በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

“ዕቅድህን . . . ሁሉ ያሳካልህ”

“ዕቅድህን . . . ሁሉ ያሳካልህ”

“በይሖዋ ሐሴት አድርግ፤ እሱም የልብህን መሻት ይሰጥሃል።”—መዝ. 37:4

መዝሙሮች፦ 135, 81

1. ወጣቶች ከወደፊት ሕይወታችሁ ጋር በተያያዘ ምን ውሳኔ ማድረግ ይኖርባችኋል? ሆኖም ከመጠን በላይ መጨነቅ የሌለባችሁ ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

እናንት ወጣቶች፣ ጉዞ ከመጀመራችሁ በፊት ወዴት እንደምትሄዱ ማቀድ አለባችሁ ቢባል ሳትስማሙ አትቀሩም። ሕይወትም ከጉዞ ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ሕይወታችሁን በየትኛው አቅጣጫ መምራት እንደምትፈልጉ ዕቅድ ማውጣት ያለባችሁ ወጣት እያላችሁ ነው። እርግጥ፣ ዕቅድ ማውጣት ቀላል ላይሆን ይችላል። ሄዘር የተባለች ወጣት “በሕይወታችሁ ምን ማድረግ እንደምትፈልጉ መወሰን በጣም ያስፈራል” ብላለች። ሆኖም አይዟችሁ! ይሖዋ ለሕዝቡ “እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ” ብሏቸዋል።—ኢሳ. 41:10

2. ይሖዋ አስደሳች ሕይወት ለመምራት የሚያስችል ዕቅድ እንድታወጡ እንደሚፈልግ እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ?

2 ይሖዋ ከወደፊት ሕይወታችሁ ጋር በተያያዘ ጥበብ የተንጸባረቀበት ዕቅድ እንድታወጡ ያበረታታችኋል። (መክ. 12:1፤ ማቴ. 6:20) ይሖዋ ደስተኛ እንድትሆኑ ይፈልጋል። የምናያቸው፣ የምንሰማቸውና የምንቀምሳቸው አስደሳች ነገሮችን መፍጠሩ ለዚህ ማስረጃ ነው። በተጨማሪም ምን ያህል እንደሚንከባከበን እንዲሁም ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል መመሪያ እንደሚሰጠን አስቡ። ይሖዋ፣ የእሱን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ ላልሆኑ ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ የማልደሰትበትንም ነገር መረጣችሁ። . . . እነሆ፣ አገልጋዮቼ ሐሴት ያደርጋሉ፤ እናንተ ግን ኀፍረት ትከናነባላችሁ። እነሆ፣ አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ።” (ኢሳ. 65:12-14) የይሖዋ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረጋቸው እሱን ያስከብረዋል።—ምሳሌ 27:11

 ደስተኛ እንድትሆን የሚረዳ ዕቅድ

3. ይሖዋ የሚያበረታታህ ምን ዓይነት ዕቅድ እንድታወጣ ነው?

3 ይሖዋ የሚያበረታታህ ምን ዓይነት ዕቅድ እንድታወጣ ነው? የሰው ልጆችን የፈጠራቸው፣ ስለ እሱ በማወቅና እሱን በታማኝነት በማገልገል ደስታ እንዲያገኙ አድርጎ ነው። (መዝ. 128:1፤ ማቴ. 5:3) የሰው ልጆች ሕይወት፣ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም በመራባት ብቻ ረክተው እንዲኖሩ ከተፈጠሩት እንስሳት ሕይወት በእጅጉ የተለየ ነው። አንተም እንስሳትን ከሚያስደስቷቸው ነገሮች የበለጡ ግቦች ላይ ለመድረስ ዕቅድ እንድታወጣ ይሖዋ ይፈልጋል፤ ይህን ማድረግህ በሕይወትህ ደስተኛ ለመሆን ያስችልሃል። ፈጣሪያችን ‘የፍቅር አምላክ’ እንዲሁም ‘ደስተኛ አምላክ’ እንደሆነ ብሎም የሰው ልጆችን “በራሱ መልክ” እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ቆሮ. 13:11፤ 1 ጢሞ. 1:11፤ ዘፍ. 1:27) አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ለመምሰል ስትጥር ደስተኛ ትሆናለህ። “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” የሚለውን ጥቅስ እውነተኝነት በሕይወት ተመልክተህ አታውቅም? (ሥራ 20:35) ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ ይህ የማይታበል ሐቅ ነው። ይሖዋ፣ ለእሱና ለሌሎች ፍቅር በማሳየት ላይ ያተኮረ ዕቅድ እንድታወጣ የሚፈልገው ለዚህ ነው።ማቴዎስ 22:36-39ን አንብብ።

