ከሞቱ ሰዎች ጋር ለመገናኘት መሞከር ስህተት ነው?

“እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ።”—ዘሌዋውያን 19:31

ሰዎች ምን ይላሉ?

ሁሉም ሰው ቢሆን በሞት የተለየው የሚወደው ሰው እየተሠቃየ እንዳልሆነ ማረጋገጫ ማግኘት እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። በመሆኑም አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “በመናፍስት ጠሪዎች ወይም ከሰው በላይ የሆነ ኃይል አላቸው በሚባሉ ግለሰቦች አማካኝነት፣ በሞት ካጣነው ሰው ጋር ለመገናኘት መሞከር ምን ችግር አለው? ደግሞም እንዲህ ማድረጋችን እንድንጽናና እና አእምሯችን እንዲያርፍ ሊያደርግ ይችል ይሆናል።”

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ከሞቱ ሰዎች ጋር ለመገናኘት መሞከርን አስመልክቶ የሚሰጠው ሐሳብ ግልጽ ነው። ይህ ድርጊት በጥንት ዘመን በጣም የተለመደ ነበር። ለምሳሌ፣ ይሖዋ አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ እንዲህ ይላል፦ “መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው።” (ዘዳግም 18:10-12) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች “የአምላክን መንግሥት አይወርሱም” በማለት ይናገራል።—ገላትያ 5:19-21

 የሞቱ ሰዎች በሕያዋን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ?

“ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም።”—መክብብ 9:5

ሰዎች ምን ይላሉ?

ብዙ ሰዎች፣ ሙታን በሆነ መልኩ ሕልውናቸው እንደሚቀጥል ያምናሉ። በመሆኑም ከሞቱ ሰዎች ጋር በመገናኘት ጥረት ያደርጋሉ። ይህንን የሚያደርጉት አንዳንድ መረጃዎችን ለማግኘት ስለሚፈልጉ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ሙታን በሕይወት ያሉ ሰዎችን እንዳይጎዱ ለማድረግ ሲሉ የሚፈልጉትን ነገር ሊያሟሉላቸው ብለው ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ . . . ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቶአል።” በሌላ አባባል በሕይወት በነበሩበት ወቅት የሚሰማቸው ነገር ሁሉ አይኖርም። (መክብብ 9:5, 6) አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ከሕልውና ውጪ እንደሆኑ ይናገራል! ማሰብ ወይም መሥራት ሌላው ቀርቶ አምላክን ማምለክ እንኳ አይችሉም። መዝሙር 115:17 “እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑት የሞቱት አይደሉም፤ ወደ ዝምታው ዓለም የሚወርዱም አይደሉም” ይላል።

ሙታን ጠሪዎች አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛ መረጃ ይሰጡ የለም?

“በሕያዋን ምትክ ሙታንን መጠየቅ ለምን አስፈለገ?”—ኢሳይያስ 8:19

ሰዎች ምን ይላሉ?

ሙታን ጠሪዎች፣ የሞቱት ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው ወይም ጓደኞቻቸው ብቻ ሊያውቁ የሚችሉትን ሚስጥር እንደሚያውቁ አንዳንዶች ይናገራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አንደኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 28 ሳኦል የተባለ ታማኝ ያልሆነ አንድ ንጉሥ፣ መናፍስት ጠሪዎችን ማናገርን የሚከለክለውን የአምላክን ሕግ እንደጣሰ ይናገራል። ሳኦል፣ በሞት ካንቀላፋው ሳሙኤል የተባለ የአምላክ ሰው ጋር ለመነጋገር ትረዳኛለች ብሎ ወዳሰባት አንዲት ሙታን ጠሪ ዘንድ ሄደ። ይሁን እንጂ ይህች ሴት በእርግጥ ከሳሙኤል ጋር ትገናኝ ነበር? በፍጹም! ይህች ሴት የተነጋገረችው ሟቹ ሳሙኤልን መስሎ ከቀረበ አንድ አታላይ አካል ጋር ነው።

ይህ አታላይ ክፉ መንፈስ ሲሆን ‘የውሸት አባት’ የሆነው የሰይጣን ወኪል ነው። (ዮሐንስ 8:44) ክፉ መናፍስት ወይም አጋንንት ‘ሙታን በሕይወት አሉ’ የሚለውን አመለካከት የሚያስፋፉት ለምንድን ነው? ዓላማቸው የአምላክን ስም ማጥፋትና ሰዎች በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንዳይጥሉ ማድረግ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ታዲያ ይህ ሲባል የሞቱ ሰዎች ምንም ዓይነት ተስፋ የላቸውም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም! በመቃብር ውስጥ ‘እንደተኙ’ ተደርገው የተገለጹት ሰዎች የትንሣኤ ተስፋ እንዳላቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። * (ዮሐንስ 11:11-13፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን፣ በሞት ያጣናቸው የምንወዳቸው ሰዎች ምንም ዓይነት ሥቃይ እንደማይደርስባቸው ማረጋገጫ ተሰጥቶናል።

^ አን.16 ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 7 “በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ያላቸው እውነተኛ ተስፋ” የሚል ርዕስ አለው። ይህን መጽሐፍ www.jw.org/am በተባለው ድረ ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል።