ሰማይ ብዙ ግምታዊ ሐሳቦች የሚሰነዘሩበትና ከፍተኛ ውዝግብ የሚያስነሳ ርዕሰ ጉዳይ ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማይ የሚያስተምረው ትምህርት ብዙዎች ካላቸው አመለካከት በጣም ይለያል።

ሰማይ ምንድን ነው?

አንዳንድ ሰዎች ምን ይላሉ?

ሰዎች ስለ ሰማይ ምንነትና በሰማይ ስለሚከናወነው ነገር የተለያየ እምነት አላቸው። ለምሳሌ ያህል፦

  • ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ሰማይን በተመለከተ የሚሰጠውን ሐሳብ ይጋራሉ፤ ኢንሳይክሎፒዲያው “ጌታን ተቀብለው የሚሞቱ ጻድቃን የኋላ ኋላ የሚኖሩት” በሰማይ እንደሆነ ይገልጻል።

  • ቤንትዞን ክረቪትስ የተባሉት ረቢ የአይሁድ እምነት ከሞት በኋላ ካለው ሕይወት ይልቅ አሁን ባለው ሕይወት ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል። ያም ቢሆን እንዲህ ብለዋል፦ “ነፍስ፣ በሰማይ ታላቅ እፎይታ የምታገኝ ከመሆኑም ሌላ ከመቼውም ጊዜ በላይ አምላክን እንዳወቀችና ከእሱ ጋር እንደተቀራረበች ይሰማታል።” በሌላ በኩል ግን ክረቪትስ “በአይሁድ እምነት፣ ሰዎች ወደ ሰማይ እንሄዳለን ብለው ቢያምኑም የኦሪት መጻሕፍት ስለዚህ ጉዳይ ብዙ የሚናገሩት ነገር የለም” ብለዋል።

  • ሂንዱዎችና ቡድሂስቶች በሰማይ የተለያዩ መንፈሳዊ ዓለማት እንዳሉ ያምናሉ። በእነሱ አመለካከት ሰማይ ጊዜያዊ ማረፊያ ሲሆን ከዚያ በኋላ ሰውየው በምድር ላይ ዳግመኛ ይወለዳል፤ አሊያም ወደ ኒርቫና ማለትም ከሰማይ ወደሚልቅ ደረጃ ይሸጋገራል።

  • አንዳንዶች ሰለ ሰማይ የሚነገርን ማንኛውንም አስተምህሮ አይቀበሉም፤ እንዲያውም የሕፃን ልጅ ጨዋታ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

ሰማይ ብዙ ግምታዊ ሐሳቦች የሚሰነዘሩበት ርዕሰ ጉዳይ ነው

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሰማይ” የሚለው ቃል ከአንድ በላይ ትርጉም አለው። ለምሳሌ ያህል፦

  • ዘፍጥረት 1:20 “ከምድር በላይ በሰማያት ጠፈር ላይ” የሚበርሩ ወፎች እንደተፈጠሩ ይናገራል። በዚህ አገባቡ “ሰማያት” የሚለው ቃል በዓይን የሚታየውን የምድራችንን ከባቢ አየር ያመለክታል።

  • ኢሳይያስ 13:10 ‘የሰማያት ከዋክብትንና የኅብረ ከዋክብት ስብስቦቻቸውን’ ይኸውም ሕዋ የምንለውን ክልል ይጠቅሳል።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሰማያት ስላለው የአምላክ ማደሪያ’ እና ‘በሰማይ ስላሉ መላእክት’ ይናገራል። (1 ነገሥት 8:30፤ ማቴዎስ 18:10) “ሰማያት” እና “ሰማይ” የሚሉት ቃላት ዘይቤያዊ አገላለጾች ሳይሆኑ አንድን የተወሰነ የመኖሪያ ስፍራ የሚያመለክቱ እንደሆኑ ልብ በል። *

