በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ቁጥር 1 2016

አሉታዊ ስሜቶችን መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

አሉታዊ ስሜቶችን መቋቋም የሚቻልበት መንገድ

አንድ ሕፃን ሲወለድ ሙሉ በሙሉ የሌሎች እርዳታ ያስፈልገዋል። እኛም ሕፃን ሳለን ደኅንነታችን የተመካው በወላጆቻችን እንክብካቤ ላይ ነበር። መራመድ ስንጀምር ደግሞ ትላልቅ ሰዎች ግዙፍ ሆነው ይታዩን ነበር። በተለይ ወላጆቻችን ቅርብ ካልሆኑ ይህ ሁኔታ በጣም ያስደነግጠናል። የእናታችንን ወይም የአባታችንን እጅ ስንይዝ ግን መረጋጋት ይሰማናል።

ከፍ እያልን ስንሄድ፣ ወላጆቻችን ፍቅርና ማበረታቻ ሲሰጡን ጥሩ ስሜት ይሰማናል። ወላጆቻችን እንደሚወዱን ማወቃችን ይበልጥ የመረጋጋት ስሜት እንዲኖረን አድርጓል። ያደረግነውን ነገር ጠቅሰው ሲያደንቁን በራሳችን ይበልጥ እንተማመናለን፤ እንዲሁም የበለጠ ለማድረግ እንነሳሳለን።

እያደግን ስንሄድ ደግሞ የቅርብ ጓደኞቻችን ተጨማሪ ድጋፍ ሰጥተውናል። እነሱ አጠገባችን ሲሆኑ ይበልጥ እንረጋጋለን፤ በትምህርት ቤት ያለው ሁኔታም ቢሆን ያን ያህል አያስፈራንም።

እርግጥ ነው፣ በእንዲህ ዓይነት የተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ የሚያድጉት ሁሉም ልጆች አይደሉም። አንዳንድ ልጆች የቅርብ ጓደኛ የላቸውም፤ ሌሎቹ ደግሞ ከወላጆቻቸው በቂ ድጋፍ አግኝተው አላደጉም። ሜሊሳ * እንዲህ ብላለች፦ “ቤተሰቦች በአንድነት ሆነው የተለያዩ ነገሮችን ሲያከናውኑ የሚያሳዩ ፎቶዎችን ሳይ፣ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ምናለ እንዲህ ያለ ሕይወት አሳልፌ ቢሆን ኖሮ እያልኩ እመኛለሁ።” ምናልባት አንተም እንዲህ ይሰማህ ይሆናል።

አስተዳደጋችን በስሜታችን ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ

በልጅነትህ በራስ መተማመን ኖሮህ አላደግህ ይሆናል። ወይም ከወላጆችህ ያን ያህል ፍቅርና ማበረታቻ አላገኘህ ይሆናል። ምናልባትም ወላጆችህ በየጊዜው ይጣሉ ከነበረና በዚህ ምክንያት ፍቺ ከፈጸሙ ለእነሱ ፍቺ ተጠያቂው አንተ እንደሆንክ ሊሰማህ ይችላል። ከዚህ የከፋው ደግሞ ወላጆችህ ስሜትህን የሚጎዳ ነገር እየተናገሩህ ወይም አካላዊ ጥቃት እያደረሱብህ አድገህ ሊሆን ይችላል።

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያደጉ ልጆች ምን ይሆናሉ? አንዳንዶች ዕፅ መውሰድ የሚጀምሩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ከመጠን በላይ መጠጣት ሊጀምሩ ይችላሉ። አንዳንዶች የተፈላጊነት ስሜት እንዲሰማቸው ሲሉ የወንጀለኛ ቡድን አባል ይሆናሉ። ወይም ደግሞ ያጡትን ፍቅር ለማግኘት ሲሉ ሳያስቡበት የፍቅር ግንኙነት ይመሠርታሉ። ሆኖም በዚህ መንገድ የሚመሠረተው የፍቅር ግንኙነት ብዙ አይዘልቅም፤ ይህ ደግሞ የበለጠ ያለመረጋጋት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።

የወላጅን ትኩረት አጥተው ያደጉ ልጆች ሁሉ እነዚህ ነገሮች ውስጥ ባይገቡ እንኳ ለራሳቸው የሚኖራቸው ግምት ዝቅተኛ  ሊሆን ይችላል። አና የተባለች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ብዙ ጊዜ እንደማልረባ ትነግረኝ ስለነበር የማልጠቅም ሰው እንደሆንኩ አምኜ ተቀበልኩ። ከእሷ ፍቅርም ሆነ ምስጋና ያገኘሁበት ጊዜ ትዝ አይለኝም።”

በራስ የመተማመን ስሜት እንድናጣ የሚያደርገን አስተዳደጋችን ብቻ አይደለም። የትዳር መፍረስ፣ በእርጅና ምክንያት የሚመጡ ችግሮች ወይም መልካችንንና ቁመናችንን በተመለከተ የሚያሳስቡን ነገሮች በራስ የመተማመን ስሜት እንዳይኖረን ሊያደርጉ ይችላሉ። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ደስታችንን ሊያጠፋብን እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያበላሽብን ይችላል። ታዲያ ይህን ስሜት ለመቋቋም ምን ማድረግ እንችላለን?