4, 5. ኢየሱስ ደስተኛ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው?

4 ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለእናንት ወጣቶች ግሩም ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ ልጅ እያለ ይጫወትና ጥሩ ጊዜ ያሳልፍ እንደነበር ጥያቄ የለውም። የአምላክ ቃል “ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው” ይላል። (መክ. 3:4) ኢየሱስ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ይጥር ነበር። የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት፣ የቤተ መቅደሱ መምህራን ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ባለው ‘የመረዳት ችሎታና በመልሱ ተደንቀው’ ነበር።—ሉቃስ 2:42, 46, 47

5 ኢየሱስ አዋቂ ከሆነ በኋላም ደስተኛ ነበር። ደስተኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደረገው ምንድን ነው? አምላክ የሰጠው ተልዕኮ ‘ለድሆች ምሥራች መናገርን እንዲሁም ለታወሩት ማየትን ማወጅን’ እንደሚጨምር ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 4:18) ኢየሱስ፣ አምላክ የሰጠውን ተልዕኮ መወጣቱ ደስተኛ እንዲሆን አድርጎታል። በመዝሙር 40:8 ላይ የሚገኘው “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል” የሚለው ሐሳብ የኢየሱስን ስሜት የሚገልጽ ነው። ኢየሱስ በሰማይ ስላለው አባቱ ለሰዎች ማስተማር ያስደስተው ነበር። (ሉቃስ 10:21ን አንብብ።) በአንድ ወቅት ስለ እውነተኛው አምልኮ ለአንዲት ሴት ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 4:31-34) ኢየሱስ ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር ማሳየቱ ደስተኛ እንዲሆን አድርጎታል። አንተም እንዲህ ካደረግህ ደስተኛ ትሆናለህ።

6. ተሞክሮ ካላቸው ክርስቲያኖች ጋር ስለ ወደፊት ዕቅድህ መወያየትህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

6 በርካታ ክርስቲያኖች በወጣትነታቸው አቅኚዎች ሆነው በማገልገላቸው ደስታ አግኝተዋል። ታዲያ ልታወጣ ያሰብከውን ዕቅድ በተመለከተ ለምን አታማክራቸውም? “መመካከር ከሌለ የታቀደው ነገር ሳይሳካ ይቀራል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።” (ምሳሌ 15:22) እንዲህ ያሉ መንፈሳዊ ሰዎች፣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በሕይወትህ ሙሉ የሚጠቅምህ ትምህርት እንደሚሰጥህ ይነግሩሃል። ኢየሱስ በሰማይ እያለ ከአባቱ የተማረ ቢሆንም በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅትም መማሩን ቀጥሎ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ምሥራቹን የሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ ማቅረብ እንዲሁም በመከራ ውስጥ ታማኝነትን መጠበቅ ደስታ እንደሚያስገኝ ተምሯል። (ኢሳይያስ 50:4ን አንብብ፤ ዕብ. 5:8፤ 12:2) ለአንተም ከፍተኛ ደስታ ሊያስገኙልህ የሚችሉ አንዳንድ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎችን እስቲ እንመልከት።

ደቀ መዛሙርት ማድረግ —ስኬት የሚያስገኝ ሥራ

7. በርካታ ወጣት ክርስቲያኖች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የሚደሰቱት ለምንድን ነው?

