አገልግሎታችን አስፈላጊና ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ ከምንሰብክላቸው ሰዎች መካከል ይህን የማይገነዘቡ አሉ። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማወቅ ቢፈልጉም እንኳ ከእኛ ጋር የአምላክን ቃል ማጥናት አስፈላጊ መሆኑ ላይታያቸው ይችላል።

የጌቨን ሁኔታ ይህን ያሳያል፤ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ቢጀምርም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ግብዣ ሲቀርብለት ፈቃደኛ አልሆነም። እንዲህ ብሏል፦ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ እውቀት በጣም አነስተኛ ነበር፤ አለማወቄ ደግሞ እንዲታወቅብኝ አልፈለግኩም። እንዳልታለል እሰጋ ነበር፤ ከዚህም ሌላ የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን አልፈለግኩም።” አንተ ምን ይመስልሃል? ጌቨን መቼም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንደማያጠና ይሰማህ ነበር? እንዲህ ሊሰማህ አይገባም! የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በሰዎች ላይ የሚያሳድሩትን በጎ ተጽዕኖ እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ጥንት ለነበሩት ሕዝቦቹ “ካፊያ ሣር ላይ እንደሚወርድ፣ . . . ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠባል” ብሏቸው ነበር። (ዘዳ. 31:19, 30፤ 32:2) ከጤዛ ጋር በተያያዘ እስቲ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ፤ እነዚህ ነጥቦች በአገልግሎታችን ላይ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት መርዳት እንደምንችል ይጠቁሙናል።—1 ጢሞ. 2:3, 4

 አገልግሎት ከጤዛ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

ጤዛ ኃይለኛ አይደለም። በአየር ውስጥ ያለው የውኃ ተን ቀስ በቀስ እየወረደ ሲጠራቀም ጤዛ ይፈጠራል። የይሖዋ ቃላት ‘እንደ ጤዛ እንደሚንጠባጠቡ’ መገለጹ ለሕዝቦቹ የሚናገረው በደግነት፣ በአሳቢነት እንዲሁም ኃይለኛ ባልሆነ መንገድ መሆኑን ያመለክታል። እኛም ለሌሎች አመለካከት አክብሮት ስናሳይ ይሖዋን እንመስለዋለን። ሰዎች፣ ራሳቸው አመዛዝነው ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ እናበረታታለን። እንደዚህ ያለ አሳቢነት በምናሳይበት ጊዜ የምንናገራቸው ቃላት በቀላሉ ተቀባይነት ሊያገኙና አገልግሎታችንም ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን ይችላል።

ጤዛ መንፈስን ያድሳል። ሌሎችን ይበልጥ መርዳት የምንችለው እንዴት እንደሆነ የምናስብ ከሆነ አገልግሎታችን መንፈስ የሚያድስ ይሆናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጌቨን፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ጫና አልተደረገበትም። ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ ቀርቦ ያነጋገረው ክሪስ የተባለ ወንድም፣ ጌቨን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት አስደሳች እንዲሆንለት ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን ይሞክር ነበር። ክሪስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጭብጥ ወይም ዋና መልእክት እንዳለውና ጌቨን ይህንን ማወቁ በሚገኝባቸው ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበውን ትምህርት በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንደሚያስችለው ነገረው። ቀጥሎም ክሪስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን እሱን ያሳመነው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሆነ ገለጸለት። ይህም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ብዙ ውይይት እንዲያደርጉ መንገድ ከፈተ። ጌቨን በእነዚህ ውይይቶች መንፈሱ የታደሰ ሲሆን በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ።

ጤዛ ሕይወትን ያለመልማል። በእስራኤል ምድር፣ ዝናብ ለብዙ ወራት የማይጥልበት ሞቃትና ደረቅ የሆነ ወቅት አለ። በመሆኑም ከጤዛ የሚገኘው እርጥበት ባይኖር ኖሮ ተክሎች ጠውልገው ይደርቁ ነበር። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ አስቀድሞ በትንቢት እንደተናገረው በመንፈሳዊ ሁኔታ ድርቅ አለ። (አሞጽ 8:11) ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ አጋሮቻቸው በሆኑት “ሌሎች በጎች” እየታገዙ የመንግሥቱን መልእክት ሲሰብኩ ‘ከይሖዋ ዘንድ እንደሚወርድ ጠል’ እንደሚሆኑ ይሖዋ ቃል ገብቶ ነበር። (ሚክ. 5:7፤ ዮሐ. 10:16) ይሖዋ የሚያዘጋጀው ሕይወትን የሚያለመልም መንፈሳዊ ጠል፣ ለሰዎች የምንሰብከውን የመንግሥቱን ምሥራችም ይጨምራል፤ ታዲያ ይህን መልእክት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን?

ጤዛ ከይሖዋ የሚገኝ በረከት ነው። (ዘዳ. 33:13) አገልግሎታችን፣ ቀና ምላሽ ለሚሰጡ ሰዎች በረከት ሊሆንላቸው ይችላል። ጌቨን እንዲህ ዓይነት በረከት አግኝቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ አማካኝነት ለጥያቄዎቹ ሁሉ መልስ አገኘ። ብዙም ሳይቆይ እድገት አድርጎ የተጠመቀ ሲሆን አሁን ከሚስቱ ከጆይስ ጋር የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ እያደረገ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች ምድርን በመንግሥቱ መልእክት እያረሰረሷት ነው

አገልግሎታችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱት

ስለ ጤዛ ማሰባችን፣ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ በግለሰብ ደረጃ የምንጫወተውን ሚና ከፍ አድርገን እንድንመለከትም ሊያበረታታን ይችላል። እንዴት? እያንዳንዷ የውኃ ጠብታ በራሷ ብዙም ጥቅም የላትም፤ ይሁንና በርካታ የውኃ ጠብታዎች ሲጠራቀሙ ምድርን ያረሰርሳሉ። በተመሳሳይም በአገልግሎቱ በግለሰብ ደረጃ የምናበረክተው ድርሻ ለእኛ በጣም ትንሽ መስሎ ይታየን ይሆናል። ይሁን እንጂ ፈቃደኛ የሆኑት የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ በኅብረት የሚያከናውኑት ሥራ “ለብሔራት ሁሉ” ምሥክርነት እንዲሰጥ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (ማቴ. 24:14) ታዲያ አገልግሎታችን ለሰዎች ከይሖዋ እንደመጣ በረከት ይሆንላቸው ይሆን? የምንሰብከው መልእክት እንደ ጤዛ ኃይለኛ ያልሆነ፣ መንፈስን የሚያድስና ሕይወትን የሚያለመልም ከሆነ ለምንሰብክላቸው ሰዎች በረከት እንደሚሆንላቸው የተረጋገጠ ነው!