በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ግንቦት 2017

“ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?”

“ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?”

“የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?”—ዮሐ. 21:15

መዝሙሮች፦ 143, 65

1, 2. ጴጥሮስ ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ሲሞክር ካደረ በኋላ ምን አጋጠመው?

ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል ሰባቱ፣ ሌሊቱን ሙሉ በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ለማጥመድ ቢሞክሩም አንድም ዓሣ አልያዙም። ከሞት የተነሳው ኢየሱስ የባሕሩ ዳርቻ ላይ ቆሞ ደቀ መዛሙርቱን እየተመለከታቸው ነው። ከዚያም “‘መረቡን ከጀልባዋ በስተ ቀኝ ጣሉት፤ ዓሣ ታገኛላችሁ’ አላቸው። እነሱም መረቡን ጣሉ፤ ከዓሣውም ብዛት የተነሳ መረቡን መጎተት አቃታቸው።”—ዮሐ. 21:1-6

2 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ቁርስ ካበላቸው በኋላ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ ዘወር ብሎ “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?” አለው። ኢየሱስ “ከእነዚህ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? ጴጥሮስ ዓሣ የማጥመድ ሥራውን በጣም ይወደው ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ይበልጥ የሚወደው ማንን እንደሆነ ጴጥሮስን እየጠየቀው ይመስላል። ጴጥሮስ፣ ለዓሣዎቹና ዓሣ ለማጥመድ ሥራው የነበረው ፍቅር ከኢየሱስና እሱ ካስተማራቸው ነገሮች ይበልጥበት ይሆን? ጴጥሮስ “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መልሷል። (ዮሐ. 21:15) ደግሞም ጴጥሮስ ከተናገረው ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል። ከዚያ ጊዜ አንስቶ፣ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በመጠመድና በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደ ዓምድ በመሆን ክርስቶስን እንደሚወደው አሳይቷል።

3. ክርስቲያኖች ምን ዓይነት አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል መገንዘብ አለባቸው?

3 ኢየሱስ ለጴጥሮስ ከተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን? ለክርስቶስ  ያለን ፍቅር እንዳይቀዘቅዝ እንዲሁም ትኩረታችን ተከፋፍሎ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ ከመስጠት ወደኋላ እንዳንል መጠንቀቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ የዚህ ሥርዓት ጭንቀት ምን ያህል ጫና ሊያሳድርብን እንደሚችል በሚገባ ያውቃል። ኢየሱስ፣ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ አንዳንዶች “የመንግሥቱን ቃል” ተቀብለው እድገት ማድረግ ቢጀምሩም “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል ቃሉን [እንደሚያንቀው]” ገልጾ ነበር። (ማቴ. 13:19-22፤ ማር. 4:19) በእርግጥም ጠንቃቆች ካልሆንን፣ በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ትኩረታችንን ሊሰርቁትና መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችንን ሊያዳክሙት ይችላሉ። በመሆኑም ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል፦ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።”—ሉቃስ 21:34

4. ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ለማወቅ ምን ሊረዳን ይችላል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

4 ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ከተወያየ በኋላ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ክርስቶስ የሰጠንን ሥራ ከምንም በላይ በማስቀደም ለእሱ ጥልቅ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ታዲያ ምንጊዜም ለዚህ ሥራ ቅድሚያ እየሰጠን መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላለን? በየጊዜው ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘በሕይወቴ ውስጥ ከምንም በላይ የምወደው ነገር ምንድን ነው? ይበልጥ የምደሰተው መንፈሳዊ ነገሮችን በማከናወን ነው? ወይስ በሌሎች እንቅስቃሴዎች በመካፈል?’ ሚዛናዊ ካልሆንን ለክርስቶስና ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለንን ፍቅር ሊያዳክሙብን የሚችሉ ሦስት ነገሮችን ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን፤ እነሱም ሰብዓዊ ሥራ፣ መዝናኛና ቁሳዊ ነገሮች ናቸው።

ለሰብዓዊ ሥራ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑራችሁ

5. የቤተሰብ ራሶች ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት አለባቸው?

5 ጴጥሮስ ዓሣ የሚያጠምደው መተዳደሪያው ስለሆነ እንጂ ለመዝናናት አልነበረም። በዛሬው ጊዜ ያሉ የቤተሰብ ራሶችም ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር የማሟላት ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። (1 ጢሞ. 5:8) ይህን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ጠንክረው መሥራት ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰብዓዊ ሥራ ብዙውን ጊዜ ውጥረት የሚፈጥር ነገር ሆኗል።

6. በዛሬው ጊዜ ሠራተኞች በሥራ ቦታቸው ምን ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?