7 ኢየሱስ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሏል። (ማቴ. 28:19, 20) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ለመሰማራት ካቀድክ፣ በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀ እርካታ የሚያስገኝና አምላክን የሚያስከብር ሥራ መርጠሃል። እርግጥ ነው፣  እንደማንኛውም የሥራ መስክ ሁሉ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራም ውጤታማ ለመሆን ጊዜ ያስፈልግሃል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ በአቅኚነት ማገልገል የጀመረ ቲመቲ የተባለ አንድ ወንድም በቅርቡ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋን በሙሉ ጊዜዬ ማገልገል የምፈልገው እሱን እንደምወደው ማሳየት የምችልበት መንገድ ስለሆነ ነው። መጀመሪያ አካባቢ ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር አልቻልኩም ነበር፤ ወደ ሌላ ክልል ከተዛወርኩ በኋላ ግን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተወሰኑ ሰዎችን ማስጠናት ጀመርኩ። እንዲያውም ከጥናቶቼ አንዱ ወደ መንግሥት አዳራሹ መምጣት ጀመረ። ለነጠላ ወንድሞች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት * ውስጥ ለሁለት ወር ያህል ከሠለጠንኩ በኋላ አዲስ የአገልግሎት ምድብ ተሰጠኝ፤ በዚያም አራት ሰዎችን ጥናት ማስጀመር ችያለሁ። ሰዎችን ማስተማር ያስደስተኛል፤ ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የሰዎቹን ሕይወት ሲለውጥ ለመመልከት ያስችለኛል።”—1 ተሰ. 2:19

8. አንዳንድ ወጣት ክርስቲያኖች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ተሳትፏቸውን መጨመር የቻሉት እንዴት ነው?

8 አንዳንድ ወጣት ክርስቲያኖች ደግሞ ሌላ ቋንቋ ተምረዋል። በሰሜን አሜሪካ የሚኖረውን ጄከብን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሰባት ዓመት ልጅ በነበርኩበት ወቅት አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች ብዙዎቹ ቬትናማውያን ነበሩ። ስለ ይሖዋ ልነግራቸው ስለፈለግሁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ቋንቋቸውን ለመማር ዕቅድ አወጣሁ። ቋንቋውን በአብዛኛው የተማርኩት የእንግሊዝኛና የቬትናምኛ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን በማነጻጸር ነበር። በተጨማሪም በአቅራቢያችን ባለ በቬትናምኛ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ካሉ ክርስቲያኖች ጋር ጓደኝነት መሠረትኩ። ከዚያም 18 ዓመት ሲሆነኝ አቅኚ ሆንኩ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ለነጠላ ወንድሞች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ውስጥ ሠለጠንኩ። ይህም አሁን ላለሁበት ምድብ አዘጋጅቶኛል፤ በቬትናምኛ በሚመራ ቡድን ውስጥ እያገለገልኩ ሲሆን በዚያ ያለሁት የጉባኤ ሽማግሌ እኔ ብቻ ነኝ። በርካታ ቬትናማውያን ቋንቋቸውን በመማሬ በጣም ይገረማሉ። ወደ ቤታቸው እንድገባ የሚጋብዙኝ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀምራቸዋለሁ። አንዳንዶቹ እድገት አድርገው ተጠምቀዋል።”—ከሐዋርያት ሥራ 2:7, 8 ጋር አወዳድር።

9. ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የትኞቹን ጠቃሚ ትምህርቶች እንድታገኝ ይረዳሃል?

