ነገሩ ግራ የሚያጋባ ነው፤ ብዙ ሰዎች ሥራቸውን፣ ቤታቸውን ሌላው ቀርቶ ጡረታቸውን ጭምር የማጣት አደጋ ተደቅኖባቸውም እንኳ ገንዘብ ሊገዛ የሚችለውን ማንኛውንም ነገር መግዛት ይፈልጋሉ።

ማስታወቂያ ለሚሠሩ ግለሰቦች፣ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ማጥመድ ቀላል ነው፤ የማስታወቂያ አዘጋጆች ማራኪ የሆኑ ማስታወቂያዎችን በመጠቀም፣ ትልቅ ቤትና አዲስ ሞዴል መኪና እንዲሁም በታዋቂ አምራቾች የተሠሩ ልብሶች የግድ እንደሚያስፈልጉን ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። ገንዘብ ከሌለንስ? ምንም ችግር የለውም፤ በዱቤ መግዛት እንችላለን! ብዙ ሰዎች ዕዳ በዕዳ ሆነውም እንኳ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ነገር ሀብታም መስሎ መታየት ነው።

ይሁንና እነዚህ ሰዎች፣ ውሎ አድሮ እውነታውን መጋፈጣቸው አይቀርም። ዘ ናርሲሲዝም ኤፒደሚክ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የተሳካለት ሰው ለመምሰል ሲባል ውድ የሆኑ ዕቃዎችን በዱቤ መግዛት፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ስንል ዕፅ ከመውሰድ አይለይም። ሁለቱም ነገሮች መጀመሪያ ላይ ቀላል ከመሆናቸውም ሌላ ሰዎቹ የፈለጉትን እንዳገኙ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ፤ ይሁንና ይህ ስሜት አይዘልቅም። ሁለቱም አካሄድ መጨረሻ ላይ ቤሳ ቤስቲን እንድታጣ የሚያደርግህ ከመሆኑም በላይ ከባድ ጭንቀት ውስጥ ይከትትሃል።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ” ማንጸባረቅ ሞኝነት መሆኑን ያጋልጣል። (1 ዮሐንስ 2:16) እንደ እውነቱ ከሆነ ንብረት የማካበት አባዜ ከተጠናወተን በሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ይኸውም በገንዘብ ሊገዙ የማይችሉትን ነገሮች ልናጣ እንችላለን። ከእነዚህ መካከል እስቲ ሦስቱን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

 1. አንድነት ያለው ቤተሰብ

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ብሪያን * የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት፣ አባቷ ለሥራውና ለገንዘብ ከመጠን ያለፈ ትኩረት እንደሚሰጥ ይሰማታል። እንዲህ ብላለች፦ “የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ እንዲያውም ከዚያ በላይ አለን፤ አባቴ ግን ሁልጊዜ ስለሚጓዝ በአብዛኛው ቤት አይኖርም። የሚጓዘው በሥራው ምክንያት እንደሆነ አውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ለቤተሰቡም ትኩረት መስጠት ያለበት ይመስለኛል!”

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የብሪያን አባት ምን ባለማድረጉ ሊቆጭ ይችላል? ለቁሳዊ ነገሮች ከመጠን ያለፈ ትኩረት መስጠቱ ከልጁ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ምን ተጽዕኖ እያሳደረ ነው? ቤተሰቡ ከገንዘብ የበለጠ ከእሱ የሚፈልጉት ነገር ምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች፦

  • “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተጠምደው . . . ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:10

  • “ጥላቻ ባለበት ጮማ ከመብላት፣ ከምትወዳቸው ሰዎች ጋር አትክልት መብላት ይሻላል።”—ምሳሌ 15:17 ጉድ ኒውስ ትራንስሌሽን

ዋናው ነጥብ፦ አንድነት ያለው ቤተሰብ በገንዘብ ሊገዛ አይችልም። የቤተሰብ አንድነት የሚገኘው አብሮ ጊዜ በማሳለፍ እንዲሁም ለቤተሰብ አባላት ፍቅር በማሳየትና ትኩረት በመስጠት ነው።—ቆላስይስ 3:18-21

 2. እውነተኛ መተማመኛ

የ17 ዓመቷ ሣራ እንዲህ ትላለች፦ “እናቴ፣ ሀብታም ባል እንዳገባ እንዲሁም የባለቤቴ ገንዘብ ባይኖር እንኳ ተደላድዬ መኖር እንድችል ጥሩ ሥራ የሚያስገኝ ትምህርት እንድማር ሁልጊዜ ትነግረኛለች። እናቴን ምንጊዜም የሚያሳስባት፣ ገንዘብ የምታገኝበት መንገድ ብቻ ይመስለኛል።”

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ ከወደፊቱ ጊዜ ጋር በተያያዘ የትኞቹ ጉዳዮች ቢያሳስቡህ ተገቢ ነው? እንዲህ ያለው ሐሳብ መስመሩን ስቶ ተገቢ ያልሆነ ጭንቀት የሚሆነው መቼ ነው? የሣራ እናት፣ ገንዘብ መተማመኛ ሊሆን እንደማይችል እንድትገነዘብ ልጇን ልትረዳት የምትችለው እንዴት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች፦

  • “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸውና ሌባ ሰብሮ ገብቶ ሊሰርቀው በሚችልበት በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት ማከማቸት ተዉ።”—ማቴዎስ 6:19

  • “ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን . . . አታውቁም።”—ያዕቆብ 4:14

ዋናው ነጥብ፦ ገንዘብ ማከማቸት የወደፊት ሕይወትህ አስተማማኝ እንዲሆን አያደርግም። ገንዘብ ሊሰረቅ የሚችል ነገር ከመሆኑም በላይ ከበሽታ ሊያድን ወይም ሞትን ሊያስቀር አይችልም። (መክብብ 7:12) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው፣ እውነተኛ መተማመኛ ማግኘት የሚቻለው አምላክንና ዓላማውን በማወቅ ነው።—ዮሐንስ 17:3

 3. እርካታ ያለው ሕይወት

የ24 ዓመቷ ታንያ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ኑሮን ቀላል ማድረግን አስተምረውናል። ብዙውን ጊዜ ከመሠረታዊ ፍላጎታችን የሚተርፍ ነገር ኖሮን ባያውቅም እኔና መንትያ እህቴ አስደሳች የልጅነት ሕይወት አሳልፈናል።”

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ረክቶ መኖር አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? ለገንዘብ ባለህ አመለካከት ረገድ ለቤተሰብህ ምን ዓይነት ምሳሌ እየሆንህ ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች፦

  • “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ ካለን በእነዚህ ነገሮች ረክተን መኖር ይገባናል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:8

  • “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3

ዋናው ነጥብ፦ በሕይወት ውስጥ ከገንዘብ እንዲሁም ገንዘብ ከሚገዛቸው ነገሮች የበለጠ የሚያስፈልግ ነገር አለ። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ [አይደለም]።” (ሉቃስ 12:15) በሕይወት ውስጥ ከምንም በላይ እርካታ የሚያስገኘው እንደሚከተሉት ላሉ አስፈላጊ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ነው፦

  • የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?

  • ወደፊት ምን ይመጣል?

  • መንፈሳዊ ፍላጎቴን ላሟላ የምችለው እንዴት ነው?

የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው።

^ አን.8 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።