በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሐምሌ 2017

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን፣ ሌሎች ከሚያደርሱበት ጥቃት ራሱን ለመከላከል ሲል እንደ ሽጉጥ ወይም ጠመንጃ ያለ የጦር መሣሪያ መያዙ ተገቢ ነው?

ክርስቲያኖች የራሳቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ሲሉ ተገቢ የሆኑ እርምጃዎችን መውሰድ ቢችሉም ይህን የሚያደርጉት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በማይጋጭ መልኩ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ራስን ከሌሎች ሰዎች ጥቃት ለመከላከል ሲባል ሽጉጥ፣ ጠመንጃ ወይም ሌሎች መሣሪያዎችን መጠቀም ስህተት መሆኑን ይጠቁማሉ። በዚህ ረገድ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱንን ነጥቦች እስቲ እንመልከት፦

በይሖዋ ዓይን ሕይወት በተለይ ደግሞ የሰው ሕይወት ቅዱስ ነው። መዝሙራዊው ዳዊት፣ ይሖዋ “የሕይወት ምንጭ” እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። (መዝ. 36:9) በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ራሱን ወይም ንብረቱን ከጥቃት ለመከላከል ሲል ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ከመረጠ፣ የሰው ሕይወት ላለማጥፋት አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ ያደርጋል፤ ምክንያቱም የሰው ሕይወት ካጠፋ በደም ዕዳ ተጠያቂ ይሆናል።—ዘዳ. 22:8፤ መዝ. 51:14

አንድ ሰው ራሱን ከጥቃት ለመከላከል የሚጠቀምባቸው የተለያዩ መሣሪያዎች፣ የሰው ሕይወት እንዲያጠፋና በደም ዕዳ ተጠያቂ እንዲሆን ሊያደርጉት እንደሚችሉ የታወቀ ነው፤ በተለይ ሽጉጥ ወይም ጠመንጃ መያዙ ግን በአጋጣሚም ይሁን ሆን ብሎ የሰውን ሕይወት በቀላሉ እንዲያጠፋ ሊያደርገው ይችላል። * በተጨማሪም ጥቃት የሚሰነዝረው ግለሰብ ራሱ፣ ቀድሞውንም ስጋት ላይ ሊሆን ይችላል፤ በመሆኑም ሌላው ግለሰብ የጦር መሣሪያ እንደያዘ ሲያይ ይበልጥ ሊደናገጥና ሁኔታዎቹ ተባብሰው የሰው ሕይወት ሊጠፋ ይችላል።

ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ ተከታዮቹ ሰይፍ እንዲይዙ የነገራቸው ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል እንዲጠቀሙበት አስቦ አይደለም። (ሉቃስ 22:36, 38) ኢየሱስ ሰይፍ  እንዲይዙ የነገራቸው፣ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ቢመጡባቸውም እንኳ ጥቃት መሰንዘር እንደሌለባቸው ሊያስተምራቸው ስለፈለገ ነው። (ሉቃስ 22:52) ጴጥሮስ ሰይፉን በመምዘዝ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮውን በቆረጠው ጊዜ ኢየሱስ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ” በማለት አዞታል። ከዚያም ኢየሱስ “ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” በማለት አንድ ጠቃሚ እውነታ ተናገረ፤ በዛሬው ጊዜ ያሉ ተከታዮቹም በዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ይመራሉ።—ማቴ. 26:51, 52

ከሚክያስ 4:3 ጋር በሚስማማ መልኩ የአምላክ ሕዝቦች “ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ።” ይህም፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው ከሚታወቁባቸው ነገሮች አንዱ ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ከሰጠው ከሚከተለው ምክር ጋር ይስማማል፦ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። . . . ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ።” (ሮም 12:17, 18) ጳውሎስ ‘ዘራፊዎች የሚያደርሱትን አደጋ’ ጨምሮ ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሙትም ከሰጠው ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ ኖራል፤ የራሱን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ፈጽሞ አልጣሰም። (2 ቆሮ. 11:26) በአምላክና በቃሉ ውስጥ በሰፈረው ጥበብ ያዘለ ምክር ተማምኗል፤ ደግሞ ይህ ጥበብ “ከጦር መሣሪያ ይልቅ” የተሻለ ነው።—መክ. 9:18

ክርስቲያኖች፣ ሕይወት ከማንኛውም ቁሳዊ ነገር የበለጠ ዋጋ እንዳለው ይገነዘባሉ። “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም።” (ሉቃስ 12:15) በመሆኑም ጥበበኛ የሆኑ ክርስቲያኖች፣ የጦር መሣሪያ የታጠቀን ዘራፊ በገርነት በማነጋገር መፍትሔ ማግኘት ካልቻሉ ኢየሱስ የተናገረውን “ክፉን ሰው አትቃወሙት” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ያደርጋሉ። ሌላው ቀርቶ እጀ ጠባባችንን እና መደረቢያችንን፣ በሌላ አባባል የፈለገውን ነገር ሁሉ መስጠት ሊኖርብን ይችላል። (ማቴ. 5:39, 40፤ ሉቃስ 6:29) * እርግጥ ነው፣ ከሁሉ የተሻለው መፍትሔ የጥቃት ሰለባ ላለመሆን መጠንቀቅ ነው። “ኑሮዬ ይታይልኝ” የሚል መንፈስ ከማንጸባረቅ የምንቆጠብና በጎረቤቶቻችን ዘንድ ሰላም ወዳድ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን የምንታወቅ ከሆነ የወንጀለኞችን ትኩረት ላንስብ እንችላለን።—1 ዮሐ. 2:16፤ ምሳሌ 18:10

ክርስቲያኖች ለሌሎች ሕሊና ይጠነቀቃሉ። (ሮም 14:21) አንድ የጉባኤው አባል ራሱን ከሌሎች ሰዎች ጥቃት ለመከላከል ሲል ሽጉጥ ወይም ጠመንጃ እንዳስቀመጠ የእምነት ባልንጀሮቹ ቢያውቁ፣ አንዳንዶቹ ነገሩ በጣም ሊያስደነግጣቸው አልፎ ተርፎም ሊያሰናክላቸው ይችላል። ለሌሎች ያለን ፍቅር የእነሱን ፍላጎት ከራሳችን ጥቅም እንድናስቀድም ያነሳሳናል፤ ይህም ሕጋዊ መብታችን እንደሆነ የሚሰማንን ነገር መሥዋዕት ማድረግን ይጨምራል።—1 ቆሮ. 10:32, 33፤ 13:4, 5

ክርስቲያኖች ለሌሎች ምሳሌ ለመሆን ጥረት ያደርጋሉ። (2 ቆሮ. 4:2፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) ራሱን ከሌሎች ሰዎች ጥቃት ለመከላከል ሲል ሽጉጥ ወይም ጠመንጃ ያስቀመጠ አንድ ክርስቲያን፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ከተሰጠውም በኋላ ለውጥ ማድረግ ካልፈለገ ምሳሌ እንደሚሆን ተደርጎ ሊታይ አይችልም። በመሆኑም በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነቶችን ወይም ልዩ መብቶችን ለመሸከም ብቁ አይሆንም። በሥራው ምክንያት የጦር መሣሪያ ከሚይዝ ክርስቲያን ጋር በተያያዘም ይኸው ሐሳብ ይሠራል። እንዲህ ያለው ክርስቲያን ሌላ ሥራ መፈለጉ ምንኛ የተሻለ ነው! *

አንድ ክርስቲያን ራሱን፣ ቤተሰቡን ወይም ንብረቱን ከጥቃት እንዴት መከላከል እንዳለበት የሚያደርገው ውሳኔ በአብዛኛው ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተወ ነው፤ ከሥራ ምርጫ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የአምላክን ጥበብ እና ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። በመንፈሳዊ የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ ለእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አክብሮት ስላላቸው ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች ጥቃት ለመከላከል ሲሉ ሽጉጥ ወይም ጠመንጃ ላለመያዝ ይወስናሉ። ክርስቲያኖች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመመራት በአምላክ እንደሚታመኑ የሚያሳዩ ከሆነ፣ እውነተኛና ዘላቂ ደህንነት እንደሚያገኙ ያውቃሉ።—መዝ. 97:10፤ ምሳሌ 1:33፤ 2:6, 7

በታላቁ መከራ ወቅት ክርስቲያኖች በይሖዋ ስለሚተማመኑ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል እርምጃ አይወስዱም

^ አን.3 አንድ ክርስቲያን፣ ለምግብነት የሚጠቀምባቸውን እንስሳት ለማደን ወይም ራሱን ከዱር አራዊት ጥቃት ለመከላከል ሲል እንደ ጠመንጃ ወይም ሽጉጥ ያለ የጦር መሣሪያ እንዲኖረው ሊወስን ይችላል። ይሁን እንጂ መሣሪያውን በማይጠቀምበት ጊዜ፣ ጥይቶቹን ካወጣና ምናልባትም መሣሪያውን ከፈታታው በኋላ ቢቆልፍበት የተሻለ ይሆናል። መሣሪያ መያዝ ሕጋዊ ባልሆነበት፣ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንዲይዙ በሚፈቀድበት ወይም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላ ዓይነት እገዳ ባለበት አገር ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሕጉን ይታዘዛሉ።—ሮም 13:1

^ አን.2 ተገዶ መደፈርን መከላከል የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ በሚያዝያ 1994 ንቁ! ላይ የወጣውን “ተገዶ መደፈርን መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.4 የጦር መሣሪያ መያዝ በሚጠይቅ ሥራ ላይ መሰማራትን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኅዳር 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31⁠ን እና የሐምሌ 15, 1983 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 25-26⁠ን ተመልከት።