በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  መስከረም 2017

ራስን የመግዛት ባሕርይን አዳብሩ

ራስን የመግዛት ባሕርይን አዳብሩ

“የመንፈስ ፍሬ . . . ራስን መግዛት ነው።”—ገላ. 5:22, 23

መዝሙሮች፦ 121, 36

1, 2. (ሀ) ራስን መግዛት አለመቻል ምን መዘዝ ያስከትላል? (ለ) በአሁኑ ወቅት፣ ራስን ስለ መግዛት ማጥናታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ራስን መግዛት አምላካዊ ባሕርይ ነው። (ገላ. 5:22, 23) ይሖዋ ፍጹም በሆነ መንገድ ራሱን የመግዛት ችሎታ አለው። የሰው ልጆች ግን ፍጹማን ስላልሆኑ ራሳቸውን መግዛት ተፈታታኝ ይሆንባቸዋል። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ በሰዎች ላይ የሚደርሱት አብዛኞቹ ችግሮች የሚመነጩት ራስን ካለመግዛት ነው። አንዳንዶች ራሳቸውን መግዛት ስለሚያቅታቸው ከትምህርት ወይም ከሥራ ጋር በተያያዘ ዛሬ ነገ የማለት ልማድ የሚታይባቸው ከመሆኑም ሌላ የሚጠበቅባቸውን ነገር በትጋት ለማከናወን ይቸገራሉ። በተጨማሪም ራሳቸውን የማይገዙ ሰዎች ተሳዳቢዎች፣ ሰካራሞችና ዓመፀኞች ሊሆኑ፣ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ሊዘፈቁ እንዲሁም ለፍቺ፣ ለሱስ፣ ለእስር፣ ለስሜት ቀውስ፣ በፆታ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎችና ላልተፈለገ እርግዝና ሊዳረጉ ይችላሉ፤ እነዚህ ችግሮች ራስን አለመግዛት ከሚያስከትላቸው መዘዞች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።—መዝ. 34:11-14

2 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ራሳቸውን መግዛት የሚያቅታቸው ሰዎች በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት ያስከትላሉ። የሚያሳዝነው ራስን የመግዛት ችግር ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ነው። ራስን መግዛትን አስመልክቶ በ1940ዎቹ የተደረጉ ጥናቶችን በቅርቡ ከተደረጉ ጥናቶች ጋር በማነጻጸር የተገኘው ውጤት ሰዎች ይበልጥ ራሳቸውን የማይገዙ እንደሆኑ ያሳያል። የአምላክ ቃል ተማሪዎች እንደመሆናችን መጠን ይህ መሆኑ አያስገርመንም፤ ምክንያቱም “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ እንደምንኖር ከሚያሳዩት ምልክቶች መካከል አንዱ ሰዎች “ራሳቸውን የማይገዙ” መሆናቸው እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—2 ጢሞ. 3:1-3

3. ክርስቲያኖች ራስን የመግዛት ባሕርይን ማዳበር ያለባቸው ለምንድን ነው?

3 ራስን የመግዛት ባሕርይን ማዳበርህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሁለት  ዋና ዋና ምክንያቶችን እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ስሜታቸውን መቆጣጠር የሚችሉ ሰዎች በጥቅሉ ሲታይ ለከፍተኛ ችግር የሚዳረጉበት አጋጣሚ ዝቅተኛ እንደሆነ ተስተውሏል። ራሳቸውን የሚገዙ ሰዎች ይበልጥ የተረጋጉ ናቸው፤ ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ይችላሉ እንዲሁም ስሜታቸውን ከማይቆጣጠሩ ሰዎች አንጻር ሲታይ ለጭንቀት፣ ለብስጭትና ለመንፈስ ጭንቀት የሚዳረጉበት አጋጣሚ አነስተኛ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ፈታኝ ሁኔታዎችን የመቋቋም እንዲሁም ተገቢ ያልሆኑ ስሜቶችን የመቆጣጠር ችሎታ ማዳበራችን የአምላክን ሞገስ ላለማጣት ወሳኝ ነገር ነው። አዳምና ሔዋን ያጋጠማቸው አሳዛኝ ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። (ዘፍ. 3:6) ከአዳምና ከሔዋን በኋላ የኖሩ በርካታ ሰዎችም ራሳቸውን መግዛት ባለመቻላቸው ያጋጠማቸውን አሳዛኝ ሁኔታ ማሰብ እንችላለን።

4. ራሳቸውን ለመግዛት የሚቸገሩ ሰዎች የትኛውን ነጥብ ማወቃቸው ሊያበረታታቸው ይችላል?

