በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

‘ጥበብን ትጠብቃለህ?’

‘ጥበብን ትጠብቃለህ?’

በአንድ ገጠራማ አካባቢ ስለሚኖር ድሃ ልጅ የሚነገር ተረት አለ። የመንደሩ ሰዎች ልጁ ሞኝ እንደሆነ በማሰብ ያሾፉበት ነበር። ጎብኚዎች ወደ አካባቢው ሲመጡ፣ አንዳንድ የመንደሩ ሰዎች ጓደኞቻቸው ፊት ይቀልዱበታል። ከብር የተሠራ ትልቅ ሳንቲምና ከወርቅ የተሠራ ትንሽ ሳንቲም ያሳዩትና “የምትፈልገውን መርጠህ ውሰድ” ይሉታል። የወርቁ ሳንቲም የብሩን ሳንቲም እጥፍ ዋጋ ያለው ቢሆንም ልጁ የብሩን ሳንቲም ይወስድና እየሮጠ ይሄዳል።

አንድ ጎብኚ ልጁን “የወርቁ ሳንቲም የብሩን ሳንቲም እጥፍ ዋጋ እንዳለው አታውቅም?” ብሎ ጠየቀው። ልጁ ፈገግ ብሎ “አውቃለሁ” አለ። ጎብኚው “ታዲያ የብሩን ሳንቲም የምትወስደው ለምንድን ነው? የወርቁን ሳንቲም ብትወስድ እኮ እጥፍ ገንዘብ ይኖርሃል!” አለው። ልጁም “የወርቁን ሳንቲም ብወስድማ ሰዎች ከእኔ ጋር ይህን ጨዋታ መጫወት ያቆማሉ። እስካሁን ምን ያህል የብር ሳንቲሞች እንዳጠራቀምኩ ታውቃለህ?” በማለት መለሰ። እዚህ ተረት ላይ የተጠቀሰው ትንሽ ልጅ አዋቂዎችንም ሊጠቅም የሚችል ባህርይ እንዳለው አሳይቷል፤ ይህም ጥበብ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ጥበብንና [“ማስተዋል የታከለበትን ጥበብና፣” ግርጌ] የማመዛዘን ችሎታን ጠብቅ፤ በዚያን ጊዜ በመንገድህ ላይ ተማምነህ ትሄዳለህ፤ እግርህም ፈጽሞ አይሰናከልም።” (ምሳሌ 3:21, 23) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው “ጥበብ” ምን እንደሆነና ጥበብ እንዳለን የሚያሳይ እርምጃ እንዴት መውሰድ እንደምንችል ማወቃችን ከደህንነታችን ጋር የተያያዘ ነው። ጥበብ ‘እግራችን’ እንዳይሰናከል ስለሚረዳን በመንፈሳዊ ሁኔታ ከመውደቅ ይጠብቀናል።

ጥበብ ምንድን ነው?

ጥበብ ከእውቀትና ከማስተዋል ይለያል። አንድ ሰው እውቀት አለው የሚባለው መረጃዎች ሲኖሩት ነው። ማስተዋል ያለው ሰው ደግሞ አንዱ መረጃ ከሌላው መረጃ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ይገነዘባል። ጥበብ ያለው ሰው ግን እውቀትንና ማስተዋልን አንድ ላይ አቀናጅቶ፣ ማመዛዘን የታከለበት እርምጃ ይወስዳል።

ለምሳሌ አንድ ሰው፣ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንብቦ መረዳት ይችል ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ወቅትም የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች በትክክል ይመልስ ይሆናል። በተጨማሪም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ሊጀምር ብሎም ጥሩ መልሶች ሊሰጥ ይችላል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች መንፈሳዊ እድገት እያደረገ እንዳለ ይጠቁሙ ይሆናል፤ ታዲያ ይህ ማለት ጥበብ አዳብሯል ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። ምናልባት እነዚህን ነገሮች ማድረግ የቻለው ጥሩ የመረዳት ችሎታ ስላለው ብቻ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የተማረውን እውነት ተግባራዊ ሲያደርግ ይኸውም እውቀትንና ማስተዋልን በትክክለኛው መንገድ ሲጠቀም ጥበብን እያዳበረ እንደሆነ ያሳያል። የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች በጥንቃቄ የታሰበባቸው በመሆናቸው ጥሩ ውጤት ሲያስገኙ ደግሞ ማስተዋል የታከለበት ጥበብ እያንጸባረቀ መሆኑ በግልጽ ይታያል።

