ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው?

“በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም።” —ዮሐንስ 1:18

ሰዎች ምን ይላሉ?

ብዙ ሰዎች ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ብለው አያምኑም። ያም ሆኖ አንዳንዶች ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል መሆኑን ያሳያሉ ብለው የሚያስቧቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይጠቅሳሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ አይገልጽም፤ ወይም ከአምላክ ጋር እኩል ነው አይልም። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ከአምላክ እንደሚያንስ በግልጽ ያስተምራል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ራሱ “አብ ከእኔ ይበልጣል” ብሎ መናገሩን ይገልጻል። (ዮሐንስ 14:28) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም” ይላል። (ዮሐንስ 1:18) ስለዚህ ኢየሱስን ብዙ ሰዎች ስላዩት እሱ እግዚአብሔር እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሆነ አልተናገሩም። ለምሳሌ ያህል የወንጌል ጸሐፊው ዮሐንስ በጽሑፍ ስላሰፈራቸው ነገሮች ሲናገር “እነዚህ የተጻፉት ኢየሱስ፣ እሱ በእርግጥ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ እንድታምኑ [ነው]” ብሏል።—ዮሐንስ 20:31 *

 ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነበር?

“ሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ።”—ሉቃስ 2:8

ሰዎች ምን ይላሉ?

አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ የተወለደበት ቀን እንደሆነ በሚታሰበው በታኅሣሥ 25 ገናን ያከብራሉ። ሌሎች ደግሞ የኢየሱስን ልደት የሚያከብሩት በጥር መጀመሪያ ላይ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን ለይቶ አይጠቅስም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ “ሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ” በማለት ይገልጻል። (ሉቃስ 2:8) እነዚያ እረኞች በታኅሣሥ ወይም በጥር ወር መንጎቻቸውን እየጠበቁ ሜዳ ላይ ያድራሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ለምን?

ኢየሱስ በተወለደበት ስፍራ በታኅሣሥና በጥር ወራት የአየሩ ጠባይ እጅግ ቀዝቃዛ ነው። ይህን ወቅት በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ሕዝቡም ሁሉ . . . ስለ ታላቁ ዝናብ እየተንቀጠቀጡ [ነበር]” በማለት ይዘግባል። (ዕዝራ 10:9, 13 የ1954 ትርጉም፤ ኤርምያስ 36:22) በዚህ ወቅት እረኞች ከመንጎቻቸው ጋር “በሜዳ” ሊያድሩ አይችሉም።

ኢየሱስ ከሞት ተነስቷል?

“አምላክ ግን [ኢየሱስን] ከሞት አስነሳው።”—የሐዋርያት ሥራ 3:15

ሰዎች ምን ይላሉ?

አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን ጨምሮ ማንም ሰው ከሞት መነሳት አይችልም ብለው ያምናሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ኢየሱስ ለተከታዮቹ ‘ብዙ መከራ እንደሚደርስበትና እንደሚገደል ብሎም በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ’ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 16:21) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ከተገደለና ከተነሳ በኋላ ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች እንደተገለጠላቸው ይዘግባል። (1 ቆሮንቶስ 15:6) እነዚያ የዓይን ምሥክሮች ኢየሱስ ከሞት ስለመነሳቱ አንዳች ጥርጣሬ አልነበራቸውም። ለዚህ እምነታቸው ሲሉ ለመሞትም እንኳ ፈቃደኞች ነበሩ!—የሐዋርያት ሥራ 7:51-60፤ 12:1, 2

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ምድር ገነት እንደምትሆን ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ የሰው ልጆች በሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በር እንደከፈተ ያስተምራል። (መዝሙር 37:11, 29፤ ራእይ 21:3, 4) ኢየሱስና ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው አባቱ ይሖዋ ላሳዩን ፍቅር ምስጋና ይግባቸውና በዚያ ምድራዊ ገነት ውስጥ አስደሳች የሆነ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ አለን።—ዮሐንስ 3:16፤ ሮም 6:23

^ አን.7 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ቃል በቃል ልጆች የምትወልድለት ሚስት እንዳለችው አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ በቀጥታ በአምላክ የተፈጠረ በመሆኑና ከአባቱ ጋር የሚመሳሰል ባሕርይ ስላለው “የአምላክ ልጅ” ብሎ ይጠራዋል።