የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው አገሮች ከሚያገለግሉ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል በርካታ ነጠላ እህቶች ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ለአሥርተ ዓመታት በውጭ አገር አገልግለዋል። ከዓመታት በፊት፣ ወደ ውጭ አገር ተዛውረው ለማገልገል ሲያስቡ እርምጃ እንዲወስዱ የረዳቸው ምን ነበር? በውጭ አገር በማገልገላቸው ምን ትምህርት አግኝተዋል? ምን ዓይነት ሕይወትስ አሳልፈዋል? ወደ ሌላ አገር ተዛውረው ካገለገሉ ተሞክሮ ያላቸው እህቶች መካከል ለተወሰኑት ቃለ ምልልስ አድርገናል። በጣም አስደሳች በሆነ የአገልግሎት መስክ የመካፈል ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ነጠላ እህቶች ከእነዚህ እህቶች ተሞክሮ ጥቅም እንደሚያገኙ እርግጠኞች ነን። እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ብንሆን የእነሱን ምሳሌ በመመርመር ጥቅም ማግኘት እንችላለን።

ስጋትን ማሸነፍ

አኒታ

ነጠላ እህቶች ‘በእርግጥ ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውሬ በአቅኚነት ማገልገል እችል ይሆን?’ የሚል ስጋት ያድርባቸው ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ በ70ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘው አኒታ፣ ወደ ሌላ አገር ተዛውራ ማገልገል እንደምትችል አይሰማትም ነበር። አኒታ ያደገችው በእንግሊዝ ሲሆን በ18 ዓመቷ አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎችን ስለ ይሖዋ ማስተማር ያስደስተኝ ነበር፤ ሆኖም በውጭ አገር ላገለግል እችላለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም። የውጭ አገር ቋንቋ ተምሬ አላውቅም፤ አዲስ ቋንቋ ልማር እንደምችልም አይሰማኝም ነበር። ስለሆነም በጊልያድ ትምህርት ቤት እንድማር ስጋበዝ ደነገጥኩ። እንደ እኔ ላለ እዚህ ግባ የማይባል ሰው እንዲህ ዓይነት ግብዣ መቅረቡ አስደነቀኝ። ሆኖም ‘ይሖዋ እንደምችል ከተሰማው፣ የማልሞክርበት ምንም ምክንያት የለም’ ብዬ አሰብኩ። ይህ ከሆነ አሁን ከ50 ዓመት በላይ አልፏል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በጃፓን በሚስዮናዊነት እያገለገልኩ ነው።” አኒታ አክላም እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ለወጣት እህቶች ፈገግ ብዬ ‘በጣም አስደሳች በሆነ የአገልግሎት መስክ መካፈል ከፈለጋችሁ ሻንጣችሁን ይዛችሁ ተከተሉኝ!’ እላቸዋለሁ። ብዙዎቹ እንዲህ በማድረጋቸው ደስተኛ ነኝ።”

ራስን ማደፋፈር

አብዛኞቹ በውጭ አገር ያገለገሉ እህቶች መጀመሪያ ላይ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ፈራ ተባ ብለው ነበር። ታዲያ ድፍረት ያገኙት እንዴት ነው?

ሞሪን

አሁን በ60ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘው ሞሪን “ልጅ ሳለሁ፣ ሌሎችን የሚጠቅምና ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት እፈልግ ነበር” በማለት ተናግራለች። ሃያ ዓመት ሲሞላት ተጨማሪ አቅኚዎች ወደሚያስፈልጉበት ወደ ኩዊቤክ፣ ካናዳ ተዛወረች። ሞሪን እንዲህ ብላለች፦ “ከጊዜ በኋላ በጊልያድ ትምህርት ቤት እንድካፈል ተጋበዝኩ፤ ሆኖም ጓደኞቼን ትቼ ወደማላውቀው ቦታ መሄድ አስፈርቶኝ ነበር። አባቴን እያስታመመች የነበረችውን እናቴን ትቶ መሄዱም ቢሆን አስጨንቆኝ ነበር። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ይሖዋን በእንባ ጭምር በመማጸን በርካታ ሌሊቶችን አሳልፌያለሁ። ያሳሰበኝን ነገር ለወላጆቼ ስነግራቸው  ግብዣውን እንድቀበል አበረታቱኝ። በተጨማሪም ጉባኤው ለወላጆቼ ፍቅራዊ ድጋፍ እያደረገ እንዳለ ተመለከትኩ። በተለያዩ መንገዶች የይሖዋን እጅ ማየቴ እኔንም እንደሚንከባከበኝ እንድተማመን ረዳኝ። ከዚያም ለመሄድ ቆረጥኩ!” ሞሪን ከ1979 ጀምሮ ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በምዕራብ አፍሪካ በሚስዮናዊነት አገልግላለች። በአሁኑ ወቅት በካናዳ እናቷን እየተንከባከበችና በልዩ አቅኚነት እያገለገለች ትገኛለች። በውጭ አገር በማገልገል ያሳለፈቻቸውን ዓመታት ስታስታውስ እንዲህ ትላለች፦ “ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ የሚያስፈልገኝን ነገር በሚያስፈልገኝ ጊዜ አሟልቶልኛል።”

