ተወዳጅ የሆነው የብራዚላውያን ባሕላዊ ምግብ ፋዡአዳ ይባላል

ቱካን የሚባለው ወፍ

የብራዚል ጥንታዊ ነዋሪዎች በአደን፣ ከዱር ምግብ በመሰብሰብና በግብርና የሚተዳደሩ ነበሩ። በኋላም ፖርቹጋላውያን አሳሾች የሮማ ካቶሊክ ሃይማኖትን ይዘው መጡ፤ ከዚህም የተነሳ በአካባቢው ብዙ አብያተ ክርስቲያናትና የጸሎት ቤቶች የተሠሩ ሲሆን አንዳንዶቹ በወርቅ የቅጠል ቅርጾች በተለበጡ የእንጨት ቅርጻ ቅርጾች የተዋቡ ነበሩ።

ከ16ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ ባለው ጊዜ ባሪያዎችን የሚያጓጉዙ መርከቦች አራት ሚሊዮን የሚያህሉ አፍሪካውያንን ወደ ብራዚል ያመጡ ሲሆን በዚያም በእርሻዎች ላይ ተሰማርተው ይሠሩ ነበር። አፍሪካውያኑም ይዘዋቸው የመጡ የራሳቸው የአምልኮ ሥርዓቶች ስለነበሯቸው ማኩምባ እና ካንዶምብላ እንደሚባሉት ያሉ የአፍሮ ብራዚሊያን ሃይማኖቶች ሊፈጠሩ ችለዋል። የአፍሪካውያን ተጽዕኖ በብራዚል ሙዚቃ፣ ውዝዋዜና የምግብ አሠራር ላይ በግልጽ ይታያል።

ፋዡአዳ የሚባለው ከፖርቹጋላውያን የተወሰደው ባሕላዊ ምግብ ሥጋንና ጥቁር አደንጓሬን በማደባለቅ የሚሠራ ወጥ ሲሆን ከሩዝና ከጎመን ጋር ይቀርባል። በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ዘመን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ከአውሮፓ (በዋነኝነት ከጀርመን፣ ከጣሊያን፣  ከፖላንድና ከስፔን) እንዲሁም ከጃፓንና ከሌሎችም አካባቢዎች መጥተው ከሕዝቡ ጋር ተቀላቀሉ።

በዛሬው ጊዜ በመላው ብራዚል ከ11,000 በላይ በሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ 750,000 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። እነሱም ከ800,000 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመራሉ። በቂ የስብሰባ ቦታዎችን ለማዘጋጀት ሲባል ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱ 31 የግንባታ ቡድኖች በአካባቢው ከሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመሆን በየዓመቱ ከ250 እስከ 300 የሚሆኑ የመንግሥት አዳራሾችን ይገነባሉ እንዲሁም ይጠግናሉ። ከመጋቢት 2000 ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል 3,647 የሚያክሉት ተጠናቀዋል።

ይህን ያውቁ ኖሯል?

የአማዞን ወንዝ የውኃ መጠን ከማንኛውም ወንዝ የሚበልጥ ሲሆን ከ6,275 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት አለው

በዓለም ካሉት ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች መካከል ሰፊው ደን የሚገኘው በአማዞን ወንዝ ተፋሰስ ነው