4 ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ራስን የመግዛት ባሕርይን ፍጹም በሆነ መንገድ ሊያንጸባርቁ አይችሉም። ይሖዋ አገልጋዮቹ በዚህ ረገድ የሚያደርጉትን ትግል ያውቃል፤ እንዲሁም የኃጢአት ዝንባሌያቸውን መቆጣጠር እንዲችሉ ሊረዳቸው ይፈልጋል። (1 ነገ. 8:46-50) ይሖዋ እሱን የማገልገል ልባዊ ፍላጎት ያላቸውን ሆኖም በአንዳንድ የሕይወታቸው ዘርፎች ራሳቸውን ለመግዛት የሚቸገሩ ግለሰቦችን ልክ እንደ አፍቃሪ ወዳጅ በመሆን ያበረታታቸዋል። በዚህ ርዕስ ሥር ይሖዋ ራስን በመግዛት ረገድ የተወልንን ፍጹም ምሳሌ እንመለከታለን። ከዚያም ራስን የመግዛት ባሕርይን በማሳየት ረገድ ጥሩና መጥፎ ምሳሌ የሚሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችን ታሪክ እንመረምራለን። በተጨማሪም ራስን የመግዛት ችሎታችንን ይበልጥ ለማሻሻል የሚረዱ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንመለከታለን።

ይሖዋ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል

5, 6. ይሖዋ ራስን በመግዛት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?

5 ይሖዋ ራስን የመግዛት ባሕርይን ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃል፤ ምክንያቱም እሱ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ፍጹም ነው። (ዘዳ. 32:4) እኛ ግን ፍጹማን አይደለንም። ያም ቢሆን ይሖዋ የተወውን ምሳሌ መመርመራችን ራስን መግዛት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል፤ ይህም እሱ የተወልንን ምሳሌ በተሻለ መንገድ ለመከተል ይረዳናል። ለመሆኑ ይሖዋ ራሱን እንደሚገዛ ያሳየባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

6 ይሖዋ፣ ሰይጣን ዓመፅ ባስነሳበት ወቅት ራስን የመግዛት ባሕርይን ያንጸባረቀው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ሰይጣን ያስነሳው ዓመፅ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባ ነበር። ዲያብሎስ በይሖዋ ላይ ያቀረበው ውንጀላ ታማኝ የሆኑትን መንፈሳዊ ፍጥረታት አበሳጭቷቸው፣ አስቆጥቷቸውና አስከፍቷቸው ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። አንተም በሰይጣን ዓመፅ ምክንያት እየደረሱብን ያሉትን ችግሮች ስትመለከት እንደዚያ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና ይሖዋ የችኮላ እርምጃ አልወሰደም። የወሰደው እርምጃ በሚገባ የታሰበበትና ተስማሚ ነበር። ይሖዋ ጉዳዩን የያዘበት መንገድ ለቁጣ የዘገየና ፍትሐዊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። (ዘፀ. 34:6፤ ኢዮብ 2:2-6) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ የፈቀደው “ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው”፤ ከዚህ ይልቅ ሁሉም ሰዎች ‘ለንስሐ እንዲበቁ ይፈልጋል።’—2 ጴጥ. 3:9

7. ይሖዋ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 ይሖዋ ራስን በመግዛት ረገድ የተወውን ምሳሌ መመርመራችን እኛም ከመናገራችንና እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ እንዳለብን ያስገነዝበናል፤ የችኮላ እርምጃ መውሰድ የለብንም። ከበድ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ መውሰድ እንድትችል ጊዜ ወስደህ በጉዳዩ ላይ አስብበት። ትክክል የሆነውን ነገር ለመናገር ወይም ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (መዝ. 141:3) ተቆጥተህ ባለህበት ሰዓት፣ ስሜታዊ እርምጃ መውሰድ ይቀናህ ይሆናል። ሆኖም አብዛኞቻችን ተቆጥተን ሳለን በተናገርነው ወይም ባደረግነው ነገር ተጸጽተን እንደምናውቅ ጥርጥር የለውም!—ምሳሌ 14:29፤ 15:28፤ 19:2

