በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ—የጥናት እትም  |  ጥቅምት 2016

በሌላ አገር ስታገለግሉ መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ

በሌላ አገር ስታገለግሉ መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ

“አንተ የተናገርከውን በልቤ ውስጥ እንደ ውድ ሀብት እሸሽጋለሁ።”—መዝ. 119:11

መዝሙሮች፦ 142, 92

1-3. (ሀ) ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባው ነገር ምንድን ነው? (ለ) አዲስ ቋንቋ የሚማሩ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

በዛሬው ጊዜ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹ “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” እንደሚሰበክ የሚገልጸው ራእይ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው። (ራእይ 14:6) አንተስ ሌላ ቋንቋ እየተማርክ ነው? ሚስዮናዊ ሆነህ ወይም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ሄደህ እያገለገልክ ነው? አሊያም በአገርህ ውስጥ በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ላይ መገኘት ጀምረሃል?

2 የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን መንፈሳዊነት ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። (ማቴ. 5:3) ሆኖም ሕይወታችን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተጠመደ ከመሆኑ የተነሳ ትርጉም ያለው የግል ጥናት ማድረግ ከባድ የሚሆንብን ጊዜ አለ። በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች ደግሞ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል።

3 እነዚህ ክርስቲያኖች፣ አዲስ ቋንቋ ከመማር በተጨማሪ አዘውትረው ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 2:10) ይሁንና ጉባኤው የሚመራበትን ቋንቋ በደንብ የማይረዱት ከሆነ በመንፈሳዊ በሚገባ  መመገብ የሚችሉት እንዴት ነው? በተጨማሪም ክርስቲያን ወላጆች፣ የአምላክ ቃል ወደ ልጆቻቸው ልብ ዘልቆ እንዲገባ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

በመንፈሳዊነታችን ላይ የተጋረጠ አደጋ

4. መንፈሳዊነታችን ለአደጋ እንዲጋለጥ የሚያደርገው ምን ዓይነት ሁኔታ ነው? ምሳሌ ስጥ።

4 የአምላክን ቃል በሌላ ቋንቋ መረዳት አለመቻላችን መንፈሳዊነታችን አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል። በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነህምያ፣ ከባቢሎን ከተመለሱ አይሁዳውያን ልጆች መካከል አንዳንዶቹ ዕብራይስጥ መናገር እንደማይችሉ ሲያውቅ ሁኔታው በጣም አሳስቦት ነበር። (ነህምያ 13:23, 24ን አንብብ።) እነዚህ ልጆች የአምላክን ቃል ትርጉም ሙሉ በሙሉ መረዳት አለመቻላቸው ከይሖዋና እሱ ከመረጠው ሕዝብ ጋር ባላቸው ዝምድና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበረው።—ነህ. 8:2, 8

5, 6. በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች ምን አስተውለዋል? ይህ የሆነውስ ለምንድን ነው?

5 በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸው ለእውነት ያላቸው ፍላጎት እየቀነሰ እንደሄደ ተገንዝበዋል። ልጆቹ በመንግሥት አዳራሽ የሚቀርበውን መንፈሳዊ ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ ስለማይረዱት ትምህርቱ ወደ ልባቸው አይገባም። ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ከአውስትራሊያ ወደ ደቡብ አሜሪካ የሄደው ፔድሮ [1] “መንፈሳዊ ነገሮች ልባችንንና ስሜታችንን ሊነኩት ይገባል” ብሏል።—ሉቃስ 24:32

6 በሌላ ቋንቋ የምናነበው ነገር በራሳችን ቋንቋ የምናነበውን ያህል ልባችንን ላይነካው ይችላል። በተጨማሪም በሌላ ቋንቋ ሐሳባችንን በደንብ መግለጽ አለመቻላችን ውጥረት ሊፈጥርብንና በመንፈሳዊ ሊያዳክመን ይችላል። በመሆኑም በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ያለን ፍላጎት ሳይቀዘቅዝ፣ መንፈሳዊነታችንን ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ አለብን።—ማቴ. 4:4

መንፈሳዊነታቸውን ጠብቀዋል

7. ባቢሎናውያን፣ ዳንኤል ባሕላቸውንና ሃይማኖታቸውን እንዲቀበል ለማድረግ የሞከሩት እንዴት ነው?