9 ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ጥሩ የሥራ ልማድ፣ ከሌሎች ጋር የመግባባት ችሎታ፣ በራስ የመተማመን መንፈስና ዘዴኝነትን እንድታዳብር የሚረዳ ሥልጠና ይሰጥሃል። (ምሳሌ 21:5፤ 2 ጢሞ. 2:24 ግርጌ) ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ይበልጥ አስደሳች የሚያደርገው ሌላም ምክንያት አለ፤ ለእምነትህ መሠረት የሆኑህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በደንብ ማወቅ እንድትችል ይረዳሃል። በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር አብረህ መሥራትን ትማራለህ።—1 ቆሮ. 3:9

10. ተፈታታኝ በሆነ ክልል ውስጥም እንኳ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ደስታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

10 በምታገለግልበት ክልል ውስጥ ምሥራቹን የሚቀበሉ ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም እንኳ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ መደሰት ትችላለህ። ደቀ መዛሙርት ማድረግ በቡድን የምናከናውነው ሥራ ነው። ቅን የሆኑ ሰዎችን በመፈለጉ ሥራ መላው ጉባኤ ይካፈላል። ከጊዜ በኋላ ደቀ መዝሙር የሆነውን ሰው ያገኙት አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ብቻ ቢሆኑም እንኳ፣ ቅን ልብ ያላቸውን በመፈለጉ ሥራ መላው ጉባኤ ስለተሳተፈ ሁሉም የደስታው ተካፋዮች ይሆናሉ። ብራንደንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ብራንደን፣ ሰዎች ምሥራቹን በማይቀበሉበት ክልል ውስጥ ለዘጠኝ ዓመት ያህል በአቅኚነት አገልግሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ምሥራቹን መስበክ ይሖዋ እንድናከናውነው የሰጠን ተልዕኮ ስለሆነ በዚህ ሥራ መካፈል ያስደስተኛል። አቅኚ የሆንኩት ትምህርት ከጨረስኩ ብዙም ሳልቆይ ነበር። በጉባኤያችን ያሉ ወጣት ወንድሞችን ማበረታታትና የሚያደርጉትን መንፈሳዊ እድገት መመልከት ያስደስተኛል። ለነጠላ ወንድሞች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከሠለጠንኩ በኋላ በአቅኚነት የማገለግልበት አዲስ ምድብ ተሰጠኝ። ባለሁበት ክልል ውስጥ ያስጠናኋቸው ሰዎች እድገት አድርገው ሲጠመቁ የማየት አጋጣሚ ባላገኝም ሌሎች በዚህ ረገድ ሲሳካላቸው አይቻለሁ። ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በተሟላ ሁኔታ ለመካፈል ዕቅድ በማውጣቴ ደስተኛ ነኝ።”—መክ. 11:6

 ዕቅድህ ወዴት ይመራሃል?

11. በርካታ ወጣቶች በየትኛው የቅዱስ አገልግሎት ዘርፍ እየተካፈሉ ነው?

11 ይሖዋን ለማገልገል የሚያስችሉህ በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ወጣቶች ፈቃደኛ የግንባታ ሠራተኞች ሆነው ያገለግላሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ። የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት አምላክን የሚያስከብርና ለአንተም ደስታ የሚያስገኝ ቅዱስ አገልግሎት ነው። እንደ ሌሎች የቅዱስ አገልግሎት ዘርፎች ሁሉ በዚህ መስክም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር መሥራትህ ደስታ ያስገኝልሃል። በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ሥራዎች ላይ መካፈልህ ጠቃሚ ትምህርት ለመቅሰምም ያስችልሃል፤ ለአደጋ በማያጋልጥ መንገድ መሥራትን፣ ትጉህ ሠራተኛ መሆንን እንዲሁም በኃላፊነት ቦታ ላይ ካሉት ጋር ተባብሮ መሥራትን ትማራለህ።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ክርስቲያኖች ብዙ በረከቶች ያገኛሉ (ከአንቀጽ 11-13⁠ን ተመልከት)

12. የአቅኚነት አገልግሎት ሌሎች አጋጣሚዎችን የሚከፍተው እንዴት ነው?