6 በዛሬው ጊዜ ካሉት የሥራ አጋጣሚዎች አንጻር የሠራተኞች ቁጥር ብዙ በመሆኑ ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። በርካታ ሠራተኞች ለረጅም ሰዓት ለመሥራት ይገደዳሉ፤ አንዳንድ ጊዜም የሚሰጣቸው ክፍያ አነስተኛ ነው። በተጨማሪም ድርጅቶች ምርታቸውን ከፍ ለማድረግ በሠራተኞቻቸው ላይ ሁልጊዜ የሚያሳድሩት ጫና ሠራተኞቹ በአካላዊ፣ በአእምሯዊና በስሜታዊ ሁኔታ እንዲዝሉ ያደርጋል። አሠሪዎቻቸው የሚጠብቁባቸውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ የማይሆኑ ሠራተኞች ደግሞ ሥራቸውን የማጣት አደጋ ይደቀንባቸዋል።

7, 8. (ሀ) በዋነኝነት ታማኝ መሆን ያለብን ለማን ነው? (ለ) በታይላንድ የሚኖር አንድ ወንድም ከሥራው ጋር በተያያዘ ምን ጠቃሚ ነገር ተገንዝቧል?

7 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በዋነኝነት ታማኝ መሆን ያለብን ለአምላካችን ለይሖዋ እንጂ ለአሠሪያችን አይደለም። (ሉቃስ 10:27) ሰብዓዊ ሥራ በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ መያዝ የለበትም። የምንሠራው፣ መሠረታዊ ፍላጎታችንን ለማሟላትና አገልግሎታችንን ለማከናወን የሚያስፈልገንን ነገር ለማግኘት ነው። ሆኖም ጥንቃቄ ካላደረግን ሰብዓዊ ሥራ ለአምልኳችን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። በታይላንድ የሚኖር አንድ ወንድም ያጋጠመውን እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ እንዲህ ብሏል፦ “በኮምፒውተር ጥገና ሙያ ላይ በተሰማራሁበት ወቅት ሥራዬን በጣም እወደው ነበር፤ ይሁን እንጂ ረጅም ሰዓት መሥራት ይጠበቅብኝ ነበር። በመሆኑም ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚሆን ጊዜ አልነበረኝም ማለት ይቻላል። ውሎ አድሮ ግን ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማስቀደም ከፈለግኩ በዚህ ሙያ መቀጠል እንደማልችል ተገነዘብኩ።” ታዲያ ይህ ወንድም ምን አደረገ?

 8 እንዲህ ብሏል፦ “በጉዳዩ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል ካሰብኩበትና ገንዘብ ካጠራቀምኩ በኋላ መንገድ ላይ አይስ ክሬም ለመሸጥ ወሰንኩ። መጀመሪያ ላይ የገንዘብ ችግር ያጋጠመኝ ሲሆን ተስፋ ቆርጬ ነበር። የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቼ ሲያገኙኝ የሚያሾፉብኝ ከመሆኑም ሌላ የአየር ማቀዝቀዣ ባለው ቢሮ ውስጥ ኮምፒውተር ላይ ከመሥራት ይልቅ አይስ ክሬም ለመሸጥ የመረጥኩት ለምን እንደሆነ ይጠይቁኝ ነበር። ሁኔታውን ለመቋቋምና ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚሆን ተጨማሪ ጊዜ የማግኘት ግቤ ላይ ለመድረስ እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ብዙም ሳይቆይ ሁኔታዎች መሻሻል ጀመሩ። ደንበኞቼ የሚወዱትን ጣዕም ማወቅ የቻልኩ ሲሆን አይስ ክሬም በመሥራት ረገድም የተዋጣልኝ ሆንኩ። እንዲሁም የሠራሁትን አይስ ክሬም በየቀኑ ሸጬ መጨረስ ቻልኩ። እንዲያውም ኮምፒውተር ላይ ከምሠራበት ጊዜ ይልቅ የተሻለ ገቢ አገኛለሁ። የቀድሞ ሥራዬ ላይ የነበረብኝ ውጥረትና ጭንቀት ስለቀረልኝ ይበልጥ ደስተኛ ሆኛለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ አሁን ወደ ይሖዋ የበለጠ እንደቀረብኩ ይሰማኛል።”ማቴዎስ 5:3, 6ን አንብብ።

