ተፈታታኙ ነገር

ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ከየትኛውም ዘመን ይልቅ አሁን፣ ከተለያዩ ሰዎች ጋር በቀላሉ መገናኘት ይቻላል። ይሁንና እንዲህ ያለው ግንኙነት ልባዊ መሆኑ ያጠራጥራል። አንድ ወጣት ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “ጓደኝነታችን የወረት እንደሆነ ይሰማኛል። በሌላ በኩል ግን አባቴ ለአሥርተ ዓመታት አብረው የዘለቁ ጓደኞች አሉት!”

አሁን አሁን ዘላቂና ትርጉም ያለው ጓደኝነት መመሥረት ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

የችግሩ አንዱ መንስኤ ቴክኖሎጂ ሊሆን ይችላል። በስልክ የሚላኩ መልእክቶችና ማኅበራዊ ድረ ገጾች በአካል ሳይገናኙ ጓደኝነትን ማስቀጠል የሚቻል እንዲመስለን ያደርጋሉ። ቁጭ ብሎ የልብን መነጋገር በላይ በላዩ በሚላኩ መልእክቶች ተተክቷል። አርቴፊሻል ማቹሪቲ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች በአካል ተገናኝተው የሚነጋገሩበት አጋጣሚ እየቀነሰ መጥቷል። ተማሪዎች እርስ በርስ ከሚያሳልፉት ጊዜ ይልቅ ኮምፒውተር ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ ጨምሯል።”

አንዳንድ ጊዜ ቴክኖሎጂ ከሌሎች ጋር የተቀራረበ ግንኙነት እንዳለን እንዲሰማን ያደርጋል፤ ሐቁ ግን እንዲህ ላይሆን ይችላል። የ22 ዓመቱ ብራየን * እንዲህ ብሏል፦ “ጓደኞቼን ስለውሏቸው ለመጠየቅ ቅድሚያውን ወስጄ የጽሑፍ መልእክት የምልክላቸው እኔ ብቻ እንደሆንኩ በቅርቡ ተገንዝቤያለሁ። ከዚያም ከእነሱ መካከል ምን ያህሉ ለእኔ መልእክት እንደሚልኩልኝ ማወቅ ስለፈለግኩ መጻፌን አቆምኩ። እውነቱን ለመናገር የጻፉልኝ ጥቂቶች ናቸው። ለካስ ከአንዳንዶቹ ጓደኞቼ ጋር ያሰብኩትን ያህል አንቀራረብም ነበር።”

የጽሑፍ መልእክት መላክም ሆነ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን መጠቀም ከሰዎች ጋር እንድንገናኝ በማስቻል ወዳጅነታችንን ሊያጠናክሩልን አይችሉም ማለት ነው? ይችላሉ፤ ይህ እንዲሆን ግን ከኢንተርኔት በተጨማሪ በአካል ልናገኛቸው ይገባል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ማኅበራዊ ድረ ገጾች ከሌሎች ጋር መገናኘት የምትችልበት ድልድይ ከመሆን ባለፈ ከእነሱ ጋር እንድትቀራረብ አያስችሉህም።

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

የእውነተኛ ጓደኝነትን ትርጉም ተረዳ። መጽሐፍ ቅዱስ ጓደኛ “ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ” እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 18:24) እንዲህ ዓይነት ጓደኛ ቢኖርህ ደስ አይልህም? ለመሆኑ አንተ እንዲህ ዓይነት ጓደኛ ነህ? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ እንድትችል ጓደኛህ እንዲኖረው የምትፈልጋቸውን ሦስት ባሕርያት ጻፍ። ቀጥሎ ደግሞ አንተ ለጓደኞችህ የምታሳያቸውን ሦስት ባሕርያት ጻፍ። ከዚያም እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘በኢንተርኔት ከማገኛቸው ጓደኞቼ መካከል ትልቅ ቦታ የምሰጣቸውን ባሕርያት የሚያንጸባርቁት እነማን ናቸው? እነሱ ስለ እኔ ቢጠየቁ የትኞቹን ባሕርያት እንደሚወዱልኝ ይገልጹ ነበር?’—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ፊልጵስዩስ 2:4

ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ለይ። ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ጓደኝነት የሚመሠርቱት አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ፍላጎት (ለምሳሌ በትርፍ ጊዜ የሚያከናውኗቸው ነገሮች) ስላላቸው ነው። ይሁን እንጂ ተመሳሳይ ፍላጎቶች ከማዳበር ይልቅ የጋራ እሴቶች ያሏችሁ መሆኑ ይበልጥ ጠቃሚ ነው። የ21 ዓመቷ ሊያን “ብዙ ጓደኞች የሉኝም፤ ይሁንና አሁን ያሉኝ ጓደኞች የተሻለ ሰው የመሆን ፍላጎት እንዲያድርብኝ ይረዱኛል” ብላለች።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 13:20

ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ጥረት አድርግ። ከሰዎች ጋር በአካል ተገናኝቶ መነጋገርን ሊተካ የሚችል ምንም ነገር የለም፤ ምክንያቱም የጓደኛህ የድምፅ ቃና ሲቀያየር ልታስተውል እንዲሁም ፊቱ ላይ የሚነበበውን ስሜትና አካላዊ መግለጫዎቹን ልታይ ትችላለህ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ተሰሎንቄ 2:17

ደብዳቤ ጻፍ። ደብዳቤ መጻፍ ጊዜ ያለፈበት ሊመስል ቢችልም ለአንድ ሰው ያልተከፋፈለ ትኩረት የመስጠት ፍላጎቱ እንዳለህ ይጠቁማል፤ ይህ ደግሞ ከልብ እንደምታስብለት ያሳያል። ሰዎች በተለያየ ነገር በተወጠሩበት በዚህ ዘመን እንዲህ ያለ ትኩረት ማግኘት ብርቅ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሼሪ ተርከል የተባለች ደራሲ አሎን ቱጌዘር በተባለው መጽሐፏ ላይ ለእሱ ተብሎ የተጻፈ አንድም ደብዳቤ ደርሶት ስለማያውቅ አንድ ሰው ጠቅሳለች። ይህ ሰው የደብዳቤ ልውውጥ ስለነበረበት ዘመን ሲናገር “በወቅቱ በሕይወት ባልኖርም ያ ጊዜ እንደቀረብኝ ሆኖ ይሰማኛል” ብሏል። ታዲያ በዚህ ‘ጥንታዊ የቴክኖሎጂ ውጤት’ ተጠቅመህ ለምን ጓደኛ አታፈራም?

ዋናው ነጥብ፦ እውነተኛ ጓደኝነት እንዲሁ ከመገናኘት ያለፈ ነገርን ይጨምራል። አንተ እና ጓደኛህ አንዳችሁ ለሌላው ፍቅር፣ አሳቢነት፣ ትዕግሥትና ይቅር ባይነት እንድታሳዩ ይጠይቅባችኋል። እነዚህ ባሕርያት ጓደኝነትን አስደሳች ያደርጉታል። የምትገናኙት በኢንተርኔት አማካኝነት ብቻ ከሆነ ግን እነዚህን ባሕርያት ማሳየት አስቸጋሪ ነው።

^ አን.8 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።