7 ዳንኤልና ጓደኞቹ በግዞት በተወሰዱበት ወቅት ባቢሎናውያን፣ እነዚህን ወጣቶች “የከለዳውያንን . . . ቋንቋ” በማስተማር ከባሕሉ ጋር እንዲዋሃዱ ለማድረግ ሞክረው ነበር። ከዚህም ሌላ እንዲያሠለጥናቸው የተመደበው የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን የባቢሎናውያን ስም አወጣላቸው። (ዳን. 1:3-7) ለዳንኤል የተሰጠው ስም የባቢሎን ዋነኛ አምላክ ከሆነው ከቤል ጋር የተያያዘ ነበር። ንጉሥ ናቡከደነጾር ይህን ያደረገው በዳንኤል አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ይኸውም አምላኩ ይሖዋ፣ ለባቢሎን አምላክ እንደተገዛ ሆኖ እንዲሰማው ለማድረግ ፈልጎ ሊሆን ይችላል።—ዳን. 4:8

8. ዳንኤል በሌላ አገር እየኖረም መንፈሳዊነቱን ለመጠበቅ የረዳው ምንድን ነው?

8 ዳንኤል የንጉሡ ምርጥ ምግብ ቢቀርብለትም በዚህ ምግብ “ላለመርከስ በልቡ ቁርጥ ውሳኔ” አድርጓል። (ዳን. 1:8) ዳንኤል ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ በአፍ መፍቻ ቋንቋው ያጠና ስለነበር በሌላ አገር ቢኖርም መንፈሳዊነቱን ሊጠብቅ ችሏል። (ዳን. 9:2 ግርጌ) በመሆኑም ወደ ባቢሎን ከተወሰደ ከ70 ዓመታት ገደማ በኋላም እንኳ የሚታወቀው በዕብራይስጥ ስሙ ነበር።—ዳን. 5:13

9. ከመዝሙር 119 መመልከት እንደምንችለው የአምላክ ቃል በዚህ መዝሙር ጸሐፊ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል?

9 የመዝሙር 119 ጸሐፊ ከሌሎች የተለየ አቋም ለመያዝ ብርታት ያገኘው ከአምላክ ቃል ነበር። አንዳንድ የቤተ መንግሥቱ ባለሥልጣናት የሚሰነዝሩበትን ፌዝ መቋቋም ነበረበት። (መዝ. 119:23, 61) የአምላክ ቃል ልቡን በጥልቅ እንዲነካው ፈቅዶ ነበር።—መዝሙር 119:11, 46ን አንብብ።

መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ

10, 11. (ሀ) የአምላክን ቃል ስናጠና ግባችን ምን መሆን አለበት? (ለ) ግባችንን ዳር ማድረስ የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

10 ጊዜያችን በቲኦክራሲያዊና በሰብዓዊ ኃላፊነቶች  የተጣበበ ቢሆንም ሁላችንም ለግል ጥናትና ለቤተሰብ አምልኮ ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። (ኤፌ. 5:15, 16) ይሁንና ግባችን በጥናቱ ወቅት የተወሰኑ ገጾችን መሸፈን ወይም በስብሰባዎች ላይ የምንሰጠውን ሐሳብ መዘጋጀት ብቻ መሆን የለበትም። የአምላክ ቃል ልባችንን እንዲነካውና እምነታችንን እንዲያጠናክረው ማድረግ እንፈልጋለን።

11 ይህን ግብ ለማሳካት ደግሞ ሚዛናችንን መጠበቅ ይኖርብናል፤ በምናጠናበት ጊዜ ሌሎች ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆን እኛ ራሳችን ስለሚያስፈልገን ነገር ማሰብ አለብን። (ፊልጵ. 1:9, 10) ለአገልግሎት፣ ለስብሰባዎች ወይም ንግግር ለማቅረብ ስንዘጋጅ ትምህርቱን እኛ ራሳችን እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርገው ላናስብ እንችላለን። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ የምግብ ዝግጅት ባለሙያ የሆነ ሰው ምግቡን ለሌሎች ከማቅረቡ በፊት መቅመስ ቢኖርበትም በዚህ ብቻ መኖር አይችልም። ጤናማ መሆን ከፈለገ ለራሱም ገንቢ ምግብ ማዘጋጀት ይኖርበታል። በተመሳሳይ እኛም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን የሚያረካ ምግብ ለመመገብ ጥረት ማድረግ አለብን።