12 ኬቨን የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ከልጅነቴ ጀምሮ፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመሰማራት ይሖዋን ለማገልገል እፈልግ ነበር። የ19 ዓመት ወጣት እያለሁ በአቅኚነት ተሰማራሁ። በግንባታ ሙያ የተሰማራ አንድ ወንድም ጋ የተወሰነ ሰዓት እየሠራሁ ራሴን አስተዳድር ነበር። ጣሪያዎችን፣ መስኮቶችንና በሮችን መግጠም ተምሬያለሁ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ የተጎዱ የመንግሥት አዳራሾችንና የወንድሞችን ቤቶች መልሶ በሚገነባ ቡድን ውስጥ ለሁለት ዓመት ያህል ሠራሁ። በደቡብ አፍሪካ የግንባታ ሠራተኞች እንደሚፈለጉ ስሰማ በሥራው ለመካፈል ያመለከትኩ ሲሆን ወደዚያ እንድሄድ ተጋበዝኩ። አፍሪካ ውስጥ በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ፕሮጀክት ላይ የተወሰነ ሳምንት ከቆየሁ በኋላ ወደ ሌላው ፕሮጀክት እሄዳለሁ። ያለሁበት የግንባታ ቡድን ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ ነው። የምንኖረው፣ መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናውና የምንሠራው አብረን ነው። ከዚህም ሌላ በአካባቢው ካሉ ወንድሞች ጋር በየሳምንቱ ማገልገል ያስደስተኛል። በልጅነቴ ያወጣሁት ዕቅድ ጨርሶ ባላሰብኳቸው መንገዶች ደስታ እንዳገኝ አድርጎኛል።”

13. በቤቴል የሚያገለግሉ በርካታ ወጣቶች ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

13 ይሖዋን በሙሉ ጊዜያቸው ለማገልገል ያወጡትን ዕቅድ ተግባራዊ ያደረጉ አንዳንዶች፣ አሁን  በቤቴል እያገለገሉ ነው። በቤቴል የሚከናወነው ማንኛውም ሥራ ለይሖዋ የሚቀርብ አገልግሎት ስለሆነ የቤቴል ሕይወት ደስታ ያስገኛል። የቤቴል ቤተሰብ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ደስቲን የተባለ ቤቴላዊ እንዲህ ብሏል፦ “በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ግብ ያወጣሁት በዘጠኝ ዓመቴ ነው፤ ትምህርቴን ስጨርስ አቅኚ ሆንኩ። ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ወደ ቤቴል ተጠራሁ፤ በዚያም የማተሚያ መሣሪያ ላይ መሥራትን ከጊዜ በኋላ ደግሞ የኮምፒውተር ፕሮግራም ማዘጋጀትን ተማርኩ። ቤቴል ውስጥ፣ በዓለም ዙሪያ በሚከናወነው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ስለተገኙት ውጤቶች የመስማት አጋጣሚ አለኝ። በቤቴል ማገልገል ያስደስተኛል፤ ምክንያቱም እዚህ የምናከናውነው ሥራ ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ይረዳል።”

ለወደፊት ሕይወትህ ምን ዓይነት ዕቅድ ታወጣለህ?

14. በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ዝግጅት ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

