በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ግንቦት 2017

 ከታሪክ ማኅደራችን

“ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ልባችን በቅንዓትና በፍቅር ተሞልቶ ነበር”

“ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ልባችን በቅንዓትና በፍቅር ተሞልቶ ነበር”

መስከረም 1922 ዓርብ ጠዋት 8,000 የሚሆኑ ሰዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበዋል፤ አየሩ መሞቅ ጀምሮ ነበር። የስብሰባው ሊቀ መንበር፣ በዚህ ወሳኝ ፕሮግራም ላይ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ማንኛውም ሰው ከፈለገ አዳራሹን ለቅቆ መውጣት እንደሚችል ሆኖም ተመልሶ መግባት እንደማይፈቀድለት ማስታወቂያ ተናገረ።

ስብሰባው የተጀመረው “በውዳሴ ፕሮግራም” ሲሆን የተወሰኑ መዝሙሮች ከተዘመሩ በኋላ ወንድም ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ወደ አትራኖሱ ተጠጋ። አብዛኞቹ ተሰብሳቢዎች በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ከሙቀቱ የተነሳ ወዲያ ወዲህ እያሉ ነው። ተናጋሪው፣ እነዚህ ተሰብሳቢዎች ቁጭ ብለው ፕሮግራሙን እንዲያዳምጡ ጠበቅ አድርጎ አሳሰበ። ንግግሩ እየቀረበ ሳለ፣ ከፍ ተደርጎ የተሰቀለውን የተጠቀለለ ጨርቅ ተሰብሳቢዎቹ አስተውለውት ይሆን?

የወንድም ራዘርፎርድ ንግግር “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” የሚል ርዕስ ነበረው። ወንድም ራዘርፎርድ በጥንት ጊዜ የነበሩ ነቢያት፣ ስለሚመጣው የአምላክ መንግሥት እንዴት በድፍረት እንደተናገሩ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ያብራራ ሲሆን ኃይለኛ የሆነው ድምፁ በአዳራሹ ውስጥ ያስገመግም ነበር። የንግግሩ መደምደሚያ ላይ ሲደርስ “የክብር ንጉሥ መግዛት እንደጀመረ ታምናላችሁ?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። ተሰብሳቢዎቹም በታላቅ ድምፅ “አዎ!” ብለው መለሱ።

ወንድም ራዘርፎርድም “እንግዲያው እናንት የልዑል አምላክ ልጆች ወደ መስኩ ተመልሳችሁ ሂዱ!” በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ። አክሎም እንዲህ አለ፦ “እነሆ ንጉሡ በመግዛት ላይ ነው! እናንተ ደግሞ የእሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ።”

ይህን ሲናገር፣ ከፍ ተደርጎ የተሰቀለው የተጠቀለለ ጨርቅ ተተረተረ፤ “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ” የሚለው መልእክትም ለሁሉም ታየ።

ሬይ ቦፕ “ተሰብሳቢዎቹ በከፍተኛ የደስታ ስሜት ተዋጡ” ሲል የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል። አና ጋርድነርም “ከጭብጨባው የተነሳ የቤቱ ምሰሶዎች ተነቃነቁ” ብላለች። ፍሬድ ትዋሮሽ ደግሞ “ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ ከተቀመጡበት በአንድ ላይ ተነሱ” በማለት ተናግሯል። ኢቫንጄሎስ ስኩፋስ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር “አንድ ታላቅ ኃይል ከወንበራችን አስፈንጥሮ ያስነሳን ያህል ነበር፤ ሁላችንም ብድግ ያልን ሲሆን ዓይኖቻችን በእንባ ተሞሉ” ብሏል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኙት መካከል ብዙዎች ከዚያ ቀደምም የመንግሥቱን ምሥራች በማዳረሱ ሥራ ይካፈሉ ነበር። ከስብሰባው በኋላ ግን ምሥራቹን ለመስበክ እንደ አዲስ ተነሳሱ። ኤተል ቤነኮፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ስለነበራቸው ስሜት ስትናገር “ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ [ልባቸው] በቅንዓትና በፍቅር ተሞልቶ ነበር” ብላለች። በወቅቱ የ18 ዓመት ወጣት የነበረችው ኦዴሳ ታክ ከስብሰባው ስትመለስ፣ ‘ማን ይሄዳል?’ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቆርጣ ነበር። እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “የት፣ ምን ወይም እንዴት እንደምሰብክ አላውቅም ነበር። የማውቀው ነገር ቢኖር ልክ እንደ ኢሳይያስ ‘እነሆኝ! እኔን ላከኝ’ ማለት እንደምፈልግ ነበር።” (ኢሳ. 6:8) ራልፍ ሌፍለር ደግሞ “በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ተስፋፍቶ ያለው የአምላክን መንግሥት የማስታወቅ ዘመቻ በደንብ የጀመረው በዚያ አስደሳች ቀን ነው” ሲል ተናግሯል።

በእርግጥም በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ የተደረገው  ስብሰባ በታሪክ ውስጥ ወሳኝ ቲኦክራሲያዊ ክንውን እንደተፈጸመበት ተደርጎ የሚታይ መሆኑ አያስገርምም! ወንድም ጆርጅ ጋንጋስ “ያ ስብሰባ፣ ከዚያ በኋላ አንድም ስብሰባ እንዳያመልጠኝ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደርግ አነሳስቶኛል” ሲል ተናግሯል። ደግሞም ወንድም ጋንጋስ፣ ከዚያ በኋላ አንድም ስብሰባ አላመለጠውም። ጁልያ ዊልኮክስ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “በጽሑፎቻችን ላይ በ1922 በሴዳር ፖይንት ስለተደረገው ስብሰባ የሚጠቅስ ሐሳብ ባነበብኩ ቁጥር በቃላት ለመግለጽ የሚያዳግት ደስታ ይሰማኛል። ምንጊዜም ቢሆን ‘ይሖዋ፣ በዚያ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ስለፈቀድክልኝ አመሰግናለሁ’ ለማለት ያነሳሳኛል።”

ብዙዎቻችን ለታላቁ አምላካችንና እሱ ለሾመው ንጉሥ ያለን ፍቅርና ቅንዓት እንዲቀጣጠል ብሎም ልባችን በደስታ እንዲሞላ የሚያደርግ ልዩ ትዝታ የፈጠረብን ትልቅ ስብሰባ ወደ አእምሯችን ይመጣ ይሆናል። እኛም በእነዚህ ትዝታዎች ላይ ስናሰላስል “ይሖዋ፣ በዚያ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ስለፈቀድክልኝ አመሰግናለሁ” ለማለት እንገፋፋለን።