በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሰኔ 2017

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ከአምላክ ድርጅት መመሪያ ሲሰጣቸው ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ ይገባል?

ለመታዘዝ ፈጣን መሆን አለባቸው። ራሳቸውን እንዲህ ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ፦ ‘በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎች መንፈሳዊነት ለማጠናከር አስተዋጽኦ አደርጋለሁ? የሚተላለፉትን መመሪያዎች ለመቀበልና ለመደገፍ ፈጣን ነኝ?’—w16.11 ገጽ 11

እውነተኛ ክርስቲያኖች በታላቂቱ ባቢሎን ቀንበር ሥር የሆኑት መቼ ነው?

ይህ የሆነው ሐዋርያት ከሞቱ ብዙም ሳይቆይ ነው። በዚያ ወቅት የቀሳውስት ቡድን ብቅ ማለት ጀመረ። ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የክህደት ክርስትናን በማስፋፋት በስንዴ የተመሰሉትን ክርስቲያኖች ተሰሚነት ለማሳጣት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ከ1914 በፊት በነበሩት ዓመታት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነፃ መውጣት ጀመሩ።—w16.11 ገጽ 23-25

ለፌቭር ዴታፕለ የሠራው ሥራ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው የምንለው ለምንድን ነው?

ለፌቭር በ1520ዎቹ ዓመታት ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያገኝ ለማድረግ ሲል መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፈረንሳይኛ ተረጎመ። ለፌቭር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ያብራራበት መንገድ በማርቲን ሉተር፣ በዊልያም ቲንደልና በጆን ካልቪን ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።—wp16.6 ከገጽ 10-12

‘በሥጋዊ ነገሮች ላይ በማተኮር’ እና ‘በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር’ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? (ሮም 8:6)

በሥጋዊ ነገሮች ላይ የሚያተኩር ሰው ትኩረቱ ያረፈው ፍጽምና የጎደለው ሥጋው ባሉት ምኞቶችና ዝንባሌዎች ላይ ነው፤ አዘውትሮ የሚያወራው ስለ ሥጋዊ ነገር ነው። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ሰው ግን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚኖር ከመሆኑም ሌላ መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ወደ ሞት ይመራል፤ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ግን ሕይወትና ሰላም ያስገኛል።—w16.12 ከገጽ 15-17

ጭንቀትን ለመቀነስ የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ዘዴዎች ምንድን ናቸው?

ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ ስጥ፤ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ሚዛናዊ ሁን፤ በየዕለቱ አረፍ የምትልበት ጊዜ ይኑርህ፤ በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ አሰላስል፤ በሁኔታዎች መቀለድን ተማር፤ አዘውትረህ ስፖርት ሥራ፤ እንዲሁም በደንብ ተኛ።—w16.12 ከገጽ 22-23

“ሄኖክ ሞትን እንዳያይ . . . ወደ ሌላ ቦታ ተወሰደ።” (ዕብ. 11:5) ይህ የሆነው እንዴት ነው?

አምላክ፣ ሄኖክ ሊሞት እንደሆነ ሳይታወቀው በሞት እንዲያንቀላፋ በማድረግ ወስዶታል ሊባል ይችላል።—wp17.1 ከገጽ 12-13

ልክን ማወቅ ዛሬም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ልክን ማወቅ የሚለው አገላለጽ ስለ ራስ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝን እንዲሁም አቅምን ማወቅን ያመለክታል። የእኛ ባሕርይ በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ማሰብ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ለራሳችን ከልክ ያለፈ ግምት መስጠት የለብንም።—w17.01 ገጽ 18

ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚገኘውን የበላይ አካል እንደሚመራው ሁሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የበላይ አካልም እንደመራው የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንዲገነዘቡ መንፈስ ቅዱስ ረድቷቸዋል። በመላእክት ድጋፍ የስብከት ሥራውን መርተዋል፤ እንዲሁም የሚሰጡት መመሪያ የተመሠረተው በአምላክ ቃል ላይ ነበር። በዛሬው ጊዜ ካለው የበላይ አካል ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—w17.02 ከገጽ 26-28

ቤዛው ውድ ስጦታ ነው እንድንል የሚያደርጉን ምን ምክንያቶች አሉ?

አራት ምክንያቶች አሉ፦ ስጦታውን የሰጠው አካል፣ ስጦታው የተሰጠበት ምክንያት፣ ስጦታውን ለመስጠት የተከፈለው መሥዋዕት፣ እንዲሁም የስጦታው አስፈላጊነት ናቸው። በእነዚህ ምክንያቶች ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል።—wp17.2 ከገጽ 4-6

አንድ ክርስቲያን ውሳኔ ካደረገ በኋላ ሐሳቡን መቀየር ይችላል?

ቃላችንን መጠበቃችን ተገቢ ነው። ይሁንና ውሳኔያችንን መለስ ብለን ማጤን የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል። የነነዌ ሰዎች ንስሐ በገቡ ጊዜ አምላክ በነነዌ ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ጥፋት ከማምጣት ተቆጥቧል። እኛም አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች መቀየራቸው ወይም አዲስ መረጃ ማግኘታችን ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል።—w17.03 ከገጽ 16-17

ሐሜት በጣም አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

ሐሜት፣ የተፈጠረው ችግር ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆንና ችግሩ ይበልጥ እንዲባባስ ሊያደርግ ይችላል። የተሰማን ስሜት ትክክል ሆነም አልሆነ፣ ሐሜት ማሰራጨት የተፈጠረውን ሁኔታ ለማስተካከል ሊረዳ አይችልም።—w17.04 ገጽ 21