በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ነሐሴ 2017

በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ናችሁ?

በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ናችሁ?

“እናንተም በትዕግሥት ጠብቁ።”—ያዕ. 5:8

መዝሙሮች፦ 114, 79

1, 2. (ሀ) “እስከ መቼ ነው?” የሚለውን ጥያቄ እንድንጠይቅ ሊያደርጉን የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) በጥንት ጊዜ የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ያጋጠማቸው ሁኔታ የሚያበረታታን እንዴት ነው?

“እስከ መቼ ነው?” ይህን ጥያቄ የጠየቁት ታማኝ ነቢያት የነበሩት ኢሳይያስና ዕንባቆም ናቸው። (ኢሳ. 6:11፤ ዕን. 1:2) በተጨማሪም ንጉሥ ዳዊት መዝሙር 13⁠ን ሲያቀናብር “እስከ መቼ ነው?” የሚለውን ጥያቄ አራት ጊዜ ጠይቆ ነበር። (መዝ. 13:1, 2) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዙሪያው የነበሩትን ሰዎች እምነት የለሽነት አስመልክቶ በተናገረበት ወቅት ይህን ጥያቄ አንስቷል። (ማቴ. 17:17) በመሆኑም እኛም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለውን ጥያቄ ብንጠይቅ የሚያስገርም አይደለም።

2 “እስከ መቼ ነው?” የሚለውን ጥያቄ እንድንጠይቅ የሚያደርጉን አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ምናልባት አንድ ዓይነት ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞብን ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ከዕድሜ መግፋት ወይም ከጤና ማጣት ጋር እየታገልን ይሆናል፤ በተጨማሪም “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ መኖራችን የሚያስከትልብንን ጫና ተቋቁሞ መኖር ከብዶን ይሆናል። (2 ጢሞ. 3:1) ወይም ደግሞ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ያላቸው የተሳሳተ አመለካከትና መጥፎ ምግባር እንድንዝል ሊያደርገን ይችላል። ይህን ጥያቄ እንድናነሳ ያደረገን ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ በጥንት ጊዜ የነበሩ ታማኝ አገልጋዮቹን እንዲህ ያለ ጥያቄ በማንሳታቸው እንዳልኮነናቸው ማወቃችን የሚያበረታታ ነው!

3. አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ ምን ሊረዳን ይችላል?

 3 ይሁንና እንዲህ ካሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር ፊት ለፊት በምንጋፈጥበት ጊዜ ምን ሊረዳን ይችላል? የኢየሱስ ወንድም የሆነው ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በመንፈስ መሪነት “እንግዲህ ወንድሞች፣ ጌታ እስከሚገኝበት ጊዜ ድረስ በትዕግሥት ጠብቁ” የሚል ምክር ሰጥቶ ነበር። (ያዕ. 5:7) አዎ፣ ሁላችንም ታጋሽ መሆን ያስፈልገናል። ሆኖም ይህን አምላካዊ ባሕርይ ማንጸባረቅ ምን ነገሮችን ያካትታል?

ትዕግሥት ምንድን ነው?

4, 5. (ሀ) ታጋሽ መሆን ምን ነገሮችን ያካትታል? (ለ) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በትዕግሥት የመጠበቅን አስፈላጊነት የሚያጎላ ምን ምሳሌ ተጠቅሟል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

4 መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥት የሚገኘው በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ እንደሆነ ይናገራል፤ በመሆኑም ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ያለአምላክ እርዳታ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በትዕግሥት መቋቋም አይችሉም። ትዕግሥት የአምላክ ስጦታ ነው። እኛም ታጋሽ በመሆን አምላክን ምን ያህል እንደምንወደው እናሳያለን። በተጨማሪም ታጋሽ መሆናችን ለሌሎች ያለንን ፍቅር ያሳያል። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ብዙ ጊዜ ትዕግሥት የምናጣ ከሆነ በመካከላችን ያለው የፍቅር ማሰሪያ ሊላላ ይችላል፤ በአንጻሩ ግን ታጋሾች ከሆንን ፍቅራችን ይጠናከራል። (1 ቆሮ. 13:4፤ ገላ. 5:22) ታጋሽ መሆን ሌሎች ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማንጸባረቅንም ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ ትዕግሥት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አዎንታዊ አመለካከት ይዘን እንድንቋቋም ከሚያስችለን ባሕርይ ማለትም ከጽናት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። (ቆላ. 1:11፤ ያዕ. 1:3, 4) ከዚህም ሌላ ትዕግሥት፣ ምንም ይምጣ ምን ለይሖዋ ታማኝ መሆንን እንዲሁም በደል ሲደርስብን አጸፋ ከመመለስ መቆጠብን ይጨምራል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በትዕግሥት የመጠበቅን አስፈላጊነት አምነን ለመቀበል ፈቃደኞች እንድንሆን ያበረታታናል። በያዕቆብ 5:7, 8 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ትዕግሥትን በተመለከተ ይህን አስፈላጊ ትምህርት እናገኛለን።

5 ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ በትዕግሥት መጠበቅ እንደሚያስፈልገን አምነን መቀበል ያለብን ለምንድን ነው? ያዕቆብ እኛ ያለንበትን ሁኔታ ከአንድ ገበሬ ጋር አመሳስሎታል። ምንም እንኳ አንድ ገበሬ ጠንክሮ በመሥራት ዘር የሚዘራ ቢሆንም የአየሩን ሁኔታም ሆነ የተክሉን እድገት መቆጣጠር አይችልም። ጊዜውን ማፋጠን የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። “የምድርን መልካም ፍሬ” በትዕግሥት መጠበቅ እንደሚያስፈልገው አምኖ ይቀበላል። እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች የሚፈጸሙበትን ጊዜ ስንጠባበቅ፣ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ በርካታ ነገሮች እንዳሉ እንገነዘባለን። (ማር. 13:32, 33፤ ሥራ 1:7) ልክ እንደ ገበሬው በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልገናል።

6. ነቢዩ ሚክያስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

6 ነቢዩ ሚክያስም ልክ እንደ እኛ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ መኖር አስፈልጎት ነበር። ይህ ነቢይ የኖረው ክፉው ንጉሥ አካዝ ይገዛ በነበረበት ዘመን ሲሆን በዚያን ወቅት ብዙ መጥፎ ነገሮች ይፈጸሙ ነበር። እንዲያውም በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች “መጥፎ ነገር በማድረግ የተካኑ” ሆነው ነበር። (ሚክያስ 7:1-3ን አንብብ።) ሚክያስ እነዚህ ሁኔታዎች በእሱ ጥረት ሊለወጡ እንደማይችሉ ተገንዝቦ ነበር። ታዲያ ማድረግ የሚችለው ነገር ይኖራል? እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ግን ይሖዋን በጉጉት እጠባበቃለሁ። የሚያድነኝን አምላክ በትዕግሥት እጠብቃለሁ [“በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ አሳያለሁ፣” ግርጌ]። አምላኬ ይሰማኛል።” (ሚክ. 7:7) እኛም ልክ እንደ ሚክያስ “በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ” ማሳየት ያስፈልገናል።

7. ይሖዋ የገባልንን ቃል የሚፈጽምበትን ጊዜ እንዲሁ መጠበቅ ብቻ በቂ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

7 እኛም እንደ ሚክያስ ዓይነት እምነት ካለን በፈቃደኝነት ይሖዋን ለመጠበቅ እንነሳሳለን። የእኛ ሁኔታ በታሰረበት ክፍል ውስጥ ሆኖ፣ የሞት ቅጣት የሚቀበልበትን ቀን እንደሚጠብቅ እስረኛ አይደለም። ይህ እስረኛ እየጠበቀ ያለው ከዚህ ሌላ ምንም አማራጭ ስለሌለው ነው፤ ደግሞም ያን ቀን በጉጉት ሊጠባበቀው አይችልም። የእኛ ሁኔታ ግን  ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው! ይሖዋ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጠን የገባልንን ቃል በትክክለኛውና ከሁሉ በተሻለው ጊዜ እንደሚፈጽም ስለምናውቅ እሱን በፈቃደኝነት እንጠብቃለን! በመሆኑም “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት [እንቋቋማለን]።” (ቆላ. 1:11, 12) ይሖዋ ቶሎ እርምጃ ባለመውሰዱ እያማረርንና እያጉረመረምን የምንጠብቅ ከሆነ ግን አምላካችን ደስ አይለውም።—ቆላ. 3:12

ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ታማኝ ሰዎች

8. በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ ሰዎች በተዉት ምሳሌ ላይ ስናሰላስል ምን ነገሮችን ማስታወስ ይኖርብናል?