ጥሩና መጥፎ ምሳሌ የሚሆኑ የአምላክ አገልጋዮች

8. (ሀ) አምላካዊ ባሕርያትን በማንጸባረቅ ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎችን ከየት ማግኘት እንችላለን? (ለ) ዮሴፍ በጶጢፋር ሚስት ማባበያ ያልተሸነፈው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

8 ስሜታችንን መቆጣጠራችን አስፈላጊ እንደሆነ የሚያጎሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው? ፈታኝ ሁኔታ ባጋጠማቸው ወቅት ራሳቸውን  የተቆጣጠሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል። ከእነዚህ መካከል አንዱ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ነው። ዮሴፍ የፈርዖን ዘቦች አለቃ በሆነው በጶጢፋር ቤት ውስጥ ያገለግል በነበረበት ወቅት ራሱን እንደሚገዛ አሳይቷል። የጶጢፋር ሚስት ‘የዳበረ ሰውነትና ያማረ መልክ’ በነበረው በዮሴፍ ላይ ዓይኗን ጣለችበት፤ እንዲሁም ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽም ታባብለው ጀመር። ዮሴፍ የጶጢፋር ሚስት ባቀረበችለት ተደጋጋሚ ማባበያ እንዳይሸነፍ የረዳው ምንድን ነው? አቋሙን ማላላቱ ምን መዘዝ እንደሚያስከትል ጊዜ ወስዶ እንዳሰላሰለ ጥርጥር የለውም። አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ጊዜ ደግሞ አካባቢውን ጥሎ ሸሽቷል። ዮሴፍ “እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?” በማለት ተናግሯል።—ዘፍ. 39:6, 9፤ ምሳሌ 1:10ን አንብብ።

9. ፈተናዎችን ለመቋቋም ራስህን ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

9 ዮሴፍ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን? የአምላክን ሕጎች እንድንጥስ ሊያደርጉን ከሚችሉ ፈተናዎች ለማምለጥ መሸሽ ሊያስፈልገን ይችላል። አሁን የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ከዚህ በፊት ከልክ በላይ የመብላትና የመጠጣት፣ የማጨስ፣ ዕፅ የመውሰድ፣ የፆታ ብልግና የመፈጸምና የመሳሰሉት ችግሮች ነበሩባቸው። ከተጠመቁ በኋላም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ወደ ቀድሞ ልማዶቻቸው ለመመለስ ሊፈተኑ ይችላሉ። የኃጢአት ዝንባሌዎችን አለመቆጣጠርህ በመንፈሳዊነትህ ላይ ምን አደጋ እንደሚያስከትል ጊዜ ወስደህ ማሰላሰልህ የይሖዋን ሕግ ለመጣስ በምትፈተንበት ወቅት አቋምህን ለማጠናከር ይረዳሃል። ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ እንደሚችሉና እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች መከላከል የምትችለው እንዴት እንደሆነ አስቀድመህ ለማሰብ ሞክር። (መዝ. 26:4, 5፤ ምሳሌ 22:3) እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ካጋጠሙህ ደግሞ ይሖዋ ፈተናዎቹን ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህና ራስህን መቆጣጠር እንድትችል እንዲረዳህ ጸልይ።

10, 11. (ሀ) በርካታ ወጣቶች በትምህርት ቤት ምን ዓይነት ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? (ለ) ወጣት ክርስቲያኖች መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚደረግባቸውን ጫና ለመቋቋም ምን ይረዳቸዋል?

10 በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ወጣት ክርስቲያኖች ዮሴፍ የደረሰበት ዓይነት ፈተና ይደርስባቸዋል። ኪም ያጋጠማትን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። አብረዋት ከሚማሩት ልጆች መካከል አብዛኞቹ የፆታ ግንኙነት ይፈጽሙ ነበር፤ ከሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በኋላ ሲገናኙ አብዛኛውን ጊዜ የሚያወሩት እንዲህ በማድረግ ስላሳለፉት ጊዜ ነው። ኪም ግን በዚህ ረገድ ልትናገረው የምትችለው ምንም ነገር የለም። ከሌሎች የተለየች በመሆኗ አንዳንድ ጊዜ ‘እንደተተወችና ብቸኛ እንደሆነች’ እንደሚሰማት በሐቀኝነት ተናግራለች፤ በተጨማሪም የወንድ ጓደኛ ባለመያዟ እኩዮቿ እንደ ሞኝ እንደሚመለከቷት ገልጻለች። ይሁንና ኪም ወጣቶች የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ የሚደርስባቸው ፈተና ከባድ እንደሆነ ተገንዝባ ነበር። (2 ጢሞ. 2:22) አብረዋት የሚማሩት ልጆች በተደጋጋሚ ‘አሁንም ድንግል ነሽ?’ እያሉ ይጠይቋታል። ይህም የፆታ ግንኙነት የማትፈጽምበትን ምክንያት የምታስረዳበት አጋጣሚ እንድታገኝ አስችሏታል። የፆታ ብልግና እንዲፈጽሙ የሚደረግባቸውን ግፊት ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ ያደረጉ ወጣቶቻችንን በጣም እንኮራባቸዋለን፤ ይሖዋም ቢሆን እንደሚኮራባቸው ምንም ጥርጥር የለውም!

