“እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ።”—ዕብ. 13:1

መዝሙሮች፦ 72, 119

1, 2. ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ የጻፈው ለምንድን ነው?

ወቅቱ 61 ዓ.ም. ነው። በመላው እስራኤል የሚገኙ የክርስቲያን ጉባኤዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላም አግኝተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሮም ውስጥ እስር ላይ ቢሆንም በቅርቡ እንደሚፈታ እየተጠባበቀ ነው። የእምነት አጋሩ የሆነው ጢሞቴዎስ ከእስር ከተለቀቀ ብዙም አልቆየም፤ አንድ ላይ ሆነው በይሁዳ ያሉ ክርስቲያን ወንድሞቻቸውን ለመጎብኘት አስበዋል። (ዕብ. 13:23) ይሁንና ከአምስት ዓመት በኋላ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ኢየሩሳሌም ‘በጦር ሠራዊት ትከበባለች።’ በይሁዳ በተለይ ደግሞ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ፣ እነዚህ ነገሮች መፈጸም ሲጀምሩ በፍጥነት መሸሽ እንዳለባቸው አስጠንቅቋቸዋል።—ሉቃስ 21:20-24

2 ኢየሱስ ይህን ትንቢት ከተናገረ በኋላ በነበሩት 28 ዓመታት ውስጥ በእስራኤል የሚኖሩ ታማኝ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ብዙ ተቃውሞና ስደት የደረሰባቸው ቢሆንም ተቋቁመውታል። (ዕብ. 10:32-34) ይሁን እንጂ ጳውሎስ ከእምነታቸው ጋር በተያያዘ በቅርቡ በጣም ከባድ ፈተና እንደሚያጋጥማቸው ያውቃል። (ማቴ. 24:20, 21፤ ዕብ. 12:4) ስለዚህ ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ማንኛውም ነገር እንዲዘጋጁ ፈልጓል። የሚያጋጥማቸውን ነገር ለመቋቋም የተለየ ጽናት ብሎም በሕይወት የሚያኖር ጠንካራ እምነት ያስፈልጋቸዋል። (ዕብራውያን 10:36-39ን አንብብ።) ስለሆነም ጳውሎስ እነዚህ ውድ ወንድሞችና እህቶች የሚያስፈልጋቸውን ለየት ያለ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችል ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ይሖዋ በመንፈሱ መርቶታል። ይህ ደብዳቤ በአሁኑ  ወቅት የዕብራውያን መጽሐፍ ተብሎ ይጠራል።

3. የዕብራውያን መጽሐፍ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች የጻፈውን ደብዳቤ በዛሬው ጊዜ ሁላችንም ትኩረት ልንሰጠው ይገባል። ለምን? ምክንያቱም ያለንበት ሁኔታ ከእነሱ ጋር ይመሳሰላል። ‘ለመቋቋም በሚያስቸግረው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን’ ውስጥ ያለነው የይሖዋ ሕዝቦች ብዙ ዓይነት ተቃውሞና ስደት አጋጥሞናል። (2 ጢሞ. 3:1, 12) በዚህ ጊዜ እምነታችንና ፍቅራችን ጠንካራ መሆኑን በማያሻማ መልኩ አረጋግጠናል። በእርግጥ አብዛኞቻችን የምንኖረው በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላም በሰፈነበትና ቀጥተኛ ስደት በሌለበት አካባቢ ነው። ሆኖም በጳውሎስ ዘመን እንደነበሩት ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ፈጽሞ ልንረሳው የማይገባ ሐቅ አለ፦ በቅርቡ ከእምነታችን ጋር በተያያዘ እጅግ ከባድ ፈተና ያጋጥመናል።ሉቃስ 21:34-36ን አንብብ።

4. የ2016 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? ይህ ጥቅስ መመረጡ ተገቢ የሆነውስ ለምንድን ነው?

4 በቅርቡ ለሚጠብቀን ነገር ለመዘጋጀት ምን ሊረዳን ይችላል? ጳውሎስ እምነታችንን ለማጠናከር የሚረዱ ብዙ ነገሮችን በዕብራውያን መጽሐፍ ላይ ጠቅሷል። አስፈላጊ ከሆኑት ከእነዚህ ነገሮች አንዱ በዚህ ደብዳቤ የመጨረሻ ምዕራፍ፣ ቁጥር አንድ ላይ ተገልጿል። የ2016 የዓመት ጥቅስ ሆኖ የተመረጠው ይህ ጥቅስ ነው። ጥቅሱ “እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ” በማለት ይመክረናል።—ዕብ. 13:1

የ2016 የዓመት ጥቅስ፦ “እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ።”—ዕብራውያን 13:1

እንደ ወንድማማች መዋደድ ሲባል ምን ማለት ነው?