9. ለሰብዓዊ ሥራችን ምንጊዜም ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲኖረን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

9 ትጉህ ሠራተኛ ስንሆን አምላክን እናስደስታለን፤ ደግሞም ጠንክሮ መሥራት ዋጋ ያስገኛል። (ምሳሌ 12:14) ያም ቢሆን ቀደም ሲል የተጠቀሰው ወንድም እንደተገነዘበው ለሰብዓዊ ሥራ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ኢየሱስ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥትና ጽድቅ ፈልጉ፤ እነዚህም ነገሮች ሁሉ [መሠረታዊ ነገሮች] ይሰጧችኋል” ብሏል። (ማቴ. 6:33) ለሰብዓዊ ሥራችን እና ለመንፈሳዊ ኃላፊነቶቻችን ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ‘ሥራዬ አስደሳች እንደሆነ፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ግን ያን ያህል እንደማያስደስቱ እንዲያውም አሰልቺ እንደሆኑ ይሰማኛል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጥሩ ነው። ስለ ሰብዓዊ ሥራችንና ስለ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችን ያለንን አመለካከት በቁም ነገር መመርመራችን፣ አስበልጠን የምንወደው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ያስችለናል።

10. ኢየሱስ ቅድሚያ ልንሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች ምን ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቷል?

10 ኢየሱስ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችንና ሌሎች ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማከናወን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ማርያምንና እህቷን ማርታን ለመጠየቅ ቤታቸው ሄዶ ነበር። ማርታ ምግብ ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ እያለች ሳለ ማርያም የኢየሱስ እግር ሥር ተቀምጣ የሚናገረውን ታዳምጥ ነበር። ማርታ፣ ማርያም ስላላገዘቻት ቅሬታዋን ለኢየሱስ ስትነግረው “ማርያም በበኩሏ ጥሩ የሆነውን ድርሻ መርጣለች፤ ይህም ከእሷ አይወሰድም” አላት። (ሉቃስ 10:38-42) ኢየሱስ ለማርታ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት እየሰጣት ነበር። ትኩረታችን በሰብዓዊ ነገሮች እንዳይከፋፈል ለማድረግ እንዲሁም ለክርስቶስ ፍቅር እንዳለን ለማሳየት፣ ምንጊዜም “ጥሩ የሆነውን ድርሻ” መምረጥ አለብን፤ ይኸውም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል።

ለመዝናኛ ሊኖረን የሚገባው አመለካከት

11. ቅዱሳን መጻሕፍት እረፍት ስለማድረግና ስለ መዝናኛ ምን ይላሉ?

11 ሕይወታችን በሥራ የተወጠረ በመሆኑ ዘና የምንልበትና የምናርፍበት ጊዜ ያስፈልገናል። የአምላክ ቃል “ሰው ከመብላትና ከመጠጣት እንዲሁም ተግቶ በመሥራት እርካታ ከማግኘት የሚሻለው ነገር የለም” ይላል። (መክ. 2:24) ኢየሱስም ቢሆን እረፍት የማድረግን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። በአንድ ወቅት በስብከቱ ሥራ ላይ ረዘም ያለ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ” ብሏቸዋል።—ማር. 6:31, 32

12. ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል? ምሳሌ ስጥ።

12 በእርግጥም መዝናኛ አስፈላጊ ነገር ነው። ሆኖም መዝናናት በሕይወታችን ውስጥ ዋናውን ቦታ እንዳይዝ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙዎች “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” የሚል አመለካከት ነበራቸው። (1 ቆሮ. 15:32) ዛሬም እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት በብዙ  የዓለም ክፍሎች በስፋት ይታያል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ በምዕራብ አውሮፓ የሚኖር አንድ ወጣት ከዓመታት በፊት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምሮ ነበር። ይሁንና ለመዝናኛ ትልቅ ቦታ ይሰጥ ስለነበር ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መሰብሰቡን አቆመ። ውሎ አድሮ ግን ለመዝናኛ የሰጠው ትኩረት ለብዙ ችግሮችና ለሐዘን እንደዳረገው ተገነዘበ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን እንደገና ማጥናት የጀመረ ሲሆን ከጊዜ በኋላም ብቃቶቹን በማሟላት የምሥራቹ አስፋፊ ሆነ። ከተጠመቀ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር፣ ይህ ዓለም የሚያቀርባቸውን መዝናኛዎች ከማሳደድ ይልቅ ይሖዋን ማገልገል የበለጠ ደስታ እንደሚያስገኝ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ የፈጀብኝ መሆኑ ነው።”

13. (ሀ) በመዝናኛ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ የሚያስከትለውን አደጋ በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ለመዝናኛ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲኖረን ምን ሊረዳን ይችላል?

