በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ታኅሣሥ 2017

 የሕይወት ታሪክ

ሁሉን ነገር ትቶ ጌታን መከተል

ሁሉን ነገር ትቶ ጌታን መከተል

“ለመስበክ ከሄድክ ተመልሰህ እንዳትመጣ። ከመጣህ እግርህን ነው የምሰብረው።” የአባቴ ዛቻ ጆሮዬ ላይ ቢያቃጭልብኝም እኔ ግን ለመሄድ ወሰንኩ። ጌታን ለመከተል ስል ከወሰድኳቸው እርምጃዎች መካከል ይህ የመጀመሪያው ነው። በወቅቱ ገና የ16 ዓመት ወጣት ነበርኩ።

እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥመኝ የቻለው እንዴት ነው? እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ላውጋችሁ። የተወለድኩት ሐምሌ 29, 1929 ሲሆን ያደግሁት ደግሞ በቡላካን፣ ፊሊፒንስ በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ ነው። በወቅቱ ከባድ የኢኮኖሚ ድቀት ስለነበር ያለን መሠረታዊ ነገር ብቻ ነው። በዚያ ላይ የጃፓን ሠራዊት ፊሊፒንስን ወረረ፤ ይህ ሲሆን እኔ ገና ለጋ ወጣት ነበርኩ። ይሁን እንጂ የምንኖርባት መንደር የምትገኘው ጦርነቱ ከሚካሄድበት ቦታ ራቅ ብላ ስለሆነ በጦርነቱ የደረሰብን ጉዳት የለም። በተጨማሪም በአካባቢያችን ሬድዮ፣ ቴሌቪዥን አሊያም ጋዜጣ ስለሌለ ስለ ጦርነቱ መረጃ የሚደርሰን በስሚ ስሚ ነበር።

ወላጆቼ ካፈሯቸው ስምንት ልጆች መካከል እኔ ሁለተኛው ስሆን ስምንት ዓመት ሲሞላኝ አያቶቼ ከእነሱ ጋር እንድኖር ወሰዱኝ። የካቶሊክ እምነት ተከታዮች የነበርን ቢሆንም አያቴ ስለ የትኛውም ሃይማኖት መወያየት የሚከብደው ዓይነት ሰው አይደለም፤ እንዲያውም ጓደኞቹ የሚሰጡትን አንዳንድ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ይዞ ይመጣ ነበር። በታጋሎግ ቋንቋ የተተረጎሙትን ፕሮቴክሽን፣ ሴፍቲ እና አንከቨርድ * የተሰኙ ቡክሌቶችን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ አሳይቶኝ እንደነበረ ትዝ ይለኛል። መጽሐፍ ቅዱስን፣ በተለይም አራቱን ወንጌሎች ማንበብ ያስደስተኝ ነበር። ይህም የኢየሱስን ምሳሌ የመከተል ፍላጎት እንዲያድርብኝ አድርጓል።—ዮሐ. 10:27

ጌታን ለመከተል የሚያስችል ትምህርት አገኘሁ

በ1945 የጃፓን ሠራዊት ፊሊፒንስን ለቅቆ ወጣ። በዚያው ጊዜ አካባቢ ወላጆቼ ወደ ቤት እንድመለስ ጠየቁኝ። አያቴም እንድሄድ ስላበረታታኝ ወደ ቤት ተመለስኩ።

ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ማለትም በታኅሣሥ 1945 ከአንጋት ከተማ የመጡ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች መንደራችን ውስጥ መስበክ ጀመሩ። አንድ አረጋዊ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታችን መጡና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “መጨረሻዎቹ ቀናት” ምን እንደሚል አብራሩልን። (2 ጢሞ. 3:1-5) በተጨማሪም እኚህ ወንድም በአቅራቢያችን በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ በሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ እንድንገኝ ጋበዙን። ወላጆቼ ወደ ስብሰባው ባይሄዱም እኔ ግን በፕሮግራሙ ላይ ተገኘሁ። በስብሰባው ላይ 20 የሚያህሉ ሰዎች የተገኙ ሲሆን አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን ይጠይቁ ነበር።