8 በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ ሰዎች ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽምበትን ጊዜ በትዕግሥት በመጠባበቅ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል፤ የእነሱን ታሪክ ማስታወሳችን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች እንድንሆን ይረዳናል። (ሮም 15:4) እነሱ በተዉት ምሳሌ ላይ ስናሰላስል እነዚህ ሰዎች ለምን ያህል ጊዜ በትዕግሥት መጠበቅ እንዳስፈለጋቸው፣ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች የሆኑት ለምን እንደሆነና ታጋሽ መሆናቸው ምን በረከት እንዳስገኘላቸው ለማስታወስ እንሞክር።

አብርሃም፣ የልጅ ልጆቹ ኤሳውና ያዕቆብ እስኪወለዱ ድረስ ለብዙ ዓመታት መጠበቅ አስፈልጎታል (አንቀጽ 9, 10⁠ን ተመልከት)

9, 10. አብርሃምና ሣራ ለምን ያህል ጊዜ ይሖዋን መጠበቅ ነበረባቸው?

9 እስቲ የአብርሃምንና የሣራን ምሳሌ እንመልከት። አብርሃምና ሣራ “አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት [ከሚወርሱት]” ሰዎች መካከል ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “አብርሃም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ” ይሖዋ እንደሚባርከውና ዘሩን እንደሚያበዛለት የገባውን “የተስፋ ቃል [እንዳገኘ]” ይናገራል። (ዕብ. 6:12, 15) አብርሃም በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈለገው ለምንድን ነው? በአጭሩ፣ ይሖዋ የገባለት ቃል ፍጻሜውን እንዲያገኝ ጊዜ ያስፈልግ ስለነበር ነው። ይሖዋ ለአብርሃም የገባለት ቃል ሥራ ላይ መዋል የጀመረው በኒሳን 14, 1943 ዓ.ዓ. ነው፤ አብርሃምና ሣራ አብረዋቸው ይኖሩ ከነበሩት ሰዎች ጋር የኤፍራጥስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር የገቡት በዚህ ዓመት ነበር። አብርሃም ልጁ ይስሐቅ በ1918 ዓ.ዓ.  እስኪወለድ ድረስ 25 ዓመታት መጠበቅ ነበረበት፤ የልጅ ልጆቹ ኤሳውና ያዕቆብ በ1858 ዓ.ዓ. እስኪወለዱ ድረስ ደግሞ ለተጨማሪ 60 ዓመታት መጠበቅ አስፈልጎታል።—ዕብ. 11:9

10 አብርሃም በተስፋይቱ ምድር ውስጥ ምን ያህል ርስት ተሰጥቶት ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሆኖም [ይሖዋ] በወቅቱ በዚህ ምድር ምንም ርስት፣ ሌላው ቀርቶ [አብርሃም] እግሩን ሊያሳርፍ የሚችልበት መሬት እንኳ አልሰጠውም፤ ይሁንና ገና ልጅ ሳይኖረው ለእሱም ሆነ ከእሱ በኋላ ለዘሮቹ ምድሪቱን ርስት አድርጎ እንደሚሰጣቸው ቃል ገባለት።” (ሥራ 7:5) የአብርሃም ዘሮች ለአብርሃም ቃል የተገባለትን ምድር የሚወርስ ብሔር ሆነው የተደራጁት አብርሃም ኤፍራጥስን ከተሻገረ ከ430 ዓመታት በኋላ ነበር።—ዘፀ. 12:40-42፤ ገላ. 3:17

11. አብርሃም ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ የሆነው ለምንድን ነው? በትዕግሥት በመጠበቁስ ወደፊት ምን በረከት ያገኛል?

11 አብርሃም፣ ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም እርግጠኛ ስለነበር እሱን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ሆኗል። (ዕብራውያን 11:8-12ን አንብብ።) የተገባለትን ቃል ሙሉ ፍጻሜ በሕይወት ዘመኑ የማየት አጋጣሚ ባያገኝም ይሖዋን በደስታ ጠብቋል። አብርሃም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ትንሣኤ ሲያገኝ ምን ያህል እንደሚደሰት እስቲ አስቡት። የእሱና የዘሮቹ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ያህል ሰፊ ሽፋን እንደተሰጠው ሲያውቅ እንደሚገረም ምንም ጥርጥር የለውም። * ተስፋ ከተሰጠበት ዘር ጋር በተያያዘ ይሖዋ ያለው ዓላማ እንዲፈጸም በማድረግ ረገድ ስለተጫወተው ወሳኝ ሚና ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያውቅ በጣም እንደሚደሰት መገመት እንችላለን! ለረጅም ጊዜ በመጠበቁ ፈጽሞ እንደማይቆጭ የተረጋገጠ ነው።

12, 13. ዮሴፍ በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈለገው ለምንድን ነው? አዎንታዊ አመለካከት እንዳለው ያሳየውስ እንዴት ነው?

