በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

ንቁ!  |  ቁጥር 4 2016

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ምን ይላል?

ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጋብቻ በብዙ አገሮች አወዛጋቢ ጉዳይ ነው። ይሁንና የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ እንዲህ ያለው ጋብቻ በአገር አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ መሆኑን በ2015 አውጇል። ከዚያ ወዲህ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ኢንተርኔት የሚቃኙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ጨምሯል። ኢንተርኔት ላይ በብዛት ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል አንዱ “መጽሐፍ ቅዱስ ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች ዘንድ ስለሚፈጸም ጋብቻ ምን ይላል?” የሚለው ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመው ጋብቻ ሕጋዊ ስለ መሆኑ በቀጥታ የሚናገረው ነገር የለም። ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጥያቄ፣ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ምን ይላል?’ የሚለው ነው።

ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ባይመረምሩም የዚህን ጥያቄ መልስ እንደሚያውቁት ይሰማቸዋል፤ ሆኖም የሚሰጧቸው መልሶች እርስ በርስ የሚጋጩ ናቸው! አንዳንዶች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን እንደሚያወግዝ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ‘ባልንጀራህን ውደድ’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ፣ ተቃራኒም ሆነ ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ግንኙነት እንደሚደግፍ ይናገራሉ።—ሮም 13:9

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ቀጥሎ ከቀረቡት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ እውነት የሆነው የትኛው ነው?

  1. መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን ያወግዛል።

  2. መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን ይፈቅዳል።

  3. መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶማውያንን በጭፍን መጥላትን ያበረታታል።

መልስ፦

  1. እውነት። መጽሐፍ ቅዱስ “ግብረ ሰዶማውያን . . . የአምላክን መንግሥት አይወርሱም” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ይህ ጥቅስ ለወንዶችም ለሴቶችም ይሠራል።—ሮም 1:26

  2. ሐሰት። መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚገባቸው በጋብቻ የተሳሰሩ ወንድና ሴት ብቻ እንደሆኑ ያስተምራል።—ዘፍጥረት 1:27, 28፤ ምሳሌ 5:18, 19

  3. ሐሰት። መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶምን የሚያወግዝ ቢሆንም ለግብረ ሰዶማውያን ጭፍን ጥላቻ ማሳየትን፣ በጥላቻ ተነሳስቶ በእነሱ ላይ ዓመፅ መፈጸምን ወይም ማንኛውንም ዓይነት በደል ማድረስን አያበረታታም።ሮም 12:18 [1]

 የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ያምናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንብ ከሁሉ የላቀ እንደሆነ ስለሚያምኑ ሕይወታቸውን በዚያ መሠረት ለመምራት መርጠዋል። (ኢሳይያስ 48:17) [2] ይህ ሲባል የይሖዋ ምሥክሮች ግብረ ሰዶምን ጨምሮ ከማንኛውም ዓይነት የፆታ ብልግና ይርቃሉ ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:18) [3] ይህ የይሖዋ ምሥክሮች የመረጡት የአኗኗር ዘይቤ ሲሆን እንዲህ ዓይነት ምርጫ ማድረግም መብታቸው ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች ወርቃማውን ሕግ በመከተል፣ ሰዎች እንዲያደርጉላቸው የሚፈልጉትን ነገር እነሱም ለሌሎች ያደርጋሉ

ያም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር” ጥረት ያደርጋሉ። (ዕብራውያን 12:14) የይሖዋ ምሥክሮች ግብረ ሰዶምን የማይቀበሉ ቢሆንም ሌሎች ሰዎች የእነሱን አመለካከት እንዲቀበሉ አያስገድዱም፤ በግብረ ሰዶማውያን ላይ በሚፈጸሙ ጭፍን ጥላቻ የተንጸባረቀባቸው ዓመፆች አይካፈሉም፤ ወይም እንደዚህ የመሰሉ ድርጊቶች እንደተፈጸሙ ሲሰሙ አይደሰቱም። የይሖዋ ምሥክሮች ወርቃማውን ሕግ በመከተል፣ ሰዎች እንዲያደርጉላቸው የሚፈልጉትን ነገር እነሱም ለሌሎች ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 7:12

መጽሐፍ ቅዱስ ጭፍን ጥላቻን ያበረታታል?

