በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ግንቦት 2013

 ቃለ ምልልስ | ራኬል ሃል

አንዲት አይሁዳዊት ሴት እምነቷን መለስ ብላ የመረመረችበትን ምክንያት እንደሚከተለው ገልጻለች

አንዲት አይሁዳዊት ሴት እምነቷን መለስ ብላ የመረመረችበትን ምክንያት እንደሚከተለው ገልጻለች

ራኬል ሃል የተወለደችው አይሁዳዊት ከሆነች እስራኤላዊት እናትና ወደ ይሁዲነት ከተለወጠ ኦስትሪያዊ አባት ነው። የእናቷ ወላጆች እስራኤል ነፃነቷን ባገኘችበት በ1948 ወደ እስራኤል ምድር የፈለሱ ጽዮናውያን ነበሩ። ንቁ! መጽሔት ራኬል የአይሁድ እምነቷን ጠለቅ ብላ እንድትመረምር ያደረጋት ምን እንደሆነ ጥያቄ አቅርቦላታል።

እስቲ ስለ አስተዳደግሽ ንገሪን።

የተወለድኩት በ1979 በዩናይትድ ስቴትስ ነበር። ሦስት ዓመት ሲሆነኝ ወላጆቼ ተፋቱ። እናቴ ያሳደገችኝ በአይሁዳውያን ሥርዓትና ወግ ሲሆን የሺቫስ ተብሎ ወደሚጠራው የአይሁድ ትምህርት ቤት አስገባችኝ። ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ወደ እስራኤል ሄድን፤ በዚያም ለአንድ ዓመት የቆየን ሲሆን ኪቡትዝ በሚባለው የኅብረት ሥራ ማኅበር ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ስማር ቆየሁ። ከዚያም እኔና እናቴ ወደ ሜክሲኮ ሄድን።

በአካባቢው ምኩራብ ባይኖርም አይሁዳዊ ልማዶቼን እከተል ነበር። በየሰንበቱ ሻማ አበራለሁ፤ ቶራ የተባለውን መጽሐፋችንን አነባለሁ፤ እንዲሁም በሲደር ወይም በጸሎት መጽሐፍ አማካኝነት እጸልያለሁ። በትምህርት ቤት ለክፍል ጓደኞቼ የመጀመሪያው ሃይማኖት የእኔ ሃይማኖት እንደሆነ እናገር ነበር። በተለምዶ አዲስ ኪዳን እየተባለ የሚጠራውንና በኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎትና ትምህርቶች ላይ የሚያተኩረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንብቤ አላውቅም ነበር። እንዲያውም እናቴ እዚያ ላይ በሚገኙት ትምህርቶች እንዳልበከል ስለሰጋች ፈጽሞ እንዳላነበው አስጠንቅቃኛለች።

ታዲያ አዲስ ኪዳንን ለማንበብ የወሰንሽው ለምንድን ነው?

አሥራ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ የቀለም ትምህርቴን ለመጨረስ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስኩ። እዚያም አንድ የማውቀው ክርስቲያን የሆነ ሰው በኢየሱስ ካላመንኩ ሕይወቴ የተሟላ ሊሆን እንደማይችል ነገረኝ።

እኔም “በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች ተታለዋል” አልኩት።

“አዲስ ኪዳንን አንብበሽ ታውቂያለሽ?” ሲል ጠየቀኝ።

“አይ፣ አንብቤ አላውቅም” ብዬ መለስኩለት።

“ታዲያ ምንም በማታውቂው ጉዳይ ላይ  አስተያየት መስጠት አላዋቂነት አይሆንብሽም?” አለኝ።

ስለማያውቁት ነገር አስተያየት መስጠት ትክክል እንዳልሆነ የማምን ሰው ስለነበርኩ የተናገራቸው ቃላት ልቤን ነኩት። እርማቱን ተቀብዬ የሰጠኝን መጽሐፍ ቅዱስ ቤቴ ወሰድኩና አዲስ ኪዳንን ማንበብ ጀመርኩ።

ያነበብሽው ነገር ምን ተጽዕኖ አሳደረብሽ?

የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች አይሁዳውያን መሆናቸውን ሳውቅ ተገረምኩ። በተጨማሪም ይበልጥ እያነበብኩ ስሄድ ኢየሱስ ደግ እንዲሁም ሰዎችን መበዝበዝ ሳይሆን መርዳት የሚፈልግ ትሑት አይሁዳዊ እንደነበረ አስተዋልኩ። እንዲያውም ወደ ቤተ መጻሕፍት ሄጄ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ መጻሕፍት ተዋስኩ። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አላሳመኑኝም። እንዲያውም አንዳንዶቹ መጻሕፍት ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር እንደሆነ አድርገው የሚገልጹ ሲሆን ይህ ደግሞ ፈጽሞ ሊዋጥልኝ አልቻለም። ደግሞስ ኢየሱስ የጸለየው ወደ ማን ነው? ወደ ራሱ? በተጨማሪም ኢየሱስ ሞቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ አምላክ ሲናገር “አንተ አትሞትም” * ይላል።

ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የቻልሽው እንዴት ነው?

