በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ሰኔ 2014

 ንድፍ አውጪ አለው??

እበት ለቃሚው ጥንዚዛ ያለው አቅጣጫ የማወቅ ችሎታ

እበት ለቃሚው ጥንዚዛ ያለው አቅጣጫ የማወቅ ችሎታ

የእንስሳት እዳሪ ለእበት ለቃሚ ጥንዚዛዎች ብዙ ጥቅም ይሰጣል። ለምግብነት ይጠቀሙበታል እንዲሁም እንቁላላቸውን ይጥሉበታል። አንዳንድ ወንዴ ጥንዚዛዎች ደግሞ በርከት ያለ እዳሪ ሰብስበው እንስቷ ፊት በማቅረብ እሷን ለማማለል ይሞክራሉ። እዳሪው ትኩስ ከሆነ ሽሚያው በጣም የጦፈ ይሆናል። በአንድ ወቅት 16,000 ገደማ የሚሆኑ ጥንዚዛዎች በዝሆን ፋንዲያ ላይ ተረባርበው በሁለት ሰዓት ውስጥ ድራሹን ሲያጠፉት ተመራማሪዎች ተመልክተዋል።

አንዳንድ እበት ለቃሚ ጥንዚዛዎች ከግርግሩ ለማምለጥ ሲሉ እበቱን ካድቦለቦሉ በኋላ እያንከባለሉ ይወስዱታል፤ ከዚያም ለስላሳ በሆነ አፈር ውስጥ ይቀብሩታል። ጥንዚዛዎቹ ያድቦለቦሉትን እዳሪ እያንከባለሉ የሚወስዱት ቀጥ ያለ መስመር ተከትለው ነው፤ እንዲህ ማድረጋቸው ከአካባቢው ፈጥነው ለመራቅ ብሎም የያዙት እዳሪ በሌሎች ጥንዚዛዎች የመሰረቅ አጋጣሚውን ለመቀነስ ያስችላቸዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ እበት ለቃሚ ጥንዚዛዎች በተለይ ሌሊት ላይ፣ ሳይንከራተቱ የሚፈልጉትን አቅጣጫ ይዘው መጓዝ የሚችሉት እንዴት ነው?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ እበት ለቃሚ ጥንዚዛዎች በፀሐይ ወይም በጨረቃ ብርሃን እየተመሩ እንደሚጓዙ ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች አመልክተው ነበር፤ ይሁን እንጂ በጠፍ ጨረቃም ቀጥ ባለ መስመር መጓዝ ይችላሉ። የደቡብ አፍሪካ ተመራማሪዎች እንደገለጹት ጥንዚዛዎቹ ቀጥ ባለ መስመር የሚጓዙት ከዋክብትን በተናጠል በመመልከት ሳይሆን ፍኖተ ሐሊብ የተባለው ጋላክሲ የሚፈጥረውን ብርሃን በመከተል ነው። ከረንት ባዮሎጂ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው “እንስሳት አቅጣጫ ለማወቅ የፍኖተ ሐሊብን ብርሃን እንደሚጠቀሙ በመረጃ የተደገፈ ማስረጃ ሲቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።”

ማርከስ በርን የተባለ ተመራማሪ እንደገለጸው እበት ለቃሚ ጥንዚዛዎች “በእይታ አቅጣጫን የማወቅ ችሎታቸው ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በቂ የከዋክብት ብርሃን በሌለበት ጊዜም እንኳ ውስን በሆነው የአእምሮ ችሎታቸው ተጠቅመው አቅጣጫቸውን ጠብቀው መጓዝ ይችላሉ።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በእይታ አማካኝነት ሥራቸውን የሚያከናውኑ መሣሪያዎችን በመፈልሰፍ ረገድ የሚፈጠሩትን ውስብስብ ችግሮች መፍታት ስለሚቻልበት መንገድ የሰው ልጆች ከእነዚህ ነፍሳት ብዙ መማር ይችላሉ።” ለምሳሌ እበት ለቃሚ ጥንዚዛዎች አቅጣጫን የሚያገኙበትን ዘዴ በመኮረጅ በፈረሰ ሕንፃ ውስጥ ፍለጋ የሚያካሂዱ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚሠሩ በራሪ ሮቦቶችን መሥራት ይቻላል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? እበት ለቃሚ ጥንዚዛ ያለው አቅጣጫ የማወቅ ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?

ይህን ታውቅ ነበር?

እበት ለቃሚ ጥንዚዛዎች አፈር እንዲለሰልስ ብሎም እንዲዳብር ያደርጋሉ፤ በተጨማሪም የዕፀዋትን ዘር ያሰራጫሉ፣ ዝንቦች ከልክ በላይ እንዳይበዙ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።