ሰይጣን በእርግጥ በእውን ያለ አካል ነው?

“መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው እባብ [ነው]።”—ራእይ 12:9

ሰዎች ምን ይላሉ?

አንዳንዶች ሰይጣን ዲያብሎስ በእውን ያለ አካል ሳይሆን በሰዎች ውስጥ የሚገኝ የክፋት ባሕርይ እንደሆነ ያምናሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሰይጣን በእውን ያለ አካል ነው። ሰይጣን መንፈሳዊ ፍጡር ሲሆን አምላክን በመቃወሙ ዓመፀኛ መልአክ ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ይጠራዋል። (ዮሐንስ 12:31) ይህ አካል ዓላማውን ለማሳካት ‘ሐሰተኛ ምልክቶችን ብሎም ማታለያዎችን’ ይጠቀማል።—2 ተሰሎንቄ 2:9, 10

መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን በሰማይ ከአምላክ ጋር እንደተነጋገረ ይገልጻል። ሰይጣን በሰዎች ውስጥ የሚገኝን የክፋት ባሕርይ የሚወክል ከሆነ ፍጹምና በሥነ ምግባር ረገድ እንከን የለሽ የሆነው አምላክ በውስጡ ካለ ክፋት ጋር እንዴት ሊነጋገር ይችላል? (ዘዳግም 32:4፤ ኢዮብ 2:1-6) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሰይጣን በእውን ያለ አካል እንጂ በሰውኛ የተገለጸ ክፋት አይደለም።

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

ሰይጣን የእሱን መኖር አምነህ እንዳትቀበል የሚፈልግበት ምክንያት ሳይታወቅበት በሕገ ወጥ ድርጊቱ ለመቀጠል ሲል ማንነቱን ከሚደብቅ ወንጀለኛ ጋር ተመሳሳይ ነው። ራስህን ከሰይጣን ጥቃት ለመጠበቅ ከፈለግክ መጀመሪያ ልትወስደው የሚገባ እርምጃ የእሱን መኖር አምነህ መቀበል ነው።

 ሰይጣን የሚኖረው የት ነው?

“ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ . . . ወደ እናንተ ወርዷል።”—ራእይ 12:12

ሰዎች ምን ይላሉ?

ብዙ ሰዎች ሰይጣን የሚኖረው ከመሬት በታች በሚገኝ ገሃነመ እሳት ውስጥ እንደሆነ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ በመጥፎ ሰዎች ልብ ውስጥ እንደሚኖር ይሰማቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሰይጣን መንፈሳዊ ፍጡር ስለሆነ የሚኖረውም በማይታየው ዓለም ውስጥ ነው። ሰይጣን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን አምላክና ታማኝ የሆኑት መላእክቱ ወደሚኖሩበት ስፍራ እንዳሻው እንዲመላለስ ተፈቅዶለት ነበር። (ኢዮብ 1:6) በአሁኑ ጊዜ ግን ከአምላክ ፊት ተባርሮ ከሌሎች ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር በምድር አካባቢ ተወስኖ እንዲኖር ተደርጓል።—ራእይ 12:12

ታዲያ እንዲህ ሲባል ሰይጣን የሚኖረው ምድር ላይ በሚገኝ አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ ነው ማለት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ የጥንቷ ከተማ ጴርጋሞን ‘ሰይጣን የሚኖርባት’ ቦታ ተብላ እንደተገለጸች አንብበህ ይሆናል። (ራእይ 2:13 አዲሱ መደበኛ ትርጉም) ይሁንና ይህ አገላለጽ፣ በዚያ ከተማ የሰይጣን አምልኮ በጣም ተስፋፍቶ እንደነበር የሚያመለክት ነው። በመሆኑም ሰይጣን በአንድ የተወሰነ የምድር ክፍል ላይ አይኖርም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዓለም መንግሥታት ሁሉ’ የእሱ እንደሆኑ ይናገራል።—ሉቃስ 4:5, 6

ሰይጣን ሰዎችን ሊጎዳ ወይም ሊቆጣጠር ይችላል?

“መላው ዓለም . . . በክፉው ኃይል ሥር ነው።”—1 ዮሐንስ 5:19

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ብዙ ሰዎች ሰይጣን በሚያሳድረው አሳሳች ተጽዕኖ በመሸነፍ በእሱ ቁጥጥር ሥር ወድቀዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:14) ይህ ሐቅ የሰው ልጆች በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እንዲሻሻል ማድረግ የተሳናቸው ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ያስችለናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ከዚህም በከፋ ሁኔታ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይናገራል፤ ለምሳሌ እሱም ሆነ ሌሎቹ ዓመፀኛ መላእክት ሰዎችን በመቆጣጠር አካላዊ ጥቃት የሚሰነዝሩባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩ የሚጠቁሙ ታሪኮችን ይዘግባል።—ማቴዎስ 12:22፤ 17:15-18፤ ማርቆስ 5:2-5

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ሰይጣን ኃይል ያለው መሆኑ ሊያስፈራህ አይገባም። በሰይጣን ተጽዕኖ ወይም ቁጥጥር ሥር ላለመውደቅ ከፈለግክ ሰዎችን የሚያጠምደው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ይኖርብሃል፤ እንዲህ ማድረግህ ‘የእሱን ዕቅድ ለማወቅ’ ያስችልሃል። (2 ቆሮንቶስ 2:11) መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ሰይጣን ስለሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ጠቃሚ እውቀት የምታገኝ ሲሆን ይህ ደግሞ የጥቃቱ ሰለባ ከመሆን እንድትድን ያደርግሃል።

ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪነት ያላቸውን ማናቸውም ነገሮች አስወግድ። (የሐዋርያት ሥራ 19:19) ይህም ክታቦችን፣ መናፍስታዊ ድርጊቶችን ወይም ጥንቆላን የሚያበረታቱ ጽሑፎችን፣ ቪዲዮዎችን፣ ሙዚቃዎችንና የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን ይጨምራል።

መጽሐፍ ቅዱስ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” ይላል። (ያዕቆብ 4:7) መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተግባራዊ በማድረግ ራስህን ከሰይጣን መሠሪ ዘዴዎች መጠበቅ ትችላለህ።—ኤፌሶን 6:11-18