“የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።”—ኢሳ. 48:17

መዝሙሮች፦ 117, 114

1, 2. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ለመጽሐፍ ቅዱስ ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) የምትወደው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የትኛው ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ይወዳሉ። ይህ መጽሐፍ አስተማማኝ መመሪያ የሚሰጠን ከመሆኑም ሌላ መጽናኛና ተስፋ እንድናገኝ ይረዳናል። (ሮም 15:4) መጽሐፍ ቅዱስን የምንመለከተው የሰዎችን ሐሳብ እንደያዘ መጽሐፍ ሳይሆን ‘እንደ አምላክ ቃል አድርገን’ ነው፤ “ደግሞም የአምላክ ቃል ነው።”—1 ተሰ. 2:13

2 እያንዳንዳችን የምንወደው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይኖረናል። አንዳንዶች፣ በአምላክ ልጅ በኩል የተገለጡትን የይሖዋን ማራኪ ባሕርያት ግሩም አድርገው የሚያሳዩትን የወንጌል መጻሕፍት በጣም ይወዷቸዋል። (ዮሐ. 14:9) ሌሎች ደግሞ ትንቢቶችን የያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ምናልባትም “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች” የሚገልጸውን የራእይ መጽሐፍን ማንበብ ያስደስታቸዋል። (ራእይ 1:1) ከመዝሙር መጽሐፍ መጽናኛ ወይም ከምሳሌ መጽሐፍ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ትምህርቶችን ያላገኘ ማን አለ? በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ ነው።

3, 4. (ሀ) ስለ ጽሑፎቻችን ምን ይሰማናል? (ለ) ለተወሰኑ ሰዎች ተብለው የሚዘጋጁ ምን ጽሑፎች ይቀርቡልናል?

3 መጽሐፍ ቅዱስን ስለምንወድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንንም እንወዳለን። ለምሳሌ በመጻሕፍት፣ በብሮሹሮች፣ በመጽሔቶችና በሌሎች መንገዶች ለሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ አድናቆት አለን። ይሖዋ ያደረገልን  እነዚህ ዝግጅቶች በመንፈሳዊ ምንጊዜም ንቁ እንድንሆን፣ በሚገባ እንድንመገብ እንዲሁም “በእምነት . . . ጤናሞች” እንድንሆን እንደሚረዱን እናውቃለን።—ቲቶ 2:2

4 ለሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ከሚዘጋጁት ጽሑፎች በተጨማሪ ለተወሰኑ ሰዎች የሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ይቀርቡልናል። አንዳንድ ጽሑፎች ትኩረት የሚያደርጉት በወጣቶች ላይ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የሚዘጋጁት ወላጆቻቸውን ለመርዳት ነው። ታትመው የሚወጡትም ሆነ በድረ ገጻችን ላይ ያሉት አብዛኞቹ ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁት የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችን ታሳቢ በማድረግ ነው። እንዲህ ያለ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ መኖሩ ይሖዋ “ለሕዝቦች ሁሉ ምርጥ ምግቦች የሚገኙበት ታላቅ ግብዣ” እንደሚያዘጋጅ የገባውን ቃል እየፈጸመ እንዳለ ያስታውሰናል።—ኢሳ. 25:6

5. ይሖዋ ምን ስናደርግ ይደሰታል?

5 አብዛኞቻችን መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን የምናነብበት ተጨማሪ ጊዜ ብናገኝ ደስ እንደሚለን የታወቀ ነው። አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና የግል ጥናት በማድረግ ‘ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም’ የምናደርገው ጥረት ይሖዋን እንደሚያስደስተው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኤፌ. 5:15, 16) እርግጥ ነው፣ ለሁሉም መንፈሳዊ ምግብ እኩል ትኩረት የምንሰጠው ሁልጊዜ ላይሆን ይችላል። በመሆኑም ልንጠነቀቅበት የሚገባ ነገር አለ። ይህ ነገር ምንድን ነው?

6. ይሖዋ ከሚያቀርብልን ዝግጅቶች መካከል አንዳንዱ እንዲያመልጠን ሊያደርግ የሚችለው ምንድን ነው?