13 መዝናኛ፣ እረፍት እንድናደርግና መንፈሳችን እንዲታደስ ይረዳናል። ታዲያ በመዝናኛ ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ ይኖርብናል? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ብዙዎቻችን አልፎ አልፎ ጣፋጭ ነገር መብላት እንወዳለን፤ ያም ሆኖ ኬክና ሌሎች ጣፋጭ ነገሮችን አዘውትሮ መመገብ ለጤናችን ጎጂ እንደሆነ እናውቃለን። በመሆኑም በዋነኝነት የምንመገበው ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን ነው። በተመሳሳይም በመዝናኛ ብዙ ጊዜ የምናጠፋ ከሆነ መንፈሳዊ ጤንነታችን ይጎዳል። ይህ እንዳይሆን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትረን መካፈል ይኖርብናል። ታዲያ ለመዝናኛ ያለን አመለካከት ሚዛናዊ መሆን አለመሆኑን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በአንድ ሳምንት ውስጥ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ማለትም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት፣ በመስክ አገልግሎት በመካፈል እንዲሁም በግልና በቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ምን ያህል ሰዓት እንዳሳለፍን መመዝገብ እንችላለን። ቀጥሎ ደግሞ በዚያው ሳምንት በመዝናኛ ይኸውም በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች በመካፈል፣ ቴሌቪዥን በመመልከት ወይም የቪዲዮ ጌም በመጫወት ያሳለፍነውን ሰዓት እንመዝግበው፤ ከዚያም በመዝናኛ ያሳለፍነውን ሰዓት ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ካዋልነው ሰዓት ጋር እናወዳድረው። የበለጠ ሰዓት ያሳለፍነው በየትኛው እንቅስቃሴ ነው? በጊዜ አጠቃቀማችን ረገድ ለውጥ ማድረግ ያስፈልገን ይሆን?ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ።

14. ጥሩ መዝናኛ ለመምረጥ ምን ሊረዳን ይችላል?

14 ይሖዋ፣ የምንፈልገውን መዝናኛ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ የቤተሰብ ራሶችም ለቤተሰባቸው የሚሆነውን መዝናኛ መምረጥ ይችላሉ። ሆኖም ምርጫችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት የይሖዋ መመሪያዎች ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። * ንጹሕ መዝናኛ “የአምላክ ስጦታ ነው።” (መክ. 3:12, 13) እርግጥ ነው፣ የሁላችንም የመዝናኛ ምርጫ ተመሳሳይ ላይሆን እንደሚችል እንገነዘባለን። (ገላ. 6:4, 5) የምንመርጠው መዝናኛ ምንም ይሁን ምን፣ በዚህ ረገድ ሚዛናዊ መሆን ይኖርብናል። ኢየሱስ “ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናል” ብሏል። (ማቴ. 6:21) በመሆኑም ለኢየሱስ ያለን ልባዊ ፍቅር ሐሳባችን፣ ንግግራችንና ድርጊታችን በዋነኝነት የሚያተኩረው ከመንግሥቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች እንጂ በዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎች ላይ እንዳይሆን ይረዳናል።—ፊልጵ. 1:9, 10

ከፍቅረ ንዋይ ለመራቅ የምናደርገው ትግል

15, 16. (ሀ) ፍቅረ ንዋይ ለአንድ ክርስቲያን ወጥመድ ሊሆንበት የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ከቁሳዊ ነገሮች ጋር በተያያዘ ምን ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጥቷል?

