በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ሐምሌ 2017

”ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ”

”ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ”

“እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።” —1 ተሰ. 5:11

መዝሙሮች፦ 90, 111

1, 2. ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናት ስለምንችልበት መንገድ መወያየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

“ልጃችን ከሞተ በኋላ ወደ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በጥልቅ ሐዘን ተውጠን ነበር” በማለት ሱሲ የተባለች እህት ተናግራለች። ባለቤቱ በድንገት የሞተችበት አንድ ክርስቲያን ደግሞ “በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ አካላዊ ሥቃይ ይሰማው እንደነበር” ተናግሯል። የሚያሳዝነው ሌሎች በርካታ ሰዎችም እንዲህ ዓይነት ሥቃይ አጋጥሟቸዋል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ወንድሞችና እህቶች፣ አርማጌዶን ከመምጣቱ በፊት የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ሊያጡ እንደሚችሉ አልጠበቁ ይሆናል። አንተ ራስህ የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ሐዘን የደረሰበት ሰው ታውቅ ይሆናል፤ በመሆኑም ‘ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች መጽናኛ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?’ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብህ ይችላል።

2 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ሐዘን እየቀነሰ እንደሚመጣ ሲነገር ሰምተህ ይሆናል። ይሁንና ጊዜ ማለፉ ብቻ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች የተሰበረ ልብ ይጠግነዋል? ባለቤቷን በሞት ያጣች አንዲት ሴት “ሐዘኑ እንዲቀንስልን የሚረዳን፣ ጊዜያችንን የምናሳልፍበት መንገድ ነው ቢባል ይበልጥ ትክክል እንደሆነ ይሰማኛል” ብላለች። አካላዊ ቁስል ተገቢው እንክብካቤ ከተደረገለት ውሎ አድሮ እየዳነ እንደሚሄድ ሁሉ፣ ስሜቱ የተጎዳ ሰውም ተገቢውን እርዳታ ካገኘ ቀስ በቀስ ሥቃዩ እየቀነሰ ይሄዳል። ታዲያ ሐዘን ላይ የወደቁ ሰዎች የሚሰማቸውን ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ለማስታገስ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

 ይሖዋ—“የመጽናናት ሁሉ አምላክ”

3, 4. ይሖዋ፣ ሐዘን የደረሰበትን ሰው ስሜት እንደሚረዳ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

3 ከሐዘናችን እንድንጽናና ከማንም በላይ ሊረዳን የሚችለው ሩኅሩኅ የሆነው የሰማዩ አባታችን ይሖዋ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ።) የሌሎችን ስሜት በመረዳት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነው ይሖዋ፣ “የማጽናናችሁ እኔ ራሴ ነኝ” የሚል ማረጋገጫ ለሕዝቡ ሰጥቷቸዋል።—ኢሳ. 51:12፤ መዝ. 119:50, 52, 76

4 የምሕረት አባት የሆነው ይሖዋ እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴና ንጉሥ ዳዊት ያሉ ወዳጆቹ በሞቱበት ወቅት፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ምን ያህል ከባድ ሐዘን እንደሚያስከትል ተመልክቷል። (ዘኁ. 12:6-8፤ ማቴ. 22:31, 32፤ ሥራ 13:22) ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ከሞት የሚያስነሳበትን ጊዜ እንደሚናፍቅና በጉጉት እንደሚጠብቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 14:14, 15) በዚያ ወቅት እነዚህ ሰዎች ደስተኞችና ፍጹም ጤናማ ይሆናሉ። አምላክ፣ ልጁን በጣም የሚወደው ከመሆኑም ሌላ “በየዕለቱ [በእሱ] የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው” እንደነበር የአምላክ ቃል ይናገራል፤ በመሆኑም ይህ ልጁ ተሠቃይቶ ሲሞት ይሖዋ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን ማሰብ እንችላለን። (ምሳሌ 8:22, 30) በዚያ ወቅት ይሖዋ የተሰማውን ሐዘን በቃላት መግለጽ ያዳግታል።—ዮሐ. 5:20፤ 10:17

5, 6. ይሖዋ የሚያጽናናን እንዴት ነው?

