በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ነሐሴ 2013

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ዩናይትድ ስቴትስ

በየቀኑ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሠራዊት የቀድሞ አባላት መካከል ከ20 በላይ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ። በየወሩ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ወታደሮች ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንክብካቤ ከሚያደርግላቸው የቀድሞ ወታደሮች መካከል 950 ገደማ የሚሆኑት ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ ያደርጋሉ።

ቻይና

“ለሥራ ወደ ሌላ የአገሪቱ ክፍል ከሄዱ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆነ ቻይናውያን ሴቶች መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት ከጋብቻ በፊት ያረግዛሉ፤ ይህም ከእነሱ በፊት በነበረው ትውልድ ሳያገቡ ከሚወልዱ [ቻይናውያን] ሴቶች ቁጥር ጋር ሲወዳደር ከፍተኛ ጭማሪ ነው” ሲል ቻይና ዴይሊ ዘግቧል። በተጨማሪም “ሳይጋቡ አብሮ መኖር በቻይናውያን ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ” እንደመጣ ይነገራል።

ግሪክ

በግሪክ የወባ በሽታ እንደገና እያገረሸ ነው፤ ይህ በሽታ በ1974 ከአገሪቱ ሙሉ በሙሉ የጠፋ ያህል ሆኖ ነበር። ለበሽታው ማገርሸት በምክንያትነት የሚጠቀሰው የኢኮኖሚው መውደቅና መንግሥት ለጤና ጥበቃ የሚመድበው በጀት መቀነሱ ነው።

ሕንድ

አንድ ጥናት እንዳመለከተው የምዕራባውያን ባሕል በሕንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ተጽዕኖ እያሳደረ ቢሆንም ጥናት ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል 74 በመቶ የሚሆኑት በራሳቸው “ተዋድደው ከመጋባት” ይልቅ በሌሎች አገናኝነት መጋባትን ይመርጣሉ። ጥናቱ ከተካሄደባቸው መካከል 89 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ካገቡ በኋላ ከልጆቻቸው ጋር ብቻ ከሚኖሩ ይልቅ ሌሎች ዘመዶቻቸውም አብረዋቸው ቢኖሩ እንደሚመርጡ ገልጸዋል።

ጣሊያን

“[የካቶሊክ] ቤተ ክርስቲያን በበለጸገው አውሮፓም ሆነ በአሜሪካ ኃይሏ እየተዳከመ መጥቷል። ባሕላችን ያረጀ ያፈጀ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ትላልቅ ናቸው፤ ገዳሞቻችን ባዶ ሆነዋል፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር የተንዛዛ ነው፤ የአምልኮ ሥርዓቶቻችን የተጋነኑ፣ አልባሳተ ተክህኗችን ደግሞ ከልክ በላይ የተንቆጠቆጡ ናቸው። . . . ቤተ ክርስቲያኒቱ 200 ዓመት ወደኋላ ቀርታለች።”—ከካቶሊክ ካርዲናል ካርሎ ማርያ ማርቲኒ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ፣ ከሞቱ በኋላ ኮሪዬሬይ ዴላ ሴራ በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