በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ታኅሣሥ 2017

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ክርስቲያን ባለትዳሮች ሉፕ (IUD) የተባለውን የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ከቅዱሳን መጻሕፍት አንጻር ተቀባይነት ያለው አማራጭ እንደሆነ አድርገው ሊመለከቱት ይችላሉ?

ክርስቲያን ባለትዳሮች ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መረጃዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መገምገም አለባቸው። ከዚያም በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና ይዘው ለመመላለስ የሚያስችል ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በምድር ላይ ሁለት ሰዎች (እንዲሁም ከጥፋት ውኃ በኋላ ስምንት ሰዎች) ብቻ በነበሩበት ጊዜ ይሖዋ “ብዙ ተባዙ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። (ዘፍ. 1:28፤ 9:1) መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችም ይህን መመሪያ መታዘዝ እንደሚጠበቅባቸው አይገልጽም። በመሆኑም ክርስቲያን ባለትዳሮች፣ የቤተሰባቸውን ቁጥር ለመመጠን አሊያም ለተወሰነ ጊዜ ሳይወልዱ ለመቆየት ሲሉ የእርግዝና መከላከያ ለመጠቀም ወይም ላለመጠቀም የመምረጥ ኃላፊነት አለባቸው። ታዲያ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ግምት ውስጥ ሊያስገቧቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ክርስቲያኖች ማንኛውንም የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንጻር መመዘን ይገባቸዋል። ውርጃን እንደ እርግዝና መከላከያ ዘዴ አድርገው የማይጠቀሙበት ለዚህ ነው። ሆን ብሎ ጽንስን ማስወረድ፣ እርግዝናው ቢቀጥል ኖሮ የሚወለደውን ሕፃን ሕይወት ማጥፋት ነው። ጽንስን ማስወረድ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለሕይወት አክብሮት እንድናሳይ ከሚሰጠው መመሪያ ጋር ይጋጫል። (ዘፀ. 20:13፤ 21:22, 23፤ መዝ. 139:16፤ ኤር. 1:5) ታዲያ ሉፕ ወይም IUD (intrauterine device) የሚባለውን የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ስለመጠቀምስ ምን ማለት ይቻላል?

በግንቦት 15, 1979 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 30-31 ላይ ይህን ጉዳይ የሚመለከት ማብራሪያ ወጥቶ ነበር። በዚያን ጊዜ እርግዝናን ለመከላከል በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉት የሉፕ ዓይነቶች ከፕላስቲክ የሚሠሩ ነበሩ፤ በማህፀን ውስጥ የሚቀመጡት እነዚህ የሉፕ ዓይነቶች ምንም ዓይነት ኬሚካልም ሆነ ሆርሞን የላቸውም። መጠበቂያ ግንቡ እንዲህ ዓይነቱ ዘዴ፣ እርግዝናን የሚከላከለው እንዴት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እንደማይታወቅ ገልጾ ነበር። በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ሉፕ፣ የወንዱ ዘር ከሴቷ እንቁላል ጋር እንዳይገናኝና እርግዝና እንዳይከሰት እንቅፋት የሚፈጥር ሁኔታ በማህፀን ውስጥ እንዲኖር ያደርጋል። ጽንስ ካልተፈጠረ ደግሞ ሕይወት አልጀመረም ማለት ነው።

 ሉፕ የወንዱ ዘር ከሴቷ እንቁላል ጋር እንዳይገናኝ ያደርጋል ቢባልም የወንዱ ዘር ከሴቷ እንቁላል ጋር የተገናኘባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። ከወንዱ ዘር ጋር ተገናኝቶ የዳበረው እንቁላል በማህፀን ቱቦ (Fallopian tube) ውስጥ ማደግ ሊጀምር ማለትም ከማህፀን ውጭ እርግዝና ሊከሰት (ectopic pregnancy) ይችላል፤ አሊያም ደግሞ የዳበረው እንቁላል ወደ ማህፀን ሊሄድ ይችላል። የዳበረው እንቁላል ወደ ማህፀን ከሄደ፣ በማህፀን ውስጥ የተቀመጠው ሉፕ የዳበረው እንቁላል በማህፀን ግድግዳ ላይ እንዳይጣበቅና ተፈጥሯዊው የእርግዝና ሂደት እንዳይቀጥል እንቅፋት ይፈጥራል። በዚህ መንገድ፣ በማደግ ላይ ያለው ጽንስ እንዲቋረጥ ያደርጋል፤ ይህም ውርጃ እንደመፈጸም ይቆጠራል። መጠበቂያ ግንቡ ነጥቡን ሲደመድም እንዲህ ይላል፦ “IUD [ሉፕ] መጠቀም ተገቢ ስለመሆኑ ጥያቄ የተፈጠረበት አንድ ክርስቲያን ከላይ የቀረበውን መረጃ፣ ቅዱስ ለሆነው ሕይወት አክብሮት እንድናሳይ ከሚያዝዘው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ አንጻር በቁም ነገር ሊገመግመው ይገባል።”—መዝ. 36:9

ይህ ርዕስ በ1979 ከወጣ ወዲህ በሳይንሱ ወይም በሕክምናው መስክ ከዚህ ዘዴ ጋር በተያያዘ የተሻሻለ ነገር አለ?

በአሁኑ ጊዜ በዋነኝነት የሚሠራባቸው ሁለት የሉፕ ዓይነቶች አሉ። አንደኛው፣ መዳብ የተጠቀለለበት ሉፕ ሲሆን ይህም በስፋት ጥቅም ላይ መዋል የጀመረው በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነበር። ሌላኛው ደግሞ ሆርሞን የያዘ ሉፕ ሲሆን ከ2001 ጀምሮ ገበያ ላይ ውሏል። እነዚህ ሁለት የሉፕ ዓይነቶች እርግዝናን ስለሚከላከሉበት መንገድ ምን የታወቀ ነገር አለ?

መዳብ የተጠቀለለበት ሉፕ፦ ቀደም ሲል እንደተብራራው ሉፕ፣ የወንዱ ዘር በማህፀን ውስጥ አልፎ ወደ ሴቷ እንቁላል መድረስ አስቸጋሪ እንዲሆንበት ያደርጋል። መዳብ የተጠቀለለበት ሉፕ ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ ደግሞ መዳቡ የወንዱን ዘር እንደሚገድለው ይታሰባል። * ከዚህም በላይ መዳብ የተጠቀለለበት ሉፕ በማህፀን ግድግዳ ላይ አንዳንድ ለውጦች እንደሚያስከትል ይታመናል።

ሆርሞን የያዘ ሉፕ፦ በአብዛኛው በእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ውስጥ የሚገኘው ዓይነት ሆርሞን የያዙ የተለያዩ የሉፕ ዓይነቶች አሉ። እነዚህ ሉፖች ሆርሞኑን በማህፀን ውስጥ ይለቁታል። እንደዚህ ዓይነቶቹ ሉፖች የአንዳንድ ሴቶች ማህፀን እንቁላል ማኩረት ወይም መልቀቅ (ovulation) እንዳይችል የሚያደርጉ ይመስላል። እርግጥ ነው፣ እንቁላል ካልተለቀቀ ጽንስ ሊፈጠር አይችልም። ከዚህም ባሻገር በእነዚህ ሉፖች ውስጥ ያለው ሆርሞን፣ የማህፀንን ግድግዳ እንደሚያሳሳው ይታመናል። * በተጨማሪም ይህ ዓይነቱ ሉፕ፣ በማህፀን አንገት ላይ የሚገኘውን ዝልግልግ ፈሳሽ የሚያወፍረው ሲሆን ይህም የወንዱ ዘር በሴቷ ብልት አልፎ ወደ ማህፀን እንዳይገባ ያግደዋል። መዳብ ወይም ሆርሞን የያዙ የሉፕ ዓይነቶች፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ይሠራበት ከነበረው የሉፕ ዓይነት በተጨማሪ እነዚህን ጥቅሞች ያስገኛሉ።

