኛው በገንዘብ አያያዝ ረገድ ያላችሁ ልማድ ኢየሱስ በተናገረው ነገር ላይ እምነት እንዳላችሁና እንደሌላችሁ ያሳያል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ጢሞቴዎስ 6:8

ማስተካከያ አድርጉ። ትዳር ከመሠረተ ሁለት ዓመት የሆነው አሮን “ኪራይ የሚከፈልበት የቴሌቪዥን መስመር እንደ ማስገባትና ውጭ ወጥቶ እንደ መመገብ ያሉ ነገሮች መጀመሪያ ላይ ብዙ ወጪ የማይጠይቁ ቢመስሉም ውሎ አድሮ ብዙ ኪሳራ ያስከትላሉ” ብሏል። “በአቅማችን ለመኖር አንዳንድ ነገሮችን መተው መማር አስፈልጎናል።”

^ አን.4 ይህ ርዕስ ትኩረት የሚያደርገው በአዲስ ተጋቢዎች ላይ ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁሉም ባለትዳሮች ይሠራሉ።

^ አን.14 ክፍያዎችን የምትፈጽሙት በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ወይም በክሬዲት ካርድ ከሆነ በእያንዳንዱ ፖስታ ውስጥ የገንዘቡን መጠን የያዘ ወረቀት አስቀምጡ።