በማቴዎስ 7:24-27 ላይ ኢየሱስ ቤት ስለሠሩ ሁለት ሰዎች የተናገረው ምሳሌ ይገኛል። አንደኛው ሰው “አስተዋይ” እንደሆነ ተገልጿል። ይህ ሰው ወደፊት ምን ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ ቤቱን የሠራው በዓለት ላይ ነው። አርቆ አሳቢና ብልህ መሆኑን ከዚህ ማየት ይቻላል። ገንዘብና ጊዜ እንደሚቆጥብለት በማሰብ ቤቱን በአሸዋ ላይ አልሠራም። ከዚህ ይልቅ ድርጊቱ ስለሚያስከትለው ዘላቂ ውጤት በማሰብ ጥበበኛ መሆኑን አሳይቷል። በመሆኑም ጎርፍ ሲመጣ ቤቱ ጸንቶ ቆሟል። አሁን የሚነሳው ጥያቄ ‘ይህን ጠቃሚ ባህርይ ይኸውም ጥበብን ማዳበርና መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?’ የሚል ነው።

ጥበብን ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ፣ ሚክያስ 6:9 “ጥበበኞች [የአምላክን ስም] ይፈራሉ” እንደሚል ልብ በል። የይሖዋን ስም መፍራት ማለት እሱን ማክበር ማለት ነው። ይህም ስሙ ለሚወክለው ነገር ጤናማ ፍርሃት ማሳየትን ያመለክታል፤ ይህ ደግሞ መሥፈርቶቹን ማክበርን ይጨምራል። አንድን ሰው ማክበር እንድትችል የሚያስብበትን መንገድ ማወቅ ያስፈልግሃል።  ከዚያ በኋላ በእሱ ላይ እምነት መጣልና ከእሱ መማር ትችላለህ፤ ይህም እንደ እሱ ስኬታማ ለመሆን ያስችልሃል። እኛም ድርጊታችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚነካው እንዴት እንደሆነ ካሰብንና በእሱ መሥፈርቶች ላይ ተመሥርተን ውሳኔዎችን ካደረግን ጥበብን እያዳበርን እንደሆነ እናሳያለን።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ምሳሌ 18:1 “ራሱን የሚያገል ሰው ሁሉ የራስ ወዳድነት ምኞቱን ያሳድዳል፤ ጥበብንም ሁሉ ይቃወማል” ይላል። ካልተጠነቀቅን ከይሖዋና ከሕዝቦቹ ልንርቅ እንችላለን። እንዲህ ዓይነት አካሄድ እንዳንከተል የአምላክን ስም ከሚፈሩና መሥፈርቶቹን ከሚያከብሩ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይኖርብናል። አቅማችን በፈቀደ መጠን በመንግሥት አዳራሽ ተገኝተን ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር አዘውትረን መሰብሰብ አለብን። ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ደግሞ አእምሯችንንና ልባችንን ከፍተን ትምህርቱ በግለሰብ ደረጃ እንዲነካን መፍቀድ አለብን።

ከዚህ በተጨማሪ የልባችንን አውጥተን ወደ ይሖዋ የምንጸልይ ከሆነ ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ እንችላለን። (ምሳሌ 3:5, 6) መጽሐፍ ቅዱስንና የይሖዋ ድርጅት የሚያዘጋጅልንን ጽሑፎች አእምሯችንንና ልባችንን ከፍተን ካነበብን፣ ድርጊታችን የሚያስከትለውን ዘላቂ ውጤት መገንዘብና በዚያ መሠረት አካሄዳችንን ማስተካከል እንችላለን። እንዲሁም የጎለመሱ ወንድሞች የሚሰጡንን ምክር ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ይኖርብናል። (ምሳሌ 19:20) እንዲህ ካደረግን ‘ጥበብን ሁሉ ከመቃወም’ ይልቅ ይህን አስፈላጊ ባህርይ ይበልጥ እያዳበርን መሄድ እንችላለን።