12 የአብርሃም የልጅ ልጅ ልጅ የሆነው ዮሴፍም ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደሆነ አሳይቷል። ዮሴፍ ከባድ ግፍ ተፈጽሞበታል። በመጀመሪያ፣ ገና የ17 ዓመት ልጅ ሳለ ወንድሞቹ ለባርነት ሸጡት። ከዚያም የጌታውን ሚስት አስገድዶ ለመድፈር ሞክሯል በሚል ተከሶ እስር ቤት ገባ። (ዘፍ. 39:11-20፤ መዝ. 105:17, 18) ዮሴፍ ለፈጸመው የጽድቅ ሥራ ከመባረክ ይልቅ እየተቀጣ ያለ ይመስል ነበር። ከ13 ዓመት በኋላ ግን ሁኔታው በአንዴ ተቀየረ። ከእስር ቤት የተለቀቀ ሲሆን በግብፅ ውስጥ ሁለተኛው ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆኖ ተሾመ።—ዘፍ. 41:14, 37-43፤ ሥራ 7:9, 10

13 ዮሴፍ የተፈጸመበት ግፍ እንዲመረር አድርጎት ነበር? ይሖዋ እንደተወው ተሰምቶት ይሆን? በፍጹም። ዮሴፍ በትዕግሥት እንዲጠባበቅ የረዳው ምንድን ነው? በይሖዋ ላይ የነበረው እምነት ነው። ይሖዋ ሁኔታዎችን እንደሚቆጣጠር እምነት ነበረው። ለወንድሞቹ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ ዮሴፍ እንዲህ ያለ እምነት እንዳለው ያሳያል፦ “አይዟችሁ አትፍሩ። ለመሆኑ እኔን በአምላክ ቦታ ያስቀመጠኝ ማን ነው? ምንም እንኳ እኔን ለመጉዳት አስባችሁ የነበረ ቢሆንም አምላክ ግን ይኸው ዛሬ እንደምታዩት ነገሩን ለመልካም አደረገው፤ የብዙ ሰዎችንም ሕይወት ለማዳን ተጠቀመበት።” (ዘፍ. 50:19, 20) በመጨረሻም ዮሴፍ በትዕግሥት መጠበቁ የሚያስገኘውን ውጤት ለማየት በቅቷል።

14, 15. (ሀ) ዳዊት ያሳየው ትዕግሥት አስገራሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ዳዊት በትዕግሥት እንዲጠብቅ የረዳው ምንድን ነው?

14 ንጉሥ ዳዊትም ብዙ ግፍ ተፈጽሞበታል። ይሖዋ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የቀባው ገና በልጅነቱ ቢሆንም በራሱ ነገድ ላይ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረው ከ15 ዓመት ገደማ በኋላ ነው። (2 ሳሙ. 2:3, 4) በእነዚያ ዓመታት ውስጥ፣ ታማኝ ያልነበረው ንጉሥ ሳኦል ሊገድለው ያሳድደው ነበር። * በመሆኑም ዳዊት በየአገሩ በመንከራተትና በየዋሻው በመደበቅ በስደት ለመኖር ተገዷል። ሳኦል በውጊያ ከተገደለ በኋላም እንኳ ዳዊት በመላው የእስራኤል  ብሔር ላይ ንጉሥ ሆኖ ለመግዛት ተጨማሪ ሰባት ዓመታት ገደማ መጠበቅ አስፈልጎታል።—2 ሳሙ. 5:4, 5

15 ዳዊት በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ የነበረው ለምንድን ነው? አራት ጊዜ “እስከ መቼ ነው?” ብሎ በጠየቀበት በዚያው መዝሙር ላይ የዚህን ጥያቄ መልስ ሰጥቶናል። እንዲህ ብሏል፦ “እኔ በበኩሌ በታማኝ ፍቅርህ እታመናለሁ፤ ልቤ በማዳን ሥራህ ሐሴት ያደርጋል። በእጅጉ ስለካሰኝ ለይሖዋ እዘምራለሁ።” (መዝ. 13:5, 6) ዳዊት በይሖዋ ታማኝ ፍቅር ታምኗል። ዳዊት፣ ይሖዋ እሱን ለማዳን እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ በደስታ ይጠባበቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ እንዴት እንደካሰው ያሰላስል ነበር። አዎ፣ ዳዊት በትዕግሥት መጠበቁ ፈጽሞ እንደማያስቆጨው ያውቅ ነበር።

ይሖዋ እሱ ራሱ የማያደርገውን ነገር እንድናደርግ አልጠየቀንም

16, 17. ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ የተዉልን እንዴት ነው?