11 መጽሐፍ ቅዱስ ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ራሳቸውን መግዛት ስላቃታቸው ሰዎች የሚናገሩ የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎችን ይዟል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው የደረሰባቸውን አስከፊ መዘዝም ይናገራል። እንደ ኪም ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ የሚያጋጥመው ማንኛውም ሰው በምሳሌ ምዕራፍ 7 ላይ የተጠቀሰው ሞኝ ወጣት ስላጋጠመው ችግር ማሰላሰሉ ይጠቅመዋል። አምኖን የፈጸመው ድርጊት ባስከተለው አሳዛኝ ውጤትም ላይ ማሰላሰል እንችላለን። (2 ሳሙ. 13:1, 2, 10-15, 28-32) ወላጆች ከላይ የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ላይ በመወያየት ልጆቻቸው ከፍቅር ግንኙነት ጋር በተያያዘ ራሳቸውን የመግዛት ባሕርይ እንዲያዳብሩና ጥበበኛ እንዲሆኑ መርዳት ይችላሉ።

12. (ሀ) ዮሴፍ ከወንድሞቹ ጋር በተያያዘ ስሜቱን የተቆጣጠረው እንዴት ነው? (ለ) ስሜታችንን መቆጣጠር የሚያስፈልገን በየትኞቹ ሁኔታዎች ሥር ነው?

12 ዮሴፍ በሌላ አጋጣሚም ራስን በመቆጣጠር ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ወንድሞቹ እህል ለመግዛት ወደ ግብፅ በመጡ ጊዜ ዮሴፍ በልባቸው ውስጥ ያለውን ነገር ለማወቅ ሲል ማንነቱን ደብቋቸው ነበር። ስሜቱን መቆጣጠር ሲከብደው ግን በወንድሞቹ ፊት ማልቀስ ስላልፈለገ ብቻውን ወደ ሌላ ክፍል ገባ።  (ዘፍ. 43:30, 31፤ 45:1) የእምነት ባልንጀራችን ወይም አንድ የምንወደው ሰው የሚያበሳጨን ነገር በሚያደርግበት ጊዜ ልክ እንደ ዮሴፍ ራሳችንን መቆጣጠራችን ስሜታዊ ሆነን እርምጃ እንዳንወስድ ይረዳናል። (ምሳሌ 16:32፤ 17:27) ከክርስቲያን ጉባኤ የተወገዱ ዘመዶች ካሉህ ከእነሱ ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ ላለመፍጠር ራስህን መግዛት ሊያስፈልግህ ይችላል። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር ራሳችንን መግዛት ቀላል አይደለም፤ ይሁንና ራሳችንን መግዛታችን የአምላክን ምሳሌ ለመከተልና እሱ የሰጠንን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችለን መገንዘባችን በዚህ ረገድ ሊረዳን ይችላል።

13. ስለ ንጉሥ ዳዊት ከሚናገሩት ዘገባዎች ምን ትምህርት እናገኛለን?

13 ስለ ንጉሥ ዳዊት ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችም ግሩም ትምህርት እናገኛለን። ዳዊት ኃያል ሰው የነበረ ቢሆንም ሳኦልና ሺምአይ የሚያበሳጭ ነገር ባደረጉበት ጊዜ በቁጣ ተነሳስቶ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቧል። (1 ሳሙ. 26:9-11፤ 2 ሳሙ. 16:5-10) ይህ ሲባል ግን ዳዊት ሁልጊዜ ራሱን የሚቆጣጠር ሰው ነበር ማለት አይደለም፤ ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመው ኃጢአት እንዲሁም ናባል ያደረገውን ሲሰማ የሰጠው ምላሽ ዳዊት ራሱን መቆጣጠር የተሳነው ጊዜ እንደነበር ይጠቁማሉ። (1 ሳሙ. 25:10-13፤ 2 ሳሙ. 11:2-4) ያም ቢሆን ከዳዊት ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚገኙ የበላይ ተመልካቾች ሥልጣናቸውን አላግባብ እንዳይጠቀሙበት ራሳቸውን መግዛታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ማንም ሰው በዚህ ረገድ ችግር ሊያጋጥመኝ አይችልም ብሎ በማሰብ መዘናጋት አይኖርበትም።—1 ቆሮ. 10:12

ልንወስድ የምንችላቸው ጠቃሚ እርምጃዎች

14. አንድ ወንድም ምን ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን የምንሰጠው ምላሽ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?

14 ራስን የመግዛት ባሕርይን ለማዳበር ምን ማድረግ እንችላለን? እስቲ አንድ ወንድም ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። አንድ አሽከርካሪ ሉዊጂ የተባለን ወንድም መኪና ከኋላ ይገጨዋል። ሰውየው ጥፋተኛ የነበረ ቢሆንም ሉዊጂን ሰደበው፤ ይባስ ብሎም ከእሱ ጋር ጠብ ለመፍጠር ሞከረ። ሉዊጂ መረጋጋት እንዲችል ወደ ይሖዋ ጸለየ፤ ከዚያም ሰውየውን ለማረጋጋት ጥረት አደረገ። ሰውየው ግን ሊረጋጋ አልቻለም። በመሆኑም ሉዊጂ የኢንሹራንስ ጉዳዮችን ለማስፈጸም እንዲረዳው ሲል የሰሌዳ ቁጥሩን ከያዘ በኋላ ቦታውን ለቆ ሄደ፤ ሉዊጂ ሲሄድ ሰውየው መጮኹን አላቆመም ነበር። ከአንድ ሳምንት በኋላ ሉዊጂ ለአንዲት ሴት ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርግ የሴትየዋ ባለቤት መኪናውን የገጨበት ግለሰብ መሆኑን ተገነዘበ! ሰውየው ባሳየው ምግባር በጣም ያፈረ ሲሆን ሉዊጂን ይቅርታ ጠየቀው። እንዲያውም ጉዳዩን እንዲያፋጥኑለት ለማድረግ ሲል የሉዊጂን የኢንሹራንስ ኩባንያ ማነጋገር እንደሚፈልግ ገለጸ። ሰውየው በመንፈሳዊ ውይይታቸው ላይ የተካፈለ ሲሆን በውይይቱም በጣም ተደሰተ። ሉዊጂ የተፈጠረውን ሁኔታ መለስ ብሎ ሲያስብ አደጋው በተፈጠረበት ወቅት መረጋጋቱ ምን ያህል ጠቃሚ እንደነበርና በቁጣ ገንፍሎ እርምጃ ቢወስድ ኖሮ ውጤቱ በጣም አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ተገንዝቧል።2 ቆሮንቶስ 6:3, 4ን አንብብ።

ቁጣችንን መቆጣጠራችን ወይም አለመቆጣጠራችን በአገልግሎታችን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ያሳድራል (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

15, 16. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችሁ እናንተም ሆናችሁ ቤተሰባችሁ ራስን የመግዛትን ባሕርይን እንድታዳብሩ የሚረዳችሁ እንዴት ነው?

15 ክርስቲያኖች በትጋትና ትርጉም ባለው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው ራስን የመግዛት ባሕርይን ለማዳበር ይረዳቸዋል። አምላክ ለኢያሱ እንደሚከተለው ብሎ እንደነገረው እናስታውስ፦ “ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውንም በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችል ቀንም ሆነ ሌሊት በለሆሳስ አንብበው፤ እንዲህ ካደረግክ መንገድህ ይቃናልሃል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።” (ኢያሱ 1:8) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ራስን የመግዛት ባሕርይን ለማዳበር የሚረዳን እንዴት ነው?

16 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ የምንወስደው እርምጃ የሚያስገኘውን ጥቅምም ሆነ የሚያስከትለውን ጉዳት በግልጽ የሚያሳዩ ዘገባዎችን ይዟል። ይሖዋ እነዚህ ታሪኮች ተመዝግበው እንዲቆዩ ያደረገው በዓላማ ነው። (ሮም 15:4) እነዚህን ታሪኮች ማንበባችን፣ ማጥናታችንና በእነሱ ላይ ማሰላሰላችን በእርግጥም ጥበብ ነው! እነዚህን ዘገባዎች በግል ሕይወታችሁም ሆነ በቤተሰባችሁ ውስጥ ተግባራዊ ልታደርጓቸው የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። ይሖዋ በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ  ለማድረግ እንዲረዳችሁ ጸልዩ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ራሳችሁን መግዛት እንደሚከብዳችሁ ካስተዋላችሁ ይህን አምናችሁ ተቀበሉ። ከዚያም ጉዳዩን አስመልክታችሁ ጸልዩ፤ እንዲሁም ማሻሻያ ማድረግ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት አድርጉ። (ያዕ. 1:5) በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ላይ ምርምር ማድረጋችሁ ራስን የመግዛት ባሕርይን ለማዳበር ሊረዷችሁ የሚችሉ ተጨማሪ ነጥቦችን ለማግኘት እንደሚያስችላችሁ ምንም ጥርጥር የለውም።

17. ወላጆች ልጆቻቸው ራስን የመግዛት ባሕርይን እንዲያዳብሩ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

17 እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ራስን የመግዛት ባሕርይን እንዲያዳብሩ መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? ልጆች እንዲሁ በተፈጥሯቸው ራሳቸውን የሚገዙ እንደማይሆኑ መገንዘብ ይኖርባችኋል። በተጨማሪም ልክ እንደ ሌሎች ባሕርያት ሁሉ ልጆቻችሁ ራስን የመግዛት ባሕርይን እንዲያዳብሩ ከፈለጋችሁ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባችኋል። (ኤፌ. 6:4) በመሆኑም ልጆቻችሁ ስሜታቸውን መቆጣጠር እንደሚከብዳቸው ካስተዋላችሁ ‘በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሆኛቸዋለሁ?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። በመስክ አገልግሎትና በጉባኤ ስብሰባዎች አዘውትራችሁ መካፈላችሁ እንዲሁም ቋሚ የቤተሰብ አምልኮ ማድረጋችሁ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልላችሁ አትመልከቱ። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ልጆቻችሁ ለሚያቀርቡት ጥያቄ ‘አይሆንም’ ብላችሁ ከመመለስ ወደኋላ አትበሉ! ይሖዋ በአዳምና በሔዋን ላይ ገደብ አድርጎባቸው ነበር፤ ይህ ገደብ፣ ለእሱ ሥልጣን ተገቢ አክብሮት እንዲኖራቸው የሚረዳ ነበር። በተመሳሳይም ወላጆች ልጆቻቸውን መገሠጻቸውና ለእነሱ ጥሩ ምሳሌ መሆናቸው ልጆቻቸው ራሳቸውን መቆጣጠር እንዲችሉ ያሠለጥናቸዋል። ልጆቻችሁ ለይሖዋ ሥልጣን ፍቅር እንዲኖራቸውና እሱ ላወጣቸው መሥፈርቶች አክብሮት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ጥረት አድርጉ፤ እነዚህ እሴቶች በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ልትቀርጹ ከምትችሏቸው እጅግ ውድ የሆኑ ነገሮች መካከል ይገኙበታል።—ምሳሌ 1:5, 7, 8ን አንብብ።

18. ጓደኞቻችንን በጥበብ መምረጣችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

18 ወላጆች ሆናችሁም አልሆናችሁ ጥሩ ጓደኛ የመምረጥን አስፈላጊነት አቅልላችሁ መመልከት የለባችሁም። በመሆኑም ጠቃሚ የሆኑ ግቦችን እንድትከታተሉና ከአደገኛ ሁኔታዎች እንድትርቁ የሚረዷችሁን ወዳጆች አፍሩ። (ምሳሌ 13:20) መንፈሳዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር መቀራረባችሁ ራስን በመግዛት ረገድ የተዉትን ምሳሌ እንድትከተሉ ስለሚያነሳሳችሁ በጎ ተጽዕኖ ያሳድርባችኋል። ጓደኞቻችሁም በእናንተ መልካም ምግባር እንደሚበረታቱ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ በማድረግ ራስን የመግዛት ባሕርይን ማዳበራችሁ ምንጊዜም የአምላክን ሞገስ ሳታጡ እንድትኖሩና ከምትወዷቸው ሰዎች ጋር አብራችሁ መልካም ነገሮችን በማከናወን እንድትደሰቱ ይረዳችኋል።