በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ግንቦት 2017

ጋይዮስ ወንድሞቹን የረዳበት መንገድ

ጋይዮስ ወንድሞቹን የረዳበት መንገድ

ጋይዮስ እና በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የነበሩ ሌሎች ክርስቲያኖች ተፈታታኝ ነገሮች አጋጥመዋቸው ነበር። በወቅቱ የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ ሰዎች ጉባኤዎችን ለማዳከምና ለመከፋፈል ጥረት ያደርጉ ነበር። (1 ዮሐ. 2:18, 19፤ 2 ዮሐ. 7) ዲዮጥራጢስ የተባለ ግለሰብ ደግሞ ስለ ሐዋርያው ዮሐንስ እና ስለ ሌሎች ክርስቲያኖች “ክፉ ቃላት” ይናገር ነበር፤ በተጨማሪም ተጓዥ ክርስቲያኖችን በእንግድነት የማይቀበል ሲሆን ሌሎችም የእሱን ምሳሌ እንዲከተሉ ለማድረግ ይጥር ነበር። (3 ዮሐ. 9, 10) ሐዋርያው ዮሐንስ ለጋይዮስ ደብዳቤውን ሲጽፍ የነበረው ሁኔታ ይህን ይመስላል። በ98 ዓ.ም ገደማ የተጻፈው ይህ የሐዋርያው ደብዳቤ “ሦስተኛ ዮሐንስ” በሚል ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል።

ጋይዮስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገሉን ቀጥሎ ነበር። ይሁንና ጋይዮስ ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ የጋይዮስን ምሳሌ መከተል የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ዮሐንስ የጻፈው ደብዳቤስ ይህን ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?

ለውድ ጓደኛ የተጻፈ ደብዳቤ

የሦስተኛ ዮሐንስ ፀሐፊ፣ ራሱን የጠራው “ሽማግሌው” በማለት ነው። ተወዳጅ መንፈሳዊ ልጁ የሆነው ጋይዮስ፣ ይህን በማየት ብቻ መልእክቱ የመጣው ከሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑን ማወቅ ይችል ነበር። ዮሐንስ ስለ ጋይዮስ ሲናገር “ከልብ ለምወደው ለተወዳጁ” በማለት ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ጠርቶታል። ዮሐንስ በመቀጠልም ጋይዮስ ጥሩ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ እንዳለ ሁሉ አካላዊ ጤንነቱም ጥሩ እንደሚሆን ያለውን ተስፋ ገልጿል። ይህ፣ ዮሐንስ ለጋይዮስ ያለውን አድናቆትና አሳቢነት የሚገልጽ እንዴት ያለ ግሩም ሐሳብ ነው!—3 ዮሐ. 1, 2, 4

ጋይዮስ የጉባኤ የበላይ ተመልካች ሊሆን ይችላል፤ በእርግጥ በደብዳቤው ላይ ይህን በቀጥታ የሚናገር ሐሳብ አናገኝም። ጋይዮስ የማያውቃቸውን ወንድሞች እንኳ ተቀብሎ በማስተናገዱ ዮሐንስ አመስግኖታል። ጋይዮስ ይህን ማድረጉ ታማኝነቱን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ዮሐንስ ተሰምቶታል፤ ምክንያቱም እንግዳ ተቀባይነት ከጥንት ጀምሮ የአምላክ አገልጋዮች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነው።—ዘፍ. 18:1-8፤ 1 ጢሞ. 3:2፤ 3 ዮሐ. 5

ጋይዮስ፣ ወንድሞችን በእንግድነት በመቀበሉ ዮሐንስ ያደነቀው መሆኑ የሚጠቁመው ነገር አለ፤ ይኸውም ክርስቲያኖች ሐዋርያው ዮሐንስ ካለበት ቦታ ወደተለያዩ ጉባኤዎች አዘውትረው እንደሚመላለሱና ስላጋጠማቸው ነገር ለዮሐንስ ይነግሩት እንደነበረ ያሳያል። ዮሐንስ ስለ ጉባኤዎቹ ይሰማ የነበረው በዚህ መንገድ ሳይሆን አይቀርም።

ከቦታ ቦታ የሚጓዙ ክርስቲያኖች የእምነት አጋሮቻቸው ዘንድ ማረፍ ይመርጡ እንደነበር ግልጽ ነው። ምክንያቱም በወቅቱ የነበሩት የእንግዳ ማረፊያዎች መጥፎ ስም ያተረፉ ከመሆኑም ሌላ መስተንግዷቸውም ጥሩ አልነበረም፤ በዚያ ላይ ደግሞ የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ነበሩ። በመሆኑም ጥበበኛ የሆኑ ተጓዦች በተቻለ መጠን ወዳጆቻቸው ጋ ለማረፍ ይፈልጉ  ነበር፤ ከቦታ ቦታ የሚጓዙ ክርስቲያኖችም የእምነት አጋሮቻቸው ዘንድ ያርፉ ነበር።

“የወጡት ለስሙ ሲሉ ነው”