16 ይሖዋ እሱ ራሱ የማያደርገውን ነገር እንድናደርግ አልጠየቀንም። በትዕግሥት በመጠበቅ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል። (2 ጴጥሮስ 3:9ን አንብብ።) ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ በአገዛዙ ላይ የተነሳው ጥያቄ በማያዳግም ሁኔታ ምላሽ እንዲያገኝ ሲል በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በትዕግሥት ሲጠባበቅ ቆይቷል። ስሙ ሙሉ በሙሉ የሚቀደስበትን ጊዜ “በትዕግሥት [በመጠባበቅ]” ላይ ይገኛል። ይህም ‘እሱን በጉጉት ለሚጠባበቁ ሁሉ’ ወደር የሌለው በረከት ያስገኛል።—ኢሳ. 30:18 ግርጌ

17 ኢየሱስም በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነበር። በምድር ላይ ሳለ የደረሰበትን የታማኝነት ፈተና በተሳካ ሁኔታ የተወጣ እንዲሁም በ33 ዓ.ም. የቤዛውን ዋጋ የከፈለ ቢሆንም መግዛት ለመጀመር እስከ 1914 ድረስ መጠበቅ አስፈልጎታል። (ሥራ 2:33-35፤ ዕብ. 10:12, 13) ጠላቶቹም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ የሚወገዱት በሺህ ዓመት ግዛቱ መጨረሻ ላይ ነው። (1 ቆሮ. 15:25) ይህ እስኪፈጸም ድረስ ኢየሱስ ለብዙ ዓመታት በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልገዋል፤ ይሁንና እንዲህ በማድረጉ ፈጽሞ እንደማይቆጭ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

በትዕግሥት ለመጠበቅ ምን ሊረዳን ይችላል?

18, 19. በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች እንድንሆን ምን ይረዳናል?

18 በግልጽ ማየት እንደምንችለው ይሖዋ ታጋሾች እንድንሆን ወይም በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች እንድንሆን ይፈልጋል። ይሁንና በዚህ ረገድ ምን ሊረዳን ይችላል? የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት መጸለይ ይኖርብናል። ትዕግሥት የመንፈስ ፍሬ ገጽታ እንደሆነ እናስታውስ። (ኤፌ. 3:16፤ 6:18፤ 1 ተሰ. 5:17-19) በመሆኑም በትዕግሥት ለመጽናት እንዲረዳን ይሖዋን አጥብቀን እንለምን።

19 በተጨማሪም አብርሃም፣ ዮሴፍና ዳዊት ይሖዋ የገባላቸውን ቃል ፍጻሜ በትዕግሥት እንዲጠብቁ የረዳቸው ምን እንደሆነ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። እነሱን የረዳቸው በይሖዋና እሱ ነገሮችን በሚይዝበት መንገድ ላይ የነበራቸው ጠንካራ እምነት ነው። በራሳቸውም ሆነ በግል ምቾታቸው ላይ አላተኮሩም። እነዚህ ሰዎች በመጨረሻ ምን በረከት እንዳገኙ ማሰላሰላችን በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ እንድናሳይ ያበረታታናል።

20. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

20 በመሆኑም የተለያየ ፈተናና መከራ ቢደርስብንም “በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ” ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እርግጥ ነው፣ “ይሖዋ ሆይ፣ እስከ መቼ ነው?” የምንልበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። (ኢሳ. 6:11) ይሁንና የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በሚሰጠን ብርታት በመታገዝ ልክ እንደ ኤርምያስ “ይሖዋ ድርሻዬ ነው . . . እሱን በትዕግሥት የምጠባበቀው ለዚህ ነው” ብለን መናገር እንችላለን።—ሰቆ. 3:21, 24

^ አን.11 ከዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፎች ውስጥ 15ቱ ከአብርሃም ጋር የተያያዘ ዘገባ የያዙ ናቸው። በተጨማሪም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች ከ70 ጊዜ በላይ ስለ አብርሃም ጠቅሰዋል።

^ አን.14 ሳኦል በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያጣው፣ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ ከሁለት ዓመት ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ነው፤ ይሁንና ለ38 ዓመታት ማለትም እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ መግዛቱን ቀጥሏል።—1 ሳሙ. 13:1፤ ሥራ 13:21