በወቅቱ የሚደረገው ውይይት ምንም ስላልገባኝ ትቻቸው ለመሄድ ወሰንኩ። ይሁንና ለመሄድ ልነሳ ስል የመንግሥቱን መዝሙር መዘመር ጀመሩ። በመዝሙሩ በጣም ተመስጬ እዚያው ቆየሁ።  ከመዝሙርና ከጸሎት በኋላ ሁላችንም በቀጣዩ እሁድ በአንጋት ከተማ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ተጋበዝን።

ክሩስ በተባለው የይሖዋ ምሥክር መኖሪያ ቤት በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለመገኘት አብዛኞቻችን 8 ኪሎ ሜትር ያህል በእግር መጓዝ አስፈልጎናል። በቦታው 50 የምንሆን ተሰብሳቢዎች ነበርን፤ ትናንሽ ልጆችም እንኳ ሳይቀሩ ጥልቅ በሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ መስጠታቸው በጣም አስደነቀኝ። በእነዚያ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ከተገኘሁ በኋላ፣ ቀደም ሲል ከንቲባ የነበሩት አሁን ግን በአቅኚነት የሚያገለግሉት ወንድም ዳሚያን ሳንቶስ ቤታቸው እንዳድር ጋበዙኝ። አብዛኛውን የሌሊቱን ክፍለ ጊዜ ያሳለፍነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በመወያየት ነበር።

በዚያ ዘመን አብዛኞቻችን መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ስንረዳ ወዲያውኑ እርምጃ እንወስድ ነበር። የተወሰኑ ስብሰባዎች ላይ ከተገኘን በኋላ ወንድሞች፣ እኔንና ያጠኑ የነበሩትን ሌሎች ሰዎች “መጠመቅ ትፈልጋላችሁ?” ብለው ጠየቁን። እኔም “አዎ፣ እፈልጋለሁ” አልኳቸው። ‘ጌታችንን ክርስቶስን እንደ ባሪያ ለማገልገል’ ልባዊ ፍላጎት አድሮብኝ ነበር። (ቆላ. 3:24) በመሆኑም የካቲት 15, 1946 እኔና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠና አንድ ሌላ ሰው በአቅራቢያችን በሚገኝ ወንዝ ውስጥ ተጠመቅን።

አንድ ሰው ተጠምቆ ክርስቲያን ከሆነ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል አዘውትሮ መስበክ እንደሚያስፈልገው ተገንዝበን ነበር። ሆኖም አባቴ መስበኬ ስላላስደሰተው “ለመስበክ ዕድሜህ ገና አልደረሰም። ደግሞም ወንዝ ውስጥ መጥለቅ ሰባኪ አያደርግህም” አለኝ። እኔም አምላክ የመንግሥቱን ምሥራች እንድንሰብክ እንደሚፈልግ አብራራሁለት። (ማቴ. 24:14) አክዬም “ለአምላክ የተሳልኩትን ስእለት መፈጸም እፈልጋለሁ” አልኩት። አባቴ መግቢያው ላይ የገለጽኩትን ዛቻ የሰነዘረው በዚህ ጊዜ ነው፤ እንዳልሰብክ ሊከለክለኝ ቆርጦ ነበር። ከቤተሰቤ ጋር በተያያዘ የተከሰተው ይህ ሁኔታ በሕይወቴ ውስጥ ሁሉን ነገር ትቼ መንፈሳዊ ግቦችን ለመከታተል የሚያስችለኝ አጋጣሚ እንዲከፈት አድርጓል።

በአንጋት ከተማ የሚኖረው ወንድም ክሩስና ቤተሰቡ አብሬያቸው እንድኖር ግብዣ አቀረቡልኝ። በተጨማሪም እኔንና የመጨረሻ ልጃቸውን ኖራን አቅኚ እንድንሆን አበረታቱን። ኅዳር 1, 1947 ሁለታችንም የአቅኚነት አገልግሎታችንን ጀመርን። ኖራ፣ አነስ ባለች ሌላ ከተማ ውስጥ ስታገለግል እኔ ደግሞ አንጋት ውስጥ ማገልገሌን ቀጠልኩ።

