በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ሚያዝያ 2014

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መኖር ምን ዋጋ አለው?

እርዳታ ማግኘት ይቻላል

እርዳታ ማግኘት ይቻላል

“የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም [አምላክ] ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7

ያለህበትን ሁኔታ ለማሻሻል ምንም ማድረግ እንደማትችል ሲሰማህ ሞትን ልትመርጥ ትችላለህ። ይሁን እንጂ እርዳታ ልታገኝ የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።

ጸሎት፦ ጸሎት አእምሮን ለማረጋጋት የሚረዳ ነገር እንደሆነ ብቻ አድርገህ ማሰብ የለብህም፤ ወይም አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ ብቻ የምታደርገው ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስለ አንተ ከሚያስበው ከይሖዋ አምላክ ጋር የምትነጋገርበት መንገድ ነው። ይሖዋ የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ እንድትነግረው ይፈልጋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል” ይላል።—መዝሙር 55:22

ለምን ዛሬውኑ አምላክን በጸሎት አታነጋግረውም? ይሖዋ በተባለው ስሙ ተጠቅመህ የልብህን ንገረው። (መዝሙር 62:8) ይሖዋ፣ እሱን የቅርብ ወዳጅ እንድታደርገው ይፈልጋል። (ኢሳይያስ 55:6፤ ያዕቆብ 2:23) ጸሎት በማንኛውም ጊዜና በማንኛውም ቦታ ከአምላክ ጋር ልትነጋገር የምትችልበት መንገድ ነው።

“ራሳቸውን ከሚያጠፉ ሰዎች መካከል በጣም ብዙዎቹ ማለትም 90 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት ከመሞታቸው ጥቂት ቀደም ብሎ የአእምሮ ችግር” እንደነበራቸው ጥናቶች በተደጋጋሚ ማረጋገጣቸውን በአሜሪካ የሚገኝ ራስን ማጥፋትን ለመከላከል የተቋቋመ አንድ ድርጅት ገልጿል። “ይሁን እንጂ በአብዛኛው እነዚህ ሰዎች ችግሩ እንዳለባቸው አልተስተዋለም ወይም በምርመራ አልተረጋገጠም አሊያም አስፈላጊውን ሕክምና አላገኙም።”

የሚያስቡልህ ሰዎች፦ የቤተሰብህን አባሎችና ወዳጆችህን ጨምሮ የአንተ ሕይወት የሚያሳስባቸው ሰዎች አሉ፤ ምናልባትም ይህን ነግረውህ ሊሆን ይችላል። ለአንተ ከሚያስቡልህ ሰዎች መካከል ጨርሶ አግኝተህ የማታውቃቸውም ሰዎች አሉ። ለምሳሌ የይሖዋ ምሥክሮች በሚሰብኩበት ጊዜ በጣም የተጨነቁ ሰዎች ያጋጥሟቸዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች የደረሱላቸው እርዳታ በጣም በሚያስፈልጋቸውና ራሳቸውን ለማጥፋት በሚያስቡበት ጊዜ እንደነበር ተናግረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት የሚያደርጉት የስብከት ሥራ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች ለመርዳት የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን አርዓያ ስለሚከተሉ ለሰዎች ከልብ ያስባሉ። ለአንተም ያስባሉ።—ዮሐንስ 13:35

የባለሙያ እርዳታ፦ ራስን የማጥፋት ሐሳብ በአብዛኛው እንደ መንፈስ ጭንቀት ያለ የጤና ችግር መኖሩን የሚጠቁም ነው። አንድ ዓይነት አካላዊ ሕመም ቢኖርብህ በዚህ እንደማታፍር ሁሉ የመንፈስ ጭንቀት ቢያጋጥምህም ልታፍር አይገባም። እንዲያውም የመንፈስ ጭንቀት “የአእምሮ ጉንፋን” ተብሎ ተጠርቷል። ማንም ሰው ላይ ሊደርስ ይችላል፤ እንዲሁም የሕክምና እርዳታ ሊደረግለት ይችላል። *

ይህን አስታውስ፦ ብዙ ጊዜ ከገባህበት የጭንቀት ጉድጓድ በራስህ ጥረት መውጣት አትችልም። ሌሎች የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉልህ የምትጠይቅ ከሆነ ግን ሊሳካልህ ይችላል።

ዛሬ ምን ማድረግ ትችላለህ? የመንፈስ ጭንቀት ላለባቸው ሰዎች የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ ጥሩ ስም ያተረፈ ሐኪም ፈልግ።

^ አን.8 ራስህን የማጥፋቱ ሐሳብ እያየለብህ ከመጣ ወይም ከአእምሮህ ሊጠፋ ካልቻለ የባለሙያዎችን እርዳታ ለማግኘት ሞክር፤ ምናልባትም የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ነፃ የስልክ መስመሮችን መጠቀም ወይም ወደ አእምሮ ሆስፒታል መሄድ ትችላለህ። እንደነዚህ ያሉት ድርጅቶች እርዳታ ለመስጠት የሠለጠኑ ባለሙያዎች አሏቸው።