“ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም።”—3 ዮሐ. 4

መዝሙሮች፦ 134, 133

1, 2. (ሀ) ከአገራቸው ውጭ የሚኖሩ በርካታ ልጆች ምን ዓይነት ችግር ያጋጥማቸዋል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ እንወያያለን?

“ከሕፃንነቴ ጀምሮ በቤት ውስጥም ሆነ ጉባኤ ስሄድ የማወራው በወላጆቼ ቋንቋ ነበር” በማለት ጆሽዋ ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ትምህርት ቤት ከገባሁ በኋላ ግን የምንኖርበትን አገር ቋንቋ መጠቀም ይቀለኝ ጀመር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ በምንኖርበት አገር ቋንቋ ብቻ መጠቀም ጀመርኩ። በስብሰባዎች ላይ የሚተላለፈው ትምህርት ሊገባኝ አልቻለም፤ የወላጆቼን ባሕል መረዳትም እየከበደኝ መጣ።” ብዙዎች የጆሽዋ ዓይነት ሁኔታ ያጋጥማቸዋል።

2 በዛሬው ጊዜ ከ240,000,000 በላይ ሰዎች ከትውልድ አገራቸው ውጭ ይኖራሉ። በሌላ አገር የምትኖር ወላጅ ከሆንክ ልጆችህ በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉና ‘በእውነት ውስጥ እንዲመላለሱ’ በተሻለ ሁኔታ መርዳት የምትችለው እንዴት ነው? (3 ዮሐ. 4) ሌሎችስ በዚህ ረገድ እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?

ወላጆች ጥሩ ምሳሌ ሁኑ

3, 4. (ሀ) ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸው ምን እንዲያደርጉላቸው መጠበቅ የለባቸውም?

3 ወላጆች፣ እናንተ የምትተዉት ምሳሌ ልጆቻችሁ ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝ እንዲጀምሩ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ልጆቻችሁ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት” እንደምትፈልጉ ሲመለከቱ  በየዕለቱ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማግኘት በይሖዋ መታመንን ይማራሉ። (ማቴ. 6:33, 34) ስለዚህ አኗኗራችሁን ቀላል አድርጉት። ለቁሳዊ ነገሮች ስትሉ መንፈሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ከማድረግ ይልቅ መንፈሳዊ ነገሮችን አስቀድሙ። ዕዳ ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቁ። ‘በሰማይ ውድ ሀብት’ ይኸውም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት እንጂ ቁሳዊ ብልጽግናን ወይም “ከሰው የሚገኘውን ክብር” ለማትረፍ አትድከሙ።—ማርቆስ 10:21, 22ን አንብብ፤ ዮሐ. 12:43

4 ወላጆች፣ ለልጆቻችሁ ጊዜ እስክታጡ ድረስ በሌሎች ነገሮች አትጠመዱ። በተጨማሪም ልጆቻችሁ ለራሳቸው ወይም ለእናንተ ሲሉ ሀብትንና ዝናን ከማሳደድ ይልቅ ይሖዋን ለማስቀደም በመወሰናቸው እንደምትኮሩባቸው እንዲያውቁ አድርጉ። ወላጆች፣ እናንተ የተመቻቸ ሕይወት እንድትመሩ ማድረግ የልጆቻችሁ ኃላፊነት እንደሆነ አድርጋችሁ ማሰብ የለባችሁም። “ለልጆቻቸው ሀብት ማከማቸት የሚጠበቅባቸው ወላጆች ናቸው እንጂ ልጆች ለወላጆቻቸው አያከማቹም” የሚለውን ጥቅስ አስታውሱ።—2 ቆሮ. 12:14

ቋንቋ የሚፈጥረውን እንቅፋት ለመወጣት ጥረት አድርጉ

5. ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ ይሖዋ መናገር ያለባቸው ለምንድን ነው?