5. የወንድማማች መዋደድ ሲባል ምን ማለት ነው?

5 እንደ ወንድማማች እንዋደዳለን ሲባል ምን ማለት ነው? ጳውሎስ የተጠቀመበት ፊላደልፊያ የሚለው የግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺ፣ ‘አንድ ሰው ለወንድሙ ያለውን ፍቅር’ ያመለክታል። የወንድማማች መዋደድ የሚለው አገላለጽ ለቤተሰባችን አባል ወይም ለቅርብ ወዳጃችን የሚኖረንን ዓይነት ጠንካራ፣ የጠበቀና ጥልቅ ፍቅር ያመለክታል። (ዮሐ. 11:36) እንዲህ ዓይነት ፍቅር እናሳያለን ሲባል ወንድማማችና እህትማማች መስለን ለመታየት እንሞክራለን ማለት አይደለም፤ ወንድማማችና እህትማማች ነን። (ማቴ. 23:8) የሚከተለው ጥቅስ በመካከላችን ያለውን የጠበቀ ወዳጅነት በሚገባ ይገልጸዋል፦ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:10) በመሠረታዊ ሥርዓት በሚመራው አጋፔ በተባለው ፍቅር ላይ የወንድማማች መዋደድ ሲጨመር በአምላክ ሕዝቦች መካከል የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖር ያደርጋል።

6. እውነተኛ ክርስቲያኖች የወንድማማች ፍቅር የሚለውን አገላለጽ የሚረዱት እንዴት ነው?

6 አንድ ምሁር እንደተናገሩት “‘የወንድማማች ፍቅር፣’ በአንጻራዊ ሁኔታ ከክርስቲያናዊ ጽሑፎች ውጭ እምብዛም የማይሠራበት አገላለጽ ነው።” በአይሁድ እምነት መሠረት “ወንድም” የሚለው ቃል የሥጋ ዘመዳሞች ያልሆኑ ሰዎችንም የሚያመለክትበት ጊዜ ሊኖር ይችላል፤ ይሁንና ቃሉን የሚጠቀሙበት የአይሁድ ብሔር አባላትን ብቻ እንጂ አሕዛብን ለማመልከት አይደለም። ለክርስቲያኖች ግን ዜግነት ለውጥ አያመጣም፤ ሁሉም አማኞች ወንድማማች ናቸው። (ሮም 10:12) ወንድማማች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ አንዳችን ለሌላው የወንድማማች ፍቅር እንዲኖረን አስተምሮናል። (1 ተሰ. 4:9) ይሁንና እርስ በርሳችን እንደ ወንድማማች መዋደዳችንን መቀጠል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

እንደ ወንድማማች መዋደዳችንን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7. (ሀ) እንደ ወንድማማች እንድንዋደድ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) አንዳችን ለሌላው ያለንን ፍቅር ማጠናከር አስፈላጊ የሆነበትን ሌላ ምክንያት ግለጽ።

7 ዋነኛው ምክንያት፣ ይሖዋ አንዳችን ለሌላው የወንድማማች ፍቅር እንድናሳይ የሚጠብቅብን መሆኑ ነው። ወንድሞቻችንን ሳንወድ አምላክን እንወደዋለን ማለት የማይመስል ነገር ነው። (1 ዮሐ. 4:7, 20, 21) በተጨማሪም አንዳችን የሌላው ድጋፍ ያስፈልገናል። በተለይ በአስቸጋሪ ጊዜያት ወንድሞቻችን  ይበልጥ ያስፈልጉናል። ጳውሎስ ደብዳቤውን ከጻፈላቸው ዕብራውያን ክርስቲያኖች አንዳንዶቹ ብዙም ሳይቆይ ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሸሽ እንደሚኖርባቸው ያውቃል። ይህ ወቅት ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን ኢየሱስ ተናግሯል። (ማር. 13:14-18፤ ሉቃስ 21:21-23) በመሆኑም እነዚያ ክርስቲያኖች፣ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ማጠናከር ይኖርባቸዋል።—ሮም 12:9

