በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ታኅሣሥ 2017

ያዕቆብ በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የተካተተው የኤሳውን የብኩርና መብት ስለገዛ ነው?

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በጥንቷ እስራኤል በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የሚካተቱት የብኩርና መብት ያላቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ?

በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የሚካተቱት የብኩርና መብት ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ የተናገርንባቸው ጊዜያት ነበሩ። በዕብራውያን 12:16 ላይ ከሰፈረው ሐሳብ በመነሳት እዚህ ድምዳሜ መድረስ የሚቻል ይመስል ነበር። ጥቅሱ ኤሳው “ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው” እንደነበረና “ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን [ለያዕቆብ] አሳልፎ እንደሰጠ” ይናገራል። ይህ ሐሳብ ያዕቆብ ‘የብኩርና መብት’ ማግኘቱ በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ ለመካተት የሚያስችል አጋጣሚም እንደከፈተለት የሚጠቁም ይመስላል።—ማቴ. 1:2, 16፤ ሉቃስ 3:23, 34

ይሁን እንጂ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ስንመረምር በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የተካተቱት፣ የበኩር ልጆች ብቻ እንዳልሆኑ ማስተዋል እንችላለን። እስቲ አንዳንድ ማስረጃዎችን እንመልከት፦

ከያዕቆብ (እስራኤል) ልጆች መካከል በኩሩ ከልያ የተወለደው ሮቤል ነው። ያዕቆብ በጣም ከሚወዳት ሚስቱ ከራሔል የወለደው የበኩር ልጁ ደግሞ ዮሴፍ ነው። ሮቤል በሠራው ስህተት የተነሳ፣ የብኩርና መብቱ ወደ ዮሴፍ ተላለፈ። (ዘፍ. 29:31-35፤ 30:22-25፤ 35:22-26፤ 49:22-26፤ 1 ዜና 5:1, 2) ያም ሆኖ የመሲሑ የዘር  ሐረግ የመጣው በሮቤልም ሆነ በዮሴፍ በኩል አልነበረም። መሲሑ የመጣው የያዕቆብ አራተኛ ልጅ በሆነውና ከልያ በተወለደው በይሁዳ በኩል ነበር።—ዘፍ. 49:10

ሉቃስ 3:32 በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የተካተቱ ሌሎች ስድስት ሰዎችን ይጠቅሳል። እያንዳንዱ ሰው የበኩር ልጅ የነበረ ይመስላል። ለምሳሌ፣ ቦዔዝ ኢዮቤድን የወለደ ሲሆን ኢዮቤድም እሴይን ወልዷል።—ሩት 4:17, 20-22፤ 1 ዜና 2:10-12

ሆኖም የእሴይ ልጅ የሆነው ዳዊት ለቤቱ የበኩር ልጅ አልነበረም። እንዲያውም ዳዊት ከእሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች መካከል የመጨረሻው ነው። ሆኖም ዳዊት በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ ተካትቷል። (1 ሳሙ. 16:10, 11፤ 17:12፤ ማቴ. 1:5, 6) በተመሳሳይም፣ ሰሎሞን የዳዊት የበኩር ልጅ ባይሆንም በመሲሑ የዘር ሐረግ ዝርዝር ውስጥ ስሙ ይገኛል።—2 ሳሙ. 3:2-5

እንዲህ ሲባል ግን የበኩር ልጅ መሆን ምንም የሚያስገኘው ጥቅም አልነበረም ማለት አይደለም። የበኩር ልጅ በቤተሰብ ውስጥ የተከበረ ቦታ ያለው ሲሆን ብዙውን ጊዜም አባቱን ተክቶ የቤተሰብ ራስ የሚሆነው እሱ ነው። በተጨማሪም ከቤተሰቡ ንብረት ሁለት እጥፍ የመውረስ መብት ነበረው።—ዘፍ. 43:33፤ ዘዳ. 21:17፤ ኢያሱ 17:1

ይሁንና የብኩርና መብት ወደ ሌላ ልጅ ሊተላለፍ ይችላል። ለምሳሌ፣ አብርሃም የእስማኤልን የብኩርና መብት ወስዶ ለይስሐቅ ሰጥቶታል። (ዘፍ. 21:14-21፤ 22:2) ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ደግሞ የሮቤል የብኩርና መብት ከእሱ ተወስዶ ለዮሴፍ ተሰጥቷል።

አሁን ደግሞ ዕብራውያን 12:16⁠ን መለስ ብለን እንመልከት፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በመካከላችሁ ሴሰኛ ሰውም ሆነ ለአንድ ጊዜ መብል ሲል የብኩርና መብቱን አሳልፎ እንደሰጠው እንደ ኤሳው ቅዱስ ነገሮችን የማያደንቅ ሰው እንዳይገኝ ተጠንቀቁ።” እዚህ ጥቅስ ላይ ሊተላለፍ የተፈለገው ነጥብ ምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ላይ የተናገረው በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ ስለተካተቱ ሰዎች አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያኖችን “ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ [እንዲጓዙ]” እየመከራቸው ነበር። እንዲህ ካደረጉ ‘የአምላክን ጸጋ አያጡም’፤ በተቃራኒው ግን የፆታ ብልግና ከፈጸሙ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊደርስባቸው ይችላል። (ዕብ. 12:12-16) ይህ ከሆነ ደግሞ እንደ ኤሳው ሆኑ ማለት ነው። ኤሳው ‘ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት ሳያሳይ’ የቀረ ሲሆን ቃል በቃል ሥጋዊ ሰው ሆኗል።

ኤሳው የኖረው በጥንት ዘመን ስለሆነ ምናልባትም ቤተሰቡን ወክሎ አልፎ አልፎ መሥዋዕት የማቅረብ መብት ሳያገኝ አልቀረም። (ዘፍ. 8:20, 21፤ 12:7, 8፤ ኢዮብ 1:4, 5) ይሁን እንጂ ኤሳው ሥጋዊ አመለካከት የነበረው ሰው በመሆኑ፣ ብኩርናው የሚያስገኝለትን መብቶች በሙሉ በምስር ወጥ ለውጧል። ምናልባትም በአብርሃም ዘሮች ላይ እንደሚመጣ በትንቢት የተነገረው መከራ እንዳይደርስበት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 15:13) በተጨማሪም ኤሳው ሁለት አረማዊ ሴቶችን ማግባቱ ሥጋዊ ሰው ማለትም ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች አድናቆት የሌለው ሰው መሆኑን ያሳያል፤ ኤሳው ያደረገው ውሳኔ ወላጆቹንም ቢሆን አሳዝኗል። (ዘፍ. 26:34, 35) በእርግጥም ኤሳው፣ እውነተኛውን አምላክ የምታመልክ ሴት ለማግባት ጥረት ካደረገው ከያዕቆብ ምንኛ የተለየ ነበር!—ዘፍ. 28:6, 7፤ 29:10-12, 18

ታዲያ እስካሁን ካየናቸው ሐሳቦች በመነሳት በኢየሱስ ማለትም በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የተካተቱትን ሰዎች በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? አንዳንድ የበኩር ልጆች በመሲሑ የዘር ሐረግ ውስጥ የተካተቱ ቢሆንም ይህ የሆነው ሁልጊዜ አይደለም። ክርስቶስ የእሴይ የመጨረሻ ልጅ በነበረው በዳዊት በኩል እንደሚመጣ አይሁዳውያን መናገራቸው፣ ይህን ሐቅ እንደተቀበሉ የሚያረጋግጥ ነው።—ማቴ. 22:42