በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ንዑስ መምረጫው ሂድ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

አማርኛ

መጠበቂያ ግንብ  |  ቁጥር 1 2016

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም አለው?

ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም ያስገኛል?

ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም ያስገኛል?

“ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እናምናለን፤ ደግሞም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንዳንድ ጊዜ “ሐቀኝነት” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺው “በተፈጥሮው ጥሩ የሆነን ነገር” ያመለክታል። ይህ ቃል ከሥነ ምግባር አንጻር ውብ መሆን ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።

ክርስቲያኖች፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን” በማለት የተናገረውን ሐሳብ በቁም ነገር ይመለከቱታል። ይህ ምን ማድረግን ይጠይቃል?

በውስጣችን ያለ ትግል

አብዛኞቹ ሰዎች ከቤት ከመውጣታቸው በፊት ጠዋት ጠዋት በመስተዋት ራሳቸውን ይመለከታሉ። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ማራኪ ሆነው መታየት ስለሚፈልጉ ነው። ሆኖም ፀጉርን ከማሳመር ወይም ጥሩ ልብስ ከመልበስ የበለጠ አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። በእርግጥም፣ ውስጣዊ ማንነታችን በውጫዊው መልካችን ላይ ውበት ሊጨምርልን ወይም ሊቀንስብን ይችላል።

የአምላክ ቃል፣ መጥፎ የሆነውን ነገር የማድረግ ዝንባሌ እንዳለን በግልጽ ይናገራል። ዘፍጥረት 8:21 “የሰው የልብ ዝንባሌ ከልጅነቱ ጀምሮ መጥፎ ነው” ይላል። በመሆኑም ሐቀኛ ለመሆን በውስጣችን ካለው ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ ጋር መታገል ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከኃጢአት ጋር የሚያደርገውን ትግል እንደሚከተለው በማለት ጥሩ አድርጎ ገልጾታል፦ “በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በሰውነቴ ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።”—ሮም 7:22, 23

ለምሳሌ ያህል፣ ልባችን መጥፎ የሆነውን ነገር እንድናደርግ በሚገፋፋን ወቅት ወይም ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ለመፈጸም በምንፈተንበት ጊዜ ልባችን የሚለንን ከመፈጸም ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም ማለት አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብን መምረጥ እንችላለን። በውስጣችን ያለውን መጥፎ አስተሳሰብ ለማስወገድ የምንመርጥ ከሆነ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ሐቀኝነት የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ ሐቀኛ ሆነን መኖር እንችላለን።

በትግሉ አሸናፊ መሆን ይቻላል

ሐቀኛ መሆን ከፈለግን ከሥነ ምግባር አንፃር በጥብቅ የምንከተለው አቋም ሊኖረን ይገባል። የሚያሳዝነው ነገር፣ ሰዎች ከሥነ ምግባር አቋማቸው ይልቅ ስለ አለባበሳቸውና ስለ መልካቸው ስለሚጨነቁ ለዚህ ብዙ ጊዜ ሲያጠፉ ይታያል። እነዚህ ሰዎች ሐቀኝነትን የሚለኩት ባሉበት ሁኔታ ላይ ተመሥርተው ነው። (ኦነስት) ትሩዝ አባውት ዲስኦነስቲ የተባለው መጽሐፍ ይህን ሁኔታ በዚህ መንገድ አስቀምጦታል፦ “እኛ ለራሳችን ባወጣነው መሥፈርት መሠረት ሐቀኛ እንደሆንን እስከተሰማን ድረስ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ብንፈጽምም ምንም አይመስለንም።” ታዲያ ምን ያህል ሐቀኛ መሆን አለብን በሚለው ጉዳይ ረገድ ልንተማመንበት የምንችል መሥፈርት አለ? ደስ የሚለው ነገር፣ ሊረዳን የሚችል ነገር አለ።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ጠቃሚ እርዳታ እንደሚያበረክት አስተውለዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙት የሥነ ምግባር ደንቦች ተወዳዳሪ የላቸውም። (መዝሙር 19:7) ከቤተሰብ ሕይወት፣ ከሥራ፣ ከሥነ ምግባር፣ ከመንፈሳዊነት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ ልንተማመንበት  የምንችል መመሪያ ይሰጠናል። ጠቃሚነቱ ደግሞ ጊዜ የማይሽረው እንደሆነ ታይቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሕጎች እና መመሪያዎች ለሁሉም ብሔር፣ ዘር፣ ጎሣና ሕዝብ ይጠቅማሉ። ይህን መጽሐፍ በመመርመር፣ በሚናገረው ሐሳብ ላይ በማሰላሰል እንዲሁም ምክሩን ተግባራዊ በማድረግ ልባችን ሐቀኛ እንዲሆን ማሠልጠን እንችላለን።