8. ታላቁ መከራ ሳይጀምር አሁኑኑ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

8 እስከ ዛሬ ሆኖ የማያውቀው ታላቅ መከራ የጥፋት ነፋሳት በቅርቡ ይለቀቃሉ። (ማር. 13:19፤ ራእይ 7:1-3) ይህ በሚሆንበት ጊዜ “ሕዝቤ ሆይ፣ ሂድ ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ከኋላህ ዝጋ። ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ጊዜ ተሸሸግ” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተሰጠ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልገናል። (ኢሳ. 26:20) “ውስጠኛው ክፍል” የሚለው አገላለጽ ጉባኤዎቻችንን ሊያመለክት ይችላል። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር አንድ ላይ ተሰባስበን ይሖዋን የምናመልከው በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ነው። ያም ሆኖ አዘውትረን መሰብሰባችን ብቻውን በቂ አይደለም። ጳውሎስ እነዚህን አጋጣሚዎች “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች” እርስ በርስ ለመነቃቃት እንዲጠቀሙባቸው ዕብራውያን ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል። (ዕብ. 10:24, 25) የወንድማማች ፍቅር ከአሁኑ ማዳበራችን አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ወደፊት የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተናና መከራ ለመቋቋም ያስችለናል።

9. (ሀ) በዛሬው ጊዜ እንደ ወንድማማች እንደምንዋደድ ለማሳየት የሚያስችሉ ምን አጋጣሚዎች አሉን? (ለ) የይሖዋ ሕዝቦች ለወንድሞቻቸው ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳዩ ምሳሌዎች ተናገር። (ተጨማሪ ሐሳቡንም ተመልከት።)

9 ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት አሁንም እንኳ ጠንካራ የወንድማማች ፍቅር ማዳበር ያስፈልገናል። በርካታ ወንድሞቻችን በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ፣ በሱናሚ ወይም በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች የተነሳ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አንዳንድ ወንድሞች ደግሞ ተቃውሞና ስደት እያጋጠማቸው ነው። (ማቴ. 24:6-9) ይህም እንዳይበቃ፣ ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት በዚህ ሥርዓት ውስጥ ስለምንኖር በየዕለቱ ኢኮኖሚያዊ ጫና ያታግለናል። (ራእይ 6:5, 6) እንዲህ ያሉት ችግሮች እየጨመሩ ሲሄዱ የወንድማማች ፍቅራችንን ጥልቀት ለማሳየት የሚያስችሉን አጋጣሚዎችም ይጨምራሉ። ‘የብዙዎች ፍቅር ቢቀዘቅዝም’ እኛ ግን የወንድማማች ፍቅራችን ምንጊዜም እንዲቀጥል ማድረግ አለብን።—ማቴ. 24:12 [1]

እንደ ወንድማማች መዋደዳችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

10. ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመረምራለን?

10 በርካታ ችግሮች ቢያጋጥሙንም እንደ ወንድማማች መዋደዳችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ለወንድሞቻችን እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር እንዳለን በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን? ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ” ካለ በኋላ ክርስቲያኖች እንዲህ ማድረግ የሚችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች ጠቅሷል። ከዚህ ቀጥሎ ስድስቱን እንመረምራለን።

11, 12. እንግዳ ተቀባይ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

11 “እንግዳ መቀበልን አትርሱ።” (ዕብራውያን 13:2ን አንብብ።) “እንግዳ መቀበል” ተብሎ የተተረጎመው ሐረግ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ለእንግዶች ደግነት ማሳየት” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይህ ሐረግ የአብርሃምንና የሎጥን ታሪክ ያስታውሰን ይሆናል። ሁለቱም ሰዎች ለማያውቋቸው እንግዶች ደግነት አሳይተዋል። እነዚህ እንግዶች መላእክት መሆናቸውን በኋላ ላይ ተገነዘቡ። (ዘፍ. 18:2-5፤ 19:1-3) ጳውሎስ የእነሱን ምሳሌ የጠቀሰው፣ ዕብራውያን ክርስቲያኖች እንግዳ ተቀባዮች በመሆን የወንድማማች ፍቅር እንዲያሳዩ ለማበረታታት ነው።

12 እኛስ ሌሎችን ቤታችን ጠርተን ምግብ በመጋበዝ ወይም የሚያንጽ ጭውውት በማድረግ እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን እናሳያለን? እንግዳ ተቀባይ መሆን ሲባል ሰፊ ወይም ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ግብዣ ማድረግ ያስፈልገናል ማለት አይደለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የምንጋብዘው፣ ብድር ሊመልሱልን የሚችሉ ሰዎችን ብቻ መሆን የለበትም።  (ሉቃስ 10:42፤ 14:12-14) ዋናው ግባችን ወንድሞቻችንን ማስደመም ሳይሆን ማበረታታት ነው! የወረዳ የበላይ ተመልካቻችንን እና ባለቤቱን ባንግባባቸውም እንኳ ደስ ብሎን በእንግድነት እንቀበላቸዋለን? (3 ዮሐ. 5-8) ሕይወታችን በሩጫ የተሞላ ከመሆኑም ሌላ ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር በተያያዘ በሚያጋጥመን ጭንቀት የተነሳ ‘እንግዳ መቀበልን እንዳንረሳ’ መጠንቀቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

13, 14. ‘በእስር ላይ ያሉትን ሁልጊዜ ማስታወስ’ የምንችለው እንዴት ነው?

