በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉ ምክንያቶች

4. ከሳይንስ ጋር የማይጋጭ መሆኑ

4. ከሳይንስ ጋር የማይጋጭ መሆኑ

በዘመናችን ሳይንስ በእጅጉ መጥቋል። በዚህም ምክንያት ጥንት የነበሩ ጽንሰ ሐሳቦች ለአዲሶቹ ቦታ ለቀዋል። በአንድ ወቅት እውነት ነው ተብሎ ተቀባይነት አግኝቶ የነበረ ነገር አሁን የተሳሳተ አመለካከት እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። የሳይንስ መማሪያ መጻሕፍት ብዙውን ጊዜ እንደገና ተሻሽለው መውጣት ያስፈልጋቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ አይደለም። ሆኖም ይህን መጽሐፍ በጣም አስደናቂ የሚያደርገው ከሳይንስ ጋር የሚስማሙ ነገሮችን መጥቀሱ ብቻ ሳይሆን ከሳይንስ ጋር የሚጋጩ ሐሳቦችን አለመጥቀሱም ጭምር ነው።

ኢሳይንሳዊ ከሆኑ አመለካከቶች የጸዳ ነው።

በጥንት ዘመን በርካታ የተሳሳቱ አመለካከቶች ሰፊ ተቀባይነት አግኝተው ነበር። ምድርን በሚመለከት ብቻ እንኳ ጠፍጣፋ እንደሆነች እንዲሁም ከታች ደግፈው የያዟት ነገሮች እንደነበሩ የሚናገሩ በርካታ አመለካከቶች ነበሩ። ሳይንስ በሽታዎች ስለሚዛመቱበትም ሆነ መከላከል ስለሚቻልበት መንገድ ከማወቁ ከረጅም ጊዜ በፊት ሐኪሞች ውጤታማ ያልሆኑ ብቻ ሳይሆን ለሞት ሊዳርጉ የሚችሉ የሕክምና ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከ1,100 በላይ በሆኑ ምዕራፎቹ ላይ አንድ ጊዜም እንኳ እንዲህ ዓይነት ሳይንሳዊ ያልሆኑ አመለካከቶችን ወይም ጎጂ ተግባሮችን ደግፎ አልተናገረም።

ከሳይንስ አንጻር ትክክል የሆኑ ሐሳቦች።

መጽሐፍ ቅዱስ ከ3,500 ዓመታት በፊት ምድር “በባዶው ላይ” እንደተንጠለጠለች ተናግሮ ነበር። (ኢዮብ 26:7) ኢሳይያስም በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ስለ ‘ምድር ክበብ’ በግልጽ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 40:22) ክብ የሆነችው ምድር ያለአንዳች ድጋፍ ባዶ በሆነው ሕዋ ላይ ተንጠልጥላ እንደምትገኝ የሚናገረው ሐሳብ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር የሚስማማ አይደለም?

በ1500 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ የተጻፈው የሙሴ ሕግ (በመጀመሪያዎቹ አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል) ሕሙማንን በተገለለ ቦታ ስለማስቀመጥ፣ ከአስከሬን ጋር በተያያዘ ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄና፣ ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ ስለሚቻልበት መንገድ የሚገልጽ ትክክለኛ ሐሳብ ይዟል።—ዘሌዋውያን 13:1-5፤ ዘኍልቍ 19:1-13፤ ዘዳግም 23:13, 14

የሳይንስ ሊቃውንት በተራቀቁ ቴሌስኮፖች አማካኝነት ሰማይን አሻቅበው በመመልከት ብሎም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ አጽናፈ ዓለም “የተገኘው” በድንገት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ይሁንና እንዲህ ያለውን ማብራሪያ የወደዱት ሁሉም የሳይንስ ሊቃውንት አይደሉም። አንድ ፕሮፌሰር እንደሚከተለው በማለት ገልጸዋል:- “አጽናፈ ዓለም መጀመሪያ አለው ከተባለ ያንን የሚያስጀምር ማስፈለጉ የግድ ነው፤ ታዲያ እንዲህ ያለ አስደናቂ ውጤት ያለበቂ ምክንያት እንዴት ሊገኝ ይችላል?” ሆኖም ቴሌስኮፕ ከመፈልሰፉ ከረዥም ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው ቁጥሩ ላይ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በማለት በግልጽ ተናግሯል።—ዘፍጥረት 1:1

ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊና ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስስ መጽሐፍ ቢሆንም ከሳይንስ ጋር የሚጋጭ አንድም ሐሳብ የለበትም። እንዲህ ላለው መጽሐፍ ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጠው አይገባም? *

^ አን.9 መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር የሚጋጭ ሐሳብ እንደሌለው የሚያሳዩ ተጨማሪ ምሳሌዎችን ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተሰኘ ብሮሹር ገጽ 18-21 ተመልከት።