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሁለቱም የሉፕ ዓይነቶች በማህፀን ግድግዳ ላይ ለውጥ እንደሚያስከትሉ ይታመናል። በዚህ ዘዴ የምትጠቀም ሴት እንቁላል ብታኮርትና እንቁላሉ ከወንዱ ዘር ጋር ተገናኝቶ ጽንስ ቢፈጠርስ? ጽንሱ ወደ ማህፀን ሊገባ ቢችልም የማህፀን ግድግዳ በመሳሳቱ፣ ጽንሱ ግድግዳው ላይ መጣበቅ አይችልም። ይህም እርግዝናውን ገና ከጅምሩ ያጨናግፈዋል። ይሁን እንጂ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎችን የሚወስዱ ሴቶች ሊያጋጥማቸው እንደሚችለው ሁሉ፣ ሉፕ ከሚጠቀሙ ሴቶች ጋር በተያያዘም እንዲህ ያለው “መጨንገፍ” ሊያጋጥም የሚችለው ከስንት አንዴ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በመሆኑም መዳብ ወይም ሆርሞን የያዙ የሉፕ ዓይነቶች ጨርሶ ጽንስ እንዳይፈጠር ይከላከላሉ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ሰው የለም። ይሁን እንጂ ሳይንሳዊ ማስረጃው እንደሚጠቁመው እንዲህ ያሉት የሉፕ ዓይነቶች ቀደም ሲል በተመለከትናቸው መንገዶች፣ ጽንስ እንዳይፈጠር ስለሚከላከሉ እርግዝና የመከሰቱ አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነው።

ሉፕ ለመጠቀም የሚያስቡ ክርስቲያን ባለትዳሮች፣ በአካባቢያቸው ስለሚገኙ የሉፕ ዓይነቶች እንዲሁም ይህ ዘዴ ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞችና በሚስትየው ላይ ስለሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት ብቃት ካለው የሕክምና ባለሙያ ጋር መወያየት ይችላሉ። ባልና ሚስቱ ማንም ሰው፣ ሌላው ቀርቶ የሕክምና ባለሙያም እንኳ ቢሆን ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲወስንላቸው መጠበቅም ሆነ መፍቀድ አይኖርባቸውም። (ሮም 14:12፤ ገላ. 6:4, 5) ይህን ውሳኔ ማድረግ ያለባቸው ራሳቸው ናቸው። ባልና ሚስቱ፣ አምላክን ለማስደሰትና በእሱ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዘው ለመመላለስ የሚያስችላቸውን የጋራ ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል።—ከ1 ጢሞቴዎስ 1:18, 19 እና 2 ጢሞቴዎስ 1:3 ጋር አወዳድር።

^ አን.4 የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ያወጣው አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “ሉፑ ላይ ያለው መዳብ ከበዛ ይህ ዘዴ ከ99 በመቶ በላይ ውጤታማ ይሆናል። ይህም ሲባል ሉፕ ከሚጠቀሙ 100 ሴቶች መካከል በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አንዷም እንኳ አታረግዝም እንደ ማለት ነው። በሉፑ ላይ ያለው መዳብ በቀነሰ መጠን የዚህ ዘዴ ውጤታማነትም ይቀንሳል።”

^ አን.5 ሆርሞን የያዙ የሉፕ ዓይነቶች የማህፀንን ግድግዳ ስለሚያሳሱ ከባድ የወር አበባ ፍሰትን ለመቆጣጠር ሲባል፣ ያገቡም ሆኑ ያላገቡ ሴቶች እንዲጠቀሙባቸው የሚታዘዙበት ጊዜ አለ።