5 ይሖዋ እንደሚያጽናናን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በመሆኑም ከደረሰብን ሐዘን ጋር በተያያዘ የልባችንን አውጥተን ለእሱ ከመናገር ወደኋላ ልንል አይገባም። ይሖዋ ሥቃያችንን እንደሚረዳልንና በጣም የሚያስፈልገንን መጽናኛ እንደሚሰጠን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይሁን እንጂ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

6 አምላክ እኛን የሚረዳበት አንዱ መንገድ ‘ከመንፈስ ቅዱስ ማጽናኛ’ እንድናገኝ በማድረግ ነው። (ሥራ 9:31) በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል፣ ታላቅ የመጽናናት ምንጭ ነው። ኢየሱስ፣ በሰማይ ያለው አባት “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን [ለመስጠት]” ፈቃደኛ እንደሆነ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 11:13) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሱሲ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እንዲያጽናናን በጉልበታችን ተንበርክከን የለመንንባቸው በርካታ ጊዜያት አሉ። እንዲህ ያለ ልመና ባቀረብንበት ጊዜ ሁሉ የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን ጠብቆልናል።”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።

ኢየሱስ—ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት

7, 8. ኢየሱስ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ሊያጽናና እንደሚችል እርግጠኛ የምንሆነው ለምንድን ነው?

7 የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ እንደ ርኅራኄና የሌሎችን ስሜት መረዳት ያሉትን የይሖዋን ባሕርያት በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ፍጹም በሆነ መልኩ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 5:19) ኢየሱስ ወደ ምድር የተላከው “ልባቸው የተሰበረውን” እና “የሚያለቅሱትንም ሁሉ” እንዲያጽናና ነው። (ኢሳ. 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:17-21) በመሆኑም ጥልቅ የሆነ የርኅራኄ ስሜት ያሳይ ነበር፤ የሌሎችን ሥቃይ የሚረዳ ከመሆኑም ሌላ ሥቃያቸውን ለማስታገስ ከልቡ ይፈልግ ነበር።—ዕብ. 2:17

8 ኢየሱስ ልጅ እያለ፣ የቤተሰቡን አባላት ወይም ሌሎች የሚያውቃቸውን ሰዎች በሞት አጥቶ እንደሚሆን የታወቀ ነው። አሳዳጊ አባቱ የሆነው ዮሴፍ የሞተው፣ ኢየሱስ ገና ለጋ ወጣት እያለ ሳይሆን አይቀርም። * ሩኅሩኅ የሆነው ኢየሱስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ እንዲህ ያለ ሐዘን ሲገጥመው፣ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፤ በዚያ ላይ ደግሞ የእናቱን፣ የወንድሞቹንና የእህቶቹን ሐዘን ሲመለከት ስሜቱ በጥልቅ ተጎድቶ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም።

9. አልዓዛር በሞተ ጊዜ ኢየሱስ የሌሎችን ስሜት እንደሚረዳ ያሳየው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት የሰዎችን ስሜት ይረዳ እንዲሁም ራሱን በሌሎች ቦታ ያስቀምጥ ነበር። በጣም የሚወደው ወዳጁ አልዓዛር  በሞተበት ወቅት የተፈጸመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ፣ አልዓዛርን ሊያስነሳው እንደሆነ ቢያውቅም የማርያምና የማርታ መሪር ሐዘን ወደ ልቡ ዘልቆ ተሰምቶት ነበር። ሐዘናቸው በጥልቅ ስለተሰማው እንባውን አፍስሷል።—ዮሐ. 11:33-36

10. በዛሬው ጊዜም ኢየሱስ እንደሚራራልን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

10 ኢየሱስ የተናገራቸው ርኅራኄ የሚንጸባረቅባቸውና የሚያጽናኑ ቃላት በዛሬው ጊዜ ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው? ቅዱሳን መጻሕፍት “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ለዘላለምም ያው ነው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጡናል። (ዕብ. 13:8) ‘የሕይወት ዋና ወኪል’ የሆነው ኢየሱስ፣ ሐዘን ምን ስሜት እንደሚፈጥር ከራሱ ተሞክሮ ስለሚያውቅ “በፈተና ላይ ላሉት ሊደርስላቸው ይችላል።” (ሥራ 3:15፤ ዕብ. 2:10, 18) በመሆኑም ክርስቶስ የሌሎች ሐዘን በጥልቅ እንደሚሰማው፣ ስሜታቸውን እንደሚረዳላቸው እንዲሁም ‘በሚያስፈልጋቸው ጊዜ’ እንደሚያጽናናቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።ዕብራውያን 4:15, 16ን አንብብ።