5 በትንቢት እንደተነገረው “ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ” ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት እየጎረፉ ነው። (ዘካ. 8:23) ይሁንና ልጆቻችሁ የእናንተን ቋንቋ በደንብ የማይረዱ ከሆነ እውነትን ለእነሱ ማስተማር ከባድ ሊሆንባችሁ ይችላል። የላቀ ቦታ የምትሰጧቸው ጥናቶቻችሁ ልጆቻችሁ ናቸው፤ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ደግሞ ይሖዋን “ማወቅ” አለባቸው። (ዮሐ. 17:3) ልጆቻችሁ የይሖዋን ትምህርቶች እንዲያውቁ፣ አመቺ በሆነ ጊዜ ሁሉ ስለ እነዚህ ትምህርቶች ‘መናገር’ ይኖርባችኋል።—ዘዳግም 6:6, 7ን አንብብ።

6. ልጆቻችሁ የእናንተን ቋንቋ ማወቃቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

6 ልጆቻችሁ በአካባቢው የሚነገረውን ቋንቋ በትምህርት ቤትና በዙሪያቸው ካሉት ሰዎች መማራቸው አይቀርም፤ የእናንተን ቋንቋ በዋነኝነት መማር የሚችሉት ግን በቋንቋችሁ አዘውትራችሁ የምታነጋግሯቸው ከሆነ ነው። ልጆቻችሁ የእናንተን ቋንቋ ማወቃቸው የልባቸውን አውጥተው እንዲያዋሯችሁ ያስችላል፤ ሌሎች ጥቅሞችም አሉት። ልጆቻችሁ የተለያዩ ቋንቋዎችን መቻላቸው ለአእምሯዊ እድገታቸው አስተዋጽኦ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሚያስችል አጋጣሚ ሊከፍትላቸው ይችላል። ከወላጆቿ ጋር ከአገሯ ውጭ የምትኖረው ካሮሊና እንዲህ ብላለች፦ “በሌላ አገር ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ መሄድ ደስ ይላል። ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ማገልገል አስደሳች ነው።”

7. ልጆቻችሁ የእናንተን ቋንቋ በደንብ የማይረዱ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

7 ይሁን እንጂ በሌላ አገር የሚኖሩ አንዳንድ ልጆች የሚኖሩበትን አገር ባሕልና ቋንቋ እየለመዱ ሲሄዱ፣ የወላጆቻቸውን ቋንቋ የመናገር ፍላጎታቸውም ሆነ ችሎታቸው እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል። የእናንተ ልጆች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከሆነ አሁን ያላችሁበትን አገር ቋንቋ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለመማር ጥረት ማድረግ ትችላላችሁ? ልጆቻችሁ የሚያወሩትን ነገር፣ መዝናኛዎቻቸውን እንዲሁም ትምህርት ቤት የሚማሩትን ነገር መረዳት አልፎ ተርፎም ከአስተማሪዎቻቸው ጋር ራሳችሁ መነጋገር መቻላችሁ፣ ልጆቻችሁ በክርስትና ጎዳና እንዲመላለሱ ለመርዳት የተሻለ አጋጣሚ ይሰጣችኋል። እርግጥ ነው፣ አዲስ ቋንቋ መማር ጊዜ፣ ጥረትና ትሕትና ይጠይቃል። ሆኖም ልጃችሁ መስማት የማይችል ቢሆን ኖሮ ከእሱ ጋር ለመግባባት ስትሉ የምልክት ቋንቋ አትማሩም ነበር? ታዲያ ልጃችሁ በተሻለ መንገድ የሚገባው እናንተ ከምትናገሩት የተለየ ቋንቋ ከሆነ ይህን ቋንቋ ለመቻል ጥረት ማድረጋችሁ ተገቢ አይሆንም? *

8. ልጆቻችሁ የሚናገሩት ቋንቋ የሚከብዳችሁ ቢሆንም እንኳ እነሱን መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

8 በሌላ አገር የሚኖሩ አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸው የሚናገሩትን ቋንቋ አጥርተው መናገር ሊከብዳቸው እንደሚችል አይካድም። ይህም ‘የቅዱሳን  መጻሕፍትን’ ጥልቅ እውቀት ለልጆቻቸው ማስተማር አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ሊያደርግ ይችላል። (2 ጢሞ. 3:15) እናንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟችሁ ከሆነ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲያውቁና እንዲወዱት መርዳት እንደማትችሉ ሆኖ አይሰማችሁ። ሻን የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “እናታችን ያሳደገችን ብቻዋን ሲሆን እኔና እህቶቼ ይበልጥ የምንረዳውን ቋንቋ እሷ በደንብ አትችለውም፤ እኛ ደግሞ የእሷን ቋንቋ መናገር ይከብደን ነበር። ያም ቢሆን የአምላክን ቃል ስታጠና፣ ስትጸልይና በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ ለመምራት ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ መመልከታችን ይሖዋን ማወቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንድንገነዘብ አድርጎናል።”

9. ወላጆች፣ በሁለት ቋንቋዎች ማጥናት የሚያስፈልጋቸውን ልጆች መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

9 አንዳንድ ልጆች ስለ ይሖዋ ለመማር በሁለት ቋንቋዎች ይኸውም ትምህርት ቤት በሚማሩበትና ቤት ውስጥ በሚናገሩበት ቋንቋ መጠቀም ያስፈልጋቸው ይሆናል። በመሆኑም አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር በሁለቱም ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችን እንዲሁም በድምፅ የተቀዱ ነገሮችንና ቪዲዮዎችን ይጠቀማሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በሌላ አገር የሚኖሩ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና እንዲመሠርቱ ለመርዳት ሰፋ ያለ ጊዜ መመደብና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።

በየትኛው ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ብትሄዱ ይሻላል?

10. (ሀ) አንድ ቤተሰብ በየትኛው ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ መሄድ እንዳለበት የሚወስነው ማን ነው? (ለ) የቤተሰቡ ራስ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ምን ማድረግ ይኖርበታል?

10 “የባዕድ አገር ሰዎች” የሚኖሩት የእነሱን ቋንቋ ከሚናገሩ የይሖዋ ምሥክሮች ርቀው ከሆነ በአካባቢው በሚነገረው ቋንቋ ወደሚካሄድ ጉባኤ መሄድ ይኖርባቸዋል። (መዝ. 146:9) ይሁንና የአፍ መፍቻ ቋንቋችሁን የሚጠቀም ጉባኤ በአካባቢያችሁ የሚገኝ ከሆነ ‘ቤተሰባችን በየትኛው ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ቢሄድ የተሻለ ይሆናል?’ የሚል ጥያቄ ይነሳል። የቤተሰቡ ራስ በጉዳዩ ላይ በደንብ ካሰበበትና ከጸለየበት እንዲሁም ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር ከተማከረበት በኋላ ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። (1 ቆሮ. 11:3) የቤተሰቡ ራስ ውሳኔ ሲያደርግ የትኞቹን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል? ውሳኔ ለማድረግስ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይረዱታል? እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

11, 12. (ሀ) አንድ ልጅ ከስብሰባዎች በሚያገኘው ጥቅም ላይ ቋንቋ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? (ለ) አንዳንድ ልጆች የወላጆቻቸውን ቋንቋ መማር የማይፈልጉት ለምንድን ነው?

11 ወላጆች፣ ልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሚዛናዊ ሆነው ማጤን ይኖርባቸዋል። እርግጥ ነው፣ አንድ ልጅ የሚገባው ቋንቋ ምንም ይሁን ምን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በደንብ መረዳት እንዲችል በየሳምንቱ በስብሰባዎች ላይ ለጥቂት ሰዓታት የሚያገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ብቻውን በቂ አይደለም። ሆኖም ወላጆች ልትዘነጉት የማይገባ ነገር አለ፦ ልጆቻችሁ፣ በሚገባ በሚረዱት ቋንቋ በሚካሄድ ስብሰባ ላይ በመገኘት ብቻ እናንተ ከምታስቡት በላይ ትምህርት ሊቀስሙ ይችላሉ። ልጆቻችሁ ጉባኤው የሚመራበትን ቋንቋ በደንብ የማይረዱት ከሆነ ግን ብዙም ጥቅም ላያገኙ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 14:9, 11ን አንብብ።) በተጨማሪም አንድ ልጅ እያደገ ሲሄድ፣ በአመለካከቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ብሎም ልቡን የሚነካው የአገሩ ቋንቋ ወይም የአፍ መፍቻ ቋንቋው ላይሆን ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ልጆች በወላጆቻቸው ቋንቋ ሐሳብ ቢሰጡና ክፍል ቢያቀርቡም እንኳ የሚናገሩት ነገር ከልባቸው የመነጨ ላይሆን ይችላል።

12 ከዚህም ሌላ በአንድ ልጅ አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ቋንቋ ብቻ አይደለም። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የጆሽዋ ሁኔታ ይህን ያሳያል። እህቱ ኤስተር እንደተናገረችው ‘በልጆች አስተሳሰብ ላይ የወላጆቻቸው ቋንቋ፣ ባሕልና ሃይማኖት ተጽዕኖ ያሳድራሉ።’ ልጆች የወላጆቻቸው ባሕል ካልገባቸው የእነሱን ቋንቋ እንዲሁም ሃይማኖት መማር አይፈልጉ ይሆናል። ታዲያ በሌላ አገር የሚኖሩ ወላጆች ምን ማድረግ ይችላሉ?

13, 14. (ሀ) ከሌላ አገር የመጡ አንድ ባልና ሚስት ቤተሰባቸው በአካባቢው በሚነገረው ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ እንዲሄድ የወሰኑት ለምንድን ነው? (ለ) ባልና ሚስቱ የራሳቸውን መንፈሳዊነት ለመጠበቅ ምን አድርገዋል?

13 ክርስቲያን ወላጆች ከራሳቸው ፍላጎት ይልቅ የልጆቻቸውን መንፈሳዊነት ሊያስቀድሙ ይገባል። (1 ቆሮ. 10:24) የጆሽዋና የኤስተር አባት የሆነው  ሳሙኤል እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ፣ እውነት የልጆቻችንን ልብ የሚነካው በየትኛው ቋንቋ ሲማሩት እንደሆነ ለማስተዋል ሞከርን፤ እንዲሁም ጥበብ ለማግኘት ጸለይን። ለጸሎታችን ያገኘነው መልስ እኛ ከምንመርጠው የተለየ ነበር። ልጆቻችን በእኛ ቋንቋ ከሚመሩ ስብሰባዎች እምብዛም እየተጠቀሙ እንዳልሆነ ስንገነዘብ ግን በአካባቢው ቋንቋ ወደሚካሄድ ጉባኤ ለመዛወር ወሰንን። ከልጆቻችን ጋር ሆነን አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ እንገኝ እንዲሁም እናገለግል ነበር። በተጨማሪም የአካባቢውን ወንድሞች ቤታችን እንጋብዛቸው እንዲሁም አብረውን ሽርሽር እንዲሄዱ እናደርግ ነበር። እንዲህ ያለ ጥረት ማድረጋችን ልጆቻችን ከወንድሞች ጋር እንዲቀራረቡ ረድቷቸዋል፤ በተጨማሪም ይሖዋን እንዲያውቁት ብሎም እንደ አምላካቸው ብቻ ሳይሆን እንደ አባታቸውና እንደ ወዳጃቸው እንዲመለከቱት አድርጓል። ይህ፣ የእኛን ቋንቋ ከመቻል የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ ይሰማናል።”

14 ሳሙኤል አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ደግሞ መንፈሳዊነታችንን ለመጠበቅ ስንል በእኛ ቋንቋ ወደሚመሩ ስብሰባዎችም እንሄድ ነበር። ጊዜያችን በጣም የተጣበበ ከመሆኑም ሌላ ይደክመን ነበር። ሆኖም ያደረግነውን ጥረትና የከፈልነውን መሥዋዕት ይሖዋ ስለባረከልን አመስጋኞች ነን። ሦስቱም ልጆቻችን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ናቸው።”

ወጣቶች ምን ማድረግ ይችላሉ?

15. ክርስቲና የተባለች እህት በአካባቢው ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ብታገለግል የተሻለ እንደሚሆን የተሰማት ለምንድን ነው?

