በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ልክን ማወቅ ዛሬም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ልክን ማወቅ ዛሬም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

“ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።”—ምሳሌ 11:2

መዝሙሮች፦ 33, 88

1, 2. በአንድ ወቅት ልኩን ያውቅ የነበረ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያጣው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ንጉሥ ሳኦል እስራኤልን መግዛት ሲጀምር ልኩን የሚያውቅና በሌሎች ዘንድ አክብሮት ያተረፈ ሰው ነበር። (1 ሳሙ. 9:1, 2, 21፤ 10:20-24) ሆኖም ንጉሥ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ እብሪተኛ እንደሆነ የሚያሳዩ ድርጊቶችን መፈጸም ጀመረ። በአንድ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስራኤልን ለመውጋት መጥተው ነበር። ነቢዩ ሳሙኤል ወደ ጊልጋል መጥቶ ለይሖዋ መሥዋዕት እንደሚያቀርብ ለሳኦል ነግሮት ነበር። ሳሙኤል ግን ባለው ጊዜ ሳይመጣ ቀረ። እስራኤላውያንም ሳኦልን ጥለውት መሸሽ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ሳኦል ትዕግሥቱ ስላለቀ ሳሙኤልን ከመጠበቅ ይልቅ እሱ ራሱ መሥዋዕቱን አቀረበ፤ ሆኖም እንዲህ የማድረግ ሥልጣን አልነበረውም። ይሖዋም ሳኦል ባደረገው ነገር አልተደሰተም።—1 ሳሙ. 13:5-9

2 ሳሙኤል ወደ ጊልጋል ሲመጣ ሳኦልን ገሠጸው። ሳኦል እርማቱን ከመቀበል ይልቅ ሰበብ አስባብ መደርደር፣ ጥፋቱን በሌሎች ላይ ማላከክ እንዲሁም ድርጊቱን ማቃለል ጀመረ። (1 ሳሙ. 13:10-14) ይህ ድርጊቱና ከዚያ በኋላ የፈጸማቸው ሌሎች ነገሮች የኋላ ኋላ ንግሥናውን አልፎ ተርፎም የይሖዋን ሞገስ እንዲያጣ አድርገውታል። (1 ሳሙ. 15:22, 23) ሳኦል ጅማሬው ጥሩ ቢሆንም ፍጻሜው አሳዛኝ ሆኗል።—1 ሳሙ. 31:1-6

3. (ሀ) በርካታ ሰዎች ልክን ስለማወቅ ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን?

 3 የፉክክር መንፈስ በነገሠበት በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ስኬታማ ለመሆን ከሌሎች ልቀው መገኘት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። በመሆኑም ልክን ማወቅ አስፈላጊ እንዳልሆነ ያስባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከጊዜ በኋላ ወደ ፖለቲካው ዓለም የገባ አንድ ታዋቂ የፊልም ተዋናይ “‘ልክን ማወቅ’ የሚለው ቃል ለእኔ አይሠራም፤ ወደፊትም ቢሆን በዚሁ እንደምቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል። ታዲያ ልክን ማወቅ በአሁኑ ጊዜም በጣም አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው? ልክን ማወቅ ሲባል ምን ማለት ነው? ምን ማለትስ አይደለም? በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን። በቀጣዩ የጥናት ርዕስ ላይ ደግሞ ‘አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ወይም ሌሎች ተጽዕኖ በሚያደርጉብን ጊዜም እንኳ ይህን ባሕርይ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?’ የሚለውን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን።

ልክን ማወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4. የእብሪት ድርጊት የሚባለው ምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ልክን ማወቅን ከእብሪት ጋር እያነጻጸረ ይናገራል። (ምሳሌ 11:2ን አንብብ።) ዳዊት ‘አገልጋይህን ከእብሪት ድርጊቶች ጠብቀው’ በማለት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ልመና አቅርቧል። (መዝ. 19:13) ‘የእብሪት ድርጊት’ የሚባለው ምንድን ነው? ይህ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት በችኮላ ወይም በማን አለብኝነት ያልተፈቀደ ነገር ማድረግን ለማመልከት ነው። በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ሁላችንም እንደ እብሪት ሊቆጠር የሚችል ድርጊት የምንፈጽምበት ጊዜ ይኖራል። ሆኖም ንጉሥ ሳኦል ካጋጠመው ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው በእብሪት ድርጊታችን ከገፋንበት ይዋል ይደር እንጂ ከአምላክ ጋር ያለን ግንኙነት አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም። መዝሙር 119:21 ስለ ይሖዋ ሲናገር “እብሪተኛ የሆኑትን . . . ትገሥጻለህ” ይላል። ይሖዋ እንዲህ የሚያደርገው ለምንድን ነው?