ጋይዮስ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ አሁንም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያሳይ ዮሐንስ አበረታቶታል፤ ሐዋርያው “አምላክ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታ [ተጓዦቹን] ሸኛቸው” ሲል ጠይቆታል። እዚህ ላይ ተጓዦቹን መሸኘት ሲባል ለቀጣዩ ጉዟቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ማሟላትን የሚያመለክት ነው። ጋይዮስ ከዚያ ቀደም ለተቀበላቸው እንግዶች እንዲህ እንዳደረገ ግልጽ ነው፤ እንግዶቹ ስለ ጋይዮስ ፍቅርና እምነት ለዮሐንስ መናገራቸው ይህን ያሳያል።—3 ዮሐ. 3, 6

እነዚህ እንግዶች ሚስዮናውያን፣ የዮሐንስ መልእክተኞች አሊያም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሊሆኑ ይችላሉ። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ እነዚህ ሰዎች ጉዞውን ያደረጉት ለምሥራቹ ሲሉ ነበር። ዮሐንስ ስለ እነሱ ሲናገር “የወጡት ለስሙ ሲሉ ነው” ብሏል። (3 ዮሐ. 7) ዮሐንስ ቀደም ሲል ስለ አምላክ ስለጠቀሰ (ቁጥር 6ን ተመልከት) “ለስሙ ሲሉ” የሚለው አገላለጽ የይሖዋን ስም የሚያመለክት ይመስላል። በመሆኑም እነዚህ ወንድሞች የክርስቲያን ጉባኤ አባል ከመሆናቸው አንጻር ጥሩ አቀባበል ሊደረግላቸው ይገባል። ዮሐንስ እንደተናገረው “በእውነት ውስጥ አብረን የምንሠራ እንሆን ዘንድ እንዲህ ላሉ ሰዎች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የማሳየት ግዴታ አለብን።”—3 ዮሐ. 8

አስቸጋሪውን ሁኔታ እንዲቋቋም የተሰጠ እርዳታ

ዮሐንስ ለጋይዮስ ደብዳቤ ለመጻፍ የተነሳሳው እሱን ለማመስገን ብቻ አይደለም። ጋይዮስ ያጋጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲወጣ ሊረዳው ስለፈለገም ጭምር ነው። ዲዮጥራጢስ የተባለው የጉባኤው አባል ተጓዥ ክርስቲያኖችን በእንግድነት ለመቀበል አልፈለገም ነበር፤ ይህን ያደረገበት ምክንያት ምን እንደሆነ አይታወቅም። ዲዮጥራጢስ፣ ሌሎችም እንግዶችን እንዳይቀበሉ ለመከላከል ይሞክር ነበር።—3 ዮሐ. 9, 10

ታማኝ ክርስቲያኖች አጋጣሚው ቢኖራቸውም እንኳ ዲዮጥራጢስ ጋ ማረፍ እንደማይፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ዲዮጥራጢስ በጉባኤው ውስጥ የመሪነት ቦታ ለመያዝ የሚፈልግ ከመሆኑም በላይ ከዮሐንስ የመጣ ማንኛውንም ነገር በአክብሮት አይቀበልም ነበር፤ በተጨማሪም ስለ ሐዋርያውና ስለ ሌሎች ክፉ ቃላት ይለፈልፍ ነበር። ዮሐንስ፣ ዲዮጥራጢስን ሐሰተኛ አስተማሪ ብሎ በቀጥታ ባይጠራውም ዲዮጥራጢስ የሐዋርያውን ሥልጣን እየተቃወመ እንደነበር ግልጽ ነው። ዲዮጥራጢስ፣ ትልቅ ቦታ ለማግኘት የነበረው ፍላጎትና ከክርስቲያኖች የማይጠበቅ አመለካከት መያዙ በታማኝነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነበር። የዲዮጥራጢስ ሁኔታ፣ ሥልጣን ለማግኘት የሚመኙና ትዕቢተኛ የሆኑ ሰዎች በጉባኤ ውስጥ ክፍፍል ለመፍጠር ጥረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ዮሐንስ “መጥፎ የሆነውን ነገር አትከተል” በማለት ለጋይዮስ የሰጠው ምክር ለሁላችንም ይሠራል።—3 ዮሐ. 11

መልካም ለማድረግ የሚያነሳሳ ግሩም ምክንያት

ዮሐንስ፣ ከዲዮጥራጢስ በተቃራኒ ድሜጥሮስ የተባለ አንድ ክርስቲያን ጥሩ ምሳሌ እንደሆነ ጠቅሷል። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሁሉም ወንድሞች ስለ ድሜጥሮስ በሚገባ መሥክረዋል፤ . . . እንዲያውም እኛም ጭምር ስለ እሱ እየመሠከርን ነው፤ የምንሰጠው ምሥክርነት ደግሞ እውነት እንደሆነ ታውቃለህ።” (3 ዮሐ. 12) ድሜጥሮስ የጋይዮስ እርዳታ አስፈልጎት ይሆናል፤ በመሆኑም ሐዋርያው፣ ድሜጥሮስን ለማስተዋወቅና እንዲቀበሉት ለማሳሰብ ይህን ደብዳቤ ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል። ደብዳቤውን ለጋይዮስ ያደረሰውም ድሜጥሮስ ራሱ ሊሆን ይችላል። ድሜጥሮስ ከዮሐንስ መልእክተኞች አንዱ ምናልባትም ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከሆነ ዮሐንስ የጻፈውን ነገር ይበልጥ አብራርቶለት ይሆናል።