ዌንዲ

አሁን በ60ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘውና የአውስትራሊያ ተወላጅ የሆነችው ዌንዲ፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለች በአቅኚነት ማገልገል ጀመረች። አቅኚነት ስለጀመረችበት ጊዜ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ዓይናፋር ስለሆንኩ የማላውቃቸውን ሰዎች ማነጋገር ይከብደኝ ነበር። ሆኖም አቅኚነት ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር መነጋገር እንድችል አስተምሮኛል፤ ይህም ይበልጥ በራሴ እንድተማመን አደረገኝ። በኋላ ግን በራስ መተማመን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ተረዳሁ። አቅኚነት በይሖዋ እንድታመን ረድቶኛል፤ ስለዚህ በውጭ አገር ማገልገል ያን ያህል ከባድ እንዳልሆነ ማሰብ ጀመርኩ። በተጨማሪም ከ30 ዓመት በላይ በጃፓን በሚስዮናዊነት ያገለገለች አንዲት ነጠላ እህት ለሦስት ወር ወደ ጃፓን መጥቼ እንዳገለግል ጋበዘችኝ። ከእሷ ጋር ማገልገሌ ወደ ውጭ አገር የመዛወር ፍላጎቴን አቀጣጠለው።” ዌንዲ በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ከአውስትራሊያ በስተ ምስራቅ 1,770 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኝ ቫንዋቱ የተባለች ደሴት ተዛወረች።

ዌንዲ አሁንም በቫንዋቱ በሚገኝ የርቀት የትርጉም ቢሮ ውስጥ ታገለግላለች። እንዲህ ብላለች፦ “ገለልተኛ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ቡድኖችና ጉባኤዎች ሲመሠረቱ ማየት በጣም ያስደስተኛል። በእነዚህ ደሴቶች ውስጥ ለሚከናወነው የይሖዋ ሥራ ትንሽም ቢሆን አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሌ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ክብር እንደሆነ ይሰማኛል።”

ኩሚኮ (መሃል)

በአሁኑ ጊዜ በ60ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘው ኩሚኮ፣ በጃፓን የዘወትር አቅኚ ሆና ታገለግል በነበረበት ወቅት በአቅኚነት አብራት ታገለግል የነበረችው እህት ወደ ኔፓል እንዲዛወሩ ሐሳብ አቀረበችላት። ኩሚኮ እንዲህ ብላለች፦ “እህት በተደጋጋሚ ትጠይቀኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን እንቢ አልኩ። አዲስ ቋንቋ መማሩና ከአዲስ አካባቢ ጋር መላመዱ አስፈርቶኝ ነበር። ወደ ውጭ አገር ለመዛወር የሚያስፈልገውን ገንዘብ የማግኘቱም ጉዳይ አሳስቦኝ ነበር። እነዚህ ነገሮች እያሳሰቡኝ ሳለ፣ የሞተር ብስክሌት አደጋ ገጠመኝና ሆስፒታል ገባሁ። በዚያ ሳለሁ ‘ከዚህ በኋላስ ምን እንደሚያጋጥመኝ ምን አውቃለሁ? ከባድ በሽታ ሊይዘኝና ወደ ውጭ አገር ሄዶ በአቅኚነት የማገልገል አጋጣሚዬን ከነአካቴው ላጣው እኮ እችላለሁ። ቢያንስ ለአንድ ዓመት እንኳ ወደ ሌላ አገር ሄጄ ማገልገል ያቅተኛል?’ ብዬ አሰብኩ። ይሖዋ እርምጃ እንድወስድ እንዲረዳኝ ተማጸንኩት።” ኩሚኮ ከሆስፒታል ከወጣች በኋላ ኔፓልን ጎበኘች፤ ከዚያም እሷና አብራት በአቅኚነት ታገለግል የነበረችው እህት ወደ ኔፓል ተዛወሩ።

 ኩሚኮ በኔፓል በማገልገል ያሳለፈቻቸውን ወደ አሥር የሚጠጉ ዓመታት በማስታወስ እንዲህ ብላለች፦ “አስጨንቀውኝ የነበሩት ችግሮች ልክ እንደ ቀይ ባሕር በፊቴ ተከፈሉ። የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄጄ ለማገልገል በመወሰኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። ብዙ ጊዜ፣ ወደ አንድ ቤት ሄደን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ስንናገር አምስት ወይም ስድስት ሰዎች ከጎረቤት መጥተው ያዳምጣሉ። ትናንሽ ልጆችም እንኳ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገር ትራክት እንድሰጣቸው በአክብሮት ይጠይቁኛል። ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ባሉበት እንዲህ ያለ ክልል ውስጥ ማገልገል በጣም አስደሳች ነው።”

ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም

ቃለ ምልልስ ያደረግንላቸው እነዚህ ደፋር እህቶች አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመዋቸዋል። ታዲያ እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች የተቋቋሙት እንዴት ነው?