15 በዕድሜ ከፍ ያሉ ልጆች፣ በደንብ በሚያውቁት ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ቢሄዱ ይሖዋን በተሻለ መንገድ ማገልገል እንደሚችሉ ይሰማቸው ይሆናል። እንዲህ ከሆነ ወላጆች፣ ልጆቻቸው እነሱን እንዳልፈለጓቸው ሊያስቡ አይገባም። ክርስቲና እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “የወላጆቼ ቋንቋ በተወሰነ መጠን ቢገባኝም በስብሰባዎች ላይ የሚሰጠውን ትምህርት መረዳት ግን ይከብደኝ ነበር። የ12 ዓመት ልጅ በነበርኩበት ወቅት፣ ትምህርት ቤት በምጠቀምበት ቋንቋ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። የምማረው ነገር እውነት መሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባኝ ያኔ ነው! ትምህርት ቤት በምጠቀምበት ቋንቋ መጸለይ ስጀምር ደግሞ ሌላ ትልቅ ለውጥ አየሁ። ለይሖዋ የልቤን አውጥቼ መናገር ቻልኩ!” (ሥራ 2:11, 41) ክርስቲና 18 ዓመት ሲሆናት ጉዳዩን ከወላጆቿ ጋር ከተወያየችበት በኋላ በአካባቢው ቋንቋ ወደሚካሄድ ጉባኤ ለመዛወር ወሰነች። “ትምህርት ቤት በምጠቀምበት ቋንቋ ስለ ይሖዋ መማሬ እርምጃ እንድወስድ አነሳሳኝ” ብላለች። ብዙም ሳይቆይ ክርስቲና የዘወትር አቅኚ ሆና በደስታ ማገልገል ጀመረች።

16. ናዲያ የተባለች እህት በወላጆቿ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ በመቆየቷ የተጠቀመችው እንዴት ነው?

16 ወጣቶች በአካባቢው ቋንቋ ወደሚካሄድ ጉባኤ ብትሄዱ ትመርጣላችሁ? ከሆነ እንዲህ ማድረግ የፈለጋችሁበትን ምክንያት ራሳችሁን ጠይቁ። በአካባቢው ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ መሄዳችሁ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳችኋል? (ያዕ. 4:8) ወይስ ይህን ለማድረግ ያሰባችሁት ወላጆቻችሁ እንዳይቆጣጠሯችሁ ስለምትፈልጉ አሊያም ብዙም ጥረት ላለማድረግ ስትሉ ነው? በአሁኑ ወቅት በቤቴል የምታገለግለው ናዲያ “እኔ፣ ወንድሜና እህቶቼ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ስንሆን በአካባቢው ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ መዛወር ፈልገን ነበር” ብላለች። ወላጆቻቸው ግን ይህን ማድረግ ለልጆቹ መንፈሳዊ እድገት ጠቃሚ እንዳልሆነ አስተዋሉ። ናዲያ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቻችን የእነሱን ቋንቋ እንድንማር ጥረት በማድረጋቸው እንዲሁም በእነሱ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ እንድንቆይ በመወሰናቸው አሁን አመስጋኞች ነን። ይበልጥ ደስተኞች እንድንሆን የረዳን ከመሆኑም ሌላ ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ለመርዳት የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ እንዲኖረን አድርጓል።”

ሌሎች እርዳታ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?

17. (ሀ) ይሖዋ ልጆችን የማሳደግን ኃላፊነት የሰጠው ለማን ነው? (ለ) ወላጆች ለልጆቻቸው እውነትን በማስተማር ረገድ እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይችላሉ?

17 ይሖዋ፣ ልጆችን በእውነት ውስጥ የማሳደግን ኃላፊነት የሰጠው ለወላጆች እንጂ ለአያቶች ወይም ለሌላ ለማንም ሰው አይደለም። (ምሳሌ 1:8ን እና 31:10, 27, 28ን አንብብ።) ይሁንና የሚኖሩበትን አገር ቋንቋ የማይችሉ ወላጆች የልጆቻቸውን ልብ  ለመንካት በሚያደርጉት ጥረት እገዛ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ወላጆች እንዲህ ዓይነት እገዛ ለማግኘት ቢጠይቁ፣ የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት የማሟላት ኃላፊነታቸውን ለሌሎች አሳልፈው እንደሰጡ ተደርጎ ሊታይ አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ ይህን ማድረጋቸው ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት የሚደገፍ ነው። (ኤፌ. 6:4) ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች የቤተሰብ አምልኳቸውን መምራት እንዲሁም ለልጆቻቸው ጥሩ ጓደኞች መምረጥ የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሐሳብ እንዲሰጧቸው መጠየቅ ይችላሉ።