‘ከቅዱሳን መጻሕፍት የምናገኘው መጽናኛ’

11. አንተን በግለሰብ ደረጃ የሚያጽናኑህ የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

11 አልዓዛር በሞተበት ወቅት ኢየሱስ በጥልቅ ሐዘን እንደተዋጠ የሚገልጸው ዘገባ፣ አጽናኝ በሆነው የአምላክ ቃል ውስጥ ከምናገኛቸው በርካታ የሚያጽናኑ ሐሳቦች መካከል አንዱ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏልና” ይላል፤ በመሆኑም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚያጽናኑ ሐሳቦች በብዛት መገኘታቸው የሚያስገርም አይደለም። (ሮም 15:4) አንተም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ ቀጥሎ እንደቀረቡት ያሉት ጥቅሶች ሊያጽናኑህ ይችላሉ፦

  • “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።”—መዝ. 34:18, 19

  • “በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።”—መዝ. 94:19

  • “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እንዲሁም የወደደን፣ በጸጋም አማካኝነት ዘላለማዊ መጽናኛና መልካም ተስፋ የሰጠን አባታችን የሆነው አምላክ ልባችሁን ያጽናኑ፤ እንዲሁም ምንጊዜም . . . ያጽኗችሁ።”—2 ተሰ. 2:16, 17 *

ጉባኤው—ታላቅ የመጽናኛ ምንጭ

12. ሌሎችን ማጽናናት የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ምንድን ነው?

12 ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች መጽናኛ ማግኘት የሚችሉበት ሌላው መንገድ ደግሞ የክርስቲያን ጉባኤ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:11ን አንብብ።) “የተደቆሰ መንፈስ” ያላቸውን ሰዎች ማበርታትና ማጽናናት የምትችሉት እንዴት ነው? (ምሳሌ 17:22) “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” የሚለውን ጥቅስ አስታውሱ። (መክ. 3:7) ዳሊን የተባለች ባለቤቷን በሞት ያጣች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን መግለጽ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ሐዘን የደረሰበትን ሰው ለማጽናናት ልታደርጉ የምትችሉት በጣም አስፈላጊ ነገር፣ ሐሳቡን ሲገልጽ ሳታቋርጡት ማዳመጥ ነው።” ወንድሟ የራሱን ሕይወት ያጠፋው ዩኒያም አክላ እንዲህ ብላለች፦ “የሚሰማቸውን ሐዘን ሙሉ በሙሉ መረዳት ባትችሉም እንኳ ስሜታቸውን ለመረዳት እንደምትፈልጉ ማሳየታችሁ በራሱ ያጽናናቸዋል።”

13. ከሐዘን ጋር በተያያዘ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

13 ሐዘን በሰዎች ላይ የሚፈጥረው ስሜትና ሐዘናቸውን የሚገልጹበት መንገድ የተለያየ እንደሆነም አስታውሱ። አንዳንድ ጊዜ፣ አንድ ሰው የሚሰማውን የስሜት ሥቃይ ሙሉ በሙሉ የሚያውቀው ግለሰቡ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም ውስጡ የታመቀውን ስሜት በቃላት መግለጽ ይከብደው ይሆናል። የአምላክ ቃል “ልብ የራሱን ምሬት ያውቃል፤ ደስታውንም ሌላ ሰው ሊጋራው አይችልም” ይላል።  (ምሳሌ 14:10) ሐዘን የደረሰበት ሰው ሐሳቡን ቢገልጽም እንኳ ምን ለማለት እንደፈለገ መረዳት ቀላል የማይሆንባቸው ጊዜያት አሉ።

14. ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለማጽናናት ምን ማለት እንችላለን?

