በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መስከረም 2017

“የአምላክ ቃል . . . ኃይለኛ ነው”

“የአምላክ ቃል . . . ኃይለኛ ነው”

“የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው።”—ዕብ. 4:12

መዝሙሮች፦ 96, 94

1. የአምላክ ቃል ኃይል እንዳለው እርግጠኞች የሆንነው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ቃል ማለትም አምላክ ለሰው ልጆች ያስተላለፈው መልእክት “ሕያውና ኃይለኛ” እንደሆነ ሙሉ እምነት አለን። (ዕብ. 4:12) ብዙዎቻችን የምንመራው ሕይወት፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ከዚህ ቀደም ሌቦች፣ የዕፅ ሱሰኞች ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት የሚመሩ ነበሩ። ሌሎች ደግሞ በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ሁሉ ነገር የተሟላላቸው ቢሆኑም በሕይወታቸው ውስጥ የጎደላቸው ነገር እንዳለ ይሰማቸው ነበር። (መክ. 2:3-11) ምንም ተስፋ ያልነበራቸውና ግራ የተጋቡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ባለው ሰዎችን የመለወጥ ኃይል በመታገዝ በሕይወት መንገድ ላይ መጓዝ ሲጀምሩ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚል ተከታታይ ርዕስ መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡትን እንዲህ ያሉ በርካታ ተሞክሮዎች በማንበብ እንደተደሰትን ግልጽ ነው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክርስቲያኖች እውነትን ከተቀበሉ በኋላም እንኳ ቀጣይ የሆነ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እንደሚረዳቸው ማስተዋል ችለናል።

2. የአምላክ ቃል ኃይል እንዳለው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የታየው እንዴት ነው?

2 በዘመናችን ያሉ በርካታ ሰዎች የአምላክን ቃል በማጥናት ትልቅ ለውጥ ማድረጋቸው ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም! እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች፣ ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ የነበራቸውን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ክርስቲያኖችን ያስታውሱናል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11ን አንብብ።) ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክን መንግሥት እንዳይወርሱ የሚያደርጓቸውን የተለያዩ ድርጊቶች ከዘረዘረ በኋላ “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ” በማለት ተናግሯል። ሆኖም  እነዚህ ሰዎች በቅዱሳን መጻሕፍትና በአምላክ መንፈስ እርዳታ ለውጥ ማድረግ ችለዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ እውነትን ከተቀበሉ በኋላም ከባድ መንፈሳዊ ችግሮችን ማሸነፍ ነበረባቸው። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አንድ ቅቡዕ ወንድም ከክርስቲያን ጉባኤ እንደተወገደና ከጊዜ በኋላ እንደተመለሰ ይናገራል። (1 ቆሮ. 5:1-5፤ 2 ቆሮ. 2:5-8) እነዚህ የእምነት ባልንጀሮቻችን የተለያዩ ችግሮች እንዳጋጠሟቸውና ከአምላክ ቃል ባገኙት እርዳታ እነዚህን ችግሮች እንደተወጡ ማንበባችን የሚያበረታታ አይደለም?

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 በእርግጥም የአምላክ ቃል ታላቅ ኃይል አለው፤ በመሆኑም በእጃችን የሚገኘውን ይህን መሣሪያ በጥሩ ሁኔታ ልንጠቀምበት እንፈልጋለን። (2 ጢሞ. 2:15) በዚህ ርዕስ ሥር የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል (1) በግል ሕይወታችን፣ (2) በአገልግሎታችን፣ (3) በስብሰባዎች ላይ ስናስተምር በተሟላ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። እንዲህ ማድረጋችን፣ የሚጠቅመንን ነገር ለሚያስተምረን ለአፍቃሪው አባታችን ለይሖዋ ፍቅርና አድናቆት እንዳለን ለማሳየት ይረዳናል።—ኢሳ. 48:17

በግል ሕይወታችን

4. (ሀ) የአምላክ ቃል በሕይወታችን ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብበት ጊዜ ለማግኘት ምን ዘዴ ተጠቅመሃል?

4 የአምላክ ቃል በሕይወታችን ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ከፈለግን ቃሉን አዘውትረን ማንበባችን አስፈላጊ ነው፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ኢያሱ 1:8) እርግጥ ነው፣ የአብዛኞቻችን ፕሮግራም በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተጣበበ ነው። ያም ቢሆን ማንኛውም ነገር፣ ሌላው ቀርቶ የግድ ልንወጣቸው የሚገቡ ኃላፊነቶቻችንም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራማችንን እንዲያስተጓጉሉብን መፍቀድ አይኖርብንም። (ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ።) በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የሚያነቡበት ጊዜ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ዘዴ ቀይሰዋል፤ አንዳንዶች ጠዋት እንቅስቃሴያቸውን ከመጀመራቸው በፊት ማንበቡን አመቺ ሆኖ አግኝተውታል፤ ሌሎች ደግሞ ከመተኛታቸው በፊት አሊያም ቀን ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡበት ጊዜ መድበዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች “ሕግህን ምንኛ ወደድኩ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” በማለት የተናገረውን የመዝሙራዊውን ሐሳብ ይጋራሉ።—መዝ. 119:97

5, 6. (ሀ) ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በአምላክ ቃል ላይ በምናሰላስልበት ጊዜ ይበልጥ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (ሐ) የአምላክን ቃል ማንበብህና ባነበብከው ነገር ላይ ማሰላሰልህ በግል ሕይወትህ የጠቀመህ እንዴት ነው?

5 መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ በተጨማሪ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰላችን አስፈላጊ ነው። (መዝ. 1:1-3) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጊዜ የማይሽረው ጥበብ በግል ሕይወታችን በሚገባ ልንጠቀምበት የምንችለው ይህን ካደረግን ብቻ ነው። የምናነበው የታተመውንም ይሁን በኤሌክትሮኒክ ቅጂ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዋነኛው ግባችን መልእክቱ ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባና ለተግባር እንዲያነሳሳን ማድረግ ሊሆን ይገባል።

6 ከምናሰላስለው ነገር ይበልጥ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ካነበብን በኋላ ቆም ብለን ራሳችንን የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ይህ ዘገባ  ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በሕይወቴ ተግባራዊ እያደረግኩ ያለሁት እንዴት ነው? ማሻሻያ ማድረግ የምችለው በየትኞቹ አቅጣጫዎች ነው?’ በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰላችንና ያነበብነውን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል እንዲረዳን ወደ ይሖዋ መጸለያችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይበልጥ እንድንነሳሳ ይረዳናል። በዚህ መንገድ የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል በግል ሕይወታችን በሚገባ ልንጠቀምበት እንችላለን።—2 ቆሮ. 10:4, 5

በአገልግሎታችን

7. በአገልግሎታችን የአምላክን ቃል በሚገባ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

7 በአገልግሎታችን ላይ የአምላክን ቃል በሚገባ ለመጠቀም ምን ሊረዳን ይችላል? ስንሰብክና ስናስተምር በተደጋጋሚ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መጥቀስ ይኖርብናል። አንድ ወንድም ይህን ጉዳይ ለማስረዳት እንዲህ ብሏል፦ “ከይሖዋ ጋር ከቤት ወደ ቤት እያገለገልክ ቢሆን ሁሌም አንተ ብቻ ተናጋሪ ትሆናለህ? ወይስ ይሖዋ እንዲናገር ታደርጋለህ?” በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀጥታ ስናነብላቸው ይሖዋ እንዲያነጋግራቸው እያደረግን ነው ማለት ይቻላል። ለምንወያይበት ርዕሰ ጉዳይ ተስማሚ የሆነ አንድ ጥቅስ እኛ ልንናገር ከምንችለው ከየትኛውም ሐሳብ የበለጠ ኃይል አለው። (1 ተሰ. 2:13) በመሆኑም ‘ምሥራቹን ለምሰብክላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለማንበብ የተቻለኝን ሁሉ ጥረት አደርጋለሁ?’ በማለት ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው።

8. በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ጥቅሶችን ማንበባችን ብቻ በቂ ያልሆነው ለምንድን ነው?

8 እርግጥ ነው፣ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማንበባችን ብቻ በቂ አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በርካታ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው እውቀት በጣም አነስተኛ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበሩ ሰዎችም ተመሳሳይ ነገር ሊባል ይችላል። (ሮም 10:2) በመሆኑም ለአንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስላነበብንለት ብቻ ግለሰቡ ጥቅሱን ይረዳዋል ብለን መደምደም አይኖርብንም። የምናነጋግራቸው ሰዎች ነጥቡን እንዲረዱት ለማድረግ ቁልፍ ቃላትን ደግመን በማንበብ ወይም ሌላ ዘዴ በመጠቀም የጥቅሱን ዋና ሐሳብ ነጥለን ማውጣት አለብን፤  ከዚያም ትርጉሙን ማብራራት ያስፈልገናል። እንዲህ ማድረጋችን የአምላክ ቃል ወደምናነጋግራቸው ሰዎች ልብና አእምሮ ዘልቆ እንዲገባ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።—ሉቃስ 24:32ን አንብብ።

9. ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲኖራቸው በሚያደርግ መልኩ ጥቅሶችን ማስተዋወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

9 በተጨማሪም ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲኖራቸው በሚያደርግ መልኩ ጥቅሶችን ማስተዋወቃችን አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ “ፈጣሪያችን ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል እንመልከት” ማለት እንችላለን። ስለ ክርስትና እምብዛም እውቀት የሌለውን ሰው ስናነጋግር ደግሞ “አንድ ቅዱስ መጽሐፍ ምን እንደሚል ባሳይህ ደስ ይለኛል” ልንለው እንችላለን። የምናነጋግረው ሰው ስለ ሃይማኖት ግድ የሌለው ከሆነ ደግሞ “ይህን ጥንታዊ አባባል ከዚህ በፊት ሰምተኸው ታውቃለህ?” ብለን ልንጠይቀው እንችላለን። የእያንዳንዱን ግለሰብ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው ማስተካከል ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 9:22, 23

10. (ሀ) አንድ ወንድም ያጋጠመውን ተሞክሮ ተናገር። (ለ) በአገልግሎትህ ላይ የአምላክ ቃል ኃይል እንዳለው የተመለከትከው እንዴት ነው?

10 በርካታ አስፋፊዎች የአምላክን ቃል በአገልግሎት ላይ መጠቀማቸው በሚያነጋግሯቸው ሰዎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስተውለዋል። እስቲ አንድ ተሞክሮ እንመልከት። አንድ ወንድም መጽሔቶቻችንን ለበርካታ ዓመታት ላነበቡ አንድ አረጋዊ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ አደረገላቸው። ወንድም በቅርቡ የወጣውን መጠበቂያ ግንብ እንዲሁ ሰጥቷቸው ከመሄድ ይልቅ በመጽሔቱ ውስጥ የሚገኘውን 2 ቆሮንቶስ 1:3, 4⁠ን አነበበላቸው። ጥቅሱ “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ . . . በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያጽናናናል” ይላል። ሰውየው በተነበበላቸው ጥቅስ ልባቸው በጥልቅ ስለተነካ ጥቅሱን በድጋሚ እንዲያነብላቸው ወንድምን ጠየቁት። ከዚያም እኚህ ሰው፣ እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው መጽናኛ በጣም ያስፈልጋቸው እንደነበር ገለጹ። ሰውየው በዚህ ጥቅስ ምክንያት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት አደረባቸው። በእርግጥም የአምላክ ቃል ያለው ኃይል በአገልግሎታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል ቢባል አትስማማም?—ሥራ 19:20

በስብሰባዎች ላይ ስናስተምር

11. በስብሰባዎች ላይ ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞች ምን ኃላፊነት አለባቸው?

11 ሁላችንም በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ መገኘት ያስደስተናል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የምንገኝበት ዋነኛ ዓላማ ይሖዋን ማምለክ ነው። በተጨማሪም በስብሰባዎቻችን ላይ ከሚሰጠው መንፈሳዊ መመሪያ በእጅጉ እንጠቀማለን። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞች ባገኙት ትልቅ መብት ደስተኞች ናቸው። ይሁንና ይህ መብት ከባድ ኃላፊነት እንደሚያስከትልም መገንዘብ ይኖርባቸዋል። (ያዕ. 3:1) ምንጊዜም ቢሆን፣ የሚያስተምሩት ትምህርት ሙሉ በሙሉ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ አለባቸው። በስብሰባዎች ላይ ንግግር የማቅረብ መብት ካለህ የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል በንግግርህ ላይ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው?

12. አንድ ተናጋሪ ንግግሩ በዋነኝነት ያተኮረው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲሆን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

12 ንግግርህ በዋነኝነት ያተኮረው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ እንዲሆን ጥረት አድርግ። (ዮሐ. 7:16) ይህ ምን ማድረግን ይጠይቃል? በመጀመሪያ ደረጃ፣ የአድማጮች ትኩረት በምትጠቀምባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ እንዲያርፍ ማድረግ ይኖርብሃል፤ የአድማጮች ትኩረት በሌላ በማንኛውም ነገር ላይ ማለትም በምትጠቀምባቸው ተሞክሮዎች፣ ምሳሌዎች ሌላው ቀርቶ ንግግሩን በምታቀርብበት መንገድ ላይ እንዳያርፍ ጥንቃቄ አድርግ። በተጨማሪም አንድ ሰው ብዙ ጥቅሶችን ስላነበበ ብቻ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስተምሯል ሊባል እንደማይችል አስታውስ። እንዲያውም ብዙ ጥቅሶችን ማንበብ አድማጮች አንዱንም ሳይጨብጡ እንዲሄዱ ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም ቁልፍ ጥቅሶችን በጥንቃቄ ምረጥ፤ ከዚያም ጥቅሶቹን አንብብ፣ ጥሩ አድርገህ አብራራ፣ ምሳሌዎችን ተጠቀም እንዲሁም ጥቅሶቹ ከትምህርቱ ጋር የሚያያዙት እንዴት እንደሆነ ግለጽ። (ነህ. 8:8) ንግግርህ የተመሠረተው ድርጅቱ ባዘጋጀው አስተዋጽኦ ላይ ከሆነ አስተዋጽኦውንና በውስጡ የሚገኙትን ጥቅሶች በሚገባ አጥናቸው። በአስተዋጽኦው ላይ ያሉት ነጥቦች ከጥቅሶቹ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ለማስተዋል ሞክር። ከዚያም ቁልፍ ጥቅሶችን በመምረጥ በአስተዋጽኦው  ላይ ያሉትን ነጥቦች አብራራ። (በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም በተባለው መጽሐፍ ከጥናት 21 እስከ 23 ላይ አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮችን ማግኘት ትችላለህ።) ከሁሉም በላይ ግን በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ውድ እውነት ለማስተላለፍ እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቅ።—ዕዝራ 7:10ን እና ምሳሌ 3:13, 14ን አንብብ።

13. (ሀ) አንዲት እህት በጉባኤ ስብሰባ ላይ በተጠቀሰ ጥቅስ ምክንያት ሕይወቷ የተቀየረው እንዴት ነው? (ለ) በስብሰባዎቻችን ላይ ጥቅሶች ከተብራሩበት መንገድ በግልህ ምን ጥቅም አግኝተሃል?

13 በአውስትራሊያ የምትገኝ አንዲት እህት በክርስቲያን ጉባኤ ላይ በተጠቀሰ አንድ ጥቅስ ምክንያት ሕይወቷ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። ይህች እህት አሳዛኝ የልጅነት ሕይወት አሳልፋለች። ከጊዜ በኋላ ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በጎ ምላሽ በመስጠት ራሷን ወስና የተጠመቀች ቢሆንም ይሖዋ እንደሚወዳት ማመን ይከብዳት ነበር። በኋላ ግን አምላክ እንደሚወዳት ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን ችላለች። አመለካከቷን እንድትቀይር የረዳት ምንድን ነው? በስብሰባ ላይ ሲብራራ በሰማችው አንድ ጥቅስ ላይ ማሰላሰሏና ተያያዥ በሆኑ ሌሎች ጥቅሶች ላይ ምርምር ማድረጓ ነው። * አንተስ በጉባኤ፣ በወረዳ አሊያም በክልል ስብሰባዎች ላይ የሰማኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለውጥ እንድታደርግ አነሳስቶህ ያውቃል?—ነህ. 8:12

14. ለይሖዋ ቃል ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 በእርግጥም ይሖዋ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ስለሰጠን በጣም አመስጋኞች ነን። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ቃሉን ለሰው ልጆች ሰጥቷል፤ በተጨማሪም ቃሉ ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር የሰጠው ተስፋ እንዲፈጸም አድርጓል። (1 ጴጥ. 1:24, 25) የአምላክን ቃል አዘውትረን ማንበባችን፣ በግል ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረጋችንና ቃሉን ሌሎችን ለመርዳት መጠቀማችን ተገቢ ነው። እንዲህ በማድረግ አምላክ ለሰጠን ውድ ስጦታ ፍቅርና አድናቆት እንዳለን እናሳያለን፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ስጦታውን ለሰጠን አካል ማለትም ለይሖዋ አምላክ ፍቅርና አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን።

^ አን.13 አመለካከቴን እንድቀይር ያደረገኝ ነገር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።