አምላክ ያስብልናል

በዚህ ረገድ እርዳታ ማግኘት እንደምንችል እርግጠኛ መሆን ይኖርብናል። እኛን ለመርዳት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ ያለው አካል አለ፤ እሱም አምላክ ነው።

አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።” (ኢሳይያስ 41:10, 13) አምላክ በምሳሌያዊ ሁኔታ እጃችንን እንደሚይዘን ማወቁ እንዴት የሚያጽናና ነው። በመሆኑም የምንጨነቅበት ምንም ምክንያት የለም!

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ተጨንቀው የነበረ ቢሆንም አምላክ እጃቸውን እንደያዛቸው ተሰምቷቸዋል። የሳሙኤል እናት የሆነችው ሐና ልጅ መውለድ ስላልቻለች የከንቱነት ስሜት አድሮባት ነበር። መሃን በመሆኗ መሳለቂያ ሆና ነበር። በዚህ ምክንያት ሐና የምግብ ፍላጎቷ የጠፋ ሲሆን ብዙ ጊዜ ታለቅስ ነበር። (1 ሳሙኤል 1:6, 8) ሆኖም የሚሰማትን ሁሉ አውጥታ ለአምላክ ከተናገረች በኋላ ሐዘኗ ጠፋ።—1 ሳሙኤል 1:18

መዝሙራዊው ዳዊትም ቢሆን በአንድ ወቅት ስጋት አድሮበት ነበር። ንጉሥ ሳኦል ለበርካታ ዓመታት አሳድዶታል። ዳዊት፣ በርካታ የግድያ ሙከራዎች የተደረጉበት ሲሆን በችግር እንደተዋጠ የተሰማው ወቅት ነበር። (መዝሙር 55:3-5፤ 69:1) ይህ ሁሉ ቢደርስበትም ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በሰላም እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁም፤ ይሖዋ ሆይ፣ ተረጋግቼ እንድኖር የምታደርገኝ አንተ ብቻ ነህና።”—መዝሙር 4:8

ሐናም ሆነች ዳዊት ያስጨነቃቸውን ነገር በይሖዋ ላይ የጣሉ ሲሆን እሱም እንደሚደግፋቸው በሕይወታቸው አይተዋል። (መዝሙር 55:22) እኛስ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

 የመረጋጋት ስሜት እንዲኖርህ የሚረዱ ሦስት ነገሮች

1. ይሖዋን እንደ አባትህ አድርገህ በመመልከት በእሱ ታመን።

ኢየሱስ “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ” ስለሆነው ስለ አባቱ እንድናውቅ አበረታቶናል። (ዮሐንስ 17:3) ሐዋርያው ጳውሎስም “እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” በማለት አረጋግጦልናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:27) ያዕቆብ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት ጽፏል።—ያዕቆብ 4:8

በሰማይ የሚኖር ብሎም የሚወደንና የሚያስብልን አባት እንዳለን ማወቅ ጭንቀትን ለመቋቋም በእጅጉ ይረዳናል። እውነት ነው፣ በአምላክ ላይ እምነት መጣል በአንድ ጀምበር የሚመጣ ነገር አይደለም፤ ሆኖም ብዙዎች ይህን በማድረጋቸው በጣም ተጠቅመዋል። ካሮሊን እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን እንደ አባቴ መመልከት ስጀምር፣ ስሜቴን አውጥቼ የምነግረው አንድ አካል እንዳገኘሁ ሆኖ ተሰማኝ፤ ይህ ደግሞ እፎይታ እንዲሰማኝ አድርጓል።”

ሬቸል እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ትተውኝ በሄዱበት ወቅት የደኅንነት ስሜት እንዲሰማኝ የረዳኝ ይሖዋ ነው። እሱን አነጋግረው እንዲሁም በችግሬ እንዲረዳኝ እጠይቀው ነበር። ደግሞም ረድቶኛል።” *

2. መንፈሳዊ ቤተሰብ ለማግኘት ጥረት አድርግ።

ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ አንዳቸው ሌላውን እንደ ወንድምና እንደ እህት እንዲመለከቱ አስተምሯቸዋል። “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 23:8) የእሱ እውነተኛ ተከታዮች እርስ በርስ በመዋደድ ልክ እንደ አንድ መንፈሳዊ ቤተሰብ እንዲሆኑ ይፈልጋል።—ማቴዎስ 12:48-50፤ ዮሐንስ 13:35