14 በሐዘን የተዋጠን ሰው ለማጽናናት ምን ማለት እንዳለብን ማወቅ ከባድ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበበኞች ምላስ . . . ፈውስ ነው” ይላል። (ምሳሌ 12:18) ብዙዎች ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለማጽናናት የሚያስችሉ ሐሳቦችን የምትወዱት ሰው ሲሞት ከተባለው ብሮሹር ላይ አግኝተዋል። * ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ፣ ያዘኑ ሰዎችን ማጽናናት የምትችሉበት ዋነኛው መንገድ “ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ነው። (ሮም 12:15) ጋቢ የተባለች ባሏን በሞት ያጣች እህት፣ አንዳንድ ጊዜ ሐዘኗን መግለጽ የምትችለው በማልቀስ ብቻ እንደሆነ ተናግራለች። አክላም “ወዳጆቼ አብረውኝ ማልቀሳቸው የሚያጽናናኝ ለዚህ ነው። እንዲህ ሲያደርጉ ሐዘኔን የሚጋራኝ ሰው እንዳለ ይሰማኛል” ብላለች።

15. ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ቀርበን ማነጋገር ከከበደን እነሱን ለማጽናናት ምን ማድረግ እንችላለን? (“ የሚያጽናኑ ሐሳቦች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

15 ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ቀርባችሁ ማነጋገር ከከበዳችሁ በካርድ፣ በኢ-ሜይል፣ በሞባይል አጭር መልእክት ወይም በደብዳቤ አማካኝነት የሚያጽናኑ ሐሳቦችን ጽፋችሁ ልትልኩላቸው ትችላላችሁ። አንድ የሚያጽናና ጥቅስ፣ ከሞተው ግለሰብ ጋር በተያያዘ የምታደንቁትን ወይም የምታስታውሱትን ባሕርይ አሊያም አብራችሁ ያሳለፋችሁትን አስደሳች ጊዜ ጠቅሳችሁ መጻፍ ትችላላችሁ። ዩኒያ እንዲህ ብላለች፦ “የሚያጽናና አጭር መልእክት ሲደርሰኝ ወይም አንዲት ክርስቲያን አብረን ጊዜ እንድናሳልፍ ስትጋብዘኝ በጣም እጽናናለሁ። ወንድሞቼ እንዲህ ሲያደርጉ እንደሚወዱኝና እንደሚያስቡልኝ ይሰማኛል።”

16. ሌሎችን ለማጽናናት ከሚረዱን ውጤታማ መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?

16 ሐዘን ከደረሰበት የእምነት ባልንጀራችሁ ጋር  አብራችሁ ስትሆኑ አልፎ ተርፎም እሱ በሌለበት ስለ እሱ ጠቅሳችሁ መጸለያችሁ ትልቅ ጥቅም እንዳለው አትርሱ። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ስሜታችሁ ስለሚረበሽ ሐሳባችሁን በጸሎት መግለጽ ሊከብዳችሁ ይችላል፤ ይሁንና ድምፃችሁ እየተቆራረጠና እያለቀሳችሁም ቢሆን ስለ ግለሰቡ የምታቀርቡት ልባዊ ጸሎት፣ ሐዘኑ ቀለል እንዲልለት ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ዳሊን እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “አንዳንድ ጊዜ እህቶች እኔን ለማጽናናት ሲመጡ አብረውኝ እንዲጸልዩ እጠይቃቸዋለሁ። መጸለይ ሲጀምሩ አብዛኛውን ጊዜ ሐሳባቸውን መግለጽ ቢያታግላቸውም ቀስ በቀስ ድምፃቸው እየተረጋጋ ይመጣል፤ ከዚያም ልባዊ የሆነ ጸሎት ያቀርባሉ። ያላቸው ጠንካራ እምነት፣ ፍቅራቸውና አሳቢነታቸው እምነቴን በእጅጉ አጠናክሮልኛል።”

ሌሎችን ማጽናናታችሁን ቀጥሉ

17-19. ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናታችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

17 ከሐዘን ለመጽናናት የሚወስደው ጊዜ ከሰው ወደ ሰው ሊለያይ ይችላል። ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለማጽናናት፣ በርካታ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት አብረዋቸው እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፤ ሆኖም በዚህ ጊዜ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው ሰው ወደ ዕለታዊ ሕይወቱ ከተመለሰ በኋላ ባሉት ወራትም ጭምር እነሱን ለመርዳት ጥረት ማድረጉ አስፈላጊ ነው። “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።” (ምሳሌ 17:17) ሐዘን የደረሰበት ሰው ለመጽናናት የሚወስድበት ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን፣ የእምነት ባልንጀሮቹ ከጎኑ መሆናቸው በእጅጉ ያጽናናዋል።1 ተሰሎንቄ 3:7ን አንብብ።