13 “በእስር ላይ ያሉትን . . . ሁልጊዜ አስታውሷቸው።” (ዕብራውያን 13:3ን አንብብ።) እዚህ ላይ ጳውሎስ በአጠቃላይ እስር ላይ ስላሉ ሰዎች መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በእምነታቸው ምክንያት እስር ቤት ስለገቡ ወንድሞች መናገሩ ነበር። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ይህን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት እሱ ራሱ ከታሰረ አራት ዓመት ያህል ሆኖታል። (ፊልጵ. 1:12-14) ሐዋርያው ‘በእስር ላይ ላሉት ስለራሩላቸው’ ዕብራውያን ክርስቲያኖችን አመስግኗቸዋል። (ዕብ. 10:34) ጳውሎስ እስር ቤት በነበረበት ጊዜ ሄደው ከረዱት ወንድሞች በተለየ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከጳውሎስ በአካል ርቀው ነበር። ታዲያ እነዚህ ወንድሞች ሁልጊዜ ሊያስታውሱት የሚችሉት እንዴት ነው? ስለ እሱ ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ ነው።—ዕብ. 13:18, 19

14 ዛሬም የምንኖረው እስር ቤት ካሉ ወንድሞቻችን ርቀን ይሆናል። በወኅኒ ቤቱ አቅራቢያ የሚኖሩ ወንድሞች እንደሚያደርጉት እስር ላይ ያሉት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማሟላት አንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህን ታማኝ ወንድሞች ሁልጊዜ በማስታወስ፣ እነሱን በጸሎታችን ላይ በመጥቀስ እንዲሁም እነሱን አስመልክተን ይሖዋን በመማጸን ርኅራኄና የወንድማማች ፍቅር ልናሳይ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በኤርትራ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ሌላው ቀርቶ ልጆች ታስረዋል፤ ከእነዚህ መካከል ከ20 ዓመት በላይ በእስር ያሳለፉት ጳውሎስ እያሱ፣ ይስሃቅ ሞገስ እና ነገደ ተኽለማርያም ይገኙበታል፤ ታዲያ እነዚህን ወንድሞች ሁልጊዜ እናስታውሳቸዋለን?

15. ጋብቻችንን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?

15 “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር . . . ይሁን።” (ዕብራውያን 13:4ን አንብብ።) የወንድማማች ፍቅር ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንጊዜም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን መጠበቅ ነው። (1 ጢሞ. 5:1, 2) አንድ ክርስቲያን ‘ከገደቡ አልፎ’ ከአንድ ወንድም ወይም እህት አሊያም ከቤተሰባቸው አባል ጋር የፆታ ብልግና በመፈጸም ይህን ግለሰብም ሆነ ቤተሰቡን ‘መጠቀሚያ ቢያደርጋቸው’ እንዲህ ያለው ምግባር ለወንድማማች ፍቅር መሠረት የሆነው የመተማመን ስሜት እንዲጠፋ ያደርጋል። (1 ተሰ. 4:3-8) ከዚህም በተጨማሪ አንዲት ሚስት፣ ባለቤቷ የብልግና ምስሎችን በመመልከት በእሷ ላይ ክህደት እንደፈጸመ ብታውቅ ምን ሊሰማት እንደሚችል አስቡት። እንዲህ ያለው ድርጊት ባሏ ለእሷ ፍቅር፣ ለጋብቻ ዝግጅት ደግሞ አክብሮት እንዳለው የሚያሳይ ነው?—ማቴ. 5:28

16. ባለን ነገር ረክተን መኖር የወንድማማች ፍቅር እንድናሳይ የሚረዳን እንዴት ነው?

16 “ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።” (ዕብራውያን 13:5ን አንብብ።) ባለን ነገር እውነተኛ እርካታ የምናገኘው በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ነው። ባለን ነገር ረክተን መኖር ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር ያስችለናል። (1 ጢሞ. 6:6-8) እንዲሁም ከይሖዋና ከወንድሞቻችን ጋር ያለን ግንኙነት፣ ገንዘብ ሊገዛው ከሚችለው ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ባለው ነገር ረክቶ የሚኖር ሰው አያጉረመርምም፣ አያማርርም እንዲሁም ስህተት አይፈላልግም፤ ከምቀኝነትና ከስግብግብነት ይርቃል፤ እንዲህ ያሉት ባሕርያት የወንድማማች ፍቅር እንዳያድግ እንቅፋት ይሆናሉ። ባለን ነገር ረክተን መኖር ግን የልግስና መንፈስ እንድናዳብር ይረዳናል።—1 ጢሞ. 6:17-19

17. “ሙሉ ልብ” ያለን መሆኑ የወንድማማች ፍቅር ለማሳየት የሚረዳን እንዴት ነው?