6 ከሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ መካከል አንዳንዱ እኛን እንደማይመለከተን አድርገን የምናስብ ከሆነ የሚያመልጠን ነገር ይኖራል፤ ይህ ደግሞ አደገኛ ነው። ለምሳሌ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እኛን እንደማይጠቅመን ቢሰማንስ? አሊያም ደግሞ አንድ ትምህርት በዋነኝነት የተዘጋጀው ለእኛ ባይሆንስ? ገረፍ ገረፍ አድርገን እናልፈዋለን? ወይም ጨርሶ ሳናነበው እንተወዋለን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በጣም ሊጠቅመን የሚችል ትምህርት እያመለጠን ነው። በዚህ ወጥመድ ውስጥ ላለመውደቅ ምን ማድረግ እንችላለን? የሚቀርቡልን መንፈሳዊ ትምህርቶች ምንጭ አምላክ መሆኑን ሁላችንም ልናስታውስ ይገባል። ይሖዋ “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ” በማለት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ተናግሯል። (ኢሳ. 48:17) ከሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችና ከሚቀርብልን የተለያየ መንፈሳዊ ምግብ ጥቅም ለማግኘት የሚረዱንን ሦስት ነጥቦች እስቲ እንመልከት።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጥቅም ለማግኘት የሚረዱ ነጥቦች

7. ለመማር ዝግጁ ሆነን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 ለመማር ዝግጁ ሆነህ አንብብ። የአምላክ ቃል “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው፤ እንዲሁም . . . ይጠቅማሉ” በማለት በግልጽ ይናገራል። (2 ጢሞ. 3:16) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መጀመሪያ የተጻፉት ለአንድ ግለሰብ ወይም ለተወሰኑ ሰዎች ነው። ቅዱሳን መጻሕፍትን፣ ለመማር ዝግጁ ሆነን ማንበብ ያለብንም ለዚህ ነው። አንድ ወንድም “አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሳነብ፣ ከማነበው ነገር ብዙ ትምህርት ላገኝ እንደምችል ለማስታወስ እሞክራለሁ” በማለት ተናግሯል። አክሎም “ይህም በግልጽ ከሰፈረው ሐሳብ በስተ ጀርባ ያለውን ትምህርት ለማግኘት እንድጥር ያነሳሳኛል” ብሏል። የአምላክን ቃል ማንበብ ከመጀመራችን በፊት፣ ለመማር ዝግጁ እንድንሆንና ይሖዋ ሊያስተምረን የሚፈልገውን ትምህርት ለማስተዋል የሚያስችል ጥበብ እንድናገኝ መጸለያችን አስፈላጊ ነው።—ዕዝራ 7:10፤ ያዕቆብ 1:5ን አንብብ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችሁ የላቀ ጥቅም ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው? (አንቀጽ 7ን ተመልከት)

8, 9. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን? (ለ) ይሖዋ ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ያወጣቸው ብቃቶች ስለ እሱ ምን ያስተምሩናል?

8 ጥያቄ ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ቆም እያልክ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራስህን ጠይቅ፦ ‘ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? ትምህርቱን በሕይወቴ ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? ይህን ሐሳብ ሌሎችን ለመርዳት ልጠቀምበት  የምችለው እንዴት ነው?’ እንደነዚህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ ስናሰላስል ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን ይበልጥ ጥቅም ማግኘት እንደምንችል የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቁባቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች እንመልከት። (1 ጢሞቴዎስ 3:2-7ን አንብብ።) አብዛኞቻችን የጉባኤ ሽማግሌዎች ስላልሆንን ይህ ጥቅስ በሕይወታችን ውስጥ ልንጠቀምበት የምንችል ትምህርት እንዳልያዘ ይሰማን ይሆናል። ይሁንና ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ የሚሆኑትን አንዳንድ ሐሳቦች ስንመለከት፣ ከዚህ ጥቅስ ሁላችንም የተለያዩ ጥቅሞች ልናገኝ እንደምንችል እንገነዘባለን።

9 ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረኛል? ይሖዋ እነዚህ ብቃቶች በዝርዝር እንዲሰፍሩ ማድረጉ፣ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ላቅ ያሉ መሥፈርቶችን እንዲያሟሉ የሚፈልግ መሆኑን ያሳያል። ይሖዋ፣ ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል፤ እንዲሁም “በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን” ጉባኤ የሚይዙበትን መንገድ በተመለከተ ይጠይቃቸዋል። (ሥራ 20:28) አምላክ፣ በተሾሙት የበታች እረኞች እንክብካቤ ሥር ሆነን ያለ ስጋት እንድንኖር ይፈልጋል። (ኢሳ. 32:1, 2) ከእነዚህ ነጥቦች አንጻር፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቁባቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች መኖራቸው ይሖዋ ምን ያህል በጥልቅ እንደሚያስብልን እንድንገነዘብ ያደርገናል።

