በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? | ፈተና

ፈተና

ፈተና

አንድ ሰው በፈተና ሲሸነፍ ትዳሩ ሊፈርስ፣ ጤንነቱ ሊቃወስ፣ ሕሊናው ሊወቅሰው እንዲሁም ሌሎች አስከፊ መዘዞች ሊያስከትልበት ይችላል። ራሳችንን ከፈተና መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

አንድ ሰው ተፈተነ ሲባል ምን ማለት ነው?

ማንኛውም ሰው አንድን ነገር በተለይ ደግሞ ስህተት የሆነን ነገር ለማድረግ ከጓጓ መፈተኑ አይቀርም። ለምሳሌ በአንድ የገበያ አዳራሽ ውስጥ ስትዘዋወር አንድ የምትፈልገው ነገር አየህ እንበል። ማንም ሳያይህ ዕቃውን ሰርቀህ ልትወስደው እንደምትችል ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም ሕሊናህ ይህን ማድረግ እንደሌለብህ ይነግርሃል። በመሆኑም ሐሳብህን ቀይረህ መንገድህን ትቀጥላለህ። እንዲህ ማድረግህ ፈተናውን እንዳሸነፍክ ያሳያል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

አንድ ነገር ለማድረግ መፈተንህ በራሱ መጥፎ ሰው እንደሆንክ የሚያሳይ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ፈተና እንደሚያጋጥመን ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 10:13) ዋናው ነገር በምንፈተንበት ጊዜ የምንወስደው እርምጃ ነው። አንዳንዶች በውስጣቸው ያደረውን መጥፎ ምኞት ለማስወገድ ጥረት ስለማያደርጉ ውሎ አድሮ በፈተና ይሸነፋሉ። ሌሎች ግን እንዲህ ያለውን ምኞት ወዲያውኑ ከአእምሮአቸው ያወጡታል።

“እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል።”—ያዕቆብ 1:14

አንድ ሰው አንድ ነገር ለማድረግ ሲፈተን ቶሎ እርምጃ መውሰዱ ጥበብ የሆነው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ መጥፎ ድርጊት የሚመሩትን እርምጃዎች ይናገራል። ያዕቆብ 1:15 “[መጥፎ] ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች” ይላል። በሌላ አባባል አንዲት የፀነሰች ሴት መውለዷ እንደማይቀር ሁሉ በልባችን ውስጥ ያደረውን መጥፎ ምኞት ለማስወገድ ጥረት የማናደርግ ከሆነ ኃጢአት መሥራታችን አይቀርም። ይሁን እንጂ መጥፎ ምኞቶችን መቆጣጠር እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ለእነዚህ ምኞቶች ባሪያ አንሆንም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

 

አእምሯችን መጥፎ ምኞቶችን ሊያስተናግድ እንደሚችል ሁሉ ሊያስወግዳቸውም ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ራሳችንን በሥራ በማስጠመድ፣ ከጓደኛችን ጋር በመጫወት ወይም ጤናማ የሆኑ ነገሮችን በማሰብ ትኩረታችንን ወደ ሌላ አቅጣጫ የምናዞር ከሆነ በውስጣችን የተፀነሰው መጥፎ ምኞት ይወገዳል። (ፊልጵስዩስ 4:8) በተጨማሪም በፈተና መሸነፋችን ሊያስከትል የሚችለውን ስሜታዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ጉዳት ማሰባችን ጠቃሚ ነው። (ዘዳግም 32:29) ከዚህም በላይ ወደ ይሖዋ መጸለያችን በእጅጉ ሊረዳን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ወደ ፈተና እንዳትገቡ ሳታሰልሱ ጸልዩ’ ብሏል።—ማቴዎስ 26:41

“አትታለሉ፤ አምላክ አይዘበትበትም። አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።” —ገላትያ 6:7

 ራሳችሁን ከፈተና ልትጠብቁ የምትችሉት እንዴት ነው?

እውነታው፦

 

ፈተና ማስተዋል የጎደለውን ወይም ጠንቃቃ ያልሆነን ሰው አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ማታለያ ወይም ወጥመድ መሆኑን አትርሳ። (ያዕቆብ 1:14 የግርጌ ማስታወሻ) በተለይ ከፆታ ብልግና ጋር በተያያዘ ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል፤ በዚህ ወጥመድ የተያዘ ሰው ከባድ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል።—ምሳሌ 7:22, 23

መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

 

ኢየሱስ ክርስቶስ “ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:29) እርግጥ ኢየሱስ ቃል በቃል ዓይናችንን አውጥተን እንድንጥል ማሳሰቡ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አምላክን ማስደሰትና የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለግን የአካል ክፍሎቻችንን መግደል በሌላ አባባል መጥፎ ድርጊቶችን ማስወገድ እንዳለብን መናገሩ ነው። (ቆላስይስ 3:5) ይህም አንድ መጥፎ ድርጊት ለመፈጸም ስንፈተን ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይጠይቃል። አንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ “ከንቱ ነገር እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ” ሲል ጸልዮአል።—መዝሙር 119:37

እርግጥ፣ ራስን መግዛት ከባድ ሊሆን ይችላል። ‘ሥጋችን ደካማ’ እንደሆነ የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 26:41) ስለሆነም ስህተት መሥራታችን አይቀርም። ይሁን እንጂ ከልብ ከተጸጸትንና ኃጢአት ልማድ እንዳይሆንብን የቻልነውን ያህል ጥረት ካደረግን “መሐሪና ሩኅሩኅ” የሆነው ፈጣሪያችን ይሖዋ ይቅር ይለናል። (መዝሙር 103:8) ይህ እንዴት የሚያጽናና ነው!

“ያህ ሆይ፣ አንተ ስህተትን የምትከታተል ቢሆን ኖሮ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ማን ሊቆም ይችል ነበር?”—መዝሙር 130:3