አንዳንዶች ግን መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች ለግብረ ሰዶማውያን ጭፍን ጥላቻ እንዲያድርባቸው እንደሚያደርግና የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንብ በጥብቅ የሚከተሉ ሰዎች ተቻችሎ በመኖር እንደማያምኑ ይገልጻሉ። ‘መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው፣ ሰዎች ጠባብ አስተሳሰብ በነበራቸው ዘመን ነው’ ብለው ይናገራሉ። ‘በዛሬው ጊዜ ግን ሰዎች ምንም ዓይነት ዘር፣ ዜግነት ወይም የአኗኗር ዘይቤ (ከፆታ ጋር በተያያዘ) ቢኖራቸው እንቀበላቸዋለን’ ይላሉ። እንዲህ የሚሉ ሰዎች፣ ግብረ ሰዶምን አለመቀበል ከእኛ የተለየ የቆዳ ቀለም ያለውን ሰው ለመቀበል ፈቃደኛ ካለመሆን ተለይቶ እንደማይታይ ይገልጻሉ። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ ንጽጽር ተገቢ ነው? አይደለም። ለምን?

ምክንያቱም ግብረ ሰዶምን በመጥላትና ግብረ ሰዶማውያንን በመጥላት መካከል ልዩነት አለ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች ሁሉንም ዓይነት ሰዎች እንዲያከብሩ ይመክራል። (1 ጴጥሮስ 2:17) [4] ይህ ሲባል ግን ክርስቲያኖች ማንኛውንም ዓይነት ድርጊት መቀበል አለባቸው ማለት አይደለም።

አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ማጨስ ጎጂ አልፎ ተርፎም መጥፎ ድርጊት እንደሆነ ይሰማሃል እንበል። የሥራ ባልደረባህ አጫሽ ቢሆንስ? ስለ ማጨስ ያለህ አመለካከት ከእሱ የተለየ ስለሆነ ብቻ ጠባብ አስተሳሰብ እንዳለህ ተደርገህ ትፈረጃለህ? እሱ ሲያጨስ አንተ አለማጨስህ ለእሱ ጭፍን ጥላቻ እንዳለህ የሚያሳይ ነው? የሥራ ባልደረባህ ስለ ማጨስ ያለህን አመለካከት እንድትለውጥ ሊያስገድድህ ቢሞክርስ? እሱ ራሱ ጠባብ አስተሳሰብ እንዳለውና የሌሎችን አመለካከት እንደማያከብር የሚያሳይ አይሆንም?

የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፈረው የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት ሕይወታቸውን ለመምራት መርጠዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዛቸውን ድርጊቶች አይደግፉም። ይሁን እንጂ ከእነሱ የተለየ አኗኗር ባላቸው ሰዎች ላይ አያፌዙም፤ እንዲሁም በደል አይፈጽሙባቸውም።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ደግነት የጎደለው ነው?

ግብረ ሰዶም የመፈጸም ዝንባሌ ስላላቸው ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ ዓይነቱ ዝንባሌ የኖራቸው ተፈጥሯቸው ስለሆነ ነው? ይህ ከሆነ ደግሞ ግብረ ሰዶም መፈጸማቸው ስህተት እንደሆነ መናገር ጭካኔ አይሆንም?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች ግብረ ሰዶም የመፈጸም ፍላጎት የሚያድርባቸው ለምን እንደሆነ አይናገርም፤ ሆኖም አንዳንድ ባሕርያት ሥር የሰደዱ እንደሆኑ ይገልጻል። ያም ሆኖ አምላክን ማስደሰት ከፈለግን ግብረ ሰዶምን ጨምሮ ከአንዳንድ ምግባሮች መራቅ እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—2 ቆሮንቶስ 10:4, 5

አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ደግነት የጎደለው እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ የሚሉት ‘ምኞታችንን መፈጸም አለብን’ እንዲሁም ‘በተለይ የፆታ ስሜት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ስለሆነ ልንቆጣጠረው አይገባም፤ ደግሞም አንችልም’ ብለው ስለሚያስቡ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሰዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር እንደሚችሉ ይናገራል፤ ይህም ለሰዎች ክብር እንደሚሰጥ የሚያሳይ ነው። ከእንስሳት በተለየ መልኩ ሰዎች ምኞታቸውን ከመፈጸም መቆጠብ ይችላሉ።—ቆላስይስ 3:5 [5]

የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት፦ አንዳንድ ባለሙያዎች፣ እንደ ግልፍተኝነት ያሉ ባሕርያት በተፈጥሮ ሊወረሱ እንደሚችሉ ይገልጻሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ለግልፍተኝነት መንስኤ የሆኑትን ነገሮች ለይቶ ባይጠቅስም  አንዳንድ ሰዎች ‘በቀላሉ ቱግ የሚሉ’ እና ‘በቀላሉ የሚቆጡ’ እንደሆኑ ይናገራል። (ምሳሌ 22:24፤ 29:22) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው” የሚል ምክር ይሰጠናል።—መዝሙር 37:8፤ ኤፌሶን 4:31