18 የሚወዱትን ሰው በሞት ላጡ ሰዎች አንዳንድ ሙዚቃዎች፣ ፎቶግራፎች ወይም አብረው ያከናውኗቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች ሌላው ቀርቶ አንድ ዓይነት መዓዛ፣ ድምፅ አሊያም ወቅቶች ሲቀያየሩ የሚኖረው ሁኔታ እንኳ ሐዘናቸው በድንገት እንዲያገረሽባቸው ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ሰው፣ አንዳንድ ነገሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለብቻው ሲያደርግ ለምሳሌ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ወይም በመታሰቢያው በዓል ላይ ሲገኝ በሐዘን ሊዋጥ ይችላል። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የተጋባንበትን ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ለብቻዬ ማሳለፍ በጣም እንደሚከብደኝ ጠብቄ ነበር፤ ደግሞም ሁኔታው ቀላል አልነበረም። ሆኖም የተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች በዚያ ዕለት ብቻዬን እንዳልሆን ሲሉ ከቅርብ ጓደኞቼ ጋር አብሬ ጊዜ እንዳሳልፍ ዝግጅት አደረጉ።”

19 ይሁን እንጂ ሐዘን ያጋጠማቸው ሰዎች ማበረታቻ ማግኘት የሚያስፈልጋቸው በአንዳንድ ለየት ያሉ ወቅቶች ብቻ እንዳልሆነ መዘንጋት የለብንም። ዩኒያ እንዲህ ብላለች፦ “ለየት ባሉ ወቅቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጊዜያትም ሰዎች አብረውን ሲሆኑና ሲረዱን በጣም እንጠቀማለን። እንዲህ ማድረጋቸው ትልቅ ትርጉም ያለው ከመሆኑም ሌላ በእጅጉ ያጽናናናል።” እርግጥ ነው፣ ሐዘናቸውን ጨርሶ ማስወገድ ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው ምክንያት በሕይወታቸው ውስጥ የተፈጠረውን ክፍተት ሙሉ በሙሉ መድፈን እንደማንችል የታወቀ ነው፤ ያም ቢሆን ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰዳችን በተወሰነ መጠን ሊያጽናናቸው ይችላል። (1 ዮሐ. 3:18) ጋቢ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ይሖዋ ሽማግሌዎችን ስለሰጠኝ ከልቤ አመሰግነዋለሁ፤ እነዚህ አፍቃሪ እረኞች እያንዳንዱን አስቸጋሪ ወቅት መወጣት እንድችል ረድተውኛል። አፍቃሪ በሆነው በይሖዋ እቅፍ ውስጥ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርገውኛል።”

20. ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች በጣም የሚያጽናኑ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

20 ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ የክርስቶስን ድምፅ ሰምተው በሚወጡበት’ ወቅት፣ የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነው ይሖዋ ሐዘንን ጨርሶ በማስወገድ ሁሉንም ሰው እንደሚያጽናና ማወቃችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! (ዮሐ. 5:28, 29) መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ሞትን ለዘላለም ያስወግዳል፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳ. 25:8 ግርጌ) በዚያ ወቅት የምድር ነዋሪዎች በሙሉ ‘ከሚያለቅሱ ጋር በማልቀስ’ ፋንታ “ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ [ይላቸዋል]።”—ሮም 12:15

^ አን.8 ስለ ዮሴፍ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰው ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ በነበረበት ወቅት ነው። ኢየሱስ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመቀየር የመጀመሪያ ተአምሩን በፈጸመበት ወቅት ዮሴፍ አልተጠቀሰም፤ ከዚያ በኋላም ቢሆን ስለ ዮሴፍ የሚናገር ሐሳብ አናገኝም። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ እያለ ማርያምን እንዲንከባከባት አደራ የሰጠው ለሐዋርያው ዮሐንስ ነው፤ ዮሴፍ በሕይወት ቢኖር ኖሮ ኢየሱስ ይህን የሚያደርግ አይመስልም።—ዮሐ. 19:26, 27

^ አን.14 በኅዳር 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ኢየሱስ እንዳደረገው ሐዘንተኞችን አጽናኑ” የሚለውን ርዕስም ተመልከት።