17 “በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው’ . . . እንላለን።” (ዕብራውያን 13:6ን አንብብ።) ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን፣ በይሖዋ መታመናችን ድፍረት እንድናገኝ ያስችለናል። ይህ ዓይነቱ ድፍረት ደግሞ አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል።  እንዲህ ያለው አዎንታዊ አመለካከት በወንድማማች ፍቅራችን ላይ ሲደመር የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለማነጽና ለማበረታታት ያስችለናል። (1 ተሰ. 5:14, 15) በታላቁ መከራ ወቅት ዓለም ጭንቅ ውስጥ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ መዳናችን እንደቀረበ ስለምናውቅ “ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እናደርጋለን።—ሉቃስ 21:25-28

ሽማግሌዎች ለእኛ ሲሉ የሚያከናውኑትን ሥራ ታደንቃላችሁ? (አንቀጽ 18ን ተመልከት)

18. ለጉባኤ ሽማግሌዎች ያለንን ወንድማዊ ፍቅር ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

18 “አመራር የሚሰጡትን አስቡ።” (ዕብራውያን 13:7, 17ን አንብብ።) ሽማግሌዎቻችን የገንዘብ ጥቅም የማያገኙ ቢሆንም ለእኛ ሲሉ ምን ያህል እንደሚደክሙ ስናስብ ለእነሱ ያለን ወንድማዊ ፍቅርና አድናቆት ይበልጥ ይጠናከራል። እኛ በፈጸምነው ነገር የተነሳ ደስታቸውን እንዲያጡ ወይም እንዲያዝኑ በጭራሽ አንፈልግም። እንዲያውም ታዛዥ በመሆንና ለእነሱ በመገዛት “በሚያከናውኑት ሥራ የተነሳ በፍቅር ለየት ያለ አሳቢነት [ልናሳያቸው]” ይገባል።—1 ተሰ. 5:13

ይህን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋችሁን ቀጥሉ

19, 20. የወንድማማች ፍቅር “ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ” ማሳየታችንን መቀጠል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

19 የይሖዋ ሕዝቦች በመካከላቸው ባለው የወንድማማች ፍቅር እንደሚታወቁ ምንም ጥርጥር የለውም። ጳውሎስ በእሱ ዘመን ይህ እውነት እንደነበር ገልጿል። ከዚያም ሁሉም ‘ይህን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ’ አበረታቷቸዋል። (1 ተሰ. 4:9, 10) ምንጊዜም ቢሆን ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልገናል!

20 እንግዲያው ዓመቱን ሙሉ የዓመት ጥቅሳችንን ስንመለከት በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ እናሰላስል፦ ይበልጥ እንግዳ ተቀባይ መሆን የምችለው እንዴት ነው? በእስር ቤት ያሉትን ወንድሞቻችንን ማስታወስ የምችለው እንዴት ነው? አምላክ ላደረገው የጋብቻ ዝግጅት ተገቢውን አክብሮት አሳያለሁ? ባለኝ ነገር ለመርካት ምን ሊረዳኝ ይችላል? ይበልጥ በይሖዋ መታመን የምችለው እንዴት ነው? አመራር ከሚሰጡት ጋር በተሟላ መንገድ መተባበር የምችለው እንዴት ነው? በእነዚህ ስድስት አቅጣጫዎች ማስተካከያ ለማድረግ ከጣርን የዓመት ጥቅሳችን በመንግሥት አዳራሻችን ግድግዳ ላይ የተሰቀለ ምልክት ከመሆን ያለፈ ትርጉም ይኖረዋል። ጥቅሱ “እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች መዋደዳችሁን ቀጥሉ” የሚለውን ምክር እንድንሠራበት ያሳስበናል።—ዕብ. 13:1

^ [1] (አንቀጽ 9) የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ ጊዜ የወንድማማች ፍቅር እንዳላቸው ያሳዩባቸውን ምሳሌዎች ለማግኘት የሐምሌ 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-9 እና የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕ. 19 እንዲሁም የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! የተባለውን መጽሐፍ ምዕ. 20 ተመልከት።