“ከሰማይ ተመልከት፤ ከፍ ካለው የቅድስናና የክብር መኖሪያህም ሆነህ እይ።”ኢሳይያስ 63:15

 ጥሩ ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምድር ጊዜያዊ የመኖሪያ ቦታ ማለትም ለጥቂት ጊዜ የምንኖርባትና ከሞትን በኋላ ወደ ሰማይ የምንሽጋገርባት ቦታ እንደሆነች አይናገርም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ለሰው ልጆች መጀመሪያ በነበረው ዓላማ ውስጥ ሞት እንዳልነበረ በግልጽ ይናገራል። እስቲ የሚከተለውን አስብ፦

  • አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት” ብሏቸዋል። (ዘፍጥረት 1:28) ምድር የተፈጠረችው የሰው ልጆች ለዘላለም የሚኖሩባት ቋሚ መኖሪያ እንድትሆን ነው። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የሚሞቱት አምላክን ሳይታዘዙ ከቀሩ ብቻ ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ግን አምላክን አልታዘዙም።—ዘፍጥረት 2:17፤ 3:6

  • የመጀመሪያው ሰው አለመታዘዙ በእሱና በሚስቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በዘሮቻቸውም ላይ ሞት አስከትሏል። (ሮም 5:12) ታዲያ የሰው ዘር ከዚህ በኋላ ተስፋ የለውም ማለት ነው?

  • መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን” ይላል። * (2 ጴጥሮስ 3:13) አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ለምድር የነበረውን ዓላማ ስለሚያሳካ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” የሚለው ተስፋ ፍጻሜውን ያገኛል። (ራእይ 21:3, 4) ይህ ጥቅስ የሚናገረው በሰማይ ስለሚኖረው ሕይወት ነው ወይስ በምድር? አንድ ነገር “ከእንግዲህ ወዲህ . . . አይኖርም” እንዲባል መጀመሪያ ላይ የነበረ መሆን አለበት። ሰማይ ላይ ደግሞ ሞት ኖሮ አያውቅም። በመሆኑም ይህ ጥቅስ የሚናገረው በምድር ላይ ስለሚኖረው ሁኔታ ነው። ለሰው ልጆች መኖሪያ ተደርጋ የተሰጠችው ይህችው ምድር ናት፤ እኛም ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር አብረን ለመኖር የምንጓጓው በዚህችው ምድር ላይ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ከሞት ተነስተው ከወዳጆቻቸው ጋር እንደሚገናኙ ይናገራል።—ዮሐንስ 5:28, 29

ብዙ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማይ ምን እንደሚያስተምር ሲገነዘቡ በጣም ይደነቃሉ። ለምሳሌ ቀደም ሲል የካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበረ ጆርጅ የተባለ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ፣ በምድር ላይ ለዘላለም ሰለ መኖር የሚናገረውን ሐሳብ አጽናኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ወደ ሰማይ ከመሄድ ይልቅ እዚሁ ምድር ላይ መኖራችን ይበልጥ ትርጉም ይሰጣል።” *

“ሰማያት የይሖዋ ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት።”መዝሙር 115:16

^ አን.13 እርግጥ ነው፣ አምላክ ሥጋዊ አካል የለውም፤ ከዚህ ይልቅ መንፈስ ነው። (ዮሐንስ 4:24) በመሆኑም እሱ የሚኖርበት ቦታ እኛ ከምንኖርበት ግዑዝ ጽንፈ ዓለም የተለየ መንፈሳዊ ዓለም መሆን አለበት።

^ አን.19 “አዲስ ምድር” የሚለው አገላለጽ አዲስ ፕላኔትን የሚያመለክት ሳይሆን በምድር ላይ የሚኖረውን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝ ማኅበረሰብ የሚያመለክት ምሳሌያዊ አገላለጽ ነው።—መዝሙር 66:4

^ አን.20 መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ይኸውም 144,000 ሰዎች ብቻ ከኢየሱስ ጋር እንደሚገዙ ይናገራል።—1 ጴጥሮስ 1:3, 4፤ ራእይ 14:1