እውነት እርስ በርሱ ሊጋጭ ስለማይችል እውነትን ለማግኘት ቆርጬ ተነሳሁ። ስለሆነም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲደር ሳልጠቀም እያለቀስኩ ከልቤ ወደ አምላክ ጸለይኩ። ጸሎቴን እንደጨረስኩ በሩ ተንኳኳ። ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት የሚጠቀሙበትን አንድ መጽሐፍ ሰጡኝ። ይህ ጽሑፍና ከእነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተከታታይ ያደረግኳቸው ውይይቶች እምነታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ እንዳምን አደረጉኝ። ለምሳሌ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የሥላሴ ክፍል ሳይሆን “የአምላክ ልጅ” * እንዲሁም ‘የአምላክ ፍጥረት መጀመሪያ’ * እንደሆነ ያምናሉ።

ከዚያ በኋላ ብዙም ሳልቆይ ወደ ሜክሲኮ ተመለስኩና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶችን ማጥናት ቀጠልኩ። እነዚህ ትንቢቶች በጣም በርካታ መሆናቸው አስደነቀኝ! እንዲያም ሆኖ ጥርጣሬዬ ጨርሶ አልተወገደልኝም። ‘ትንቢታዊ መግለጫዎቹን የሚያሟላው ኢየሱስ ብቻ ነው?’ እንዲሁም ‘መሲሕ መስሎ ለመኖር የጣረ የተዋጣለት ተዋናይ ቢሆንስ?’ እያልኩ አስብ ነበር።

ታዲያ አመለካከትሽን እንድትለውጪ ያደረገሽ ምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ማንም አታላይ አስመስሎ ሊሠራ የማይችላቸውን ትንቢቶች አሳዩኝ። ለምሳሌ ከ700 ዓመት በፊት ነቢዩ ሚክያስ መሲሑ በቤተልሔም፣ ይሁዳ * እንደሚወለድ ተንብዮ ነበር። የሚወለድበትን ቦታ አስቀድሞ መወሰን የሚችል ሰው ይኖራል? ኢሳይያስ መሲሑ እንደተናቀ ወንጀለኛ ተቆጥሮ እንደሚገደል፣ ይሁንና መቃብሩ ከባለጠጎች ጋር እንደሚሆን ጽፏል። * እነዚህ ትንቢቶች በሙሉ በኢየሱስ ላይ ተፈጽመዋል።

የመጨረሻው ማረጋገጫ የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ መሲሑ የንጉሥ ዳዊት ዘር እንደሚሆን ይናገራል። * የጥንቶቹ አይሁዶች የሕዝብና የግል የትውልድ ሐረጎችን መዝገብ ይይዙ ስለነበር ኢየሱስ ከዳዊት የዘር ሐረግ የመጣ ባይሆን ኖሮ ጠላቶቹ ሐሰተኛነቱን ለማጋለጥ መለከት ያስነፉ ነበር! ይሁንና ኢየሱስ ከዳዊት ጋር የነበረው ዝምድና ሊታበል የማይችል በመሆኑ ይህን ሊያደርጉ አልቻሉም። እንዲያውም በርካታ ሰዎች ‘የዳዊት ልጅ’ * ሲሉ ጠርተውታል።

ኢየሱስ ከሞተ ከ37 ዓመት በኋላ በ70 ዓ.ም. የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን በመደምሰሱ የትውልድ መዛግብቱ ጠፍተዋል ወይም ወድመዋል። በመሆኑም የመሲሑን ማንነት በዘር ሐረጉ ማወቅ እንዲቻል መሲሑ ከ70 ዓ.ም. በፊት መገለጥ ይኖርበታል።

ይህን መገንዘብሽ ምን ለውጥ እንድታደርጊ አነሳሳሽ?

በዘዳግም 18:18, 19 ላይ አምላክ በእስራኤል እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ እንደሚያስነሳ ትንቢት ተነግሯል። አምላክ “ማንም ሰው ነቢዩ በስሜ የሚናገረውን ቃሌን ባይሰማ፣ እኔ ራሴ በተጠያቂነት እይዘዋለሁ” ብሏል። በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያደረግኩት ጥልቅ ጥናት ይህ ነቢይ የናዝሬቱ ኢየሱስ እንደሆነ አሳምኖኛል።