አብዛኞቹ ሰዎች ይህ ምክር ተገቢ እንዳልሆነ አይሰማቸውም፤ እንዲሁም የግልፍተኝነት ባሕርይ ላላቸው ሰዎች እንዲህ ዓይነት ምክር መሰጠቱ ደግነት የጎደለው እንደሆነ አድርገውም አያስቡም። እንዲያውም ግልፍተኝነት በተፈጥሮ የሚወረስ ባሕርይ እንደሆነ የሚያምኑ ባለሙያዎች እንኳ ሰዎች እንደነዚህ ያሉትን ዝንባሌዎች እንዲቆጣጠሩ ለመርዳት ይጥራሉ።

የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ከሚጋጭ ከማንኛውም ምግባር ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ አቋም አላቸው። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ግብረ ሰዶምን በተመለከተ ብቻ አይደለም፤ ተቃራኒ ፆታ ባላቸው ያልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ግንኙነት በተመለከተም እንዲሁ ይሰማቸዋል። ከእነዚህ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን አካል በመቆጣጠር እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል። ይህም . . . ስግብግብነት በሚንጸባረቅበት ልቅ የፍትወት ስሜት አይሁን።”—1 ተሰሎንቄ 4:4, 5

“አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ”

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስትናን የተቀበሉ ሰዎች የተለያየ አስተዳደግና አኗኗር የነበራቸው ሲሆን አንዳንዶቹም በሕይወታቸው ላይ ጉልህ ለውጥ አድርገዋል። በቆሮንቶስ የነበሩትን ክርስቲያኖች እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ስለ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ቀላጮች ወይም ግብረ ሰዶማውያን’ ከጠቀሰ በኋላ ስለ ቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲናገር “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

መጽሐፍ ቅዱስ “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ” ሲል ግብረ ሰዶማዊ የነበሩና ከዚህ ድርጊት የራቁ ሰዎች ከዚያ በኋላ እንዲህ ዓይነት ምኞት ፈጽሞ አያድርባቸውም ማለቱ ነው? ይህ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ . . . እንዲህ ካደረጋችሁ የሥጋን ምኞት ከቶ አትፈጽሙም” የሚል ምክር ይሰጣል።—ገላትያ 5:16

መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክርስቲያን ተገቢ ያልሆነ ምኞት ፈጽሞ አያድርበትም እንደማይል ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ምኞት ላለመፈጸም እንደሚመርጡ ይናገራል። ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉትን ምኞቶች ይቆጣጠሯቸዋል፤ በእነዚህ ምኞቶች ላይ ማውጠንጠን ድርጊቱን ወደ መፈጸም ሊመራቸው እንደሚችል ስለሚገነዘቡ እንዲህ ከማድረግ ይቆጠባሉ።—ያዕቆብ 1:14, 15 [6]

በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በምኞት እና በድርጊት መካከል ልዩነት እንዳለ በግልጽ ያሳያል። (ሮም 7:16-25) ግብረ ሰዶም የመፈጸም ምኞት ወይም ፍላጎት ያለው አንድ ሰው፣ ከሌሎች መጥፎ ምኞቶች ለምሳሌ ከቁጣ፣ ከምንዝር ወይም ከስግብግብነት ጋር በተያያዘ እንደሚያደርገው ሁሉ ይህን ዓይነቱን ምኞትም በአእምሮው ላለማውጠንጠን ራሱን መቆጣጠር ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 9:27፤ 2 ጴጥሮስ 2:14, 15

የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን የሥነ ምግባር ደንብ የሚደግፉ ቢሆንም ሌሎች የእነሱን አመለካከት እንዲቀበሉ አያስገድዱም። አሊያም ደግሞ ከእነሱ የተለየ አኗኗር ያላቸውን ሰዎች መብት ለማስጠበቅ የወጡ ሕጎችን ለማስቀየር አይሞክሩም። የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት የሰላም መልእክት ሲሆን ሊሰማቸው ለሚፈልግ ሰው ሁሉ መናገር ያስደስታቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 20:20

^ 1. ሮም 12:18፦ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም [ኑሩ]።”

^ 2. ኢሳይያስ 48:17፦ “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።”

^ 3. 1 ቆሮንቶስ 6:18 (የግርጌ ማስታወሻ)፦ “ከፆታ ብልግና ሽሹ!”

^ 4. 1 ጴጥሮስ 2:17፦ “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ።”

^ 5. ቆላስይስ 3:5፦ “በምድር ያሉትን የአካል ክፍሎቻችሁን ግደሉ፤ እነሱም የፆታ ብልግና፣ ርኩሰት፣ ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት . . . ናቸው።”

^ 6. ያዕቆብ 1:14, 15፦ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች።”