10, 11. (ሀ) ሽማግሌዎች ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ ብቃቶች ስናነብ ትምህርቱን በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ይህን ሐሳብ ሌሎችን ለመርዳት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ትምህርቱን በሕይወቴ ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው? አንድ የተሾመ ወንድም፣ ራሱን ከእነዚህ መንፈሳዊ ብቃቶች አንጻር በየጊዜው መገምገምና በምን ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልገው መመርመር ይኖርበታል። “የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር” አንድ ወንድም እነዚህን ብቃቶች በቁም ነገር ሊያስብባቸው ይገባል፤ ምክንያቱም እነዚህን ብቃቶች ለማሟላት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለበት። (1 ጢሞ. 3:1) ለነገሩ በዚህ ጥቅስ ላይ ከተዘረዘሩት ብቃቶች መካከል አብዛኞቹ፣ ይሖዋ ከሁሉም ክርስቲያኖች የሚጠብቃቸው ስለሆኑ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከዚህ ጥቅስ ትምህርት ሊያገኝ ይችላል። ለምሳሌ፣ ሁላችንም ምክንያታዊ ልንሆንና ጤናማ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል። (ፊልጵ. 4:5፤ 1 ጴጥ. 4:7) ሽማግሌዎች “ለመንጋው ምሳሌ” ለመሆን ሲጥሩ እኛም ከእነሱ ትምህርት ልንወስድና ‘በእምነታቸው ልንመስላቸው’ ይገባል።—1 ጴጥ. 5:3፤ ዕብ. 13:7

11 ይህን ሐሳብ ሌሎችን ለመርዳት ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ለክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ያወጣቸውን ብቃቶች በመጠቀም፣ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያሉ ሽማግሌዎች ከሕዝበ  ክርስትና ቀሳውስት የሚለዩት እንዴት እንደሆነ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ወይም ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ማብራራት እንችላለን። በተጨማሪም እነዚህን ብቃቶች ማንበባችን፣ በጉባኤያችን ያሉት ሽማግሌዎች ለእኛ ሲሉ የሚያደርጉትን ጥረት እንድናስብ ያደርገናል። ምን ያህል እንደሚደክሙ ማስታወሳችን ‘በመካከላችን በትጋት እየሠሩ ያሉትን’ በጥልቅ እንድናከብራቸው ያነሳሳናል። (1 ተሰ. 5:12) ተግተው ለሚሠሩት ለእነዚህ የበላይ ተመልካቾች ልባዊ አክብሮት የምናሳይ ከሆነ እነሱም ደስታቸው እየጨመረ ይሄዳል።—ዕብ. 13:17

12, 13. (ሀ) ባሉን መሣሪያዎች ተጠቅመን ምን ዓይነት ምርምር ማድረግ እንችላለን? (ለ) ምርምር ማድረጋችን በቀጥታ የማናገኛቸውን ትምህርቶች ለማስተዋል የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

12 ምርምር አድርግ። ባሉን የምርምር መሣሪያዎች ተጠቅመን እንደሚከተሉት ስላሉ ጉዳዮች መረጃ ለማግኘት ጥረት ማድረግ እንችላለን፦

  • ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የጻፈው ማን ነው?

  • የተጻፈው የትና መቼ ነው?

  • ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በተጻፈበት ወቅት የትኞቹ ጎላ ያሉ ክንውኖች ተፈጽመዋል?