ልጆችም ሆኑ ወላጆች ከጉባኤው ጋር መቀራረባቸው ይጠቅማቸዋል (አንቀጽ 18, 19ን ተመልከት)

18, 19. (ሀ) መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ወጣቶችን ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች ምን ማድረጋቸውን መቀጠል አለባቸው?

18 ለምሳሌ ወላጆች፣ በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ ሌሎች ቤተሰቦች እንዲገኙ አልፎ አልፎ መጋበዝ ይችላሉ። በተጨማሪም ወጣቶች መንፈሳዊ አመለካከት ካላቸው ክርስቲያኖች ጋር መቀራረባቸው እድገት እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይችላል፤ ለምሳሌ አብረው አገልግሎት ሊወጡ እንዲሁም ጤናማ በሆነ መዝናኛ ሊካፈሉ ይችላሉ። (ምሳሌ 27:17) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሻን እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “ያቀርቡኝ የነበሩ ወንድሞችን መቼም አልረሳቸውም። በስብሰባዎች ላይ ለማቀርበው የተማሪ ክፍል እንድዘጋጅ በሚረዱኝ ወቅት ከእነሱ ብዙ ተምሬያለሁ። አብረን በመዝናናት የምናሳልፈው ጊዜም ያስደስተኝ ነበር።”

19 እርግጥ ነው፣ ልጆቹን የሚረዱት ክርስቲያኖች ምንጊዜም ቢሆን ልጆቹ ለወላጆቻቸው ያላቸው አክብሮት እንዲጨምር መርዳትና ስለ ወላጆቻቸው መልካም ነገር መናገር አለባቸው፤ የእነሱን ኃላፊነት ለመውሰድ መሞከር የለባቸውም። ከዚህም ሌላ እነዚህ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤው ውጭ ባሉ ሰዎች ዘንድ ከሥነ ምግባር አንጻር ጥያቄ የሚያስነሳ ምንም ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥ. 2:12) በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ሥልጠና የመስጠቱን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ለሌሎች መተው የለባቸውም። ወላጆች፣ ሌሎች ክርስቲያኖች ለልጆቻቸው የሚሰጡትን እርዳታ መከታተል እንዲሁም እነሱ ራሳቸው ልጆቻቸውን ማስተማራቸውን መቀጠል አለባቸው።

20. ወላጆች ልጆቻቸው የይሖዋ አገልጋይ እንዲሆኑ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

20 ወላጆች የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጸልዩ፤ እንዲሁም አቅማችሁ የሚፈቅደውን ሁሉ አድርጉ። (2 ዜና መዋዕል 15:7ን አንብብ።) ከራሳችሁ ፍላጎት ይልቅ ልጃችሁ ከይሖዋ ጋር የሚኖረውን ወዳጅነት አስቀድሙ። የአምላክ ቃል የልጃችሁን ልብ እንዲነካው ለማድረግ የምትችሉትን ያህል ጣሩ። ልጃችሁ፣ የይሖዋ አገልጋይ ሊሆን እንደሚችል ምንጊዜም እምነት ይኑራችሁ። ልጆቻችሁ የአምላክን ቃል እንዲሁም የእናንተን ግሩም ምሳሌ ሲከተሉ እንደ ሐዋርያው ዮሐንስ ይሰማችኋል፤ ዮሐንስ መንፈሳዊ ልጆቹን በተመለከተ “ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም” ብሎ ነበር።—3 ዮሐ. 4

^ አን.7 በመጋቢት 2007 ንቁ! ከገጽ 10-12 ላይ የወጣውን “ሌላ ቋንቋ መማር ትችላለህ!” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።