ይሁን እንጂ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ብቻውን ሐቀኛ ለመሆን በምናደርገው ትግል እንድናሸንፍ አይረዳንም። ምክንያቱም የምንኖረው ጥሩ ሥነ ምግባር የሌላቸው ሰዎች በሞሉበት ዓለም በመሆኑ የእነሱን አካሄድ እንድንከተል ተጽዕኖ ይደርስብናል። ስለዚህ አምላክ እንዲረዳንና እንዲያግዘን ወደ እሱ መጸለይ ይኖርብናል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13) ይህንን በማድረግ እውነት ለሆነው ነገር ለመቆምና በሁሉም ነገር ሐቀኛ ለመሆን ድፍረት እናገኛለን።

ሐቀኝነት ወሮታ አለው

መግቢያችን ላይ የጠቀስነው ሂቶሺ ሐቀኛ በመሆን ረገድ ያተረፈው ጥሩ ስም ጠቅሞታል። የአሁኑ አለቃው ሐቀኛ መሆኑን ያደንቅለታል። ሂቶሺ “በንጹሕ ሕሊና የምሠራው ሥራ በማግኘቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ” በማለት ተናግሯል።

ሌሎች ሰዎችም ሐቀኝነት ወሮታ የሚያስገኝ ነገር እንደሆነ በሕይወታቸው አይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሁሉም ነገር በሐቀኝነት እንድንኖር’ የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረጋቸው የተጠቀሙ አንዳንድ ሰዎችን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

 • ንጹሕ ሕሊና

  “በ13 ዓመቴ ትምህርት አቁሜ ከሌቦች ጋር መሥራት ጀመርኩ። በመሆኑም ከገቢዬ 95 በመቶ የሚሆነው በማጭበርበር የሚገኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ትዳር የመሠረትኩ ሲሆን እኔና ባሌ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን። ይሖዋ * አምላክ ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶችን እንደሚጠላ ተማርን፤ በመሆኑም በሕይወታችን ለውጥ ለማድረግ ወሰንን። በ1990 ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።—ምሳሌ 6:16-19

  “ቀደም ሲል ቤታችን በተሰረቁ ዕቃዎች ተሞልቶ ነበር፤ አሁን ግን ምንም የተሰረቀ ዕቃ የለንም፤ በመሆኑም ንጹሕ ሕሊና አለኝ። ሐቀኝነት የጎደለው ሕይወት በመምራት ያሳለፍኳቸውን በርካታ ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ ታላቅ ምሕረት ስላሳየኝ አመስጋኝ ነኝ። አሁን ይሖዋ በእኔ እንደሚደሰት ስለማውቅ ማታ ማታ ደስ ብሎኝ ወደ መኝታዬ እሄዳለሁ።”—ሼረል፣ አየርላንድ

  “አለቃዬ፣ ከደንበኞቻችን አንዱ ጉቦ ሊሰጠኝ ሲል ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ ሲሰማ ‘አምላክህ ታማኝ ሰው እንድትሆን አድርጎሃል! ለመሥሪያ ቤታችን ትልቅ ሀብት ነህ’ አለኝ። በሁሉም ነገር ሐቀኛ መሆኔ በይሖዋ አምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረኝ አድርጓል። በተጨማሪም ቤተሰቤም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ አቋም እንዲኖራቸው ለመርዳት አስችሎኛል።”—ሶኒ፣ ሆንግ ኮንግ

 • የአእምሮ ሰላም

  “በአንድ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ የሥራ አስኪያጁ ረዳት ሆኜ እሠራለሁ። በዚህ ሥራ ላይ ሀብት ለማካበት ሲባል ሐቀኝነትን ማጉደል የተለመደ ነገር ነው። ብዙዎች ‘ሀብት የሚያስገኝና ኢኮኖሚውን የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ በትንሹም ቢሆን ሐቀኝነት ማጉደል ችግሩ ምንድን ነው?’ የሚል አመለካከት አላቸው። እኔ ግን ሐቀኛ በመሆኔ የአእምሮ ሰላም አለኝ። በአቋሜ ምክንያት ምንም ነገር ቢያጋጥመኝ እንኳ ሐቀኛ ሆኜ ለመኖር ቆርጫለሁ። አሠሪዎቼ እንደማልዋሻቸውም ሆነ እንደማልዋሽላቸው ያውቃሉ።”—ቶም፣ ዩናይትድ ስቴትስ

 • ለራስህ አክብሮት ይኖርሃል

  “አለቃዬ በሥራ ቦታችን ስለጠፉ አንዳንድ ዕቃዎች እንድዋሽ ጠየቀኝ፤ እኔ ግን ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆንኩም። ዕቃውን የሰረቁት ሰዎች ሲጋለጡ ግን አለቃዬ ሐቀኛ በመሆኔ አመሰገነኝ። ሐቀኝነት በጎደለው ዓለም ውስጥ ሐቀኛ መሆን ድፍረት ይጠይቃል። የኋላ ኋላ ግን የሌሎችን እምነትና አክብሮት ያስገኝልናል።”—ካዎሪ፣ ጃፓን

ሐቀኛ መሆን ንጹሕ ሕሊናና የአእምሮ ሰላም እንዲሁም ለራሳችን አክብሮት እንዲኖረን ስለሚያደርግ በእርግጥም ይክሳል። በዚህ ሐሳብ አትስማማም?

^ አን.18 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።