ተፈታታኙ ነገር

  • በአባትህ ሥራ ምክንያት ቤተሰባችሁ ወደ ሌላ ቦታ መዛወር አስፈለገው።

  • በጣም የምትቀርበው ጓደኛህ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደ።

  • ታላቅህ አግብቶ ከቤት ሊወጣ ነው።

እንደነዚህ ያሉ ለውጦች ሲያጋጥሙህ ለውጡን መቀበል የምትችለው እንዴት ነው?

አውሎ ነፋስ ሲያወዛውዘው ዘንበል ማለት የሚችል ዛፍ ነፋሱን ተቋቁሞ ማሳለፍ ይችላል። እንደ ዛፉ ሁሉ፣ አንተም ልትቀይራቸው የማትችላቸው ለውጦች ሲያጋጥሙህ “ዘንበል” ማለት በሌላ አባባል ለውጡን ለመልመድ ጥረት ማድረግ ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ከመወያየታችን በፊት ግን ስለ ለውጥ ማወቅ የሚኖርብህን አንዳንድ ነገሮች እንመልከት።

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

ለውጥ የማይቀር ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም [የሰው ልጆች] . . . ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል” በማለት እውነታውን ይናገራል። (መክብብ 9:11) ይዋል ይደር እንጂ የዚህን ጥቅስ እውነተኝነት በሕይወትህ ውስጥ መመልከትህ አይቀርም። እርግጥ ነው፣ ያልተጠበቁ ክስተቶች ሁሉ መጥፎ ናቸው ማለት አይደለም። ደግሞም መጀመሪያ ላይ መጥፎ የሚመስሉ አንዳንዶቹ ለውጦች በኋላ ላይ ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። የሆነ ሆኖ አብዛኞቹ ሰዎች፣ የለመዱት ነገር እንዳለ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፤ ጥሩም ሆነ መጥፎ ለውጥ ሲያጋጥማቸው ለውጡን መቀበል ይከብዳቸዋል።

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆች ለውጥ ውጥረት ሊፈጥር ይችላል። ለምን? አሊክስ * የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በሰውነታችሁ ውስጥ ለውጥ እየተካሄደ ነው። ከዚያ ውጭ ሌሎች ለውጦች ሲያጋጥሟችሁ ይበልጥ ያስጨንቃችኋል።”

ሌላው ምክንያት ደግሞ የሚከተለው ነው፦ ትላልቅ ሰዎች ለውጥ ሲያጋጥማቸው፣ ከዚያ ቀደም ተመሳሳይ ሁኔታ ሲፈጠር እንዴት እንደተቋቋሙት መለስ ብለው ማየት ይችላሉ። ወጣቶች ግን እንዲህ ያለ ተሞክሮ የላቸውም።

ለውጡን መልመድ ትችላለህ። መንፈሰ ጠንካራ የሆነ ሰው፣ ያጋጠመውን መጥፎ ሁኔታ አልፎ ወደ ቀድሞ ሁኔታው መመለስ ወይም ለውጡን መልመድ ይችላል። መንፈሰ ጠንካራ የሆነ ሰው፣ አዲስ ሁኔታን በጽናት መቋቋም የሚችል ከመሆኑም ሌላ እንቅፋት የሚመስሉ ነገሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ መመልከት ይችላል። መንፈሰ ጠንካራ የሆኑ ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ በሕይወታቸው ውስጥ ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው፣ ዕፅ በመውሰድ ወይም የአልኮል መጠጥ በመጠጣት ከችግሩ ለመሸሽ አይሞክሩም።

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

እውነታውን ተቀበል። በሕይወትህ ውስጥ ነገሮች አንተ በምትፈልገው መንገድ እንዲሄዱ እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና ይህ የሚቻል ነገር አይደለም። ጓደኞችህ ወደ ሌላ ቦታ ይዛወሩ ወይም ያገቡ ይሆናል፤ እህቶችህና ወንድሞችህ ሲያድጉ ራሳቸውን ችለው ከቤት መውጣታቸው አይቀርም፤ አሊያም ደግሞ አንተና ቤተሰብህ፣ ወዳጅ ዘመዶቻችሁንና የለመዳችሁትን አካባቢ ትታችሁ ወደ ሌላ ቦታ እንድትሄዱ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ አሉታዊ አመለካከት እንዲያድርብህ ከመፍቀድ ይልቅ እውነታውን መቀበል የተሻለ ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መክብብ 7:10

በወደፊቱ ጊዜ ላይ አተኩር። ቀድሞ በነበረህ ሁኔታ ላይ ማተኮር፣ መኪና ስታሽከረክር በኋላ መመልከቻ መስታወት እያየህ ለመንዳት ከመሞከር ጋር ይመሳሰላል። የኋላ መመልከቻ መስታወቱን አልፎ አልፎ አየት ማድረጉ ጠቃሚ ቢሆንም ከፊት ለፊትህ ባለው ነገር ላይ ትኩረት ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው። ለውጥ በሚያጋጥምህ ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በወደፊቱ ጊዜ ላይ ለማተኮር ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 4:25) ለምሳሌ ያህል፣ በሚቀጥለው ወር ወይም በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ልትደርስበት የምትችል ምን ግብ ማውጣት ትችላለህ?

አዎንታዊ በሆነ ነገር ላይ አተኩር። “መንፈሰ ጠንካራነት የአመለካከት ጉዳይ ነው” በማለት ሎራ የምትባል ወጣት ተናግራለች። “ያላችሁበት ሁኔታ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ለማሰብ ሞክሩ።” አንተስ የተፈጠረው ለውጥ ያስገኘልህን አንድ ጥቅም እንኳ መጥቀስ ትችላለህ?—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መክብብ 6:9

ቪክቶሪያ የምትባል አንዲት ወጣት፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በነበረችበት ጊዜ የቅርብ ጓደኞቿ ሁሉ ወደ ሌላ አካባቢ እንደተዛወሩ ታስታውሳለች። እንዲህ ብላለች፦ “ብቸኝነት ተሰማኝ፤ ‘ሁሉም ነገር እንደነበረው ቢቀጥል’ ብዬ ተመኘሁ። አሁን መለስ ብዬ ሳስበው ግን እድገት ማድረግ የጀመርኩት ያን ጊዜ ነው። እድገት ለማድረግ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተገንዝቤያለሁ። አዳዲስ ጓደኞችን የማፍራት አጋጣሚ እንዳለኝ ያስተዋልኩትም ያን ጊዜ ነው።” —የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 27:10

ቀድሞ በነበረህ ሁኔታ ላይ ማተኮር፣ መኪና ስታሽከረክር በኋላ መመልከቻ መስታወት እያየህ ለመንዳት ከመሞከር ጋር ይመሳሰላል

ለሌሎች መልካም ነገር አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ” ይላል። (ፊልጵስዩስ 2:4) የገጠመህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የሚረዳ አንድ ጥሩ ዘዴ ሌሎችን በችግራቸው መርዳት ነው። አና የተባለች የ17 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እያደግሁ ስሄድ፣ እንደ እኔ ዓይነት ወይም ከእኔ የባሰ ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች መርዳቴ ራሴን እንደሚጠቅመኝ ተገነዘብኩ!”

^ አን.11 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።