ጋይዮስ እንግዳ ተቀባይ መሆኑ እየታወቀ ይህን ማድረጉን እንዲቀጥል ዮሐንስ ማሳሰቢያ የሰጠው ለምንድን ነው? ጋይዮስ በድፍረት ይህን ማድረጉን እንዲቀጥል ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ዮሐንስ ተሰምቶት ይሆን? ወይስ ዲዮጥራጢስ እንግዳ ተቀባይ የሆኑ ክርስቲያኖችን ከጉባኤው ለማባረር የሚያደርገውን ጥረት በመፍራት ጋይዮስ እንግዶችን ከመቀበል ወደኋላ እንዳይል ዮሐንስ ሰግቶ ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ዮሐንስ “መልካም የሚያደርግ የአምላክ ወገን ነው” በማለት ጋይዮስን አበረታቶታል። (3 ዮሐ. 11) በእርግጥም ይህ፣ መልካም የሆነውን ለማድረግና በዚያው ለመቀጠል የሚያነሳሳ ግሩም ምክንያት ነው።

ዮሐንስ የጻፈው ደብዳቤ፣ ጋይዮስ እንግዳ ተቀባይ መሆኑን እንዲቀጥል አነሳስቶት ይሆን? ሦስተኛ ዮሐንስ፣  ‘ጥሩ የሆነውን ነገር እንዲከተሉ’ ሌሎችንም እንዲያበረታታ ሲባል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መካተቱ ይህን ያሳያል።

ከሦስተኛ ዮሐንስ የምናገኘው ትምህርት

በጥንት ዘመን ስለኖረው ተወዳጁ ወንድማችን ጋይዮስ ከዚህ ውጪ የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና ስለ እሱ ካገኘው ከዚህ ትንሽ መረጃ ብዙ ትምህርት መቅሰም እንችላለን።

“የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል” ማዳበር የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

አንደኛ፣ አብዛኞቻችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያወቅነው ይህንን እውነት ለማስተማር ሲሉ ወደተለያዩ ቦታዎች ይጓዙ በነበሩ ታማኝ ክርስቲያኖች አማካኝነት ነው። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ለምሥራቹ ሲሉ ረጅም ርቀት የሚጓዙት ሁሉም ክርስቲያኖች አይደሉም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ጉዞ የሚያደርጉትን፣ በሆነ መንገድ በመደገፍ ወይም በማበረታታት የጋይዮስን አርዓያ መከተል እንችላለን። ለምሳሌ የወረዳ የበላይ ተመልካቹንና ሚስቱን ወይም ደግሞ በአገራቸው ውስጥ አሊያም ከአገራቸው ውጭ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች ተዛውረው ለሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንችል ይሆናል። እንግዲያው ሁላችንም “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል [እናዳብር]።”—ሮም 12:13፤ 1 ጢሞ. 5:9, 10

ሁለተኛ፣ በጉባኤ ውስጥ ያለውን ሥልጣን የማይቀበሉ ሰዎች አልፎ አልፎ ቢነሱ መገረም አይኖርብንም። የሐዋርያው ዮሐንስን ሥልጣን የማያከብሩ ሰዎች ነበሩ፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሆን እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞታል። (2 ቆሮ. 10:7-12፤ 12:11-13) እኛስ በጉባኤ ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶት ነበር፦ “የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውምና፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር፣ ለማስተማር ብቁ የሆነና በደል ሲደርስበት ራሱን የሚገዛ፣ እንዲሁም ቀና አመለካከት የሌላቸውን በገርነት የሚያርም ሊሆን ይገባዋል።” የሚያበሳጭ ሁኔታ ሲያጋጥመንም እንኳ የገርነት መንፈስ ማሳየታችንን ከቀጠልን ነቃፊ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ውሎ አድሮ አመለካከታቸውን ሊያስተካክሉ ይችላሉ። ይሖዋም “ትክክለኛ የእውነት እውቀት ያገኙ ዘንድ ለንስሐ ያበቃቸው ይሆናል።”—2 ጢሞ. 2:24, 25

ሦስተኛ፣ የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ ተቋቁመው ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ የእምነት አጋሮቻችን ሊመሰገኑና ልባዊ አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። ሐዋርያው ዮሐንስ ጋይዮስን እንዳበረታታውና እያደረገ ያለው ነገር ትክክል መሆኑን እንዳረጋገጠለት ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች፣ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ‘እንዳይዝሉ’ በማበረታታት የዮሐንስን ምሳሌ መከተል ይኖርባቸዋል።—ኢሳ. 40:31፤ 1 ተሰ. 5:11

ሐዋርያው ዮሐንስ ለጋይዮስ የላከው ደብዳቤ በግሪክኛው 219 ቃላት ብቻ የያዘ በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ ትንሹ ነው። ይሁንና የያዘው መልእክት በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች ትልቅ ጠቀሜታ አለው።