የይሖዋ ምሥክሮች በሚሰበሰቡባቸው ጉባኤዎች ውስጥ አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና መጽናኛ ለመስጠት ጥረት ስለሚያደርጉ እውነተኛ መንፈሳዊ ቤተሰብ ናቸው ሊባል ይችላል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የጉባኤ ስብሰባዎች ልክ ቁስልን እንደሚፈውስ ቅባት ከደረሰባቸው የስሜት ጉዳት እንዲያገግሙ እንደረዷቸው በሕይወታቸው ማየት ችለዋል።

ኢቫ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በጉባኤያችን የነበረች በጣም የምቀርባት ጓደኛዬ የሚደርስብኝን የስሜት ሥቃይ ትረዳልኝ ነበር። ታዳምጠኛለች፤ መጽሐፍ ቅዱስ ታነብልኛለች፤ በተጨማሪም አብራኝ ትጸልያለች። ብቸኝነት እንዳይሰማኝ ታደርግ ነበር። ስሜቴን አውጥቼ እንድናገር ታበረታታኝ ስለነበር ቀለል ይለኝ ነበር። እሷ ባደረገችልኝ እርዳታ ከደረሰብኝ የስሜት ጉዳት ማገገም ችያለሁ።” ሬቸልም በበኩሏ እንዲህ ብላለች፦ “በጉባኤ ውስጥ እንደ እናትና እንደ አባት የሚሆኑልኝ ወንድሞችና እህቶች አግኝቼያለሁ። እንደምወደድና ተፈላጊ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርገዋል።”

 3. ለሌሎች ፍቅርና ደግነት አሳይ።

ለሌሎች ፍቅርና ደግነት ማሳየት ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት በር ይከፍታል። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ለሌሎች ፍቅር ባሳየን መጠን ያንኑ ያህል እንደምንቀበል ከራሳችን ተሞክሮ ማየት እንችላለን። ኢየሱስ “ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል” በማለት ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል።—ሉቃስ 6:38

ለሌሎች ፍቅር ማሳየታችንም ሆነ የሌሎችን ፍቅር ማግኘታችን ይበልጥ የመረጋጋት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ራሴ የሚሰሙኝ አንዳንድ አሉታዊ ነገሮች እውነት እንዳልሆኑ አውቃለሁ። ሌሎችን መርዳቴ ስለ ራሴ ብዙ እንዳላስብ ስለሚያደርገኝ እንዲህ ዓይነቱ አሉታዊ አስተሳሰብ እንዳይመጣብኝ ይረዳኛል። ምንጊዜም ቢሆን ለሌሎች አንድ ጥሩ ነገር ሳደርግ የእርካታ ስሜት ይሰማኛል።”

ሁሉም ሰው ተረጋግቶ የሚኖርበት ጊዜ

ከላይ የተጠቀሱት ሐሳቦች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ፈጣንና ዘላቂ የሆነ ፈውስ ያስገኛሉ ማለት አይደለም። ይሁንና በሁኔታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። ካሮሊን “አሁንም ቢሆን እንደማልፈለግ የሚሰማኝ ጊዜ አለ” ብላለች። አክላም እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “አሁን ግን ለራሴ ያለኝ ግምት የተሻለ ነው። አምላክ እንደሚያስብልኝ አውቃለሁ፤ እንዲሁም ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ የሚያደርጉ ብዙ ወዳጆች አሉኝ።” ሬቸልም ብትሆን እንደ ካሮሊን ይሰማታል፦ “በሐዘን የምዋጥባቸው ጊዜያት አሉ። አሁን ግን የማማክራቸውና ሁኔታዎችን አዎንታዊ በሆነ መንገድ መመልከት እንድችል የሚረዱኝ መንፈሳዊ ወንድሞችና እህቶች አሉኝ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በየዕለቱ ላነጋግረው የምችል በሰማይ የሚኖር አባት አለኝ። እነዚህ ነገሮች ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ይገልጻል፤ በዚህ ዓለም ውስጥ ሁላችንም የደኅንነት ስሜት ይሰማናል

ከዚህ በተጨማሪ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ይገልጻል፤ በዚህ ዓለም ውስጥ ሁላችንም የደኅንነት ስሜት ይሰማናል። የአምላክ ቃል “እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም” በማለት ተስፋ ይሰጣል። (ሚክያስ 4:4) በዚያን ጊዜ ለማንም ሰው ጥቃት የተጋለጥን አንሆንም፤ እንዲሁም ማንም ጉዳት አያደርስብንም። ሌላው ቀርቶ አሁን ወደ አእምሯችን እየመጡ የሚረብሹን መጥፎ ትዝታዎች እንኳ በዚያን ጊዜ “አይታሰቡም።” (ኢሳይያስ 65:17, 25) አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነተኛ ጽድቅ” እንዲሰፍን ያደርጋሉ። በመሆኑም በዚያን ጊዜ “ዘላቂ ጸጥታና ደህንነት” ይሰፍናል።—ኢሳይያስ 32:17