በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ቁጥር 4 2017

መልካም ስም ያለው ሰው የሌሎችን አክብሮትና አመኔታ ያተርፋል

‘መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይሻላል’

‘መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይሻላል’

መልካም ስም ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር በመሆኑ በአንዳንድ አገሮች አንድ ሰው መጥፎ ወሬ በማስወራት፣ በጽሑፍ ወይም በመገናኛ ብዙኃን የሌላውን ስም ቢያጠፋ በሕግ ሊጠየቅ ይችላል። ይህ ደግሞ “መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይመረጣል፤ መከበር ከብርና ከወርቅ ይሻላል” የሚለውን የጥንት አባባል ያስታውሰናል። (ምሳሌ 22:1) ይሁንና መልካም ስም ማትረፍ እንዲሁም የሌሎች ሰዎችን አክብሮት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጠቃሚ ሐሳቦችን ማግኘት እንችላለን።

ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መዝሙር 15 ላይ ምን እንደሚል እንመልከት። መዝሙራዊው “[በአምላክ ድንኳን] ውስጥ በእንግድነት የሚስተናገድ ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “ትክክል የሆነውን የሚያደርግ፣ በልቡም እውነትን የሚናገር ሰው ነው። . . . ስም አያጠፋም፤ በባልንጀራው ላይ መጥፎ ነገር አይሠራም፤ የወዳጆቹንም ስም አያጎድፍም። ነውረኛ የሆነን ሰው ሁሉ ይንቃል፤ . . . ጉዳት ላይ ሊጥለው ቢችልም እንኳ ቃሉን አያጥፍም። . . . ጉቦ አይቀበልም።” (መዝሙር 15:1-5) በእነዚህ ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራን ሰው ማክበር ቀላል ነው።

የሌሎችን አክብሮት ለማትረፍ የሚያስችለን ሌላው ባሕርይ ደግሞ ትሕትና ነው። ምሳሌ 15:33 “ትሕትናም ክብርን ትቀድማለች” ይላል። ትሑት የሆኑ ሰዎች በምን ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ይገነዘባሉ፤ ማሻሻያ ለማድረግም ይጥራሉ። በተጨማሪም አንድን ሰው ቅር አሰኝተው ከሆነ ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኞች ናቸው። (ያዕቆብ 3:2) ኩሩ ሰዎች ግን እንዲህ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ በትንሽ በትልቁ ቅር ይሰኛሉ። ምሳሌ 16:18 “ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” ይላል።

አንድ ሰው ስምህን ቢያጠፋስ? በቁጣ ገንፍለህ ወዲያው ምላሽ ትሰጣለህ? እንዲህ ብለህ ራስህን መጠየቅህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፦ ‘ለራሴ ስም ለመሟገት የማደርገው ጥረት ወሬው ይበልጥ እንዲስፋፋ ያደርግ ይሆን?’ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ቢችሉም “ከባልንጀራህ ጋር ስለ ራስህ ጉዳይ ተሟገት” እንጂ “ክስ ለመመሥረት አትቸኩል።” (ምሳሌ 25:8, 9) * ጉዳዩን በጥንቃቄና በሰከነ መንገድ ለመፍታት የምታደርገው ጥረት ለክስ ሂደት ወጪ ከማውጣትም ያድንሃል።

መጽሐፍ ቅዱስ የሃይማኖት መጽሐፍ ብቻ አይደለም። አስተማማኝ የሕይወት መመሪያ የያዘ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ሥራ ላይ የሚያውሉ ሁሉ ግሩም ባሕርያትን ያዳብራሉ፤ ይህም መልካም ስምና አክብሮት እንዲያተርፉ ያስችላቸዋል።

^ አን.5 አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማቴዎስ 5:23, 24 እና 18:15-17 ላይ ይገኛሉ።