5. የእብሪት ድርጊቶች እንደ ቀላል ስህተት የማይታዩት ለምንድን ነው?

5 የእብሪት ድርጊቶች አንድ ሰው ባለማወቅ እንደሚሠራቸው ስህተቶች ቀለል ተደርገው የሚታዩ አይደሉም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ልክን አለማወቅ ለይሖዋ ሉዓላዊነት አክብሮት አለማሳየት ነው። ሁለተኛ፣ ከተሰጠን ሥልጣን አልፈን የምንሄድ ከሆነ ከሌሎች ጋር መጋጨታችን አይቀርም። (ምሳሌ 13:10) በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የእብሪት ድርጊት እንደፈጸምን ሲታወቅ ለኀፍረት አልፎ ተርፎም ለውርደት ልንዳረግ እንችላለን። (ሉቃስ 14:8, 9) የእብሪት ድርጊት ምንጊዜም መጨረሻው አያምርም። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚናገሩት ልክን ማወቅ ከሁሉ የተሻለው አካሄድ ነው።

ልክን ማወቅ ምንን ይጨምራል?

6, 7. ትሕትና ምንድን ነው? ልክን ከማወቅ ጋር የሚዛመደውስ እንዴት ነው?

6 ልክን ማወቅና ትሕትና በጣም ተቀራራቢ ባሕርያት ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ትሕትና ከኩራትና ከእብሪት ነፃ መሆንን ያመለክታል። (ፊልጵ. 2:3) በጥቅሉ ሲታይ ትሑት ሰው፣ ልኩን የሚያውቅ ማለትም ስለ ችሎታውና ስላከናወነው ነገር ሚዛናዊ አመለካከት ያለው ሰው ነው፤ እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ ስህተቱን አምኖ መቀበልም ሆነ የሌሎችን ሐሳብ ማስተናገድ አይከብደውም። ትሕትና ይሖዋን በጣም ያስደስተዋል።

7 ልክን ማወቅ የሚለውም አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ስለ ራስ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝን እንዲሁም አቅምን ማወቅን ለማመልከት ነው። አንድ ሰው አቅሙን ማወቁ በሚያሳየው ባሕርይ ላይ ለውጥ ያመጣል፤ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ይህ አገላለጽ በዋነኝነት የሚያመለክተው ይህን ሳይሆን አይቀርም።

8. በአስተሳሰብም ሆነ በድርጊት ልክን የማወቅ ችግር እንዳለብን የሚጠቁሙ አንዳንድ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

8 አንድ ሰው ሳይታወቀው፣ በአስተሳሰቡም ሆነ በድርጊቱ ልኩን የማወቅ ችግር እንዳለበት የሚጠቁሙ ነገሮችን ማድረግ ሊጀምር ይችላል፤ ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህን የሚጠቁሙ አንዳንድ ምልክቶችን እስቲ እንመልከት። ለራሳችንም ሆነ ላገኘናቸው መብቶች ከልክ ያለፈ ቦታ እንሰጥ ይሆናል። (ሮም 12:16) ምናልባትም ወደ ራሳችን ተገቢ ያልሆነ ትኩረት መሳብ ጀምረን ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞ. 2:9,  10) አሊያም ደግሞ ያለንን ቦታ፣ ኃላፊነት ካላቸው ሰዎች ጋር ያለንን ቅርርብ ወይም የግል አመለካከታችንን መሠረት በማድረግ ሌሎች የእኛን አቋም እንዲቀበሉ ለመጫን እንፈተን ይሆናል። (1 ቆሮ. 4:6) አብዛኛውን ጊዜ፣ እንዲህ ስናደርግ ልካችንን ማወቅ ተስኖን እብሪተኛ ወደ መሆን እየሄድን እንደሆነ እንኳ ላይታወቀን ይችላል።

9. አንዳንዶችን የእብሪት ድርጊት ወደ መፈጸም የመራቸው ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