14 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ዝግጅት ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋን በሙሉ ጊዜህ በማገልገል ረገድ ስኬታማ እንድትሆን ከምንም ነገር በላይ የሚረዳህ መንፈሳዊ ባሕርያትን ማዳበር ነው። ስለዚህ የአምላክን ቃል በትጋት አጥና፣ ባነበብከው ነገር ላይ በጥልቀት አሰላስል፤ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እምነትህን ለመግለጽ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ተጠቀምባቸው። በትምህርት ቤት በምታሳልፋቸው ዓመታትም ምሥራቹን የመስበክ ችሎታህን ማሻሻል ትችላለህ። የሰዎችን አመለካከት በዘዴ በመጠየቅና የሚሰጡትን መልስ በጥሞና በማዳመጥ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየትን ተማር። ከዚህም ሌላ በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ ሥራዎችን ለማከናወን ራስህን ማቅረብ ለምሳሌ የመንግሥት አዳራሹን በማጽዳቱ ወይም በመጠገኑ ሥራ መካፈል ትችላለህ። ይሖዋ ትሑት የሆኑና የፈቃደኝነት መንፈስ ያላቸው ሰዎችን ይጠቀምባቸዋል። (መዝሙር 110:3ን አንብብ፤ ሥራ 6:1-3) ሐዋርያው ጳውሎስ በሚስዮናዊነት እንዲካፈል ጢሞቴዎስን የጋበዘው በወንድሞች ዘንድ “በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት” ወጣት ስለነበር ነው።—ሥራ 16:1-5

15. መተዳደሪያ ለማግኘት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

15 አብዛኞቹ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ሥራ ያስፈልጋቸዋል። (ሥራ 18:2, 3) በምትኖርበት አካባቢ ተፈላጊ በሆነ ሙያ ላይ አጠር ያለ ሥልጠና መውሰድህ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ የምትሠራው ሥራ ለማግኘት ሊረዳህ ይችላል። ዕቅድ ስታወጣ የወረዳ የበላይ ተመልካቻችሁን እንዲሁም በወረዳህ ውስጥ ያሉ አቅኚዎችን አማክር። ለአቅኚዎች ተስማሚ የሆኑት ሥራዎች የትኞቹ እንደሆኑ ጠይቃቸው። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካል።”—ምሳሌ 16:3፤ 20:18

16. በወጣትነትህ ይሖዋን በሙሉ ጊዜህ ማገልገልህ ወደፊት ለሚያጋጥሙህ ሌሎች ኃላፊነቶች እንድትዘጋጅ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

16 እርግጠኛ መሆን የምትችለው አንድ ነገር አለ፤ ይሖዋ፣ አስደሳች ሕይወትን ‘አጥብቀህ እንድትይዝ’ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:18, 19ን አንብብ።) የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጋር እንድትቀራረብና ጎልማሳ ክርስቲያን እንድትሆን ይረዳሃል። በተጨማሪም ብዙዎች በወጣትነታቸው ይሖዋን በሙሉ ጊዜያቸው ማገልገላቸው፣ በትዳራቸው ስኬታማ እንዲሆኑ እንደረዳቸው ተገንዝበዋል። ከማግባታቸው በፊት አቅኚነትን የጀመሩ አብዛኞቹ ክርስቲያኖችም፣ ከትዳር አጋራቸው ጋር በዚህ አገልግሎት መካፈላቸውን መቀጠል ችለዋል።—ሮም 16:3, 4

17, 18. የልብህ ፍላጎትና የምታወጣው ዕቅድ ምን ግንኙነት አላቸው?

17 የልብህ ፍላጎት በምታወጣው ዕቅድ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። መዝሙር 20:4 “[ይሖዋ] የልብህን ፍላጎት ያሟላልህ፤ ዕቅድህንም ሁሉ ያሳካልህ” ይላል። እንግዲያው በሕይወትህ ምን ማድረግ እንደምትፈልግ በሚገባ አስብበት። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ምን እያከናወነ እንዳለ እንዲሁም እሱን ለማገልገል አንተ ምን ማድረግ እንደምትችል አስብ። ከዚያም እሱን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ ዕቅድ አውጣ።

18 ይሖዋን በሙሉ ጊዜህ ማገልገል ጥልቅ እርካታ ያስገኝልሃል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለ ሕይወት መምራትህ አምላክን ያስከብራል። ስለዚህ “በይሖዋ ሐሴት አድርግ፤ እሱም የልብህን መሻት ይሰጥሃል።”—መዝ. 37:4

^ አን.7 የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት በተባለው ትምህርት ቤት ተተክቷል።