12, 13. በሌላ ቋንቋ በሚመሩ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ በርካታ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አዘውትረው ማጥናታቸው ጠቃሚ እንደሆነ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

12 በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ በርካታ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን ‘በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው’ አዘውትረው ማጥናት ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዘበዋል። (ሥራ 2:8 ግርጌ) ሚስዮናውያንም እንኳ በተመደቡበት አገር በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው ለመቀጠል፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ የሚያገኙት መሠረታዊ ግንዛቤ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተረድተዋል።

13 ላለፉት ስምንት ዓመታት ያህል ፋርስኛ ሲማር የቆየው አላን እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ለስብሰባ በፋርስኛ ስዘጋጅ የማተኩረው በቋንቋው ላይ  ነው። የሚያሳስበኝ ቋንቋውን መረዳቴ በመሆኑ የማነበው መንፈሳዊ ነገር ልቤን ላይነካው ይችላል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ጽሑፎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ለማጥናት ቋሚ ፕሮግራም እመድባለሁ።”

የልጆቻችሁን ልብ ለመንካት ጣሩ

14. ወላጆች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ለምንስ?

14 ክርስቲያን ወላጆች የአምላክ ቃል ቀስ በቀስ ወደ ልጆቻቸው አእምሮና ልብ ዘልቆ እንዲገባ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሰርዥ እና ባለቤቱ ሚውሪዬል በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ከሦስት ዓመት በላይ ካገለገሉ በኋላ፣ የ17 ዓመት ልጃቸው በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል እንደማያስደስተው አስተዋሉ። ሚውሪዬል “ልጃችን የአፍ መፍቻ ቋንቋው በሆነው በፈረንሳይኛ መስበክ ይወድ የነበረ ቢሆንም በሌላ ቋንቋ መስበክ ግን ያስጠላው ጀመር” ብላለች። ሰርዥ ደግሞ “ይህ ሁኔታ ልጃችን መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርግ እንቅፋት እንደሆነበት ስናስተውል ወደ ቀድሞ ጉባኤያችን ለመመለስ ወሰንን” ብሏል።

እውነት ወደ ልጆቻችሁ ልብ ጠልቆ እንዲገባ እርዷቸው (አንቀጽ 14, 15ን ተመልከት)

15. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸው በደንብ በሚረዱት ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ለመመለስ እንዲወስኑ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? (ለ) በዘዳግም 6:5-7 ላይ ለወላጆች ምን ማሳሰቢያ ተሰጥቷል?

15 ወላጆች ልጆቻቸው በደንብ በሚረዱት ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ መመለስ ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል? በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአንድ በኩል ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ እየረዱ በሌላ በኩል ደግሞ ለልጆቻቸው አዲስ ቋንቋ ለማስተማር የሚያስፈልገው ጊዜና ኃይል ያላቸው መሆኑን መመርመር ይኖርባቸዋል። ሁለተኛ፣ ልጆቻቸው ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው ጉጉት እንደቀነሰ አሊያም በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ፍላጎት እንደሌላቸው ይገነዘቡ ይሆናል። ክርስቲያን ወላጆች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካስተዋሉ፣ ልጆቻቸው እውነትን አጥብቀው እስኪይዙ ድረስ ልጆቹ በደንብ በሚረዱት ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ለመመለስ ሊወስኑ ይችላሉ።—ዘዳግም 6:5-7ን አንብብ።

16, 17. አንዳንድ ወላጆች በሌላ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ እያገለገሉ ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ሥልጠና የሚሰጡት እንዴት ነው?