9 ማንኛውም ሰው ለጊዜውም ቢሆን በሥጋዊ ምኞቶች ከተሸነፈ ከልኩ አልፎ ሊሄድ ይችላል። ለራስ ክብር እንደ መፈለግ፣ ቅናትና ግልፍተኝነት ያሉት ባሕርያት በርካታ ሰዎችን የእብሪት ድርጊት ወደ መፈጸም መርተዋቸዋል። እንደ አቢሴሎም፣ ዖዝያና ናቡከደነጾር ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች እንዲህ ባሉት የሥጋ ሥራዎች የተሸነፉ ሲሆን ይሖዋም የእብሪት ድርጊት በመፈጸማቸው እንዲዋረዱ አድርጓል።—2 ሳሙ. 15:1-6፤ 18:9-17፤ 2 ዜና 26:16-21፤ ዳን. 5:18-21

10. ሌሎች አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሱበትን ውስጣዊ ግፊት በተመለከተ ፍርድ ከመስጠት መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ስጥ።

10 ይሁንና አንድ ሰው ልኩን እንደማያውቅ የሚያሳይ ድርጊት እንዲፈጽም የሚያደርጉት ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። እስቲ በዘፍጥረት 20:2-7 እና በማቴዎስ 26:31-35 ላይ የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንደ ምሳሌ እንመልከት። አቢሜሌክ እና ጴጥሮስ የፈጸሙት ድርጊት እብሪተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው? ወይስ በዘገባው ላይ የተጠቀሰውን ድርጊት የፈጸሙት ስለ ጉዳዩ ሙሉ መረጃ ስላልነበራቸው አሊያም ስለተዘናጉ ይሆን? ማናችንም ብንሆን የሰውን ልብ ማንበብ አንችልም፤ በመሆኑም ሰዎች አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሱበትን ውስጣዊ ግፊት በተመለከተ ፍርድ ከመስጠት መቆጠባችን ጥበብ ከመሆኑም ሌላ ለእነዚህ ሰዎች ፍቅር እንዳለን ያሳያል።—ያዕቆብ 4:12ን አንብብ።

ቦታችንን ማወቅ

11. ልክን ማወቅ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያለንን ቦታ ከመገንዘብ ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?

11 ልኩን የሚያውቅ ሰው በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ምን ቦታ እንዳለው ይገነዘባል። የሥርዓት አምላክ የሆነው ይሖዋ እያንዳንዳችን በቤቱ ውስጥ የራሳችን ቦታ ወይም የሥራ ድርሻ እንዲኖረን አድርጓል። እያንዳንዱ ሰው በጉባኤ ውስጥ ያለው ሚና የተለያየ ነው፤ ይሁን እንጂ ሁላችንም እናስፈልጋለን። ይሖዋ በጸጋው ለሁላችንም የተለያየ ስጦታ፣ ችሎታ ወይም ተሰጥኦ ለግሶናል። ይሖዋ የሰጠንን ስጦታ፣ ችሎታ ወይም ተሰጥኦ እሱን ለማስከበርና ሌሎችን ለመጥቀም ልናውለው እንችላለን። (ሮም 12:4-8) ይሖዋ የመጋቢነት ኃላፊነት በአደራ ሰጥቶናል፤ ይህ አደራ ይሖዋ እንደሚያከብረንና እምነት እንደሚጥልብን የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ ኃላፊነት ያስከትልብናል።—1 ጴጥሮስ 4:10ን አንብብ።

ኢየሱስ የተወው ምሳሌ የኃላፊነት ለውጥ ሲያጋጥመን የሚጠቅመን እንዴት ነው? (አንቀጽ 12-14ን ተመልከት)

12, 13. በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያለን ቦታ ቢለወጥ መገረም የማይኖርብን ለምንድን ነው?

12 ይሁንና በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያለን ቦታ ሁልጊዜ ቋሚ አይደለም። በጊዜ ሂደት ሊለወጥ ይችላል። እስቲ የኢየሱስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። መጀመሪያ ላይ ከይሖዋ ጋር ብቻውን ነበር። (ምሳሌ 8:22) በኋላም መንፈሳዊ ፍጥረታት፣ ግዑዙ ጽንፈ ዓለምና በመጨረሻም የሰው ልጆች ሲፈጠሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል። (ቆላ. 1:16) ከዚያም ወደ ምድር እንዲመጣ ተደርጓል፤ በዚህ ወቅት መጀመሪያ ላይ የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልገው ሕፃን የነበረ ሲሆን በኋላም አድጎ አዋቂ ሰው ሆኗል። (ፊልጵ. 2:7) ሕይወቱን ለሌሎች መሥዋዕት በማድረግ ከሞተ በኋላ ደግሞ መንፈሳዊ አካል ለብሶ ወደ ሰማይ ተመልሷል። ከዚያም በ1914 የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኗል። (ዕብ. 2:9) ኢየሱስ፣ ወደፊትም ቢሆን በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ ያጋጥመዋል። ለአንድ ሺህ ዓመት ከገዛ በኋላ “አምላክ ለሁሉም ሁሉንም ነገር እንዲሆን” መንግሥቱን ለይሖዋ ያስረክባል።—1 ቆሮ. 15:28