እንዲህ ያሉ ተዛማጅ መረጃዎች፣ ፊት ለፊት የማናገኛቸውን ትምህርቶች ለማስተዋል ሊረዱን ይችላሉ።

13 ሕዝቅኤል 14:13, 14ን እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አንድ አገር ታማኝ ሳይሆን ቀርቶ በእኔ ላይ ኃጢአት ቢፈጽም እጄን በእሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ የምግብ አቅርቦቱም እንዲቋረጥ አደርጋለሁ፤ ረሃብም እሰድበታለሁ እንዲሁም ሰውንም ሆነ እንስሳን ከዚያ አጠፋለሁ። ‘እነዚህ ሦስት ሰዎች ይኸውም ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ በዚያ ቢኖሩ እንኳ በጽድቃቸው የሚያድኑት ራሳቸውን ብቻ ነው’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ።” ምርምር ስናደርግ፣ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ይህ ጥቅስ የተጻፈው በ612 ዓ.ዓ. ገደማ እንደሆነ እንገነዘባለን። በዚህ ጊዜ ኖኅና ኢዮብ ከሞቱ በርካታ መቶ ዓመታት ቢያልፉም በታማኝነት ያስመዘገቡትን ታሪክ አምላክ አልረሳውም። በሌላ በኩል ዳንኤል በወቅቱ በሕይወት ነበር። ዳንኤል፣ የኖኅንና የኢዮብን ያህል ታማኝ እንደሆነ ይሖዋ በተናገረለት ወቅት በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ከዚህ ጥቅስ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ይሖዋ፣ በዕድሜ ትንሽ የሆኑትን ጨምሮ ሁሉም ታማኝ አገልጋዮቹ ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቅ የሚያስመዘግቡትን ታሪክ ያስተውላል እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከታል።—መዝ. 148:12-14

ከተለያዩ ጽሑፎች ጥቅም ማግኘት

14. ለወጣቶች ተብለው የሚዘጋጁት ጽሑፎች ወጣቶችን የሚረዱት እንዴት ነው? እነዚህ ጽሑፎች ሌሎችንም የሚጠቅሙት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

14 በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ክፍሎች ማጥናታችን እንደሚጠቅመን ሁሉ ከሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ በሙሉም ጥቅም ማግኘት እንችላለን። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። ለወጣቶች ተብለው የሚዘጋጁ ጽሑፎች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለወጣቶች ብዙ ጽሑፎች እየተዘጋጁ ነው። [1] ከእነዚህ ጽሑፎች አንዳንዶቹ፣ ወጣቶች በትምህርት ቤት የሚያጋጥሟቸውን ተጽዕኖዎች ወይም ከጉርምስና ዕድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት እንዲችሉ የሚረዷቸው ናቸው። ታዲያ ሁላችንም እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን ማንበባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? እነዚህን ጽሑፎች ማንበባችን፣ ታማኝ የሆኑ ወጣቶች ምን እንደሚያጋጥማቸው ለመገንዘብ ይረዳናል። ይህ ደግሞ እነሱን ለመርዳትና ለማበረታታት ያስችለናል።

15. በዕድሜ ከፍ ያሉ ክርስቲያኖች፣ ለወጣቶች ለተዘጋጁ ጽሑፎች ትኩረት መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው?

15 ለወጣቶች በሚዘጋጁ ርዕሶች ላይ የሚጠቀሱት አብዛኞቹ ችግሮች ሌሎቻችንንም ያጋጥሙናል። ሁላችንም ለእምነታችን ጥብቅና መቆም፣ ስሜታችንን መቆጣጠር፣ ጎጂ የሆነ የእኩዮች ተጽዕኖን መቋቋም እንዲሁም ከመጥፎ ጓደኛና መዝናኛ መራቅ ይኖርብናል። እነዚህና ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ለወጣቶች በተዘጋጁት ጽሑፎች ላይ ተብራርተዋል። በዕድሜ ከፍ ያሉ ክርስቲያኖች፣ ለወጣቶች የተዘጋጁ ጽሑፎች ለእነሱ እንደማይመጥኑ ሊሰማቸው ይገባል?  በፍጹም! ትምህርቱ የተዘጋጀው ወጣቶችን በሚማርክ መልኩ ቢሆንም ምክሩ የተመሠረተው ጊዜ በማይሽራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ነው፤ ስለዚህ ሁላችንም ከዚህ መንፈሳዊ ዝግጅት ጥቅም ማግኘት እንችላለን።

16. ጽሑፎቻችን ወጣቶች ምን እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል?