ዳያን

የካናዳ ተወላጅ የሆነችው ዳያን “መጀመሪያ ላይ ከቤተሰብ ርቆ መሄድ በጣም ከብዶኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። አሁን በ60ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ዳያን፣ በአይቮሪ ኮስት (በአሁኗ ኮት ዲቩዋር) ለ20 ዓመታት በሚስዮናዊነት አገልግላለች። “በተመደብኩበት ክልል ውስጥ ላሉት ሰዎች ፍቅር እንዳዳብር እንዲረዳኝ ይሖዋን ጠየቅኩት። ከጊልያድ አስተማሪዎቼ አንዱ የሆነው ወንድም ጃክ ሬድፎርድ፣ መጀመሪያ ላይ ወደ ምድባችን ስንሄድ በዚያ የምናየው ሁኔታ በተለይም የሰዎቹ ድህነት ሊረብሸን አልፎ ተርፎም ሊያስደነግጠን እንደሚችል ነግሮን ነበር። ሆኖም እንዲህ አለን፦ ‘በድህነቱ ላይ ሳይሆን በሰዎቹ ላይ አተኩሩ፤ ፊታቸውንና ዓይናቸውን ተመልከቱ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲሰሙ በሚሰጡት ምላሽ ላይ ትኩረት አድርጉ።’ እኔም እሱ እንዳለው አደረግኩ፤ ይህም የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቶልኛል! ሰዎቹ አጽናኝ የሆነውን የመንግሥቱን መልእክት ሲሰሙ ፊታቸው ይፈካ ነበር!” ዳያን የውጭ አገር ኑሮን እንድትለምድ የረዳት ሌላው ነገር ምን ነበር? “ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መሠረትኩ፤ እንዲሁም ጥናቶቼ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሲሆኑ ማየት የሚያስገኘውን ከፍተኛ ደስታ ማጣጣም ቻልኩ። የተመደብኩበት ክልል ልክ እንደ ቤቴ ሆኖ ይሰማኝ ጀመር። ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት፣ በዚያ መንፈሳዊ እናቶችንና አባቶችን፣ ወንድሞችንና እህቶችን አግኝቻለሁ።”—ማር. 10:29, 30

አሁን በ40ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘው አን ሥራችን በታገደበት አንድ የእስያ አገር ውስጥ በማገልገል ላይ ትገኛለች። እንዲህ ብላለች፦ “በተለያዩ አገሮች ውስጥ ባገለገልኩባቸው ዓመታት፣ ከእኔ በጣም የተለየ አስተዳደግና ባሕርይ ካላቸው እህቶች ጋር ኖሬአለሁ። በእነዚህ ልዩነቶች የተነሳ በመካከላችን አለመግባባት የተፈጠረበት እንዲሁም ስሜቴ የተጎዳበት ጊዜ ነበር። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ፣ አብረውኝ ከሚኖሩት እህቶች ጋር ይበልጥ ለመቀራረብና ባሕላቸውን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እሞክር ነበር። እንዲሁም ይበልጥ አፍቃሪና ምክንያታዊ ለመሆን ጥረት አደርግ ነበር። ይህ ጥረቴ ጥሩ ውጤት በማስገኘቱ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ የዘለቀና ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት መመሥረት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፤ ይህ ወዳጅነት በተመደብኩበት ክልል ለመጽናት አስችሎኛል።”

ኡተ

 አሁን በ50ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው የጀርመን ተወላጅ የሆነችው ኡተ፣ በ1993 በማዳጋስካር በሚስዮናዊነት እንድታገለግል ተመደበች። እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ፣ የአካባቢውን ቋንቋ መማር፣ እርጥበታማ ከሆነው የአየር ሁኔታ ጋር መላመድ እንዲሁም እንደ ወባና አሜባ ካሉ በሽታዎች ጋር መታገል ነበረብኝ። ሆኖም ብዙ ሰዎች ረድተውኛል። በአካባቢው የሚኖሩ እህቶች፣ ልጆቻቸውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ቋንቋውን እንድለምድ በትዕግሥት ረድተውኛል። አብራኝ በሚስዮናዊነት የምታገለግለው እህትም በፍቅር ታስታምመኝ ነበር። ከሁሉ በላይ የረዳኝ ግን ይሖዋ ነው። ያስጨነቀኝን ነገር በመጥቀስ አዘውትሬ ወደ እሱ እጸልይ ነበር። ከዚያም ጸሎቴ መልስ እስኪያገኝ ድረስ አንዳንድ ጊዜ ለቀናት አሊያም ደግሞ ለወራት በትዕግሥት እጠብቃለሁ። ይሖዋ ለችግሮቼ ሁሉ መፍትሔ ሰጥቶኛል።” ኡተ በማዳጋስካር ማገልገል ከጀመረች አሁን 23 ዓመት ሆኗታል።