13 እኛም ብንሆን በሕይወታችን ውስጥ የተለያዩ ለውጦች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ እንጠብቃለን፤ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያሉ ለውጦች የሚያጋጥሙን በምናደርጋቸው ውሳኔዎች የተነሳ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ነጠላ የነበረ አንድ ሰው ትዳር ሊመሠርት በኋላም ልጆች ሊወልድ ይችላል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ሲል ኑሮውን  ቀለል ሊያደርግ ይችላል። እነዚህ ውሳኔዎች የሚያስገኙት መብት እንዳለ ሁሉ የሚያስከትሉት ኃላፊነትም አለ። በሕይወታችን ውስጥ የሚከሰቱት ለውጦች፣ በይሖዋ ሥራ የምናደርገው ተሳትፎ እንዲጨምር ወይም እንዲቀንስ ሊያደርጉ ይችላል። ወጣት ነህ ወይስ በዕድሜ የገፋህ? የጤንነትህ ሁኔታስ እንዴት ነው? ይሖዋ እያንዳንዳችን በእሱ አገልግሎት ውስጥ የተሻለ አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችልበትን አቅጣጫ ምንጊዜም ያስባል። ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ነው፤ እንዲሁም የምናደርገውን ነገር ሁሉ ከፍ አድርጎ ይመለከታል።—ዕብ. 6:10

14. ልካችንን ማወቃችን ምንጊዜም እርካታና ደስታ እንድናገኝ የሚረዳን እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ በተሰጠው የሥራ ምድብ ሁሉ ደስተኛ ነበር፤ እኛም ደስተኛ መሆን እንችላለን። (ምሳሌ 8:30, 31) ልኩን የሚያውቅ ሰው በተሰጠው ሥራ ወይም ኃላፊነት ረክቶ ይኖራል። መብት ስለማግኘት አይጨነቅም፤ ወይም ሌሎች ባገኙት መብት ላይ አያተኩርም። ከዚህ ይልቅ አሁን ያለውን ኃላፊነት ከይሖዋ እንዳገኘው አድርጎ ስለሚመለከተው ከሥራው ደስታና እርካታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል። እንዲሁም ሌሎች ከይሖዋ ለተቀበሉት መብት ወይም ኃላፊነት ከልብ የመነጨ አክብሮት እንዳለው ያሳያል። ልካችንን ማወቃችን ለሌሎች የሚገባቸውን ክብርና ድጋፍ በመስጠት ደስታ እንድናገኝ ይረዳናል።—ሮም 12:10

ልክን ማወቅ ምን ማለት አይደለም?

15. ጌድዮን ልክን በማወቅ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

15 ጌድዮን ልክን በማወቅ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። የይሖዋ መልአክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገለጠለት ወቅት ጌድዮን ያን ያህል ቦታ የሚሰጠው ሰው እንዳልሆነና የተሰጠውን ተልእኮ ለመቀበል ብቃት እንደሌለው  ተናግሯል። (መሳ. 6:15) ይሖዋ የሰጠውን ኃላፊነት ከተቀበለ በኋላ ደግሞ ሥራው ምን ነገሮችን እንደሚያካትት በሚገባ ለመረዳት እንዲሁም የይሖዋን አመራር ለማግኘት ጥረት አድርጓል። (መሳ. 6:36-40) ጌድዮን ደፋርና ቆራጥ የነበረ ቢሆንም ማንኛውንም ነገር የሚያከናውነው በጥንቃቄና በማስተዋል ነበር። (መሳ. 6:11, 27) የተሰጠውን ተልእኮ ለራሱ ክብር ለማግኘት አልተጠቀመበትም። ከዚህ ይልቅ ተልእኮውን እንዳጠናቀቀ በደስታ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመልሷል።—መሳ. 8:22, 23, 29

16, 17. ልኩን የሚያውቅ ሰው መንፈሳዊ እድገት ስለማድረግ ሲያስብ ምን ነገር ግምት ውስጥ ያስገባል?