16 በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወላጆች በውጭ አገር ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ወይም ቡድን ቢሄዱም ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ስለ ይሖዋ ማስተማር ችለዋል። ከ9 እስከ 13 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሦስት ሴቶች ልጆች ያሉት ቻርልስ፣ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ በሊንጋላ ቋንቋ በሚመራ ቡድን ውስጥ ይሰበሰባል። እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችንን ስናስጠናና የቤተሰብ አምልኮ ስናደርግ በቋንቋችን ለመጠቀም ወስነናል። ሆኖም ልጆቹ እየተዝናኑ ሊንጋላ መማር እንዲችሉ በዚህ ቋንቋ የልምምድ ፕሮግራም አለን፤ እንዲሁም ጨዋታዎችን እንጫወታለን።”

የአካባቢውን ቋንቋ ለመማርና በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አድርጉ (አንቀጽ 16, 17ን ተመልከት)

17 የአምስትና የስምንት ዓመት ሴት ልጆች ያሉት ኬቨን፣ ልጆቹ በሌላ ቋንቋ በሚመሩ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርበው ትምህርት በደንብ ስለማይገባቸው እነሱን ለመርዳት ዝግጅት አድርጓል። እንዲህ ይላል፦ “እኔና ባለቤቴ ሁለቱንም ልጆቻችንን የምናስጠናቸው አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ ማለትም በፈረንሳይኛ ነው። በተጨማሪም በፈረንሳይኛ በሚመራ ስብሰባ ላይ በወር አንድ ጊዜ የመገኘት ግብ አለን፤ እንዲሁም በፈረንሳይኛ በሚካሄዱ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እረፍት ወስደን እንሄዳለን።”

18. (ሀ) በሮም 15:1, 2 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ለልጆቻችሁ የተሻለውን አማራጭ ለመወሰን የሚረዳችሁ እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ ወላጆች ምን ሐሳብ አቅርበዋል? (ተጨማሪ ሐሳቡን ተመልከት።)

18 እርግጥ ነው፣ ለልጆች መንፈሳዊነት የተሻለውን አማራጭ መወሰን የእያንዳንዱ ወላጅ ኃላፊነት ነው። [2] (ገላ. 6:5) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሚውሪዬል፣ ለልጃቸው መንፈሳዊነት ሲሉ እሷና ባለቤቷ የራሳቸውን ፍላጎት መሥዋዕት እንዳደረጉ ተናግራለች። (ሮም 15:1, 2ን አንብብ።)  ሰርዥም ሁኔታውን መለስ ብሎ ሲያስበው ትክክለኛውን ውሳኔ እንዳደረጉ ይሰማዋል። እንዲህ ብሏል፦ “በፈረንሳይኛ ወደሚመራ ጉባኤ ከተመለስን ጊዜ ጀምሮ ልጃችን መንፈሳዊ እድገት ያደረገ ሲሆን በኋላም ተጠመቀ። አሁን የዘወትር አቅኚ ሆኖ ያገለግላል። እንዲያውም በሌላ ቋንቋ ወደሚመራ ቡድን እንደገና ለመዛወር እያሰበ ነው!”

የአምላክ ቃል ወደ ልባችሁ ጠልቆ ይግባ

19, 20. ለአምላክ ቃል ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

19 ይሖዋ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች . . . የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ሲል ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች እንዲዘጋጅ በማድረግ ፍቅሩን አሳይቷል። (1 ጢሞ. 2:4) ይሖዋ፣ የሰው ልጆች መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን በተሻለ መንገድ ማርካት የሚችሉት የእሱን ቃል በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲያነቡ እንደሆነ ያውቃል።

20 ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ቅዱሳን ጽሑፎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋችን አዘውትረን በማጥናት የራሳችንንም ሆነ የቤተሰባችንን መንፈሳዊነት መጠበቅ እንችላለን፤ በተጨማሪም ይህን ስናደርግ አምላክ የተናገረውን ነገር እንደ ውድ ሀብት እንደምንቆጥረው እናሳያለን።—መዝ. 119:11

^ [1] (አንቀጽ 5) ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ [2] (አንቀጽ 18) ቤተሰባችሁን የሚጠቅሙ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማግኘት በጥቅምት 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ልጆችን በውጭ አገር ማሳደግ የሚያስከትለው ችግርና የሚያስገኘው በረከት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።