አንዳንድ ነገሮችን መተው

አቅኚ ሆኜ ማገልገል ከጀመርኩ ከሦስት ዓመት በኋላ፣ አርል ስቲዋርት የሚባል ከቅርንጫፍ ቢሮ የመጣ አንድ ወንድም በአንጋት ከተማ በሚገኝ አደባባይ ላይ ከ500 ለሚበልጡ ሰዎች ንግግር አቅርቦ ነበር። ንግግሩን ያቀረበው በእንግሊዝኛ ሲሆን እኔም ፍሬ ሐሳቡን እዚያ ለነበሩት ሰዎች በታጋሎግ ቋንቋ አብራራሁላቸው። በትምህርት ቤት የቆየሁት ለሰባት ዓመታት ብቻ ቢሆንም አስተማሪዎቻችን አዘውትረው እንግሊዝኛ የሚናገሩ መሆናቸው ጠቅሞኛል። በተጨማሪም በወቅቱ በታጋሎግ ቋንቋ ያሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በጣም ጥቂት ስለነበሩ አብዛኞቹን ጽሑፎቻችንን ያጠናኋቸው በእንግሊዝኛ ነው፤ ይህም እንግሊዝኛዬን ለማሻሻል ረድቶኛል። በመሆኑም ያንን ንግግርም ሆነ በሌሎች ጊዜያት የቀረቡ ንግግሮችን ለማስተርጎም የሚያስችል የእንግሊዝኛ እውቀት ነበረኝ።

ወንድም ስቲዋርት ንግግሩን ባስተረጎምኩለት ቀን፣ በቅርንጫፍ ቢሮው ማገልገል የሚችሉ አንድ ወይም ሁለት አቅኚ ወንድሞች እንደሚፈለጉ በአካባቢው ላሉ ጉባኤዎች ተናግሮ ነበር። ይህ ግብዣ የቀረበው ሚስዮናውያኑን ተክቶ በቤቴል የሚሠራ ሰው ስለተፈለገ ነው፤ ሚስዮናውያኑ “የቲኦክራሲው እድገት” በሚል ጭብጥ በ1950 በኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመካፈል ወደዚያ ያቀኑ ነበር። ወደ ቤቴል ከተጋበዙት ወንድሞች መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ። በመሆኑም ቤቴል ውስጥ ለማገልገል ስል፣ የለመድኩትን አካባቢ እንዲሁም የምቀርባቸውን ወንድሞችና እህቶች ትቼ ሄድኩ።

ሰኔ 19, 1950 አዲሱን የሥራ ምድብ ማለትም የቤቴል አገልግሎቴን ጀመርኩ። በወቅቱ የቤቴል አገልግሎታችንን የምናከናውነው ዙሪያውን በትላልቅ ዛፎች በተከበበ ሰፊ የሆነ አሮጌ ቤት ውስጥ ነበር፤ ግቢው አንድ ሄክታር ስፋት ነበረው። በዚያ የሚያገለግሉ ብዙ ነጠላ ወንድሞች ነበሩ። በማለዳ ተነስቼ ኩሽና ውስጥ እሠራለሁ። ከሦስት ሰዓት ገደማ በኋላ ደግሞ በልብስ ንጽሕና ክፍሉ ውስጥ ልብሶችን እተኩሳለሁ። ከሰዓትም በዚሁ ፕሮግራም መሠረት ሥራዎችን አከናውናለሁ። ሚስዮናውያኑ ከብሔራት አቀፍ ስብሰባው ከተመለሱ በኋላም በቤቴል ማገልገሌን ቀጠልኩ። ቤቴል ውስጥ መጽሔቶችን በፖስታ የማሸግ እንዲሁም ከጽሑፍ ኮንትራት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የመሥራት መብት አግኝቻለሁ፤ በተጨማሪም በእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ እሠራ ነበር። የተጠየቅኩትን ሁሉ በፈቃደኝነት አከናውን ነበር።