16 ልካችንን ማወቅ አለብን ሲባል ተጨማሪ መብቶች ለማግኘት መጣጣርም ሆነ መብቶች ሲሰጡን መቀበል አይኖርብንም ማለት አይደለም። ቅዱሳን መጻሕፍት ሁላችንም እድገት ለማድረግ እንድንጣጣር ያበረታታሉ። (1 ጢሞ. 4:13-15) ታዲያ አንድ ሰው እድገት አደረገ የሚባለው አዲስ ኃላፊነት ሲቀበል ብቻ ነው? እንዲህ ብሎ መደምደም ምክንያታዊ አይደለም። አሁን ያለን የአገልግሎት መብት ምንም ይሁን ምን፣ የይሖዋን በረከት እስካገኘን ድረስ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ እንችላለን። ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ የሰጠንን ችሎታዎች ማሻሻል እንዲሁም መልካም ሥራዎችን በማከናወን ረገድ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን።

17 ልኩን የሚያውቅ ሰው አንድ አዲስ ኃላፊነት ከመቀበሉ በፊት ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ከእሱ ምን እንደሚጠበቅ ለማወቅ ጥረት ያደርጋል። ከዚያም ያለበትን ሁኔታ በሐቀኝነት ይመረምራል። ለምሳሌ ያህል፣ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ችላ ሳይል ተጨማሪ ሥራ ወይም ኃላፊነት መቀበል ይችላል? አዲሱን ኃላፊነቱን መቀበል እንዲችል አሁን ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹን ለሌሎች መስጠት ይችላል? ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱም እንኳ ‘አይ’ የሚል መልስ ከሰጠ፣ በተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሌላ ሰው ይህን ኃላፊነት ቢቀበል ይመረጣል። በጸሎት በመታገዝ ያለንበትን ሁኔታ በሐቀኝነት መመርመራችን አቅማችንን ያላገናዘበ ነገር ከማድረግ እንድንቆጠብ ይረዳናል። ልካችንን ማወቃችን ከአቅማችን በላይ የሆነን ነገር ‘አልችልም’ ማለት እንዲቀለን ያደርጋል።

18. (ሀ) ልካችንን ማወቃችን አንድ አዲስ ኃላፊነት ወይም መብት ሲሰጠን ምን ለማድረግ ያነሳሳናል? (ለ) ሮም 12:3 ልካችንን እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

18 ስለ ጌድዮን ከሚናገረው ዘገባ መመልከት እንደሚቻለው አንድ አዲስ ኃላፊነት ስንቀበል ሊሳካልን የሚችለው የይሖዋን አመራርና በረከት ካገኘን ብቻ ነው። ይሖዋም ቢሆን ‘ልካችንን አውቀን ከእሱ ጋር እንድንሄድ’ ግብዣ አቅርቦልናል። (ሚክ. 6:8) በመሆኑም ምንጊዜም ቢሆን አዲስ ኃላፊነት ስንቀበል ወደ ይሖዋ መጸለይ እንዲሁም እሱ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል። አረማመዳችን ፍጹም ከሆነው የይሖዋ እርምጃ ጋር እንዲስማማ ማድረግን መማር አለብን። ‘ታላቅ የሚያደርገን’ የይሖዋ ትሕትና እንጂ የእኛ ችሎታ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። (መዝ. 18:35) ልካችንን አውቀን ከአምላክ ጋር መሄዳችን ራሳችንን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርገን ወይም በጣም ዝቅ አድርገን እንዳንመለከት ይረዳናል።—ሮም 12:3ን አንብብ።

19. ልክን ማወቅን ማዳበር ያለብን ለምንድን ነው?

19 ልኩን የሚያውቅ ሰው ለይሖዋ የሚገባውን ክብር ይሰጣል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ፈጣሪና የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ነው። (ራእይ 4:11) ልክን ማወቅ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ በተሰጠን ቦታ ረክተን እንድንኖርና ውጤታማ እንድንሆን ይረዳናል። ልካችንን ማወቃችን አክብሮት የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም ይጠብቀናል፤ እንዲሁም በይሖዋ ሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲኖር ያደርጋል። በተጨማሪም ሌሎች ከእኛ እንደሚሻሉ አድርገን እንድናስብና ጠንቃቃ በመሆን ከባድ ስህተቶችን ከመፈጸም እንድንርቅ ያስችለናል። ከዚህ አንጻር ልክን ማወቅ ዛሬም ቢሆን ለሁሉም የአምላክ ሕዝቦች አስፈላጊ ባሕርይ ነው፤ ይሖዋም ይህን ባሕርይ የሚያዳብሩ ሰዎችን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ይሁንና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ ይህን ባሕርይ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በቀጣዩ የጥናት ርዕስ ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን።