በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መስከረም 2017

እንደ ይሖዋ ሩኅሩኅ ሁኑ

እንደ ይሖዋ ሩኅሩኅ ሁኑ

“ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ።”—ዘፀ. 34:6

መዝሙሮች፦ 57, 147

1. ይሖዋ ራሱን ለሙሴ የገለጠለት በምን መንገድ ነው? ይህስ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

በአንድ ወቅት አምላክ ራሱን ለሙሴ ሲገልጥ ስሙንና ባሕርያቱን ነግሮታል። መጀመሪያ ላይ የጠቀሳቸው ባሕርያት ደግሞ ምሕረትና ርኅራኄ ናቸው። (ዘፀአት 34:5-7ን አንብብ።) ይሖዋ ስለ ኃይሉ ወይም ስለ ጥበቡ መናገር ይችል ነበር። ይሁንና ይሖዋ ጎላ አድርጎ የገለጸው አገልጋዮቹን ለመርዳት ፈቃደኛ መሆኑን የሚያሳዩ ባሕርያቱን ነው፤ ምክንያቱም ሙሴ በዚያን ወቅት አምላክ እንደሚደግፈው የሚያሳይ ማረጋገጫ ይፈልግ ነበር። (ዘፀ. 33:13) አምላክ እነዚህን ማራኪ ባሕርያት ከሌሎቹ ባሕርያቱ ሁሉ አስቀድሞ እንደጠቀሰ ማወቃችን የሚያበረታታ አይደለም? ይህ ርዕስ የሌሎችን ሥቃይ ወይም መከራ መረዳትንና ያጋጠማቸውን ችግር ለማቅለል ልባዊ ፍላጎት ማሳየትን በሚያመለክተው በርኅራኄ ባሕርይ ላይ ትኩረት ያደርጋል።

2, 3. (ሀ) የሰው ልጆች ርኅራኄ የማሳየት ተፈጥሯዊ ችሎታ አላቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ስለ ርኅራኄ ይበልጥ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 ሰዎች የተፈጠሩት በአምላክ መልክ ነው። ይሖዋ ሩኅሩኅ በመሆኑ የሰው ልጆችም በተፈጥሯቸው ርኅራኄ የማሳየት ችሎታ አላቸው፤ እውነተኛውን አምላክ የማያውቁ ሰዎችም ጭምር የሌሎች ደህንነት ያሳስባቸዋል። (ዘፍ. 1:27) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ርኅራኄ ስላሳዩ ሰዎች የሚናገሩ በርካታ ዘገባዎች ይገኛሉ። በሰለሞን ፊት ቆመው የልጁን እውነተኛ ወላጅ ማንነት በተመለከተ ስለተካሰሱ ሁለት ዝሙት አዳሪዎች የሚናገረውን ዘገባ ለማሰብ ሞክር። ሰለሞን ትክክለኛዋን እናት ለማወቅ ሲል ልጁ ለሁለት እንዲሰነጠቅ ትእዛዝ ሰጠ፤ በዚህ ወቅት የልጁ እናት አንጀቷ ተላወሰ። ይህም ከባድ እርምጃ እንድትወስድ ማለትም  ልጇን ለሌላኛዋ ሴት ለመስጠት እንድትስማማ አድርጓታል። (1 ነገ. 3:23-27) የሕፃኑን የሙሴን ሕይወት ያተረፈችውን የፈርዖንን ልጅ ታሪክም መጥቀስ እንችላለን። ሙሴ የዕብራውያን ልጅ እንደሆነና ሊገደል እንደሚገባው የምታውቅ ቢሆንም ‘ለሕፃኑ ስላዘነችለት’ ወይም ስለራራችለት እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ ልታሳድገው ወሰነች።—ዘፀ. 2:5, 6

3 ስለ ርኅራኄ ይበልጥ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን እንድንመስል ስለሚያበረታታን ነው። (ኤፌ. 5:1) የተፈጠርነው ርኅራኄ ማሳየት እንድንችል ተደርገን ቢሆንም ከአዳም የወረስነው አለፍጽምና ራስ ወዳዶች መሆን እንዲቀናን ያደርገናል። አንዳንድ ጊዜ ‘ሌሎችን እንርዳ ወይስ የራሳችንን ፍላጎት እናስቀድም’ የሚለውን ጉዳይ መወሰን ከባድ ሊሆንብን ይችላል። አንዳንዶች በውስጣቸው ያለውን የራስ ወዳድነት ስሜት ለማሸነፍ ሁልጊዜ ትግል ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ታዲያ ርኅራኄን ለማዳበር ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በመጀመሪያ፣ ይሖዋ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች ርኅራኄ ያሳዩት እንዴት እንደሆነ ጊዜ ወስደህ ለመመርመር ጥረት አድርግ። ከዚያም በዚህ ረገድ የአምላክን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት እንደሆነና ይህን ማድረግህ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልህ ለማሰብ ሞክር።

ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ፍጹም ምሳሌ የሆነው ይሖዋ

4. (ሀ) ይሖዋ መላእክቱን ወደ ሰዶም የላከው ለምንድን ነው? (ለ) ስለ ሎጥና ስለ ልጆቹ ከሚናገረው ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ርኅራኄ እንዳሳየ የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎችን እናገኛለን። አምላክ ለሎጥ ያደረገለትን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጻድቅ የነበረው ሎጥ የሰዶምና የገሞራ ነዋሪዎች በሚፈጽሙት ዓይን ያወጣ ምግባር “እጅግ እየተሳቀቀ ይኖር” ነበር። በእርግጥም አምላክ መጥፎ ሥነ ምግባር የነበራቸው እነዚህ ሰዎች እንዲጠፉ መወሰኑ ተገቢ ነበር። (2 ጴጥ. 2:7, 8) አምላክ ሎጥን ከሚመጣው ጥፋት ለማዳን መላእክቱን ላከ። መላእክቱም ሎጥና ቤተሰቡ ጥፋት የተበየነባቸውን ከተሞች ለቀው እንዲወጡ አቻኮሏቸው። ሆኖም “ሎጥ በዘገየ ጊዜ ይሖዋ ስለራራለት [መላእክቱ] የእሱን እጅ፣ የሚስቱን እጅና የሁለቱን ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዋ አስወጡት።” (ዘፍ. 19:16) ይህ ዘገባ፣ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ የሚያሳይ አይደለም?—ኢሳ. 63:7-9፤ ያዕ. 5:11 ግርጌ፤ 2 ጴጥ. 2:9

5. እንደ 1 ዮሐንስ 3:17 ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ርኅራኄ ለማሳየት የሚረዱን እንዴት ነው?

5 ይሖዋ ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ከመሆኑም በላይ ይህን ባሕርይ ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለሕዝቦቹ አስተምሯል። የአንድን ሰው ልብስ መያዣ አድርጎ መውሰድን አስመልክቶ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕግ እንደ ምሳሌ እንመልከት። (ዘፀአት 22:26, 27ን አንብብ።) አንድ ጨካኝ የሆነ አበዳሪ፣ መያዣ አድርጎ የወሰደውን ልብስ ለማስቀረት ሊፈተን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ተበዳሪው ለብሶ የሚተኛው ልብስ እንዲያጣ ያደርገዋል። ይሁንና ይሖዋ ሕዝቡ እንዲህ ያለውን ርኅራኄ የጎደለው አመለካከት እንዲያስወግዱና ርኅራኄ የጎደለው ድርጊት እንዳይፈጽሙ ነግሯቸዋል። ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ሕዝቡ ርኅራኄ እንዲያሳዩ ይፈልግ ነበር። ከዚህ ሕግ በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት መገንዘባችን እኛንም ለተግባር አያነሳሳንም? ወንድሞቻችን እንዲሞቃቸው ማድረግ ማለትም ችግራቸው ቀለል እንዲልላቸው መርዳት እየቻልን ሲቸገሩ ዝም ብለን ልናያቸው ይገባል?—ቆላ. 3:12፤ ያዕ. 2:15, 16፤ 1 ዮሐንስ 3:17ን አንብብ።

6. ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆኑት እስራኤላውያን ወደ እሱ እንዲመለሱ ካደረገው ተደጋጋሚ ጥረት ምን እንማራለን?

6 ይሖዋ ሕዝቡ የሆኑት እስራኤላውያን ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜም እንኳ ርኅራኄ ያሳያቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የአባቶቻቸው አምላክ ይሖዋ ለሕዝቡና ለማደሪያው ስፍራ ስለራራ መልእክተኞቹን እየላከ በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃቸው ነበር።” (2 ዜና 36:15) እኛም ከኃጢአት መንገዳቸው በመመለስ የአምላክን ሞገስ ሊያገኙ ለሚችሉ ሰዎች ተመሳሳይ ርኅራኄ ልናሳይ አይገባም? ይሖዋ በቅርቡ በሚመጣው የፍርድ ቀን ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) በመሆኑም ይሖዋ ክፉዎችን ለማጥፋት እርምጃ እስኪወስድ ድረስ የእሱን ርኅራኄ  የሚያሳየውን የማስጠንቀቂያ መልእክት ማወጃችንን እንቀጥል።

7, 8. አንድ ቤተሰብ ይሖዋ ርኅራኄ እንዳሳየው የተሰማው ለምንድን ነው?

7 የአምላክን ርኅራኄ የሚያሳዩ በርካታ ተሞክሮዎችን መጥቀስ ይቻላል። ሚላን * የተባለ የ12 ዓመት ልጅና ቤተሰቡ በ1990ዎቹ የእርስ በርስ ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ወቅት ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሚላን፣ ወንድሙ፣ ወላጆቹና የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች በአውቶቡስ ተሳፍረው ከቦስኒያ ወደ ሰርቢያ እየተጓዙ ነበር። ይህን ጉዞ የሚያደርጉት በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲሆን የሚላን ወላጆች የሚጠመቁት በዚህ ስብሰባ ላይ ነበር። ሆኖም ድንበር ላይ ሲደርሱ ወታደሮች የሚላንን ቤተሰብ በዜግነታቸው ምክንያት ከአውቶቡሱ እንዲወርዱ አደረጓቸው፤ ሌሎቹን ወንድሞች ግን እንዲሄዱ ፈቀዱላቸው። ወታደሮቹ ሚላንንና ቤተሰቡን ለሁለት ቀን ካቆዩአቸው በኋላ የወታደሮቹ ኃላፊ እነዚህን ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለበት አለቃውን በሬዲዮ ጠየቀው። ኃላፊው አለቃውን የሚያነጋግረው ከቤተሰቡ አጠገብ ቆሞ ስለነበር አለቃው “አውጥተህ ረሽናቸው!” ሲለው ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ሰሙ።

8 ኃላፊው ከወታደሮቹ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ሁለት ሰዎች ወደ ቤተሰቡ ጠጋ ብለው የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ነገሯቸው። ሁለቱ ሰዎች ቤተሰቡ ስላጋጠመው ሁኔታ የሰሙት በአውቶቡሱ ላይ ከተሳፈሩ ሌሎች ሰዎች ነበር። እነዚህ ሰዎች ሚላንና ወንድሙ ወደ እነሱ መኪና ገብተው ድንበሩን እንዲያቋርጡ ነገሯቸው፤ ምክንያቱም ልጆች ድንበሩን ለማቋረጥ የይለፍ ወረቀት ማሳየት አይጠበቅባቸውም ነበር። የሚላንን ወላጆች ደግሞ ከኬላው በስተጀርባ ዞረው ድንበሩን እንዲያቋርጡና እዚያ እንዲጠብቋቸው ነገሯቸው። ሚላን ሐሳቡ በጣም ስላስፈራው ምን እንደሚል ግራ ገባው። ወላጆቹም ቢሆኑ “ወታደሮቹ እንዲህ ስናደርግ ዝም ብለው የሚያዩን ይመስላችኋል?” የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር። ይሁንና ወታደሮቹ የሚላን ወላጆች በአጠገባቸው ሲያልፉ ዓይናቸው የተያዘ ይመስል ጨርሶ ልብ አላሏቸውም ነበር። በመሆኑም የሚላን ወላጆች ድንበሩን አቋርጠው ከልጆቻቸው ጋር መገናኘት ቻሉ። ከዚያም ስብሰባ ወደሚያደርጉበት ከተማ ሄዱ። ሚላንና ቤተሰቡ እርዳታ ለማግኘት ያቀረቡትን ልባዊ ጸሎት ይሖዋ እንደሰማቸው ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ነበሩ። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመጠበቅ ሲል ቀጥተኛ እርምጃ ያልወሰደባቸው ጊዜያት እንዳሉ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አሉ። (ሥራ 7:58-60) ይሁንና ሚላን በወቅቱ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ “ይሖዋ በመላእክቱ አማካኝነት የወታደሮቹን ዓይን በማሳወር እንዳዳነን ሆኖ ይሰማኛል” በማለት ተናግሯል።—መዝ. 97:10

9. ኢየሱስ፣ ይከተሉት የነበሩት ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ሲመለከት ምን አደረገ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

9 ርኅራኄ በማሳየት ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ሕዝቡ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር” እጅግ ራርቶላቸዋል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ያሉበትን አሳዛኝ ሁኔታ ሲመለከት ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ [ነገር] ያስተምራቸው ጀመር” ይላል። (ማቴ. 9:36፤ ማርቆስ 6:34ን አንብብ።) ኢየሱስ ተራውን ሕዝብ የመርዳት አንዳች ፍላጎት ካልነበራቸው ከፈሪሳውያን ፈጽሞ የተለየ አመለካከት ነበረው። (ማቴ. 12:9-14፤ 23:4፤ ዮሐ. 7:49) አንተስ በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎችን የመርዳት ልባዊ ፍላጎት በማሳየት የኢየሱስን ምሳሌ ትከተላለህ?

10, 11. ርኅራኄ ማሳየት ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ አለ? አብራራ።

10 እርግጥ ነው፣ ርኅራኄ ማሳየት ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ አለ። ከላይ ከተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች መመልከት እንደምንችለው አምላክ በእነዚያ ሁኔታዎች ሥር ርኅራኄ ማሳየቱ ተገቢ ነበር። ንጉሥ ሳኦል ያሳየው ርኅራኄ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ሳኦል የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን አለመግደሉ ርኅራኄ ማሳየት እንደሆነ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል፤ የአማሌቃውያንን እንስሳትም ቢሆን አላጠፋም። ይሁንና ይሖዋ አማሌቃውያንንም ሆነ እንስሶቻቸውን አንድም ሳያስቀር እንዲያጠፋ ለሳኦል ነግሮት ነበር። ሳኦል ታዛዥ ባለመሆኑ ንግሥናው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አጥቷል። (1 ሳሙ. 15:3, 9, 15 ግርጌ) ይሖዋ ጻድቅ ፈራጅ ነው። የሰዎችን ልብ በትክክል ማንበብ ስለሚችል ርኅራኄ ማሳየት ተገቢ የማይሆንበትን  ጊዜ ያውቃል። (ሰቆ. 2:17፤ ሕዝ. 5:11) እሱን ለመታዘዝ እምቢተኛ በሆኑ ሁሉ ላይ የፍርድ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ እየቀረበ ነው። (2 ተሰ. 1:6-10) በዚያን ወቅት፣ ክፉ እንደሆኑ ለተፈረደባቸው ሁሉ ምንም ዓይነት ርኅራኄ አያሳይም። እንዲያውም ክፉዎችን ማጥፋቱ ለጻድቃን ማለትም በሕይወት እንዲተርፉ ለሚያደርጋቸው ሰዎች ርኅራኄ እንዳለው የሚያሳይ ይሆናል።

11 እነማን መትረፍ፣ እነማን ደግሞ መጥፋት እንዳለባቸው የመወሰን ሥልጣን እንደሌለን ግልጽ ነው። ሆኖም የፍርድ ቀን ከመምጣቱ በፊት ሰዎችን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ታዲያ ለሰዎች ተገቢ የሆነ ርኅራኄ ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? እስቲ ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።

ተገቢ የሆነ የርኅራኄ ስሜት ማዳበርና ማንጸባረቅ

12. ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ርኅራኄ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

12 በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ ሰዎችን እርዱ። ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ለወንድሞቻቸውም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ርኅራኄ እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል። (ዮሐ. 13:34, 35፤ 1 ጴጥ. 3:8) ርኅራኄ የሚለው ቃል ካሉት ትርጉሞች መካከል አንዱ “አብሮ መሠቃየት” የሚል ነው። አንድ ሰው ርኅራኄ ካለው የሌሎችን ሥቃይ ለማሥታገስ እርምጃ ይወስዳል፤ ምናልባትም ይህን የሚያደርገው ችግራቸውን መወጣት እንዲችሉ በመርዳት ሊሆን ይችላል። ርኅራኄ ማሳየት የምትችሉባቸውን አጋጣሚዎች በንቃት ተከታተሉ! ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ሥራዎችን በማገዝ ምናልባትም የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሄዶ በመግዛት ልትረዱት የምትችሉት ሰው ይኖር ይሆን?—ማቴ. 7:12

ሰዎችን ለመርዳት ጥረት በማድረግ ርኅራኄ አሳይ (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

13. የአምላክ ሕዝቦች የተፈጥሮ አደጋዎች ሲደርሱ የሚሰጡት ምላሽ የትኛው ባሕርይ እንዳላቸው ያሳያል?

13 አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች በሚደረገው የእርዳታ ሥራ ተካፈሉ። ብዙዎች በአደጋ የተጎዱ ሰዎች የሚደርስባቸውን ሥቃይ ሲመለከቱ ርኅራኄ ለማሳየት ይነሳሳሉ። የይሖዋ ሕዝቦች እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ፈጥነው እርዳታ በመስጠት ይታወቃሉ። (1 ጴጥ. 2:17) የአንዲትን ጃፓናዊ እህት ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ይህች እህት የምትኖርበት አካባቢ በ2011 በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥና ሱናሚ ተመቶ ነበር። ከተለያዩ የጃፓን ግዛቶች እንዲሁም ከውጭ አገር የመጡ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች የተፈጥሮ አደጋው ያስከተለውን ጉዳት ለመጠገን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ እህት ይህን መመልከቷ ‘በጣም እንዳበረታታትና እንዳጽናናት’ ተናግራለች። እንዲህ  በማለት ጽፋለች፦ “ይህ ሁኔታ ይሖዋ እንደሚያስብልን እንዳስተውል አድርጎኛል፤ በተጨማሪም የእምነት ባልንጀሮቻችን እርስ በርስ እንደሚተሳሰቡ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች እንደሚጸልዩልን እንድገነዘብ ረድቶኛል።”

14. የታመሙና በዕድሜ የገፉ ሰዎችን መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?

14 የታመሙ ወይም በዕድሜ የገፉ ሰዎችን እርዱ። ሰዎች ከአዳም በወረሱት ኃጢአት ምክንያት የሚደርስባቸውን ሥቃይ ስናይ ለእነሱ ርኅራኄ ለማሳየት እንነሳሳለን። እርጅናና ሕመም የሚወገድበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን። የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጸልየውም ለዚህ ነው። እስከዚያው ድረስ ግን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። እስቲ ይህን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ደራሲ አልዛይመርስ በሽታ የነበረባቸው በዕድሜ የገፉ እናቱ ያጋጠማቸውን ሁኔታ አስመልክቶ ጽፎ ነበር። እኚህ ሴት አንድ ቀን ልብሳቸው ላይ አመለጣቸው። ልብሳቸውን ለማጽዳት እየሞከሩ ሳለ የበሩ ደወል ተደወለ። የመጡት ሰዎች ሴትየዋን አዘውትረው ያነጋግሯቸው የነበሩ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። እነዚህ እህቶች እርዳታ ይፈልጉ እንደሆነ ሴትየዋን ጠየቋቸው። እሳቸውም “የሚያሳፍር ቢሆንም ብትረዱኝ ደስ ይለኛል” በማለት መለሱ። በመሆኑም እህቶች ሴትየዋን ረዷቸው። በኋላም ሻይ ካፈሉላቸው በኋላ ቁጭ ብለው ተጫወቱ። የሴትየዋ ልጅ እነዚህ እህቶች ባደረጉት ነገር ልቡ በጣም ተነካ። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለእነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ጥልቅ አክብሮት አለኝ። የሚሰብኩትን ነገር በሚገባ ይሠሩበታል።” አንተስ ለታመሙና በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ያለህ ርኅራኄ ችግራቸውን ለማቅለል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ እንድታደርግ ይገፋፋሃል?—ፊልጵ. 2:3, 4

15. የስብከቱ ሥራችን ምን አጋጣሚዎችን ይከፍትልናል?

15 ሰዎችን በመንፈሳዊ እርዱ። ሰዎች ያሉባቸውን ችግሮችና የሚያስጨንቋቸውን ነገሮች ስንመለከት እነሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት እንነሳሳለን። ይህን ማድረግ የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ሰዎችን ስለ አምላክና የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች ስለሚያመጣው በረከት ማስተማር ነው። ሌላው መንገድ ደግሞ በአምላክ መሥፈርቶች መመራት ያለውን ጥቅም እንዲገነዘቡ መርዳት ነው። (ኢሳ. 48:17, 18) አንተስ ይሖዋን በሚያስከብረውና ለሌሎች ርኅራኄ እንዳለህ በሚያሳየው የስብከቱ ሥራ ላይ የምታደርገውን ተሳትፎ መጨመር ትችል ይሆን?—1 ጢሞ. 2:3, 4

ርኅራኄ ማሳየታችን ራሳችንንም ይጠቅመናል!

16. ርኅራኄ ማሳየታችን ራሳችንን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

16 የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ርኅራኄ ማሳየት፣ ጤናችን እንዲሻሻልና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እንደሚረዳ ይናገራሉ። የሌሎችን ችግር ለማቅለል ጥረት ማድረጋችን ይበልጥ ደስተኞች እንድንሆንና አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል፤ በተጨማሪም የሚሰማንን የብቸኝነት ስሜት መቀነስ እንድንችል እንዲሁም በአሉታዊ አመለካከት እንዳንዋጥ ያደርጋል። በእርግጥም ርኅራኄ ማሳየታችን ራሳችንን ይጠቅመናል። (ኤፌ. 4:31, 32) በፍቅር ተነሳስተው ሌሎችን ለመርዳት የሚጣጣሩ ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ነገር እያደረጉ እንዳለ ስለሚገነዘቡ ጥሩ ሕሊና ይኖራቸዋል። ርኅራኄ ማሳየታችን ጥሩ ወዳጅ፣ የተሻለ የትዳር ጓደኛ እንዲሁም ይበልጥ አፍቃሪ ወላጅ ለመሆን ይረዳናል። ሩኅሩኅ የሆኑ ሰዎች እርዳታና ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው በአብዛኛው ሌሎች ሰዎች ይደርሱላቸዋል።—ማቴዎስ 5:7ን እና ሉቃስ 6:38ን አንብብ።

17. ሩኅሩኅ ለመሆን ጥረት ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው?

17 ርኅራኄ እንድናሳይ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ራሳችንን እንደሚጠቅመን መገንዘባችን መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ የፍቅርና የርኅራኄ ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ለመምሰልና እሱን ለማስከበር ያለን ፍላጎት መሆን ይኖርበታል። (ምሳሌ 14:31) በዚህ ረገድ ይሖዋ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። እንግዲያው እሱን በመምሰል ርኅራኄ ለማሳየት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ፤ ይህም ከወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ይረዳናል።—ገላ. 6:10፤ 1 ዮሐ. 4:16

^ አን.7 ስሙ ተቀይሯል።