“ይህን ባታደርጉ . . . ከአምላክ ባገኘሁት ሥልጣን መሠረት እመጣባችኋለሁ፤ በሁሉም አቅጣጫና በቻልኩት መንገድ ሁሉ ዘምቼባችሁ በቤተ ክርስቲያኒቱና በግርማዊነታቸው ቀንበር ሥር እንድትወድቁ ብሎም ለእነሱ እንድትገዙ አደርጋለሁ። ሚስቶቻችሁንና ልጆቻችሁን ወስጄ ባሮች አደርጋቸዋለሁ። . . . ንብረታችሁን በሙሉ እዘርፋለሁ፤ እንዲሁም ማንኛውንም በደል እፈጽምባችኋለሁ። . . . በዚህ ምክንያት ለሚደርስባችሁ ሞትም ሆነ ጉዳት ተጠያቂው ግርማዊነታቸው ወይም እኛ ሳንሆን እናንተው ራሳችሁ ናችሁ።”

ይህ አዋጅ እጅግ ምክንያታዊነት ከጎደላቸው መንግሥታዊ አዋጆች አንዱ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ሐሳብ የተወሰደው በስፓንኛ ኤል ሬኩዌሪሚዬንቶ ከሚባለው አዋጅ ሲሆን በ16ኛው መቶ ዘመን የስፔን ወራሪዎች አሜሪካ ሲደርሱ አገሪቱን ለመውረር እንዲመቻቸው ለሕዝቡ ጮክ ብለው ይህን አዋጅ ያነቡ ነበር።

የስፔን ወራሪዎች በአዋጁ መሠረት ከአገሬው ሕዝብ የሚጠብቁት ነገር ምን ነበር? ለምንስ?

ሰዎችን በግዳጅ ወደ ካቶሊክ እምነት ማስቀየር

ኮሎምበስ እግሩ አሜሪካን ከረገጠበት ከ1492 ብዙም ሳይቆይ ስፔንና ፖርቱጋል አዲሶቹን አገሮች በበላይነት የማስተዳደር መብት እንዳላቸው መናገር ጀመሩ። ሁለቱም አገሮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በምድር ላይ የክርስቶስ ወኪል እንደሆነ አድርገው ይቀበሉት ስለነበር በመካከላቸው ለተነሳው ግጭት እልባት እንዲሰጣቸው ጉዳያቸውን ለጳጳሱ አቀረቡ። ቤተ ክርስቲያኒቱም በጳጳሱ አመራር አዲሶቹን አገሮች ለስፔንና ለፖርቱጋል አከፋፈለች፤ ይሁንና ሁለቱም አገሮች ሚስዮናውያን በመላክ የአገሬውን ሰው ወደ ካቶሊክ እምነት እንዲያስለውጡ የሚያዝዝ ቅድመ ሁኔታ አስቀመጠች።

ቅኝ ግዛት ማስፋፋቱ እየቀጠለ ሲሄድ የስፔን መንግሥት፣ ወራሪዎቹ ለሚወስዱት እርምጃ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ፈለገ። የስፔን መንግሥት ርዕሰ ሊቀ ጳጳሳቱን የአምላክ ወኪል እንደሆነ አድርጎ የሚቆጥረው በመሆኑ የስፔን ወራሪዎች የአገሩን ሰዎች ለማባረር፣ ንብረታቸውን ለመቀማትና ነፃነታቸውን ለመንፈግ መብት እንዳላቸው ያምን ነበር።

 በመሆኑም የስፔን መንግሥት የጳጳሱን ውሳኔ ለአገሩ ነዋሪዎች የሚያሳውቅበት ሰነድ አዘጋጀ። በዚህ መሠረት የአገሬው ሕዝብ ክርስትናን የመቀበልና ለስፔን ንጉሥ የመገዛት ግዳጅ ነበረበት። የስፔን መንግሥት፣ ሕዝቡ ይህን አዋጅ ከተቃወመ በእነሱ ላይ በአምላክ ስም “ሕጋዊ” ጦርነት የማካሄድ መብት እንዳለው ይሰማው ነበር።

“ለፍትሕ ሲባል የጭካኔ ድርጊት መፈጸም ትክክል እንደሆነ ይታሰብ ነበር። በዚህም የተነሳ ስፔን ድርጊቷን ፍትሐዊ ለማድረግ ምክንያት መፍጠር ነበረባት።”—ፍራንሲስ ሱሊቫን፣ የካቶሊክ የሥነ መለኮት ፕሮፌሰር

“ፍትሕ የጎደለው፣ ርኩስ፣ አስነዋሪ”

የስፔን መንግሥት አዋጁ እንዲነበብ የሚያደርግበት ምክንያት ራሱን ከሕሊና ወቀሳ ነፃ ማድረግና ለቅኝ ግዛት ወረራው ሕጋዊ ሽፋን መስጠት ነበር። አብዛኛውን ጊዜ የስፔን ወራሪዎች ዘመቻቸውን ከመጀመራቸው በፊት መርከቦቻቸው ላይ እንዳሉ ወይም መሬት ወርደው የአውሮፓውያንን ቋንቋ መረዳት ለማይችሉ የአገሬው ነዋሪዎች አዋጁን ያነቡላቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜ አዋጁ የሚነበበው የአካባቢው ነዋሪዎች በፍርሃት ጥለውት ለሄዱት ባዶ ቤት ነበር።

ሕዝቡ በግዴታ ሃይማኖቱን እንዲለውጥ የተደረገው ሙከራ ለብዙ ሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። ለምሳሌ በ1550 በቺሊ በተደረገ ጦርነት 2,000 አሮኬንያኖች ተገድለዋል። ፔድሮ ደ ቫልዲቭያ የተባለ ተዋጊ በሕይወት ስለቀሩት ሰዎች ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሁለት መቶ የሚሆኑት ደጋግሜ የላኩባቸውን መልእክተኞች ባለመስማታቸውና ግርማዊነትዎ ያወጡትን አዋጅ ባለመቀበላቸው እጆቻቸውና አፍንጫቸው ተቆርጦባቸዋል።” *

አዋጁን ማንበብ የወራሪዎቹን የሕሊና ወቀሳ ጋብ አድርጎ ይሆናል። የስፔኖችን ሃይማኖት ለማስፋፋት ግን የፈየደው ነገር አልነበረም። አዋጁ ላስከተለው ጉዳት የዓይን ምሥክር የነበሩት ባርቶሎሜ ደ ላስ ካሳስ የተባሉ የአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን ሚስዮናዊ እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ አዋጅ እጅግ በጣም ፍትሕ የጎደለው፣ ርኩስ፣ አስነዋሪና ምክንያታዊ ያልሆነ ነበር! በክርስትና ሃይማኖት ላይ ይህ ነው የማይባል ውርደት አምጥቷል።” ጎንዛሎ ፈርናንደዝ ደ ኦቪዶ የተባሉ ታሪክ ጸሐፊ በአሜሪካ ጥንታዊ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸመው ግፍ ሕዝቡ ለክርስትና እምነት ጥሩ ያልሆነ አመለካከት እንዲያዳብር ማድረጉን በምሬት ተናግረዋል።

ታዲያ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች በአንድነት በመሆን በአምላክ ስም ለፈጸሙት ግፍ ተጠያቂው አምላክ ሊሆን ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ “ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ በደልንም መፈጸም ሁሉን ከሚችል አምላክ ይራቅ” ይላል።—ኢዮብ 34:10

^ አን.12 አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ አዋጅ በ1573 ተሽሯል።