በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

ክርስቲያናዊ ደግነት ያስገኘው ውጤት

ክርስቲያናዊ ደግነት ያስገኘው ውጤት

በጉጃራት፣ ሕንድ ውስጥ በምትገኝ አንዲት አነስተኛ ከተማ የሚኖር ጆን የተባለ ሰው አባት በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። ጆንን ጨምሮ አምስት ወንድሞቹና እህቶቹ እንዲሁም እናታቸው አጥባቂ የሮም ካቶሊኮች ስለነበሩ የአባታቸውን እምነት ይቃወሙ ነበር።

አንድ ቀን የጆን አባት፣ በጉባኤው ላለ አንድ ወንድም ፖስታ እንዲያደርስለት ጆንን ጠየቀው። ይሁን እንጂ ያን ዕለት ጠዋት ጆን የቆርቆሮ በርሜል ሲከፍት በርሜሉ ጣቱን ቆርጦት ነበር። ሆኖም አባቱን እምቢ ማለት ስላልፈለገ እየደማ ያለውን ጣቱን በቁራጭ ጨርቅ ጠምጥሞ ፖስታውን ለማድረስ በእግሩ ሄደ።

ጆን ፖስታውን እንዲያደርስ የተላከበት ቤት ሲደርስ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው የወንድም ሚስት ፖስታውን ተቀበለችው። ይህች እህት ፖስታውን ከጆን ስትቀበል የጆን ጣት እንደቆሰለ ስላስተዋለች ቁስሉን ለማከም ሐሳብ አቀረበችለት። ከዚያም የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ መስጫ ሣጥኗን አውጥታ በቁስል ማጠቢያ መድኃኒት ቁስሉን ካጸዳች በኋላ ጣቱን በፋሻ አሠረችለት። በኋላም ሻይ አፍልታ አቀረበችለት፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ታወያየው ነበር።

ይህች እህት ባሳየችው ደግነት ምክንያት ጆን ለይሖዋ ምሥክሮች የነበረው መጥፎ አመለካከት እየተለወጠ መጣ። በመሆኑም የአባቱና የእሱ እምነት የሚለያዩባቸውን ሁለት ርዕሰ ጉዳዮች አስመልክቶ ጥያቄ አቀረበላት፤ አንደኛው ርዕሰ ጉዳይ ‘ኢየሱስ አምላክ ነው ወይስ አይደለም’ የሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‘ክርስቲያኖች ለማርያም መጸለይ አለባቸው ወይስ የለባቸውም’ የሚለው ነው። ይህች እህት የጆን የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሆነውን ጉጃራቲ ተምራ ስለነበር ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለጥያቄዎቹ መልስ ሰጠችው፤ ከዚያም “ይህ የመንግሥት ምሥራች” (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት አበረከተችለት።

በኋላ ላይ ጆን ቡክሌቱን ሲያነብ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዳገኘ ተሰማው። በመሆኑም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቄስ ሄዶ እነዚያኑ ሁለት ጥያቄዎች አቀረበለት። ቄሱም ወዲያው በቁጣ በመገንፈል ጆን ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ወረወረበት፤ ከዚያም “አንተ ሰይጣን ሆነሃል! መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ አምላክ አይደለም የሚለው የቱ ጋ ነው? ማርያምን ማምለክ የለባችሁም የሚለውስ የቱ ጋ ነው? እኮ አሳየኛ!” እያለ ይጮኸበት ጀመር። በቄሱ ያልተጠበቀ ምላሽ የተበሳጨው ጆን “ከእንግዲህ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ድርሽ አልልም” በማለት ለቄሱ ነገረው። እንዳለውም ከዚያ በኋላ ወደ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ አያውቅም!

ጆን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረ ሲሆን ከእውነተኛው አምልኮ ጎን በመቆም ይሖዋን ማገልገል ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ሌሎች የቤተሰቡ አባላትም ተመሳሳይ እርምጃ ወሰዱ። ከዛሬ 60 ዓመት ገደማ በፊት ጆን በደረሰበት አደጋ ምክንያት በቀኝ እጁ ሌባ ጣት ላይ የተከሰተው ጠባሳ አሁንም አልጠፋም። ወደ ንጹሑ አምልኮ እንዲሳብ ምክንያት የሆነውን ያቺ እህት ያሳየችውን ደግነትም ቢሆን ጆን ፈጽሞ አይረሳውም።—2 ቆሮ. 6:4, 6