በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

 በጥንት ዘመን አንድ ሰው በሌላ ሰው እርሻ ላይ እንክርዳድ መዝራቱ በእርግጥ ሊፈጸም የሚችል ነገር ነው?

ይህ በንጉሠ ነገሥት ጀስቲንያን የተዘጋጀው ጽሑፍ (ዳይጀስት) የ1468 ቅጂ፣ በጥንት ዘመን ስለነበሩ የሕግ ጉዳዮች ከሚናገሩ ብዙ ዘገባዎች መካከል አንዱ ነው

በማቴዎስ 13:24-26 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ ጥሩ ዘር ከዘራ ሰው ጋር ይመሳሰላል። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። እህሉ አድጎ ፍሬ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም አብሮ ታየ።” የተለያዩ ጸሐፊዎች ይህ ምሳሌ በእውነታው ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑ ጥያቄ አንስተዋል፤ ይሁንና ጥንታዊ የሮም የሕግ መዛግብት ምሳሌው በእውነታ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዲህ ይላል፦ “በበቀል ተነሳስቶ በሌላ ሰው እርሻ ላይ እንክርዳድ መዝራት . . . በሮም ሕግ እንደ ወንጀል ይቆጠር ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ሕግ መውጣቱ፣ እንዲህ ያለ ድርጊት ይፈጸም እንደነበር ይጠቁማል።” አለስተር ኬር የተባሉ የሕግ ምሁር፣ ሮማዊው ንጉሠ ነገሥት ጀስቲንያን በ533 ዓ.ም አንድ ጽሑፍ (ዳይጀስት) እንዳዘጋጀ ተናግረዋል፤ ጽሑፉን ያዘጋጀው ከሮም ሕግና ክላሲካል ፔሬድ ኦቭ ሮማን ሎው ተብሎ በሚጠራው ጊዜ (ከ100-250 ዓ.ም ገደማ) የነበሩ የሕግ ባለሙያዎች ካዘጋጇቸው ጽሑፎች የተውጣጡ ነገሮችን አንድን ላይ በማጠናቀር ነው። ይህ ጽሑፍ (Digest, 9.2.27.14) ኧልፒያን የተባለው የሕግ ባለሙያ ስለዘገበው አንድ ታሪክ ያወሳል፤ በታሪኩ ላይ፣ በሁለተኛው መቶ ዘመን የኖረ ሴልሰስ የተባለ ሮማዊ የፖለቲካ ሰው ስለዳኘው አንድ የፍርድ ሂደት ተጠቅሷል። አንድ ግለሰብ፣ በሌላ ሰው እርሻ ላይ እንክርዳድ በመዝራቱ ምክንያት ሰብሉ ተበላሸ። ጽሑፉ፣ ይህ ወንጀል የተፈጸመበት የእርሻ ባለቤት ወይም ጭሰኛ ከበዳዩ ካሳ ለማግኘት የሚያስችሉትን ሕጋዊ ዝግጅቶች ይገልጻል።

በጥንት ዘመን በሮም ግዛት ውስጥ እንዲህ ያለ የተንኮል ድርጊት የተፈጸመ መሆኑ፣ ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ነገር በገሃዱ ዓለም ሊያጋጥም የሚችል እንደሆነ ይጠቁማል።

የሮም መንግሥት በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ለነበሩ የአይሁድ ባለሥልጣናት ምን ያህል ሥልጣን ሰጥቶ ነበር?

በወቅቱ ይሁዳ በሮማውያን አገዛዝ ሥር ነበረች፤ ሮማውያን ይሁዳን የሚያስተዳድሩት፣ የራሱ የጦር ሠራዊት ባለው አገረ ገዢ በኩል ነበር። የአገረ ገዢው ዋነኛ ሥራ ለሮም ቀረጥ መሰብሰብ እንዲሁም ሰላምና ፀጥታ ማስፈን ነው። ሮማውያኑ ትኩረት የሚያደርጉት ሕገ ወጥ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ በመከላከልና ረብሻ የሚፈጥሩ ሰዎችን በመቅጣት ላይ ነው። ከዚያ ውጪ ግን ሌሎቹን ዕለታዊ የአስተዳደር ጉዳዮች ለአይሁዳውያን መሪዎች ትተው ነበር።

የአይሁዳውያኑ የሳንሄድሪን ሸንጎ ለፍርድ ተቀምጦ

ሳንሄድሪን የአይሁዳውያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን የአይሁድን ሕግ ከሚመለከቱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አመራር ይሰጥ ነበር። በመላው ይሁዳ ሌሎች የበታች ፍርድ ቤቶች ነበሩ። አብዛኞቹ የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ጉዳዮች የሚታዩት፣ ያለ ሮማውያን መሪዎች ጣልቃ ገብነት በእነዚህ የበታች ፍርድ ቤቶች ሳይሆን አይቀርም። ሮማውያን ለአይሁድ ፍርድ ቤቶች ያልሰጡት አንዱ ኃላፊነት ወንጀለኞችን በሞት መቅጣት ነው፤ በአብዛኛው ይህን የማድረግ ሥልጣን የነበራቸው ሮማውያኑ ናቸው። ከዚህ የተለየ አሠራር የታየው፣ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት በእስጢፋኖስ ላይ ለመፍረድ በተሰየሙበትና በድንጋይ ተወግሮ እንዲገደል ባደረጉበት ጊዜ ነው።—ሥራ 6:8-15፤ 7:54-60

ስለሆነም የአይሁዳውያኑ የሳንሄድሪን ሸንጎ ብዙ ነገሮችን የማስፈጸም ሥልጣን ነበረው። ኤሚል ሹረር የተባሉ አንድ ምሁር እንደተናገሩት “[በሸንጎው] ሥልጣን ላይ የተጣለው ትልቁ ገደብ ሮማውያን ባለሥልጣናት በማንኛውም ጊዜ ተነስተው አንድን የፍርድ ሂደት ራሳቸው ለመመልከት ሊወስኑ መቻላቸው ነው፤ ለምሳሌ ወንጀሉ ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ከጠረጠሩ እንዲህ ያደርጉ ነበር።” ሮማዊው ሻለቃ ቀላውዴዎስ ሉስዮስ፣ የሮም ዜግነት የነበረውን ሐዋርያው ጳውሎስን በቁጥጥር ሥር ባዋለው ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሟል።—ሥራ 23:26-30