16 ጽሑፎቻችን ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲቋቋሙ የሚያግዟቸው ከመሆኑም ሌላ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉና ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ይረዷቸዋል። (መክብብ 12:1, 13ን አንብብ።) በዕድሜ ከፍ ያሉ ክርስቲያኖችም በዚህ ረገድ ጥቅም ማግኘት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሚያዝያ 2009 ንቁ! ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . . የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን አስደሳች ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ወጥቶ ነበር። ይህ ርዕስ የተለያዩ ጠቃሚ ሐሳቦችን እንዲሁም ቆርጠን በማውጣት መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ልናስቀምጠው የምንችል ሣጥን ይዞ ነበር። በዕድሜ ከፍ ያሉ ክርስቲያኖችም ከዚህ ርዕስ ጥቅም አግኝተዋል? ባለትዳርና የልጅ እናት የሆነች አንዲት የ24 ዓመት ሴት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ሁልጊዜ ትግል ይጠይቅብኝ ነበር። በዚህ ርዕሰ ትምህርት ላይ የተሰጡትን ምክሮች እየሠራሁባቸው ሲሆን ተቆርጦ እንዲወጣ የተዘጋጀውን ሣጥንም በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀምኩበት ነው። አሁን መጽሐፍ ቅዱስ የማነብበትን ጊዜ የምጠባበቀው በጉጉት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ምን ያህል ስምምነት እንዳላቸውና በተለያዩ ክሮች እንደተሠራ ውብ ጥልፍ አንድ ላይ ሲታዩ ወጥ የሆነ ሐሳብ እንደሚያስተላልፉ መገንዘብ ችያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንደ አሁኑ አስደሳች ሆኖልኝ አያውቅም።”

17, 18. ለሕዝብ ከሚዘጋጁት ጽሑፎች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

17 ለሕዝብ የሚዘጋጁ ጽሑፎች። ከ2008 ጀምሮ የመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም እየተዘጋጀ ነው፤ ይህ እትም በዋነኝነት የሚዘጋጀው ለይሖዋ ምሥክሮች ነው። ይሁንና በዋነኝነት ለሕዝብ ለማበርከት ስለሚዘጋጁት መጽሔቶቻችንስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህንም በማንበብ ጥቅም ልናገኝ እንችላለን? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ቀን በጉባኤ ስብሰባ ላይ የሕዝብ ንግግሩ ከመጀመሩ በፊት፣ ወደ መንግሥት አዳራሽ የጋበዝከው ሰው እንደመጣ ተመለከትክ። ይህን ስታይ እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም። የሕዝብ ተናጋሪው ንግግሩን ሲያቀርብ ስለ እንግዳው ማሰብህ አይቀርም። ንግግሩን የምታዳምጠው ራስህን በእንግዳው ቦታ አድርገህ ነው። በመሆኑም ንግግሩ ሲያበቃ አንተም ልብህ እንደሚነካ እንዲሁም ለትምህርቱ ያለህ አድናቆት እንደሚጨምር ጥያቄ የለውም።

18 ለሕዝብ የሚዘጋጁ ጽሑፎችን ስናነብ ተመሳሳይ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ለምሳሌ ለሕዝብ የሚበረከተው የመጠበቂያ ግንብ እትም፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሰ ጉዳዮችን የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎች ሊገባቸው በሚችል መንገድ ያብራራል። jw.org ላይ ከሚወጡት ከብዙዎቹ ርዕሶች ጋር በተያያዘም ይህ እውነት መሆኑን መመልከት ይቻላል፤ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” እንዲሁም “ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች” የሚሉት ዓምዶች ለዚህ ምሳሌ ይሆኑናል። እነዚህን ርዕሶች ስናነብ ስለምናውቃቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ያለን ግንዛቤ ይጨምራል። ከዚህም ሌላ በአገልግሎታችን ላይ ስለ እምነታችን ማብራራት የምንችልባቸው አዳዲስ መንገዶችን እንማራለን። በተመሳሳይም ንቁ! መጽሔት እውነተኛው አምላክ ስለ መኖሩ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን ከመሆኑም ሌላ እምነታችንን እንዴት ማስረዳት እንደምንችል ያሠለጥነናል።1 ጴጥሮስ 3:15ን አንብብ።

19. ይሖዋ ላደረጋቸው ዝግጅቶች አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

19 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ ‘መንፈሳዊ ጥማታችንን’ ለማርካት የሚያስችሉ የተትረፈረፉ ዝግጅቶች አድርጎልናል። (ማቴ. 5:3) እንግዲያው ከሚቀርቡልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች በሙሉ ጥቅም ማግኘታችንን እንቀጥል። እንዲህ ስናደርግ፣ የሚጠቅመንን ነገር ለሚያስተምረን አምላክ ያለንን አመስጋኝነት እናሳያለን።—ኢሳ. 48:17

^ [1] (አንቀጽ 14) ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 1 እና 2 እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ኢንተርኔት ላይ ብቻ የሚወጣው “የወጣቶች ጥያቄ” የተባለው ዓምድ ይገኙበታል።