ፊሊፒንስን ትቼ ወደ ጊልያድ ትምህርት ቤት ሄድኩ

በ1952 በጊልያድ ትምህርት ቤት 20ኛው ክፍል እንድማር ግብዣ ሲቀርብልኝ በጣም ተደሰትኩ፤ ከእኔ ሌላ ከፊሊፒንስ የተጋበዙ ሌሎች ስድስት ወንድሞችም ነበሩ። በዩናይትድ ስቴትስ ያየናቸውም ሆኑ ያጋጠሙን አብዛኞቹ ነገሮች ለእኛ እንግዳ ናቸው። በእርግጥም ሁኔታዎቹ እኔ ካደግኩባት ትንሿ መንደራችን ፈጽሞ የተለዩ ነበሩ።

በጊልያድ አብረውኝ ከተማሩት ወንድሞች መካከል የተወሰኑት

ለምሳሌ ያህል፣ ከዚያ በፊት የማናውቃቸውን በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አንዳንድ ዕቃዎች አጠቃቀም መማር ነበረብን። የአየሩ  ጠባይም ቢሆን በጣም የተለየ ነበር! አንድ ቀን ጠዋት ወደ ደጅ ስወጣ ውጭው ጥጥ የተነጠፈበት መስሏል። በረዶ መሬት ላይ ተጋግሮ ሳይ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር። በዚያ ላይ ብርዱ አጥንት ይሰብራል!

ይሁን እንጂ ከእነዚህ አዳዲስ ነገሮች ጋር ለመላመድ ያደረግኩት ትግል በጊልያድ ካገኘሁት ግሩም ሥልጠና ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አስተማሪዎቻችን ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። ትርጉም ባለው መንገድ ምርምር ማድረግና ማጥናት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ተምረናል። በጊልያድ ያገኘሁት ሥልጠና መንፈሳዊነቴን እንዳሻሽል በሚገባ ረድቶኛል።

ከተመረቅሁ በኋላ ኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ በምትገኘው በብሮንክስ ለተወሰነ ጊዜ በልዩ አቅኚነት እንዳገለግል ተመደብኩ። ይህም ሐምሌ 1953 በዚያ በተደረገው “የአዲሱ ዓለም ኅብረተሰብ” የተሰኘ ትልቅ ስብሰባ ላይ የመካፈል አጋጣሚ አስገኝቶልኛል። ከስብሰባው በኋላ ወደ ፊሊፒንስ ተመልሼ እንዳገለግል ተመደብኩ።

ምቹ የሆነውን የከተማ ሕይወት መተው

በቅርንጫፍ ቢሮው የነበሩት ወንድሞች “አሁን በወረዳ ሥራ ማገልገል ትጀምራለህ” አሉኝ። ይህም የይሖዋን በጎች ለመርዳት ራቅ ወዳሉ መንደሮችና ከተሞች የተጓዘውን የጌታችንን ፈለግ ቃል በቃል ለመከተል የሚያስችል አዲስ ምድብ ነበር። (1 ጴጥ. 2:21) የፊሊፒንስ ትልቁ ደሴት በሆነው በሉዞን በሚገኝ አንድ ወረዳ ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። ወረዳዬ የቡላካን፣ የኑዬቫ ኤሲሃ፣ የታርላክ እና የዛምቤልስ ግዛቶችን ጨምሮ በማዕከላዊ ሉዞን የሚገኝን ሰፋ ያለ አካባቢ የሚያካልል ነው። አንዳንዶቹን አነስተኛ ከተሞች ለመጎብኘት ሲየራ ማድራ የሚባሉትን አቀበት ቁልቁለት የበዛባቸው ተራሮች አቋርጬ መሄድ ነበረብኝ። ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሚሄድ የሕዝብ መጓጓዣ አልነበረም፤ በመሆኑም በትላልቅ መኪኖች ላይ በሚጫኑ ግንዶች ላይ ተቀምጬ መሄድ እችል እንደሆነ ሾፌሮቹን እጠይቅ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ የሚፈቅዱልኝ ቢሆንም ይህ ዓይነቱ መጓጓዣ ምቹ አልነበረም።

በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አብዛኞቹ ጉባኤዎች ከተቋቋሙ ገና ጥቂት ጊዜያቸው ሲሆን ያሏቸው አስፋፊዎችም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። ስለዚህ ወንድሞች የጉባኤ ስብሰባዎችንና የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማደራጀት እንዲችሉ እረዳቸው ነበር፤ እነሱም ይህን እገዛ በአድናቆት ተመልክተውታል።

ከጊዜ በኋላ፣ መላውን የቢኮል ክልል ወዳቀፈ አንድ ወረዳ ተዛወርኩ። በወረዳው ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ቡድኖች የሚገኙት ተራርቀው ነው፤ በተጨማሪም ልዩ አቅኚዎች ምሥራቹ ወዳልተሰበከባቸው ወደ እነዚህ አካባቢዎች በመምጣት ያቋቋሟቸው ናቸው። በአንድ ወቅት በእንግድነት ለተቀበሉኝ ወንድሞች መጸዳጃ ቤት መጠቀም እንደፈለግኩ ነገርኳቸው፤ ለመጸዳጃ ቤት በሚጠቀሙበት ጉድጓድ ላይ፣ ግራና ቀኝ ሁለት ግንዶች ተጋድመው ነበር። ግንዶቹን ስረግጣቸው ይዘውኝ ጉድጓዱ ውስጥ ገቡ። ከጉድጓዱ ከወጣሁ በኋላ ተጣጥቤ ለቁርስ ለመቅረብ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶብኛል!

በዚህ ወረዳ እያለሁ፣ ከእኔ ጋር በአቅኚነት ማገልገል ስለጀመረችው ስለ ኖራ ማሰብ ጀመርኩ። በወቅቱ በዱማጉዌቴ ሲቲ በልዩ አቅኚነት እያገለገለች ስለነበረ ልጠይቃት ሄድኩ። ከዚያም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ደብዳቤ ከተጻጻፍን በኋላ በ1956 ተጋባን። ከሠርጋችን በኋላ ያለውን የመጀመሪያ ሳምንት ያሳለፍነው በራፑ ራፑ ደሴት የሚገኝን አንድ ጉባኤ በመጎብኘት ነው። በዚያ ስናገለግል ተራሮችን መውጣትና መውረድ እንዲሁም ብዙ የእግር መንገድ መሄድ ጠይቆብናል፤ ቢሆንም ራቅ ባሉት በእነዚያ አካባቢዎች የሚኖሩትን  ወንድሞች ከኖራ ጋር አብረን መጎብኘት በመቻላችን በጣም ተደስተን ነበር!

ወደ ቤቴል እንደገና መጠራት

በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ለአራት ዓመት ገደማ ካገለገልን በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ እንድናገለግል ተጋበዝን። በመሆኑም ጥር 1960 ወደ ቤቴል መጣን፤ ለረጅም ዘመን የቆየንበት የቤቴል ሕይወት የጀመረው በዚህ ዓመት ነበር። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከባድ ኃላፊነቶችን ከሚወጡ ወንድሞች ጋር በማገልገል ብዙ ትምህርት ያገኘሁ ሲሆን ኖራም በቤቴል ውስጥ በተለያዩ የሥራ ምድቦች ላይ ሠርታለች።