15 በዛሬው ጊዜ ብዙዎች በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ፋሽን የሆኑ ነገሮችን፣ አዲስ የወጡ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ወይም ሌሎች ነገሮችን ማግኘታቸው ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ክርስቲያን ለእነዚህ ነገሮች ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጥ ለማወቅ ራሱን እንደሚከተለው ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘ቁሳዊ ነገሮች በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ ከመያዛቸው የተነሳ ለጉባኤ ስብሰባዎች በመዘጋጀት ከማሳልፈው ጊዜ ይልቅ አዲስ ስለወጡ መኪኖች ወይም ፋሽኖች የሚገልጹ መረጃዎችን በመከታተልና ስለ እነዚህ ነገሮች በማሰብ  የማሳልፈው ጊዜ ይበልጣል? በዕለት ተዕለት ጉዳዮች ከሚገባው በላይ ከመጠመዴ የተነሳ ለጸሎትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የምመድበው ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል?’ ለቁሳዊ ነገሮች ያለን ፍቅር ለክርስቶስ ካለን ፍቅር እየበለጠ እንደሆነ ካስተዋልን፣ ኢየሱስ “ከስግብግብነትም ሁሉ ተጠበቁ” በማለት በሰጠው ምክር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። (ሉቃስ 12:15) ኢየሱስ እንዲህ ያለ ከባድ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ለምንድን ነው?

16 ኢየሱስ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም” ብሏል። አክሎም “ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም” በማለት ተናግሯል። ይህ የሆነው ሁለቱም “ጌቶች” ሁለንተናችንን እንድንሰጣቸው ስለሚፈልጉ ነው። ኢየሱስ እንደተናገረው ማንኛውም ሰው ቢሆን “አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል።” (ማቴ. 6:24) ማንኛችንም ብንሆን ፍጹማን ባለመሆናችን ፍቅረ ንዋይን ጨምሮ “ከሥጋችን ፍላጎት” ጋር በምናደርገው ትግል ላለመሸነፍ ምንጊዜም ጥረት ማድረግ አለብን።—ኤፌ. 2:3

17. (ሀ) ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? (ለ) ፍቅረ ንዋይን ለማሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል?

17 ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ይከብዳቸዋል። ለምን? ምክንያቱም በአምላክ ዓይን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ምን እንደሆነ የማስተዋል ችሎታቸው ደንዝዟል። (1 ቆሮንቶስ 2:14ን አንብብ።) የማስተዋል ችሎታቸው መደንዘዙ ደግሞ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት ይበልጥ ከባድ እንዲሆንባቸው ያደርጋል። (ዕብ. 5:11-14) በመሆኑም አንዳንዶች፣ ሁልጊዜ ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮችን የማግኘት ምኞት ይጠናወታቸዋል፤ መቼም ቢሆን በቃኝ አይሉም። (መክ. 5:10) ደስ የሚለው ነገር ፍቅረ ንዋይን ከማሳደድ አባዜ መላቀቅ የሚቻልበት መንገድ አለ፤ እንደ መርዝ አደገኛ የሆነውን ይህን አስተሳሰብ ለማስወገድ ፍቱን መድኃኒቱ የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማንበብ ነው። (1 ጴጥ. 2:2) ኢየሱስ ይሖዋ በገለጣቸው እውነቶች ላይ ማሰላሰሉ ፈተናዎችን ለመቋቋም እንደረዳው ሁሉ፣ እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን ፍቅረ ንዋይን ለማሸነፍ ይረዳናል። (ማቴ. 4:8-10) ይህን ስናደርግ ኢየሱስን ከማንኛውም ቁሳዊ ነገር አስበልጠን እንደምንወደው እናሳያለን።

በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጠው ለየትኞቹ ነገሮች ነው? (አንቀጽ 18ን ተመልከት)

18. ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

18 ኢየሱስ ጴጥሮስን “ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?” ብሎ ሲጠይቀው፣ በሕይወቱ ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም አስፈላጊ መሆኑን እያስገነዘበው ነበር። የጴጥሮስ ስም “ትንሽ ዓለት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን እሱም እንደ ዓለት ጠንካራ የሆኑ ባሕርያትን በማንጸባረቅ ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ኖሯል። (ሥራ 4:5-20) በዛሬው ጊዜ እኛም ለሰብዓዊ ሥራ፣ ለመዝናኛና ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት በመያዝ ምንጊዜም ክርስቶስን አስበልጠን እንደምንወድ ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ብሎት ነበር፤ እኛም በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የዚህ ዓይነት ስሜት እንዳለን የሚያንጸባርቁ ይሁኑ።

^ አን.14 በጥቅምት 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ላይ “የምትመርጡት መዝናኛ ጠቃሚ ነው?” በሚለው ርዕስ ሥር ከገጽ 9-12 ከአን. 6-15 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተመልከት።