በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

“ያህን አወድሱ!”—ለምን?

“ያህን አወድሱ!”—ለምን?

“ያህን አወድሱ! . . . እሱን ማወደስ ደስ ያሰኛል፤ ደግሞም ተገቢ ነው።”—መዝ. 147:1

መዝሙሮች፦ 59, 3

1-3. (ሀ) መዝሙር 147 የተጻፈው መቼ ሊሆን ይችላል? (ለ) መዝሙር 147⁠ን በመመርመር ምን ማወቅ እንችላለን?

አንድ ሰው የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጣ አሊያም ደግሞ ግሩም ክርስቲያናዊ ባሕርይ ሲያንጸባርቅ ልናመሰግነው እንደሚገባ ግልጽ ነው። ከሰዎች ጋር በተያያዘ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ አምላክንማ እንድናወድስ የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች እንዳሉን ጥርጥር የለውም! ይሖዋን ድንቅ በሆነው የፍጥረት ሥራው ላይ ስለተንጸባረቀው ታላቅ ኃይሉ አሊያም ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ለሰው ልጆች በመስጠት ስላሳየው ፍቅሩ ልናወድሰው እንችላለን።

2 የመዝሙር 147 ጸሐፊ ይሖዋን ለማወደስ ተነሳስቷል። በተጨማሪም ሌሎችም አብረውት አምላክን እንዲያወድሱ አበረታትቷል።—መዝሙር 147:1, 7, 12ን አንብብ።

3 ይህን መዝሙር ማን እንደጻፈው አናውቅም፤ የመዝሙሩ ጸሐፊ የኖረው፣ እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ ይሖዋ በረዳቸው ጊዜ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። (መዝ. 147:2) የአምላክ ሕዝብ እውነተኛውን አምልኮ ወደሚያከናውኑበት ቦታ መመለሳቸው መዝሙራዊው፣ ይሖዋን እንዲያወድስ አነሳስቶት መሆን አለበት። ይህ መዝሙራዊ፣ ይሖዋን ለማመስገን የሚያነሳሱ ሌሎች ምክንያቶችንም ጠቅሷል። እነዚህ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? አንተስ “ሃሌሉያህ!” ብለህ ከፍ ባለ ድምፅ ይሖዋን እንድታወድስ የሚያነሳሱህ በሕይወትህ ውስጥ የተፈጸሙ ምን ነገሮች አሉ?—መዝ. 147:1 ግርጌ

 ይሖዋ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል

4. ምርኮኛ የሆኑት እስራኤላውያን፣ ንጉሥ ቂሮስ ነፃ ባወጣቸው ወቅት ምን ተሰምቷቸው መሆን አለበት? ለምንስ?

4 በግዞት የተወሰዱት እስራኤላውያን በባቢሎን ሲኖሩ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል እስቲ አስበው። የማረኳቸው ሰዎች “ከጽዮን መዝሙሮች አንዱን ዘምሩልን” በማለት ያፌዙባቸው ነበር። እስራኤላውያን በይሖዋ ለመደሰት ምክንያት ከሚሆኗቸው ነገሮች መካከል ትልቁን ቦታ የምትይዘው ኢየሩሳሌም በወቅቱ ባድማ ሆናለች። (መዝ. 137:1-3, 6) በመሆኑም አይሁዳውያኑ በዚያ ወቅት መዘመር አላሰኛቸውም። ልባቸው ስለተሰበረ የሚያስፈልጋቸው የሚያጽናናቸው ነገር ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ በትንቢት ባስነገረው መሠረት የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ ታደጋቸው። ቂሮስ፣ ባቢሎንን ድል ያደረገ ሲሆን እንዲህ ሲል አወጀ፦ “ይሖዋ . . . [በኢየሩሳሌም] ቤት እንድሠራለት አዞኛል። ከእሱ ሕዝብ መካከል የሆነ አብሯችሁ የሚኖር ማንኛውም ሰው አምላኩ ይሖዋ ከእሱ ጋር ይሁን፤ እሱም ወደዚያ ይውጣ።” (2 ዜና 36:23) ይህ ሁኔታ በባቢሎን ይኖሩ ለነበሩት እስራኤላውያን ምን ያህል የሚያጽናና እንደነበር መገመት ይቻላል!

5. መዝሙራዊው የይሖዋን የመፈወስ ኃይል በተመለከተ ምን ብሏል?

5 ይሖዋ እስራኤላውያንን ያጽናናቸው በብሔር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም ጭምር ነው። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መዝሙራዊው ስለ አምላክ ሲናገር “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል፤ ቁስላቸውን ይፈውሳል” ብሏል። (መዝ. 147:3) በእርግጥም ይሖዋ፣ አካላዊ ችግር ላጋጠማቸውም ሆነ ስሜታቸው ለተደቆሰ ሰዎች ያስባል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ፣ እኛን ለማጽናናትና የተደቆሰውን ስሜታችንን ለመፈወስ ዝግጁ ነው። (መዝ. 34:18፤ ኢሳ. 57:15) የሚያጋጥመንን ማንኛውንም መከራ ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብና ጥንካሬም ይሰጠናል።—ያዕ. 1:5

6. መዝሙራዊው በመዝሙር 147:4 ላይ የተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት ይዞልናል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

6 መዝሙራዊው ቀጥሎ ደግሞ ትኩረቱን በሰማይ ባሉት ነገሮች ላይ ያደረገ ሲሆን ይሖዋ “የከዋክብትን ብዛት ይቆጥራል፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል” በማለት ጽፏል። (መዝ. 147:4) መዝሙራዊው በሰማይ ስላሉት ፍጥረታት ስለጠቀሰ የትኩረት አቅጣጫውን እንደቀየረ ይሰማን ይሆናል፤ ይሁንና መዝሙራዊው ስለ ሰማያዊ አካላት የተናገረው ለምንድን ነው? እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ መዝሙራዊው ከዋክብትን ማየት ቢችልም ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ማወቅ የሚችልበት መንገድ አልነበረም። ከበርካታ ዘመናት በኋላ በአሁኑ ወቅት የምንኖር ሰዎች ግን ከመዝሙራዊው ይበልጥ ብዙ ከዋክብትን ማየት ችለናል። አንዳንዶች ፍኖተ ሐሊብ በተባለው በእኛ ጋላክሲ ውስጥ ብቻ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብት እንዳሉ ይገምታሉ። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ደግሞ በትሪሊዮኖች የሚቆጠሩ ጋላክሲዎች ሊኖሩ ይችላሉ! በእርግጥም የሰው ልጆች ከዋክብትን ቆጥረው መጨረስ አይችሉም! ፈጣሪ ግን ለእያንዳንዳቸው ስም ወይም መለያ ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም በይሖዋ ዘንድ እያንዳንዱ ኮከብ ከሌላው የተለየ ነው። (1 ቆሮ. 15:41) በምድር ላይ ስላሉት ሰብዓዊ ፍጥረታቱስ ምን ማለት ይችላል? እያንዳንዱ ኮከብ በማንኛውም ጊዜ የሚገኝበትን ትክክለኛ ቦታ የሚያውቀው አምላክ አንተንም በግለሰብ ደረጃ በሚገባ ያውቅሃል፤ በሌላ አባባል የት እንዳለህ፣ ምን እንደሚሰማህ እንዲሁም ምን እንደሚያስፈልግህ ሁልጊዜ ጠንቅቆ ያውቃል!

7, 8. (ሀ) ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ግምት ውስጥ ያስገባል? (ለ) ይሖዋ ስሜታችንን እንደሚረዳልን የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

7 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ስለ አንተ የሚያስብ ከመሆኑም ባሻገር በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ችግሮች ይረዳልሃል፤ እንዲሁም ችግሮችህን እንድትወጣ ለመርዳት የሚያስችል ኃይል አለው። (መዝሙር 147:5ን አንብብ።) በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለህና የተጫነብህ ሸክም ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። አምላክ ‘አፈር መሆንህን ስለሚያስታውስ’ ያለብህን የአቅም ገደብ ይገነዘባል። (መዝ. 103:14) ፍጹማን ባለመሆናችን በተደጋጋሚ ጊዜ አንድ ዓይነት ስህተት እንፈጽም ይሆናል። ሁላችንም፣ ሳናስብ በተናገርነው ነገር የተነሳ ተቆጭተን እናውቃለን፤ አሊያም ደግሞ አልፎ  አልፎ ብቅ እያለ በሚያስቸግረን የሥጋ ምኞት በመሸነፋችን ወይም በሌሎች የመቅናት ዝንባሌ ስላለን አዝነን እናውቃለን። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ድክመቶች ባይኖሩበትም እኛ ያሉብንን ድክመቶች በሚገባ ይረዳልናል፤ በዚህ ረገድ ያለው ማስተዋልም ቢሆን ወሰን የለውም፤ እንዲሁም አይመረመርም!—ኢሳ. 40:28

8 አንተም ኃያል የሆነው የይሖዋ እጅ፣ ያጋጠመህን ችግር እንድትወጣ እንዴት እንደረዳህ በግል ሕይወትህ ተመልክተህ ታውቅ ይሆናል። (ኢሳ. 41:10, 13) ኪዮኮ የተባለችን አቅኚ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ኪዮኮ ወደ አዲሱ የአገልግሎት ምድቧ ከሄደች በኋላ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጣ ነበር። ይህች እህት፣ ያጋጠማትን ችግር ይሖዋ እንደተረዳላት ያወቀችው እንዴት ነው? በአዲሱ ምድቧ ላይ ስሜቷን የሚረዱላት ሰዎች አገኘች። በመሆኑም ይሖዋ እንደሚከተለው ብሎ እንደተናገራት ሆኖ ተሰምቷታል፦ “ኪዮኮ እወድሻለሁ፤ የምወድሽም አቅኚ ስለሆንሽ ብቻ ሳይሆን ልጄ በመሆንሽና ራስሽን ለእኔ በመስጠትሽ ነው። ከእኔ ምሥክሮች አንዷ እንደመሆንሽ መጠን በሕይወትሽ ደስተኛ እንድትሆኚ እፈልጋለሁ!” አንተስ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ‘ማስተዋሉ ወሰን የሌለው’ መሆኑን በሕይወትህ ውስጥ የተመለከትክበት አጋጣሚ የለም?

ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያሟላልናል

9, 10. ይሖዋ በቅድሚያ የሚያሟላው የትኛውን ፍላጎታችንን ነው? ምሳሌ ስጥ።

9 ሁላችንም እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያሉት ነገሮች ያስፈልጉናል። አንዳንድ ጊዜ፣ በቂ ምግብ የማግኘትህ ጉዳይ ያስጨንቅህ ይሆናል። ይሁንና ምግብ እንዲኖር የሚያስችለውን ተፈጥሯዊ ዑደት ያዘጋጀው ይሖዋ መሆኑን መዘንጋት የለብህም። ይሖዋ፣ የሚበሉትን ለማግኘት ለሚጮኹ የቁራ ጫጩቶች እንኳ ምግባቸውን ይሰጣቸዋል! (መዝሙር 147:8, 9ን አንብብ።) ይሖዋ ቁራዎችን ምንጊዜም የሚመግባቸው ከሆነ የአንተንም ቁሳዊ ፍላጎት እንደሚያሟላልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—መዝ. 37:25

10 ይሖዋ፣ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ይኸውም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል፤ ይህን የሚያደርገው “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ [የሆነውን] የአምላክ ሰላም” በመስጠት ነው። (ፊልጵ. 4:6, 7) ሙትስዎ እና ባለቤቱን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በ2011 ጃፓን በሱናሚ በተመታችበት ወቅት ይሖዋ እንደተንከባከባቸው ተመልክተዋል። ከሱናሚው መትረፍ የቻሉት የቤታቸው ጣሪያ ላይ በመውጣታቸው ነበር። ሆኖም በዚያ ዕለት ንብረታቸውን በሙሉ አጥተዋል ማለት ይቻላል። ሌሊቱን ያሳለፉት፣ ምስቅልቅሉ በወጣው ቤታቸው ሁለተኛ ፎቅ ላይ ጨለማው ውስጥ በብርድ ተቆራምደው ነበር። ሲነጋ፣ በመንፈሳዊ የሚያበረታታቸው ነገር መፈለግ ጀመሩ። በቤታቸው ውስጥ ማግኘት የቻሉት የ2006 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍን ብቻ ነበር። “በታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ አስከፊ የሆኑት ሱናሚዎች” የሚለው ርዕስ የሙትስዎን ቀልብ ሳበው። ርዕሱ የሚያወሳው በ2004 በሱማትራ ስለተከሰተው የምድር መናወጥ ነው፤ ይህ የምድር መናወጥ በታሪክ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ሱናሚዎች አስከትሏል። ሙትስዎና ባለቤቱ ተሞክሮዎቹን ሲያነቡ እንባቸው ይፈስ ነበር። አምላክ፣ ትክክለኛውን መንፈሳዊ ማበረታቻ ልክ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ በመስጠት ፍቅራዊ እንክብካቤ እንዳደረገላቸው ተሰምቷቸዋል። ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገርም በደግነት አሟልቶላቸዋል። መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው የእርዳታ ቁሳቁሶችን ሰጥተዋቸዋል። ከሁሉ ይበልጥ የተበረታቱት ግን የአምላክ ድርጅት ተወካዮች ለጉባኤው ባደረጓቸው ጉብኝቶች ነው። ሙትስዎ “ይሖዋ ከእያንዳንዳችን አጠገብ ሆኖ እንደተንከባከበን ተሰምቶኛል። ይህ በጣም አጽናንቶኛል!” ብሏል። በእርግጥም አምላክ በዋነኝነት የሚያሟላልን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ነው፤ ሆኖም የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮችንም ያሟላልናል።

ከይሖዋ የማዳን ኃይል ጥቅም ማግኘት

11. ከይሖዋ የማዳን ኃይል ጥቅም ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

11 ይሖዋ ምንጊዜም ‘የዋሆችን ለማንሳት’ ዝግጁ ነው። (መዝ. 147:6ሀ) ሆኖም አምላካችን ከሚሰጠን እርዳታ ተጠቃሚ ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ከእሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ይኖርብናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ የዋህነትን ማዳበር  አለብን። (ሶፎ. 2:3) የዋህ የሆኑ ሰዎች ማንኛውንም የፍትሕ መጓደል እንዲሁም በራሳቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት አምላክ እስኪያስተካክለው ድረስ በትዕግሥት ይጠብቃሉ። ይሖዋ እንዲህ ላሉት ሰዎች ሞገሱን ያሳያቸዋል።

12, 13. (ሀ) የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ከምን መራቅ ይኖርብናል? (ለ) ይሖዋ የሚደሰተው በእነማን ነው?

12 በሌላ በኩል ግን አምላክ “ክፉዎችን . . . መሬት ላይ ይጥላል።” (መዝ. 147:6ለ) ይህ እንዴት ያለ ኃይለኛ ሐሳብ ነው! የይሖዋን ታማኝ ፍቅር ለማየትና ከቁጣው ለመሰወር ከፈለግን፣ እሱ የሚጠላቸውን ነገሮች መጥላት ይኖርብናል። (መዝ. 97:10) ለምሳሌ፣ የፆታ ብልግናን መጥላት አለብን። ይህም ሲባል የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ጨምሮ እንዲህ ወዳለው ኃጢአት ከሚመራ ማንኛውም ነገር መራቅ አለብን ማለት ነው። (መዝ. 119:37፤ ማቴ. 5:28) ይህ ከባድ ትግል ማድረግ የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና የይሖዋን በረከት ለማግኘት ስንል ማንኛውንም ጥረት ብናደርግ የሚያስቆጭ አይሆንም።

13 ይህን ትግል ስናደርግ በራሳችን ሳይሆን በይሖዋ መታመን ይኖርብናል። እርዳታ ለማግኘት “በፈረስ ጉልበት” ማለትም ሰዎች ይረዱናል ብለው በሚተማመኑባቸው ነገሮች ብንታመን ይሖዋ ይደሰታል? በፍጹም! ‘በሰው እግር ጥንካሬ’ ይኸውም በራሳችን ብርታት ወይም በሌሎች ሰዎች ኃይልም ቢሆን መመካት የለብንም። (መዝ. 147:10) ከዚህ ይልቅ ወደ ይሖዋ መቅረብና እንዲረዳን መማጸን አለብን። ከሰው ልጆች አማካሪዎች በተለየ፣ ይሖዋ እርዳታ ለማግኘት የቱንም ያህል ጊዜ ደጋግመን የምናቀርበውን ልመና መስማት አይሰለቸውም። “ይሖዋ እሱን በሚፈሩ፣ ታማኝ ፍቅሩን በሚጠባበቁ ሰዎች ይደሰታል።” (መዝ. 147:11) ይሖዋ ታማኝ ስለሆነና ስለሚወደን፣ መጥፎ ምኞቶችን እንድናሸንፍ ምንጊዜም ከጎናችን በመሆን እንደሚረዳን መተማመን እንችላለን።

14. መዝሙራዊው ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?

14 ይሖዋ፣ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሕዝቡን እንደሚረዳ ለመተማመን የሚያስችል ዋስትና ሰጥቶናል። መዝሙራዊው፣ እስራኤላውያን ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱበት ጊዜ ይሖዋ እንዴት እንደረዳቸው ሲገልጽ “እሱ የከተማሽን በሮች መወርወሪያዎች አጠናክሯል፤ በውስጥሽ ያሉትን ወንዶች ልጆች ይባርካል። በክልልሽ ውስጥ ሰላም ያሰፍናል” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 147:13, 14) መዝሙራዊው፣ አምላክ ለሕዝቡ ጥበቃ ለማድረግ ሲል የከተማዋን በሮች መወርወሪያዎች እንደሚያጠናክር ማወቁ ምንኛ አበረታቶት ይሆን!

የደረሱብን መከራዎች ከአቅማችን በላይ እንደሆኑ ሲሰማን የአምላክ ቃል የሚረዳን እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 15-17⁠ን ተመልከት)

15-17. (ሀ) ችግሮች ሲያጋጥሙን ምን ሊሰማን ይችላል? ሆኖም ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ‘ቃል በፍጥነት የሚሮጠው’ እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

15 አንተም በጣም እንድትጨነቅ የሚያደርጉ ችግሮች በሕይወትህ ውስጥ አጋጥመውህ ይሆናል። ይሖዋ ችግሮቹን ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብ ይሰጥሃል። መዝሙራዊው ስለ አምላክ ሲናገር “ትእዛዙን ወደ ምድር ይልካል፤ ቃሉም በፍጥነት ይሮጣል” ብሏል። ከዚያም መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ‘በረዶን እንደሚልክ፣ አመዳዩን እንደሚበትን እንዲሁም የበረዶውን ድንጋይ እንደሚወረውር’ ከገለጸ በኋላ “እሱ የሚልከውን ቅዝቃዜ ማን ሊቋቋም ይችላል?” ሲል ጠይቋል። አክሎም ይሖዋ “ቃሉን ይልካል፤ እነሱም ይቀልጣሉ” ብሏል። (መዝ. 147:15-18) በጥበቡና በኃይሉ ተወዳዳሪ የሌለው እንዲሁም በረዶውንና አመዳዩን የሚቆጣጠረው አምላካችን፣ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም እንቅፋት እንድትወጣ ሊረዳህ ይችላል።

16 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይመራናል። “ቃሉም በፍጥነት ይሮጣል”፤ ይህም ይሖዋ፣ ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ መንፈሳዊ አመራር እንደሚሰጠን ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በመመርመር፣ JW ብሮድካስቲንግን በመመልከት፣ jw.org ላይ የሚወጡ ነገሮችን በመከታተል፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችን በማነጋገር እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር በመቀራረብ የምታገኘውን ጥቅም እስቲ አስበው። (ማቴ. 24:45) ይሖዋ የሚያስፈልግህን አመራር በፍጥነት እንደሚሰጥህ በሕይወትህ አልተመለከትክም?

17 ሲሞን የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል በሕይወቷ ውስጥ ተመልክታለች። ከፍተኛ የዋጋ ቢስነት ስሜት  ይሰማት ስለነበር በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቷን እንኳ መጠራጠር ጀምራ ነበር። ይሁንና ተስፋ በምትቆርጥባቸው ጊዜያት ደጋግማ ወደ ይሖዋ በመጸለይ እንዲረዳት ትለምነው ነበር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራ ታጠና ነበር። ሲሞን “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ይሖዋ እንደሚያበረታታኝና እንደሚመራኝ ተመልክቻለሁ” ብላለች። ይህም ይበልጥ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራት ረድቷታል።

18. የአምላክን ሞገስ እንዳገኘህ የሚሰማህ ለምንድን ነው? “ያህን አወድሱ!” እንድትል የሚያነሳሱ ምን ምክንያቶች አሉህ?

18 መዝሙራዊው፣ የጥንቶቹ የይሖዋ ሕዝቦች በአምላክ ዘንድ ልዩ ቦታ እንደነበራቸው ያውቅ ነበር። አምላክ “ቃሉን” እንዲሁም “ሥርዓቱንና ፍርዶቹን” የሰጠው ለእነሱ ብቻ ነው። (መዝሙር 147:19, 20ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜም በምድር ላይ ካሉ ሰዎች መካከል፣ በአምላክ ስም የምንጠራው እኛ ብቻ ነን፤ ይህም ታላቅ መብት ነው። ይሖዋን ስለምናውቅ፣ ቃሉ በሕይወታችን ውስጥ ስለሚመራን እንዲሁም ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና መመሥረት ስለቻልን አመስጋኞች ነን። እንደ መዝሙር 147 ጸሐፊ ሁሉ አንተም “ያህን አወድሱ!” እንድትል እንዲሁም ሌሎችም ይህን እንዲያደርጉ እንድታበረታታ የሚያነሳሱ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉህ አይሰማህም?