በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  መጋቢት 2014

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ስፔን

በ2011 ለዘጠኝ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነና በብዙዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ የምድር መናወጥ በደቡብ ስፔን በሎርካ ከተማ ተከስቶ የነበረ ሲሆን ለዚህ መንስኤው ሰዎች ሳይሆኑ እንዳልቀረ አንድ የሳይንስ ባለሙያዎች ቡድን ገልጿል። በአካባቢው የከርሰ ምድር ውኃ በከፍተኛ መጠን ወጥቶ ለመስኖ ሥራ ጥቅም ላይ መዋሉ ከምድር ነውጡ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና እንዳለው የሥነ ምድር ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

ቻይና

በ2012 ቻይናውያን ቱሪስቶች ለዓለም አቀፍ ጉዞዎች 102 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አውጥተዋል። የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ ቻይና፣ ለዓለም አቀፍ ጉዞ ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ረገድ ጀርመንንና ዩናይትድ ስቴትስን በማስከተል ለመጀመሪያ ጊዜ የመሪነቱን ቦታ ይዛለች። የጀርመንና የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በአገር ደረጃ እያንዳንዳቸው 84 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ የሚሆን ገንዘብ አውጥተዋል።

ጃፓን

በጃፓን በሚኖሩ 68,000 በሚሆኑ ሰዎች ላይ በአማካይ ለ23 ዓመት ጥናት መደረጉን ቢኤምጄ የተባለው የብሪታንያ የሕክምና መጽሔት ዘግቦ ነበር። ይህ ጥናት እንደሚያሳየው ከ1920 እስከ 1945 ባሉት ዓመታት የተወለዱና 20 ዓመት ሳይሞላቸው በፊት ማጨስ የጀመሩ ሴቶች ጨርሶ አጭሰው ከማያውቁ ሴቶች በአማካይ አሥር ዓመት ያነሰ ዕድሜ ሲኖሩ ወንዶች ደግሞ ስምንት ዓመት ያነሰ ዕድሜ ኖረዋል።

ሞሪታንያ

በዚህ አገር ፌስታሎችን ከሌሎች አገሮች ማስገባትም ሆነ ማምረት እንዲሁም ጥቅም ላይ ማዋል በሕግ ታግዷል፤ ይህ የሆነበት ምክንያት የባሕርና የየብስ እንስሳት ፌስታል በመብላታቸው ሳቢያ እንዳይሞቱ ለመጠበቅ ሲባል ነው። መንግሥት፣ በእነዚህ ፋንታ በቀላሉ ወደ ብስባሽነት ሊቀየሩ የሚችሉ ሌሎች ከረጢቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እያበረታታ ነው።

ዓለም

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚፈጠሩ አደጋዎች የተነሳ የሚደርሰው የኢንሹራንስ ኪሳራ በዓመት በአማካይ 50 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። ይህ ዓይነቱ ኪሳራ የዋጋ ግሽበትን ግምት ውስጥ በማስገባት ከ1980ዎቹ አንስቶ ሲሰላ በየአሥር ዓመቱ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።