ሕይወታቸው በእጅጉ ተባርኳል

የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ሄደው እንደሚያገለግሉ ሌሎች አስፋፊዎች ሁሉ በውጭ አገር የሚያገለግሉ ነጠላ እህቶችም እንዲህ ማድረጋቸው ለሕይወታቸው ጣዕም እንደጨመረላቸው ይናገራሉ። እነዚህ እህቶች ካገኟቸው በረከቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ሃይዲ

አሁን በ70ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው የጀርመን ተወላጅ የሆነችው ሃይዲ ከ1968 አንስቶ በአይቮሪ ኮስት (የአሁኗ ኮት ዲቩዋር) በሚስዮናዊነት ስታገለግል ቆይታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከሁሉ በላይ ደስታ የሚሰጠኝ፣ መንፈሳዊ ልጆቼ ‘በእውነት ውስጥ ሲመላለሱ’ ማየት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናኋቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ አሁን አቅኚዎችና የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነዋል። ብዙዎቹ ‘እማማ’ ወይም ‘አያቴ’ ብለው ይጠሩኛል። በአሁኑ ጊዜ ሽማግሌ ሆነው ከሚያገለግሉት የቀድሞ ጥናቶቼ መካከል አንዱ እንዲሁም ሚስቱና ልጆቹ የሚመለከቱኝ እንደ ቤተሰባቸው አባል አድርገው ነው። ይሖዋ ወንድ ልጅ፣ ምራትና ሦስት የልጅ ልጆች ሰጥቶኛል ማለት እችላለሁ።”—3 ዮሐ. 4

ኬረን (መሃል)

አሁን በ70ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው የካናዳ ተወላጅ የሆነችው ኬረን ከ20 ዓመት በላይ በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ አገልግላለች። እንዲህ ብላለች፦ “የሚስዮናዊነት ሕይወት የራሴን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን እንድማር እንዲሁም ይበልጥ አፍቃሪና ታጋሽ እንድሆን ረድቶኛል። በተጨማሪም የተለያየ አገር ዜጋ ከሆኑ ሰዎች ጋር አብሬ መሥራቴ አመለካከቴን አስፍቶልኛል። አንድን ነገር መሥራት የሚቻልበት የተለያየ መንገድ እንዳለ ተምሬያለሁ። እንዲሁም በተለያየ አገር የሚኖሩ ወዳጆችን ማፍራት ትልቅ በረከት ነው! ሁኔታችንና ምድባችን ቢቀየርም ወዳጅነታችን እንደቀጠለ ነው።”

አሁን በ70ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የምትገኘው የእንግሊዝ ተወላጅ የሆነችው ማርግሬት፣ በላኦስ በሚስዮናዊነት አገልግላለች። እንዲህ ብላለች፦ “በሌላ አገር ማገልገሌ፣ ይሖዋ የተለያየ ዘርና አስተዳደግ ያላቸውን ሰዎች እንዴት ወደ ድርጅቱ እንደሚስብ እንድመለከት አስችሎኛል። ይህም እምነቴን በጣም አጠናክሮልኛል። ድርጅቱን እየመራ ያለው ይሖዋ እንደሆነና ዓላማዎቹ ሁሉ መፈጸማቸው እንደማይቀር ሙሉ በሙሉ እንድተማመን ረድቶኛል።”

በእርግጥም በውጭ አገር የሚያገለግሉ ነጠላ እህቶች በክርስቲያናዊ አገልግሎት ትልቅ ሥራ አከናውነዋል። ለዚህም ከፍተኛ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። (መሳ. 11:40) የእነዚህ እህቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ደግሞ የሚያስደስት ነው። (መዝ. 68:11) አንቺስ ሁኔታዎችሽን በማስተካከል በዚህ ርዕስ ውስጥ ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ቀናተኛ እህቶች የተዉትን ምሳሌ መከተል ትችዪ ይሆን? እንዲህ ካደረግሽ ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሰሽ የማየት’ አጋጣሚ ታገኛለሽ።—መዝ. 34:8