አንድ ወንድም ወደ ሴቡዋኖ ቋንቋ እያስተረጎመልኝ በትልቅ ስብሰባ ላይ ንግግር ሳቀርብ

በቤቴል ማገልገሌ በፊሊፒንስ ያለውን ፈጣን መንፈሳዊ እድገት በቅርበት ለማየት አስችሎኛል። መጀመሪያ በወጣትነቴ ወደ ቤቴል ስመጣ በመላ አገሪቱ የነበሩት አስፋፊዎች 10,000 ነበሩ። አሁን በፊሊፒንስ ከ200,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ያሉ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቴላውያንም አስፈላጊ የሆነውን የስብከት ሥራ ይደግፋሉ።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሥራው እያደገ ስለሄደ ተጨማሪ የቤቴል ሕንፃዎችን መገንባት አስፈላጊ ሆነ። ስለዚህ የበላይ አካሉ ትልቅ ሕንፃ ለመገንባት የሚያስችል ቦታ እንድናፈላልግ ጠየቀን። እኔና የሕትመት ክፍል የበላይ ተመልካቹ፣ በቅርንጫፍ ቢሮው ዙሪያ ወደሚኖሩት ሰዎች ቤት እየሄድን መሬት መሸጥ የሚፈልግ ሰው ይኖር እንደሆነ መጠየቅ ጀመርን። ሆኖም መሬቱን የሚሸጥ አንድም ሰው አላገኘንም፤ እንዲያውም በአካባቢው ከሚኖሩት ቻይናውያን አንዱ “እኛ ቻይናውያን መሬት መግዛት እንጂ መሸጥ አናውቅም” አለን።

የወንድም አልበርት ሽሮደርን ንግግር ሳስተረጉም

ይሁን እንጂ አንድ ቀን፣ በአካባቢው የሚኖር አንድ ሰው መሬቱን መግዛት እንፈልግ እንደሆነ ጠየቀን፤ ሰውየው እንዲህ ያለ ጥያቄ ያቀረበልን ኑሮውን በዩናይትድ ስቴትስ ለማድረግ ወደዚያ ሊሄድ ስለነበረ ነው። ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ አስገራሚ ነገሮች መከሰት ጀመሩ። ቅርንጫፍ ቢሮው አጠገብ የሚኖር ሌላ ሰውም መሬቱን ለመሸጥ ወሰነ፤ በዙሪያው ያሉት ሰዎችም እንዲህ እንዲያደርጉ አበረታታቸው። የሚገርመው፣ “እኛ ቻይናውያን መሬት መግዛት እንጂ መሸጥ አናውቅም” ያለንን ሰውዬ መሬትም መግዛት ቻልን። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ የቅርንጫፍ ቢሮው ይዞታ በፊት ከነበረው ከሦስት እጥፍ በላይ እንዲጨምር አድርጓል። የይሖዋ አምላክ ፈቃድ ባይሆን ኖሮ እንዲህ ያለ ነገር ሊከሰት እንደማይችል እርግጠኛ ነኝ።

በ1950 ቤቴል ስገባ በዕድሜ ትንሹ እኔ ነበርኩ። አሁን ግን ከቤቴል ቤተሰብ አባላት መካከል በዕድሜ አንጋፋዎቹ እኔና ባለቤቴ ነን። ጌታችን በመራኝ በየትኛውም አቅጣጫ እሱን በመከተሌ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። እውነት ነው፣ ወላጆቼ ከቤታቸው አባረውኛል፤ ይሖዋ ግን የእምነት አጋሮቼን ያቀፈ የአንድ ትልቅ ቤተሰብ አባል የመሆን መብት ሰጥቶኛል። የተሰጠን የሥራ ምድብ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚያቀርብልን ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። እኔና ኖራ ይሖዋ በደግነት ተነሳስቶ ላደረገልን ነገሮች ሁሉ እጅግ አመስጋኝ ነን፤ ሌሎችም ይሖዋን እንዲፈትኑት እናበረታታለን።—ሚል. 3:10

ኢየሱስ ቀረጥ ሰብሳቢ ለነበረው ለማቴዎስ ሌዊ “ተከታዬ ሁን” የሚል ግብዣ አቅርቦለት ነበር። ታዲያ ማቴዎስ ምን ምላሽ ሰጠ? “ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ በመተው ተነስቶ [ኢየሱስን] ይከተለው ጀመር።” (ሉቃስ 5:27, 28) እኔም ሁሉን ነገር ትቼ ጌታችንን ለመከተል የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሕይወቴ አግኝቼአለሁ፤ ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉና የተትረፈረፉ በረከቶችን እንዲያጣጥሙ አበረታታለሁ።

በፊሊፒንስ ላለው እድገት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያደረግን በመሆኑ ደስተኞች ነን

^ አን.6 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ፤ አሁን መታተም አቁመዋል።