 ጥበብ ቤተሰቤን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

ጥበብ ቤተሰቦችን ይጠብቃል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሚስት ባሏን ‘በጥልቅ ማክበር’ እንዳለባት ይናገራል። (ኤፌ. 5:33) አንድ ባል፣ ሚስቱ በጥልቅ እንድታከብረው ምን ማድረግ ይኖርበታል? በጉልበት ወይም በማስገደድ ሚስቱ እንድታከብረው ለማድረግ ቢሞክር ውጤቱ የሚዘልቀው ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። ሚስቱ ከእሱ ጋር ላለመጨቃጨቅ ስትል አብሯት በሚሆንበት ጊዜ መጠነኛ አክብሮት ታሳየው ይሆናል። ሆኖም እሱ በሌለበት ጊዜስ ታከብረዋለች? ይህን ማድረግ ከባድ እንደሚሆንባት የታወቀ ነው። በመሆኑም አንድ ባል ዘላቂ ውጤት የሚያስገኘው ምን እንደሆነ ማሰብ ይኖርበታል። አፍቃሪና ደግ በመሆን የመንፈስ ፍሬን የሚያንጸባርቅ ከሆነ የሚስቱን ጥልቅ አክብሮት ያገኛል። እርግጥ አንዲት ክርስቲያን ሚስት፣ ባሏ አክብሮት የሚገባው ሰው ሆነም አልሆነ ልታከብረው ይገባል።—ገላ. 5:22, 23

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባል ሚስቱን መውደድ እንዳለበትም ይናገራል። (ኤፌ. 5:28, 33) አንዲት ሚስት የባሏን ፍቅር ላለማጣት ስትል፣ ባሏ ሊያውቃቸው የሚገቡ አንዳንድ ደስ የማይሉ ነገሮችን ከእሱ መደበቅ እንደሚሻል ታስብ ይሆናል። ይሁንና ይህ በእርግጥ የጥበብ አካሄድ ነው? የደበቀችውን ነገር ከጊዜ በኋላ ሲያውቅ ውጤቱ ምን ይሆናል? ለእሷ ያለው ፍቅር ይጨምራል? ፍቅሩ እያደገ እንዲሄድ ማድረግ ከባድ ሊሆንበት ይችላል። ከዚህ ይልቅ ሚስቱ ተስማሚ ጊዜ በመምረጥ፣ ደስ ላይሉት የሚችሉትን ነገሮች በተረጋጋ መንፈስ ብታስረዳው ሐቀኝነቷን ያደንቅ ይሆናል። ይህን ማድረጓ ባሏ ይበልጥ እንዲወዳት ያደርገዋል።

አሁን ለልጆቻችሁ ተግሣጽ የምትሰጡበት መንገድ ውሎ አድሮ ከእነሱ ጋር በሚኖራችሁ ግንኙነት ላይ ለውጥ ያመጣል

ልጆች ወላጆቻቸውን ማክበር ያለባቸው ሲሆን ወላጆችም በይሖዋ ተግሳጽ ሊያሳድጓቸው ይገባል። (ኤፌ. 6:1, 4) ታዲያ ይህ ማለት ወላጆች፣ ልጃቸው ማድረግ ያለበትንና የሌለበትን ነገሮች በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ ሊያወጡ ይገባል ማለት ነው? ልጁ የቤቱን መመሪያዎችና እነዚህን መመሪያዎች ካላከበረ የሚደርስበትን ቅጣት ማወቁ ብቻ በቂ አይደለም። ጥበበኛ የሆነ ወላጅ፣ ልጁ መታዘዝ ያለበት ለምን እንደሆነም ጭምር እንዲገነዘብ ይረዳዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ልጅ እናቱን ወይም አባቱን አክብሮት በጎደለው መንገድ ተናገረ እንበል። ወላጆች በዚህ ወቅት ቢቆጡት ወይም በብስጭት ቢቀጡት ልጁ ሊያፍርና ዝም ሊል ይችላል። ሆኖም ይህ በልቡ ቂም እንዲይዝና ከወላጆቹ እንዲርቅ ሊያደርገው ይችላል።

