ስዊዘርላንድ

በስዊዘርላንድ የተደረገ አንድ ጥናት እንደገለጸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ከሌሎች ጊዜያት ይልቅ በልደታቸው ቀን የመሞታቸው አጋጣሚ 14 በመቶ ያህል ከፍ ያለ ነው። በአብዛኛው ሰዎች በልደታቸው ቀን በልብ ሕመም የመሞታቸው አጋጣሚ 18 በመቶ ከፍ ያለ ነው፤ ሴቶች በዚህ ዕለት በአእምሯቸው ውስጥ ደም የመፍሰሱ አጋጣሚ ከሌላው ቀን በ21 በመቶ እንደሚበልጥና በልደታቸው ቀን ራሳቸውን የሚያጠፉ ወንዶች ቁጥር ከሌላው ዕለት አንጻር ሲታይ 35 በመቶ ከፍ ያለ እንደሆነ ታይቷል። የሳይንስ ሊቃውንት፣ ራሳቸውን የሚያጠፉና አደጋ የሚያጋጥማቸው ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደረጉት ነገሮች ውጥረትና የአልኮል መጠጥ እንደሆኑ ይገምታሉ። አንዳንድ ባለሙያዎች ግን በዚህ ጥናት አይስማሙም፤ ብዙዎች በልደታቸው ቀን እንደሞቱ የተገለጸው ቀኑ ሲመዘገብ በተፈጠረ ስህተት ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።

እስራኤል

መልከ ቀና ወንዶች ሥራ ሲያመለክቱ ፎቶግራፋቸውን ከማመልከቻቸው ጋር አያይዘው ካስገቡ ለቃለ መጠይቅ የመጠራታቸው አጋጣሚ ከፍ ያለ ይሆናል፤ በሌላ በኩል ግን ቆንጆ ሴቶች የመጠራታቸው አጋጣሚ አነስተኛ ነው። ለምን? የእስራኤል ተመራማሪዎች እንደገለጹት ይህ የሆነው በሠራተኛ አስተዳደር ክፍል ውስጥ የሚሠሩትና ቃለ መጠይቅ የሚደረግላቸውን ሰዎች የሚወስኑት አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች በመሆናቸው ሳይሆን አይቀርም። ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት “ነገሩን ለመቀበል ቢከብድም ሴቶቹ፣ ቆንጆ አመልካቾችን የማይመርጡት በቅናት ምክንያት ነው” ይላል።

ዩናይትድ ስቴትስ

በቅርቡ አንዲት የ82 ዓመት መነኩሲት፣ 63 እና 57 ዓመት ከሆናቸው ወዳጆቻቸው ጋር ሆነው በኦክ ሪጅ፣ ቴነሲ ወደሚገኝ 100 ቶን የሚመዝን የኑክሌር ጥሬ ዕቃ የሚቀመጥበት ግቢ ጥሰው ገብተዋል፤ ፀረ ጦርነት አቋም ያላቸው እነዚህ ሦስት ሰዎች ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት በዚህ ግቢ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሕንፃ ላይ ጦርነትን የሚያወግዙ መፈክሮችን ጽፈዋል። በዓለም ላይ ከፍተኛ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ከሚታሰቡ ቦታዎች አንዱ በሆነው በዚህ ግቢ፣ ጥበቃው ላልቶ መገኘቱ “እጅግ አሳሳቢ” እንደሆነ የኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት ስቲቨን ቹ ተናግረዋል።

አውስትራሊያ

የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የትንባሆ ኩባንያዎች በሲጋራ ፓኮዎች ላይ ደማቅ ቀለሞችንና የንግድ ምልክቶችን እንዳይጠቀሙ አዝዟል። ከአሁን በኋላ ሁሉም የሲጋራ ፓኮዎች ደብዛዛ የሆነ የጥቁር ቡኒ ቀለም ያላቸውና የማጨስን አደገኛነት የሚያሳዩ ምስሎች የተለጠፉባቸው ሊሆኑ ይገባል።