በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 አገሮችና ሕዝቦች

ኤል ሳልቫዶርን እንጎብኝ

ኤል ሳልቫዶርን እንጎብኝ

ከአምስት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት ስፔናውያን አሁን ኤል ሳልቫዶር ተብላ ወደምትጠራው አገር ከመስፈራቸው በፊት የአገሪቱ ዋነኛ ጎሣ አባላት አገሪቱን ኩስካትላን በማለት ይጠሯት ነበር፤ ትርጉሙም “ዕንቁዋ ምድር” ማለት ነው። ዛሬ አብዛኛው የኤል ሳልቫዶር ሕዝብ የጥንታዊዎቹ ጎሣዎችና የአውሮፓ ሰፋሪዎች ዝርያ ናቸው።

ሳልቫዶራውያን ታታሪዎችና ተግባቢዎች በመሆናቸው ይታወቃሉ። በተጨማሪም ጨዋዎችና ሰው አክባሪዎች ናቸው። ወሬ ከመጀመራቸው በፊት ወይም በሚገበያዩበት ወቅት “ቡዌኖስ ዲያስ” (እንዴት አደራችሁ?) ወይም “ቡዌናስ ታርዴስ” (እንዴት ዋላችሁ?) ይላሉ። እንዲያውም በገጠራማው አካባቢና በትናንሽ ከተሞች የሚኖሩ ሳልቫዶራውያን በመንገድ የሚያልፈውን ሰው ሰላምታ ሳይሰጡ ማለፍን እንደ ነውር ይቆጥሩታል።

የቡና እርሻ በኤል ሳልቫዶር ታሪክ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል

ሳልቫዶራውያን በጣም ከሚወዷቸው ምግቦች አንዱ ፑፑሳ ይባላል፤ ይህ ምግብ ከበቆሎ ወይም ከሩዝ ዱቄት የተሠራ ቂጣ ሆኖ መሃሉ ላይ ቺዝና ባቄላ እንዲሁም የአሳማ ሥጋና ሌሎች ነገሮች ይኖሩታል። ብዙ ጊዜ ከፑፑሳ ጋር የቲማቲም ወጥ እንዲሁም ጎመን፣ ካሮትና ቀይ ሽንኩርት በተቀመመ ኮምጣጤ ተለውሶ የሚዘጋጅ ኩርቲዶ የተባለ ምግብ ይቀርባል። አንዳንድ ሰዎች ቢላዋና ሹካ የሚጠቀሙ ቢሆንም ፑፑሳ በባሕላዊው መንገድ የሚበላው በእጅ ነው።

ከኤል ሳልቫዶር ተወዳጅ ምግቦች አንዱ ፑፑሳ ነው

በሱቺቶቶ የሚገኘው ሎስ ቴርስዮስ ፏፏቴ

 ይህን ታውቅ ነበር? ኤል ሳልቫዶር የእሳተ ገሞራዎች አገር ተብላ ትጠራለች። በአገሪቱ ከ20 የሚበልጡ እሳተ ገሞራዎች ያሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ንቅ እሳተ ገሞራ ማለትም አሁንም በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ናቸው። ሎስ ቴርስዮስ የሚባለው ፏፏቴ በእሳተ ገሞራ አማካኝነት በተፈጠሩ ባለ ስድስት ማዕዘን ቅርጽ ባላቸው ረጃጅም የድንጋይ ዓምዶች ላይ ቁልቁል ይወረወራል።

በኤል ሳልቫዶር፣ ወደ 700 በሚጠጉ ጉባኤዎች የተደራጁ ከ38,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። በስፓንኛ፣ በእንግሊዝኛ እንዲሁም በሳልቫዶርኛ ምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን 43,000 ለሚያህሉ ሰዎች ያስተምራሉ።