ጥበበኛ ወላጆች ለልጆቻቸው እንዴት ተግሣጽ መስጠት እንዳለባቸው እንዲሁም ተግሣጹ በልጆቹ የወደፊት ሕይወት ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ያስባሉ። ወላጆች፣ ልጃቸው ያደረገው ነገር ስላሳፈራቸው ብቻ ቶሎ ብለው እርምጃ መውሰድ የለባቸውም። ምናልባትም ከልጃቸው ጋር ብቻቸውን በመሆን በተረጋጋና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ፣ ይሖዋ ወላጆቹን እንዲያከብር እንደሚጠብቅበትና ይህን ማድረጉ ዘላለማዊ ጥቅም እንደሚያስገኝለት ለልጁ ሊያስረዱት ይችላሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ልጁ ወላጆቹን ማክበሩ ይሖዋን እንደሚያከብር የሚያሳይ መሆኑን እንዲገነዘብ ይረዳዋል። (ኤፌ. 6:2, 3) እንዲህ ያለው ደግነት የተንጸባረቀበት ተግሣጽ የልጁን ልብ ሊነካው ይችላል። ወላጆቹ ከልብ እንደሚያስቡለት ስለሚገነዘብ ይበልጥ ያከብራቸዋል። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ልጁ ወደፊት አሳሳቢ ነገሮች ሲያጋጥሙት የወላጆቹን እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ እንዳይል ያደርገዋል።

አንዳንድ ወላጆች ደግሞ የልጃቸውን ስሜት ላለመጉዳት በመፍራት እርማት ከመስጠት ወደኋላ ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ልጁ ሲያድግ ምን ዓይነት ሰው ይሆናል? ይሖዋን የሚፈራ እንዲሁም የአምላክን መሥፈርቶች መከተል የጥበብ እርምጃ እንደሆነ የሚገነዘብ ሰው ይሆናል? ልቡንና አእምሮውን ከፍቶ ይሖዋ እንዲመራው ይፈቅዳል? ወይስ በመንፈሳዊ ራሱን ያገልላል?—ምሳሌ 13:1፤ 29:21

በሙያው የተካነ የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ሊሠራ ስለሚፈልገው ቅርጽ አስቀድሞ ያስባል። የሚቀርጸውን ነገር እንዳመጣለት በመቁረጥ ጥሩ ቅርጽ እንደሚወጣለት ሊጠብቅ አይችልም። ጥበበኛ ወላጆች የአምላክን መሥፈርቶች ጊዜ ወስደው ያጠናሉ እንዲሁም በተግባር ያውላሉ፤ ይህን ማድረጋቸው የይሖዋን ስም እንደሚፈሩ ያሳያል። ራሳቸውን ከይሖዋና ከድርጅቱ ባለማግለል፣ ጥበብን ማግኘትና ቤተሰባቸውን በጥበብ መገንባት ይችላሉ።

በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ውሳኔዎች በየዕለቱ ይደቀኑብናል። ስሜታዊ ሆነን ቶሎ ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ስለ ጉዳዩ ቆም ብለን ማሰባችን የተሻለ አይሆንም? የምታደርገው ውሳኔ ውሎ አድሮ የሚያስከትለውን ውጤት አመዛዝን። የይሖዋን አመራር ለማግኘትና በመለኮታዊ ጥበብ ለመመራት ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግክ “ማስተዋል የታከለበትን ጥበብ . . . ጠብቅ” የሚለውን ምክር በተግባር አውለሃል ሊባል ይችላል፤ ይህ ደግሞ ሕይወት ያስገኝልሃል።—ምሳሌ 3:21, 22 ግርጌ